
አሜሪካ እና የባሕረ ሰላጤው አጋሮቿ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ካላቆመች ማዕቀብ እንዲጣልባት ወይም ሌላ እርምጃ እንዲወሰድባት የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ለተባበሩት መንግሥታት ማቅረባቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘገበ። ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “ሕገ ወጥ ክፍያዎችን” መጣሏን እንድታቆም እንዲሁም ፈንጂ የተጠመደባቸውን ቦታዎች በሙሉ በማሳወቅ የጉዞ ነጻነትን እንድትፈቅድ ይጠይቃል።
ጭምቅ ሃሳብ
- የሆርሙዝ ወሽመጥ ለእንቅስቃሴ ክፍት መሆኑን አሜሪካ አስታወቀች
- የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ከኢራን ጋር የተገባው የተኩስ አቁም ስምምነት “አልፈረሰም” አሉ
- በኢራን ጥቃት የተፈጸመበት የኤምሬትስ የነዳጅ ማዕከል ምን ያህል ወሳኝ ነው?
- እስራኤል በሊባኖስ 17 ሰዎችን በገደለች ማግሥት ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አወጣች
- ዓለም አቀፉ የነዳጅ ጫኝ መርከብ ባለቤቶች ማኅበር የአሜሪካ እጀባ ዕቅድ “ከፍተኛ ለውጥ አያመጣም” አለ
- ትራምፕ ኢራን የአሜሪካ መርከቦችን ካጠቃች “ከምድረ ገጽ ትጠፋለች” ሲሉ ዛቱ
- አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሳለች ሲሉ የኢራን ከፍተኛ ተደራዳሪ ገለጹ
- በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የደረሰው አዲስ ጉዳት ውስን እንደሆነ የአሜሪካ የስለላ መረጃ አመለከተ
- አሜሪካ በሰባት የኢራን ፈጣን ጀልባዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች
የቀጥታ ሽፋን
- ከ 3 ሰአት በፊትሳዑዲ አረቢያ የትራምፕ ሆርሙዝን የማስከፈት ዘመቻ እንዲቋረጥ ማድረጓን ኤንቢሲ ዘገበ
የፎቶው ባለመብት,REUTERSየአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መንቀሳቀስ ያልቻሉ መርከቦችን አጅቦ ለማስወጣት የነበራቸውን ዕቅድ ያቋረጡት በሳዑዲ አረቢያ ምክንያት መሆኑን ኤንቢሲ ዘገበ።ኤንቢሲ ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ሳዑዲ አረቢያ እሁድ ዕለት ትራምፕ ዕቅዳቸውን ይፋ ሲያደርጉ መደነቃቸውን ተናግረዋል።የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖችም ሆኑ የጦር ጄቶች ከሳዑዲ የልዑል ሱልጣን የአየር ኃይል መነሳት ወይም በሆርሙዝ ወሽመጥ መውጫ ያጡትን መርከቦች ለማጀብ በሚደረገው ዘመቻ የሳዑዲ አየር ክልል መጠቀም አንደማይችሉ መናገራቸውን ምንጮቹ ለኤንቢኤስ ተናግረዋል።ትራምፕ በጉዳዮ ላይ ከሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ቢነጋገሩም ሊያሳምኗቸው እንዳልቻሉ ጨምረው ተናግረዋል።ከዚህ በኋላ ትራምፕ ወሳኝ የሆነውን የአየር ክልል ‘ፕሮጀክት ፍሪደም’ ሲሉ ለሰየሙት ወታደራዊ ዘመቻ መጠቀም ስለሚያስፈልግ ዕቅዳቸውን ለጊዜው ለማዘግየት ወስነዋል ሲሉ ምንጮቹ ለኤንቢኤስ ተናግረዋል።አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን በኢራን ላይ ጦርነት በከፈተችበት ወቅት ሳዑዲ አረቢያ የጦር ሠፈሯን እና የኤር ክልሏን የዩናይትድ ስቴትስ ጦር እንዲጠቀምበት ፈቅዳ ነበር።አንድ የአሜሪካ ባለሥጣን ለኤንቢሲ አንደተናገሩት የሳዑደ አረቢያ ትብብር በቀጠናው ለሚደረግ ማንኛውም ዘመቻ ወሳኝ ነው።ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ይዘውት በነበረው ዕቅድ የጦር አውሮፕላኖች የመከላከያ ሽፋን ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ በቀጣናው የሚገኝ የአየር ክልልን መጠቀም አስፈላጊ አድርጎታል።ማክሰኞ ምሽት አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ቆመው የሚገኙትን መርከቦች እያጀበች ለማስወጣት ይዛ የነበረውን ዕቅድ “ለአጭር ጊዜ” እንደምታቆም ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስታውቀዋል።ሰኞ ዕለት የተጀመረው “ፕሮጀክት ፍሪደም” እንዲቆም የተደረገው ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት “ትልቅ መሻሻል” እያሳየ በመምጣቱ ምክንያት “በጋራ ስምምነት” ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ጨምረው ገልጸዋል።ያጋሩ, ሳዑዲ አረቢያ የትራምፕ ሆርሙዝን የማስከፈት ዘመቻ እንዲቋረጥ ማድረጓን ኤንቢሲ ዘገበ - ከ 5 ሰአት በፊትአሜሪካ እና አጋሮቿ ሆርሙዝ ካልተከፈተ ኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የውሳኔ ሃሳብ ለተመድ አቀረቡ
