May 6, 2026

የፌደራል መንግስት ለዘንድሮው በጀት ዓመት ለመጠባበቂያነት ከያዘው 269 ቢሊዮን ብር ውስጥ 76 በመቶውን ያዋለው፤ የበጀት እጥረት ላጋጠማቸው የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ፕሮግራሞች እና ተቋማቱ በበጀት ዝግጅት ጊዜያት ላላካተቷቸው ስራዎች መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች የከፈለው የገንዘብ መጠን 847.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ጨምሮ ገልጿል።
ይህ የተገለጸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበ የገንዘብ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ባለ 117 ገጽ ሪፖርት በውስጡ ካካተታቸው ጉዳዮች መካከል “የመንግስትን ሀብት አመዳደብ” የሚመለከተው ይገኝበታል።
ሚኒስቴሩ በፕሮግራም በጀት ስርዓት መሰረት “ሀብትን ውጤታማ በሆነ መልኩ መደልደል” እና “ውጤታማነቱንና ወጪ ቆጣቢነቱን” የመከታተል እና የመገምገም ስራ ሲያከናውን መቆየቱን በሪፖርቱ አመልክቷል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2018 ለፌደራል መንግስት ያጸደቀው በጀት 1.9 ትሪሊዮን ብር ሲሆን ከእዚህ ውስጥ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች የተመደበው 1.3 ትሪሊዮን ብር ነው።

ለመስሪያ ቤቶቹ ከተመደበው የገንዘብ መጠን ውስጥ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለመክፈል ታቅዶ የነበረው አንድ ትሪሊዮን ብር ገደማ እንደነበር በሚኒስቴሩ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል። የፌደራል መንግስት ለዚህ ጊዜ ከያዘው እቅድ 81.1 በመቶውን ያህል ክፍያ ቢፈጽምም፤ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በበጀት አመቱ ላቀዷቸው ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ የገንዘብ “እጥረት” እንዳጋጠማቸው ሪፖርቱ ጠቁሟል።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች የእዚህ አመት በጀት በሚዘጋጅበት ወቅት ያላካተቷቸውን ስራዎች ለማስፈጸም የሚያስችላቸው ተጨማሪ ገንዘብ እንዲፈቀድላቸው ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል። አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ይህንን ተጨማሪ ገንዘብ የጠየቁት “ከተፈቀደላቸው በጀት ዝውውር በማድረግ መሸፈን ለማይችሏቸው” ስራዎች ማስፈጸሚያ እንደሆነም ለፓርላማ የቀረበው ሪፖርት አብራርቷል።
መስሪያ ቤቶቹ ተጨማሪውን ገንዘብ እንዲፈቀድላቸው የጠየቁት፤ የፌደራል መንግስት ለመጠባበቂያነት ከያዘው በጀት ውስጥ እንደሆነ ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ አመልክቷል። ለ2018 ዓ.ም ከጸደቀው የፌደራል መንግስት በጀት ውስጥ ለመጠባበቂያነት የተያዘው 269 ቢሊዮን ብር ነበር።

የገንዘብ ሚኒስቴር አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶቹ የጠየቁትን ተጨማሪ ገንዘብ “አስፈላጊነት ከገመገመ” በኋላል፤ ከመጠባበቂያ በጀት ውስጥ እስካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ 204.9 ቢሊዮን ብር ያህል መስጠቱን በሪፖርቱ አስታውቋል። ለአስፈጸሚ መስሪያ ቤቶች የተሰጠው ይህ ተጨማሪ የገንዘብ መጠን፤ በበጀት አመቱ ለመጠባበቂያነት ከተያዘው ውስጥ 76 በመቶውን ያህሉን የሚይዝ ነው።
ከተፈቀደላቸው በጀት በተጨማሪ ገንዘብ የተሰጣቸው አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ማንነት እና ብዛት በሚኒስቴሩ ሪፖርት አልተካተተም። ይህንን ጉዳይ የያዘውን የሚኒስቴሩን ሪፖርት ለማድመጥ የፓርላማው የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከትላንት በስቲያ ሰኞ በጠራው ስብሰባ ላይ፤ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጨምሮ ሌሎችም የግል መገናኛ ብዙሃን እንዳይገኙ በመከልከላቸው በዚህ ዘገባ ላይ ዝርዝር መረጃ ማካተት አልተቻለም። በጉዳዩ ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