የፎቶው ባለመብት,Reutersአሜሪካ እና የባሕረ ሰላጤው አጋሮቿ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ካላቆመች ማዕቀብ እንዲጣልባት ወይም ሌላ እርምጃ እንዲወሰድባት የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ለተባበሩት መንግሥታት ማቅረባቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል (ኤፒ) ዘገበ።ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “ሕገ ወጥ ክፍያዎችን” መጣሏን እንድታቆም እንዲሁም ፈንጂ የተጠመደባቸውን ቦታዎች በሙሉ በማሳወቅ የጉዞ ነጻነትን እንድትፈቅድ ይጠይቃል።የተባበሩት መንግሥታት ወሳኝ እርዳታ፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች ምርቶችን በወሸመጡ የሚያልፍበት የሰብዓዊ ኮሪደር ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ኢራን “በአስቸኳይ እንድትሳተፍ እና እንድታመቻች” የሚል ጥያቄም መካተቱን ከውሳኔ ሃሳቡ እንደተመለከተ ኤፒ ዘግቧል።አሜሪካ እና የባሕረ ሰላጤው አጋሮቿ ይህን ዓይነቱን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሲያደርጉ የመጀመሪያው አይደለም። መጋቢት መጨረሻ ላይ በተካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት ለማድረግ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በቻይና እና በሩሲያ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ውድቅ ተደርጓል።አሜሪካ እና ኢራን ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸው የተገለጸው ከዚህ ስብሰባ ከሰዓታት በኋላ ነበር።የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማርኮ ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ፤ ኢራን ወሽመጡን ለመዝጋት በመሞከር፣ መርከቦችን እንደምታጠቃ በመዛት፣ የባሕር ፈንጂዎችን በማጥመድ እና ክፍያ ለመሰብሰብ በመሞከር “የዓለምን ኢኮኖሚ አግታ” መያዝ ቀጥላለች የሚል ክስ አቅርበዋል።ለፀጥታ ምክር ቤት የቀረበው ውሳኔ ሃሳብ በመጪዎቹ ቀናት ድምጽ ይሰጥበታል ብለው እንደሚጠብቁ ሩቢዮ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አሜሪካ በሰነዱ ላይ ያደረገችው “አነስተኛ ማስተካከያ” በምክር ቤቱ የሚገኙ የቴህራን አጋሮች ውድቅ እንዳያደርጉት የታለመ እንደሆነ ግን እርግጠኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።እንደ ኤፒ ዘገባ፤ በውሳኑ ሃሳቡ ላይ ኃይል መጠቀምን የሚፈቅድ አገላለጽን በማስወጣት ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን ይህም በማዕቀብ እንዲተካ ተደርጓል።ያጋሩ, አሜሪካ እና አጋሮቿ ሆርሙዝ ካልተከፈተ ኢራን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የውሳኔ ሃሳብ ለተመድ አቀረቡ - ከ 5 ሰአት በፊትሼል የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ ውስጥ በገባበት በዚህ ጊዜ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,ዓለም የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ በገጠማት ጊዜ ሼል ከፍተኛ ትርፍ አገኘበመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ከጀመረ በኋላ ባሉት ወራት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ የነዳጅ ምርት አቅራቢ ኩባንያው ሼል ከፍተኛ ማግኘቱ ተዘገበ።ሼል እንዳስታወቀው ባለፉት ሦስት ወራት ያገኘው ትርፍ ወደ 92.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህ የገንዘብ መጠን ከተጠበቀው በላይ እና ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ካገኘው የበለጠ መሆኑን ገልጿል።ባለፈው ሳምንት የሼል ተፎካካሪ የሆነው የብሪታኒያው የነዳጅ ድርጅት ቢፒ በተመሳሳይ ወቅት ከእጥፍ በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቆ ነበር።እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ከዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና ጋዝ የሚተላለፍበት ሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቷል። ይህ እርምጃ የነዳጅ ዋጋ በአራት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የተባለ ጭማሪ እንዲታይበት ምክንያት ሆኗል።በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የሚካሄደው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ የሆነው የብሬንት ነዳጅ ዋጋ በበርሜል 73 ዶላር ገደማ ነበረ።ጦርነቱ ከጀመረ በኋላ ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ከፍ እና ዝቅ ሲል ቆይቷል። የሆርሙዝ መከፈት እና መዘጋት እንዲሁም የጦርነቱ ማቆም እና መልሶ ማገርሸት በታየበት በዚህ ወቅት የተመዘገበው ከፍተኛ ዋጋ 120 ዶላር ነበር።በሁለት ወር ውስጥ የተመዘገበው ዝቅተኛ ዋጋ ከ100 ዶላር በታች ነው። አሁን የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 101 ዶላር ገደማ ደርሷል።ያጋሩ, ሼል የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ ውስጥ በገባበት በዚህ ጊዜ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ - ከ 5 ሰአት በፊትየኢራኑ ሚኒስትር ኢንተርኔት ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መፈቀዱን ተቹ
የፎቶው ባለመብት,NurPhoto via Getty Imagesየኢራን የሳይንስ፣ ምርምር እና ቴክሎኖጂ ሚኒስትር ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የተወሰደው ኢንተርኔት የመዝጋት እርምጃ እና አገልግሎቱ ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መፈቀዱን “ከብሔራዊ ደኅንነት የተቃረነ ተግባር ነው” ሲሉ ተቹ።ሚኒስትሩ ሆስኒ ሲማይ፤ “የኢንተርኔት አገልግሎት መገደቡ የአገሪቱን የሳይንሳ እና የምርምር ግንኙነቶች እያደናቀፈ ነው፤ ለጠቅላላው ሕዝብ የኢንተርኔት መቆራረጥ መቀጠሉም የብሔራዊ ደኅንነትን የሚቃረን ተግባር ነው” ብለዋል።የአገሪቱ መንግሥትም ቢሆን በኢንተርኔት በመዘጋቱ እንደማይስማማ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ “ይህ ሁኔታ የሚቀጥልበት ምክንያት ፕሬዝዳንቱን ራሱ አላሳመነም” ሲሉ ተናግረዋል።እንደ ሚኒስትሩ ሆስኒ ሲማይ፤ የኢንተርኔት አቅርቦት ለተወሰኑ ሰዎች ተፈቅዶ ሌሎችን “ማግለሉ፤ ከኢንተርኔት መቋረጥ የበለጠ አደገኛ ድርጊት ነው” የሚል አቋማቸውን ገልጸዋል።“የተለያዩ ደረጃዎችን መሠረት ያደረገ እና የተገደበ ኢንተርኔት መፈጠር የእኩልነት አለመኖር እና የማኅበራዊ ቅሬታ ስሜቶችን ያባብሳል” ብለዋል።የኢራን ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. አንስቶ ባሉት ሁለት ወራት ውስጥ የዓለም አቀፍ ኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።የኢራን ባለሥልጣናት እና ተቋማት በቅርቡ ‘ኢንተርኔት ፕሮ’ የተሰኘ አዲስ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል። ይህ የአገልግሎት ነጋዴዎች ወይም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተጨማሪ ክፍያ በመክፈል በተገደበ ደረጃ ዓለም አቀፍ ኢንተርኔትን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።ይህ አሠራር ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶበታል። ‘ነጭ ሲም ካርድ’ ተብሎ የሚጠራውን ይህንን አገልግሎት ለተወሰኑ ቡድኖች መፈቀዱ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት በመደብ የተከፋፈለ እንዲሆን ያደርጋል እንዲሁም በተለያዩ የሕብረሰተሰብ ክፍሎች መካከል ልዩነት ይፈጥራል የሚል ትችት አቅርበዋል።‘ነጭ ሲም ካርድ’ ተብሎ የሚጠራው አገልግሎት ከፍተኛ ፍጥነት ያለው እና ምንም ዓይነት የድረ ገጽ ዕገዳ የማይደረግበት የሞባይል ስልክ መስመር ነው። ይህ ሲም ካርድ ያላቸው ሰዎች ያለ ምንም ገደብ ኢንተርኔት መጠቀም እና ለጠቅላላው የኢራን ሕዝብ የታገዱ ድረ ገጾችን መጎብኘት ይችላሉ።ኢንተርኔት የተዘጋባቸው ኢራናውያን ስለሚከተሉት አማራጭ መንገድ ተጨማሪ ያንብቡ፦ የኢራን መንግሥትን የኢንተርኔት እገዳ ለማለፍ የስታርሊንክ ቴክኖሎጂን ወደ አገሪቱ የሚያስገባው ድብቅ መረብያጋሩ, የኢራኑ ሚኒስትር ኢንተርኔት ለተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መፈቀዱን ተቹ - ከ 7 ሰአት በፊትፈረንሳይ ሆርሙዝ ለሚካሄድ ተልዕኮ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን ማቀሳቀስ ጀመረች
የፎቶው ባለመብት,AFPየምስሉ መግለጫ,ቻርለስ ደ ጎል የተሰኘው እና በጣልያን እና ጀርመን ጦር መርከቦች የሚታጀበው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብአሜሪካ እና ኢራን የጣሏቸው እገዳዎች በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ባመጡት ጫና ምክንያት የቀረበውን የሰላም ዕቅድ እንዲስማሙበት እየጠየቀች ያለችው ፈረንሳይ፤ የሆርሙዝ ወሽመጥን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሊካሄድ ለሚችል ተልዕኮ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን በቀይ ባሕር ማንቀሳቀሷ ተዘገበ።ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በኢራን ጦርነት የተፈጠረው ሁኔታ በሚረጋጋበት ወቅት ወይም ጦርነቱ ሲቋጭ በወሽመጡ የሚደረግ ጉዞ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚያደርግ ዕቅድ ላይ ለበርካታ ሳምንታት ሲሠሩ መቆየታቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።ይህንን ዕቅድ ለመተግባር ከኢራን ጋር መቀናጀት ይጠይቃል። ሁለቱ አገራት ባዘጋጇቸው ስብሰባዎች ላይ የተገኙ በርካታ አገራት በተልዕኮው ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።የፈረንሳይ ጦር ባወጣው መግለጫ፤ ቻርለስ ደ ጎል የተሰኘው እና በጣልያን እና በጀርመን ጦር መርከቦች የሚታጀበው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ በደቡባዊ ቀይ ባሕር በኩል ጉዞ እንደጀመረ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።የጦር መርከቡ ስምሪት ቀጣናው የኦፕሬሽን ሁኔታውን የመገምገም እና ደኅንነትን ለማጠናከር የሚረዱ የቀውስ አስተደዳር አማራጮችን የማስፋት ዓላማ እንዳለው ጦሩ አስታውቋል።የአጋር አገራት ኃይሎች ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በሚጣጣም የመከላከያ ማዕቀፍ ስር እንዲቀናጁ የማስቻል ዓላማ እንዳለውም ተገልጿል።ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡ አንድ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ባለሥልጣን፤ “እያቀረብን ያለነው ዕቅድ ኢራን መርከቦቿን በወሽመጡ ማሳለፍ እንድትችል፤ በምላሹም የኒውክሌር ቁሶችን፣ ሚሳዔሎችን እና ቀጣናውን በተመለከተ ከአሜሪካውያን ጋር እንድትደራደር ነው” ብለዋል።“አሜሪካም በበኩሏ በሆርሙዝ ወሽመጥ የጣለችውን ዕገዳ በማንሳት፤ በምላሹ የኢራንን የድርድር ቁርጠኝነት ታገኛለች” ሲሉ የፈረንሳይን አቋም ገልጸዋል።ያጋሩ, ፈረንሳይ ሆርሙዝ ለሚካሄድ ተልዕኮ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቧን ማቀሳቀስ ጀመረች - ከ 8 ሰአት በፊትእስራኤል ቤይሩት ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላህ ጦር ከፍተኛ አዛዥ መገደሉ ተዘገበ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesእስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት አንድ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ በዋና ከተማዋ ቤይሩት ደቡባዊ ክፍል ውስጥ መገደሉን ከቡድኑ ጋር ቅርበት ያለው ምንጭ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ተናገረ።ይህ ጥቃት እስራኤል በሊባኖስ ላይ ስታካሂድ የቆየውን ወታደራዊ ዘመቻ ያስቆመው የተኩስ አቁም ከተደረሰ ከሁለት ሳምንት በኋላ ዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ የተፈጸመ የመጀመሪያው ጥቃት ነው።የሄዝቦላህ ምንጩ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንዳስታወቀው በእስራኤል ጥቃት የተገደለው የቡድኑ ከፍተኛ አዛዥ ማሊክ ባሉት እንደሚባል እና የሄዝቦላህ ራድዋን ጦር የዘመቻ አዛዥ መሆኑን ገልጿል።ያልተረጋገጡ ዘገባዎች እንዳሉት የሄዝቦላህ አዛዡ የተገደለው እስራኤል ዒላማ ባደረገችው ሕንጻ ውስጥ ከቡድኑ መሪዎች ጋር ስብሰባ እያደረገ ሳለ ነው።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በበኩላቸው የጦራቸው ጥቃት ዒላማ የሄዝቦላህ ራድዋን ጦር አዛዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የፎቶው ባለመብት,EPA
የፎቶው ባለመብት,Getty Images
የፎቶው ባለመብት,AFP via Getty Imagesያጋሩ, እስራኤል ቤይሩት ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት የሄዝቦላህ ጦር ከፍተኛ አዛዥ መገደሉ ተዘገበ - 7 ግንቦት 2026እስራኤል የሊባኖስ ተኩስ አቁም ከተፈረመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤይሩት ውስጥ ጥቃት ፈጸመች
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesእስራኤል ከሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለመግታት የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈጸመች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ ጥቃት ፈጸመች። ይህ የእስራኤል ጥቃት ግጭቱን ማስቆም ባልቻለው ስምምነት ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል።የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ሄዝቦላህ በሚገኝበት ዳሂዬህ በተሰኘው የከተማዋ ደቡባዊ ክፍል ውስጥ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ምሥሎች ከፍተኛ እሳት መከሰቱን እና ቢያንስ አንድ ሕንጻ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ያሳያሉ።የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባወጡት መግለጫ፤ የሄዝቦላህ ራድዋን ኃይል አዛዥን ዒላማ ያደረገው ጥቃት እንዲፈጸም ውሳኔ ያስተላለፉት ራሳቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት የታጣቁ ቡድኑ አባላት ስብሰባ ላይ ነበሩ። ሄዝቦላህ እስካሁን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም።ከሦስት ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መፈጸሙን ካስታወቁ ወዲህ ዳሂዬህ ውስጥ ጥቃት ሲደርስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።የተኩስ አቁሙ ቢፈረምም እስራኤል እና ሄዝቦላህ ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል፤ አንዳቸው ሌላኛቸውንም ጥሰት በመፈጸም ይከስሳሉ።አብዛኛው የእስራኤል የአየር ጥቃት የመታው ደቡባዊ ሊባኖስን ነው። የእስራኤል ጦር በዚህ የአገሪቱ ክፍል የሄዝቦላህ የጥቃት መሠረተ ልማት እና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ይናገራል።የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው አንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከ120 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። የሚኒስቴሩ ቁጥር የተዋጊዎች እና ንጹኃንን ቁጥር ለይቶ አላስቀመጠም።የእስራኤል ጦር በድንበር በኩል ያለውን የሊባኖስ መሬት ወርሮ ይዟል። ዓላማውም የሰሜናዊ እስራኤል ማኅበረሰቦችን ደኅንነት የሚያስጠብቅ ከሄዝቦላህ ነጻ የደኅንነት ቀጣና ማቋቋም እንደሆነ ባለሥልጣናቱ ይናገራሉ።እስራኤል በተቆጣጠረችው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ መንደሮችን ሙሉ በሙሉ በማውደም ጦሯ ጋዛ ውስጥ ካደረገው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት ፈጽማለች።ያጋሩ, እስራኤል የሊባኖስ ተኩስ አቁም ከተፈረመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤይሩት ውስጥ ጥቃት ፈጸመች - 7 ግንቦት 2026ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት በአሜሪካ የቀረበውን ዕቅድ እየገመገመች መሆኑን አስታወቀች
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesዋሽንግተን እና ቴህራን ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ፤ ኢራን በአሜሪካ የቀረበው የድርድር ዕቅድ “አሁንም እየታሰበበት” መሆኑን ገለጸች።የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ረቡዕ ዕለት ባወጣው ዘገባ፤ ዋይት ሀውስ 14 ነጥቦችን የያዘ የመግባቢያ ስምምነት ከኢራን ጋር ሊፈረም ይችላል የሚል እምነት እንዳለው አስነብቦ ነበር።አንድ ከፍተኛ የኢራን ፓርላማ አባል ጉዳዩን “ምኞት” ሲሉ አጣጥለውት የነበረ ቢሆንም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን ቴህራን በአሜሪካ የስምምነት እቅድ ላይ ያላትን አቋም ለፓኪስታን አደራዳሪዎች እንደምታሳውቅ ተናግረዋል።የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኢል ባጋኢ፤ “የአሜሪካ የውሳኔ ሐሳብ አሁንም በኢራን እየተገመገመ ነው፤ እንደተጠናቀቀ አስተያየቷን ለፓኪስታን ወገን ታሳውቃለች” ሲሉ ‘ኢስና’ ለተሰኘው ለኢራን ተማሪዎች የዜና ወኪል አስረድተዋል።የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው አገራቸው “ይህንን የተኩስ አቁም ወደ ዘላቂ የጦርነት ማቆሚያ ለመቀየር እየጣረች” መሆኑን ገልጸዋል።ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ አሜሪካ “ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ከኢራን ጋር እጅግ ጥሩ ንግግር አድርጋለች” ሲሉ ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ጠቁመዋል።የአክሲዮስ ዘገባ እንደሚያመለክተው ባለ አንድ ገጹ የመግባቢያ ስምምነት፤ በዝርዝር ለሚካሄድ የኒውክሌር ድርድር በማዕቀፍነት የሚያገለግሉ 14 ነጥቦችን ይዟል።ከስምምነት ነጥቦቹ መካከል ኢራን ኒውክሌር የማበልጸግ ተግባሯን እንድታቆም ስለማድረግ፣ ማዕቀቦችን ስለማንሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ ነጻ ጉዞን መመለስ የሚሉት ይገኙበታል።በዘገባው የተጠቀሱ ሁለት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንደተናገሩት፤ ኋላ የሚደረሰው የመጨረሻ ስምምነት የሚመሠረተው በዚህ ዕቅድ ውስጥ በተካተቱት ነጥቦች ላይ ነው።ሮይተርስ የዜና ወኪልም ባወጣው ዘገባ ይህንኑ ቢያረጋግጥም፤ እስካሁን ድረስ የስምምነቱ ነጥቦች ለሕዝብ ይፋ አልሆኑም።በኤክስ ገጻቸው አክሲዮስ ላወጣው ዘገባ ምላሽ የሰጡት የኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደኅነንት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኢብራሂም ረዛኢ፤ “አሜሪካውያን ፊት ለፊት በሚደረግ ድርድር ያላገኙትን ነገር እየተሸነፉ ባሉበት ጦርነት አያገኙትም” ብለዋል።ኢራን “ጣቷ ቃታው ላይ እንደሆነ እና ዝግጁ መሆኗን” የገለጹት ረዛኢ፤ አሜሪካ “እጅ ሰጥታ” ከአቋሟ ፈቀቅ የማትል ከሆነ ቴህራን “ከባድ እና ጸጸት የሚያመጣ ምላሽ” እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም አሜሪካ እርምጃ መውሰድ እንደምትጀምር ዝተዋል። ትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ኢራን ስምምነት ላይ ካልደረሰች “ድብደባው ይጀምራል፤ በሚያሳዝን ሁኔታም ከበፊቱ የበለጠ ከፍተኛ ደረጃ እና ክብደት ይኖረዋል” ብለዋል።ያጋሩ, ኢራን ጦርነቱን ለመቋጨት በአሜሪካ የቀረበውን ዕቅድ እየገመገመች መሆኑን አስታወቀች - 6 ግንቦት 2026ከአሜሪካ ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር ወደ ስምምነት አለመድረሱን የኢራን ባለሥልጣናት ተናገሩ
የፎቶው ባለመብት,Reutersየምስሉ መግለጫ,የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢብራሂም ባጊይአንድ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣን ከአሜሪካ ጋር ከስምምነት ለመድረስ መቃረቡን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች ከእውነታነት ይልቅ የአሜሪካ “ምኞት ናቸው” በማለት ውድቅ አደረጉ።የአሜሪካው የዜና ድረ ገጽ አክሲዮስ ከሰዓታት በፊት አሜሪካ ከኢራን ጋር በባለ 14 ነጥብ የሰላም መግባቢያ ሰነድ ላይ ከስምምነት መቃረቧን እንደምታምን ዘግቧል።በዚህ ዘገባ ላይ ምላሽ የሰጡት የኢራን ፓርላማ ከፍተኛ ባለሥልጣን ኢብራሂም ራዛኢ “አሜሪካ በፊት ለፊት ድርድር ያላገኘችውን ባልተሳካ ጦርነት አታገኘውም” ሲሉ ከስምምነት የመድረሱ ጉዳይ ገና መሆኑን አመልክተዋል።ባለሥልጣኑ በፋርስ ቋንቋ በኤክስ ገጽ ላይ ባወጡት መግለጫ ኢራን ለሚመጣው ጦርነት ዝግጁ መሆኗን በመግለጽ አሜሪካ የቀረበላትን ሃሳብ ተቀብላ ካልተስማማች ኢራን “ጸጸትን የሚያስከትል” እርምጃን ትወስዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።በተጨማሪም ከኢራን ጋር የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃት በአሜሪካ የቀረበው ሃሳብ አሁንም ገና ውሳኔ ያልተሰጠው መሆኑን የኢራን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ለአገራቸው ዜና ወኪል ገልጸዋል።ኢስማኤል ባጊይ እንደተናገሩት ኢራን በቀረበው የሰላም ስምምነት ሃሳብ ላይ ያላትን አመለካከት በፓኪስታን አደራዳሪዎች በኩል ለአሜሪካ እያሳወቀች እንደሆነም አመለክተዋል።ቃል አቀባዩ ጨምረውም የሚደረገው ድርድር ከመጥፎ እሳቤ ውጪ ‘በቅን ልቦና’ ሊሆን እንደሚገባው አገራቸው እንደምታምን በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።ያጋሩ, ከአሜሪካ ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር ወደ ስምምነት አለመድረሱን የኢራን ባለሥልጣናት ተናገሩ - 6 ግንቦት 2026የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሆርሙዝ እንደሚከፈት ፍንጭ ሲሰጥ፣ ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ሰጡ
የፎቶው ባለመብት,Reutersአሜሪካ እና ኢራን ወደ ስምምነት እየተቃረቡ መሆናቸው እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥ ሊከፈት የሚችልበት ዕድል እንዳለ ፍንጭ ሰጠ።ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን የቀረበውን ስምምነት ካልተቀበለች ከፍተኛ ጥቃት እንደሚጠብቃት አስጠንቅቀዋል።አብዮታዊ ዘቡ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው “የወራሪዎች ስጋት የሚያበቃ ከሆነ” ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ መስመር መልሶ የሚከፈትበት ሁኔታ መቃረቡን አመለክቷል።መግለጫው ጨምሮም “የወራሪዎች ስጋት ሲያበቃ በአዲሱ አሠራር አሠራር መሠረት በወሽመጡ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች ዘላቂ እና አስተማማኝ ይሆናል” በማለት ኢራን ያወጣችው ወሽመጡን የማስተዳደር ደንብ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጿል።ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ጦርነቱ እና የሆርሙዝ መዘጋት ከኢራን ጋር በሚደረስ ስምምነት እንደሚያበቃ፤ ነገር ግን ኢራን ከስምምነት የማትደርስ ከሆነ የቦምብ ድብደባው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ኢራን “የተስማማንበትን የምትፈጽም ከሆነ” የተከፈተባት ጦርነት እንደሚያበቃ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ “ኢራንን ጨምሮ ለሁሉም ክፍት ይሆናል” ብለዋል።በተጨማሪም ትራምፕ ኢራን ከስምምነት የማትደርስ ከሆነ “የቦምብ ድብደባው ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን መካሄድ ይጀምራል” በማለት ማስጠንቅቀዋል።በፓኪስታን አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የሁለቱ አገራት ድርድር ከስምምነት ወደ ሚደረስበት ደረጃ እየተቃረበ መሆኑን የተለያዩ ምንጮች እየጠቆሙ ነው።ያጋሩ, የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሆርሙዝ እንደሚከፈት ፍንጭ ሲሰጥ፣ ትራምፕ ማስጠንቀቂያ ሰጡ - 6 ግንቦት 2026ቻይና በተቻለ ፍጥነት የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም እንዲከፈት ጠየቀች
የፎቶው ባለመብት,Anadolu via Getty Imagesየቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ከኢራኑ አቻቸው ጋር በተወያዩበት ወቅት የሆርሙዝ ወሽመጥ “በተቻለ ፍጥነት” ዳግም እንዲከፈት ጠየቁ።ረቡዕ ዕለት በቤይጂንግ የተገናኙት ባለሥልጣኖቹ በሁለትዮች ጉዳዮች በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተዘግቧል።የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ቤይጂንግ የሄዱት ከዶናልድ ትራምፐ ይፋዊ ጉብኝት አንድ ሳምንት ቀድመው ነው።ዋንግ ዪ “ቻይና ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ አስቸኳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ታምናለች፣ ግጭት ዳግም መቀስቀስ አስፈላጊ አይደለም” ማለታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።“የባህር ወሽመጡን በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መደበኛ እና ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ ረገድ የጋራ ስጋት አለው፤ ቻይናም የሚመለከታቸው አካላት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሚመጣው ጠንካራ ጥሪ በተቻለ ፍጥነት ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ ታደርጋለች።ቤይጂንግ በተደጋጋሚ አሜሪካ እና ኢራን እንዲደራደሩ ጥሪ የምታቀርብ ሲሆን ረቡዕ ዕለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ደግመዋል።ዋንግ አክለውም ቤይጂንግ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ላለማምረት ያላትን ቁርጠኝነት ማድነቃቸውን የቻይና የመንግሥት ሚዲያ ዘግበዋል።ያጋሩ, ቻይና በተቻለ ፍጥነት የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም እንዲከፈት ጠየቀች - 6 ግንቦት 2026አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ያስቆማል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ ሊፈራረሙ ነው- ሮይተርስ
የፎቶው ባለመብት,Reutersሮይተርስ የዜና ወኪል የፓኪስታን ምንጮችን ጠቅሶ አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል አንድ ገጽ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም መቃረባቸውን ዘገበ።በስም ያልተጠቀሱት ምንጮቹ ለሮይተርስ “በቅርቡ እናፈራርማለን፤ በጣመ ተቃርበናል” ሲሉ ተናግረዋል።አክሲዮስ በበኩሉ ዋይት ሐውስ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስቸል ሰነድ ላይ ለመፈራረም መቃረቡን እንደሚያምን ዘግቧል።ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ማናገሩን እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የተሰጣቸው ሁለት ሌሎች ምንጮችን የጠቀስው መገናኛ ብዙኃኑ የመግባቢያ ሰነዱን ሊፈረም መሆን አረጋግጠዋል።ባለ አንድ ገጽ ነው የተባለው የመግባቢያ ሰነድ ስለ ኒውክሌር ድርድር ማዕቀፍን እንደሚያስቀምጥ ተጠቅሷል።ከእነዚህም መካከል የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም መቋረጥ፣ የማዕቀብ መነሳት እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ያለ ምንም እክል መርከቦች እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ በሰነዱ ላይ መካተታቸው ተዘግቧል።በሁለቱ አገራት ንግግር ውስጥ የኒውክሌር ፕሮግራም መቋረጥ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈት ሳያግባቧቸው የቆዩ ጉዳዮች ናቸው።አክሲዮስ ምንጮችን ጠቅሶ በርካቶቹ በሰነዱ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች የመጨረሻ ስምምነት እንዳልተደረሰባቸው ዘግቧል።ዩናይትድ ስቴትስ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውሰጥ ከቴህራን ምላሽ ለማግኘት እየጠበቀች ሲሆን እስካሁን ምንም ዓይነት ስምምነት የተደረሰበት ነገር አለመኖሩን ምንጮችን ጠቅሶ አክሲዮስ ዘግቧል።ቢቢሲ ከዋይት ሐውስን እንዲሁም ከኢራን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።ያጋሩ, አሜሪካ እና ኢራን ጦርነቱን ያስቆማል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ ሊፈራረሙ ነው- ሮይተርስ - 6 ግንቦት 2026የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በ26 መርከቦች ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል
የፎቶው ባለመብት,Royal Thai Navyየኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በመካከለኛው ምሥራቅ 26 መርከቦች ላይ ጥቃቶች ደርሰዋል ሲል የዩኬ የባህር ትራንስፖርት ንግድ ተቋም (ዩኬኤምቲኦ) ገለጸ።ከየካቲት 21 ጀምሮ በባህረ ሰላጤው፣ በኦማን ባሕረ ሰላጤ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ እና አካባቢው 46 ክስተቶች እንደደረሱት አሳውቋል።ከእነዚህ ውስጥ 26ቱ ጥቃቶች ሲሆኑ 18ቱ ደግሞ “አጠራጣሪ እንቅስቃሴ” እንደነበሩ እና ሁለት የጠለፋ ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ሪፖርት ተደርጓል።በሌላ በኩል የፈረንሳይ የመርከብ ተቋም የሆነው ሲኤምኤ ሲጂኤም ዛሬ ጠዋት እንደገለጸው ሳን አንቶኒዮ የተባለው መርከብ ማክሰኞ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥን ሲያቋርጥ የጥቃት ዒላማ ሆኖ በመርከቡ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።በጥቃቱ የተጎዱት የመርከቡ ሠራተኞች ከአካባቢው መውጣታቸውን እና የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል ተብሏል።ተቋሙ አክሎም “ሲኤምኤ ሲጂኤም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ከመርከበኞቹ ጎን ይቆማል” ብሏል።ያጋሩ, የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በ26 መርከቦች ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል - 6 ግንቦት 2026ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች
የፎቶው ባለመብት,Reutersኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ድርድር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ካልሆነ በስተቀር እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።ማክሰኞ ዕለት ዶናልድ ትራምፕ ከቴህራን ጋር የሚደረገው ንግግር “ትልቅ መሻሻል” እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።ቤጂንግ የሚገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “በድርድሩ ሕጋዊ መብቶቻችን እና ጥቅሞቻችንን ለመከላከል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲሉ መናገራቸውን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።አባስ አራግቺ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ከተገናኙ በኋላ “ፍትሃዊ እና የተሟላ ስምምነትን ብቻ” እንቀበላለን ማለታቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።አራግቺ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ንግግር ለመደገፍ በሚል በሆርሙዝ ወሽመጥ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለማጀብ ጀምረውት የነበረውን ዘመቻ ስለማቆማቸው ያሉት ነገር የለም።የሆርሙዝ ወሽመጥ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ለመርከቦች እንቅስቀቃሴ ዝግ ሆኗል።በዚህም የተነሳ የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና ጋዝ አቅርቦት በመስተጓጎሉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተከስቷል።ትራምፕ በትናንትናው ዕለት “በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ እየቀጠለ ሳለ ፕሮጀክት ፍሪደም. . . ስምምነቱ ይጠናቀቅ እና ይፈረም እንደሆነ ለማየት ለአጭር ጊዜ እንዲቆም በጋራ ተስማምተናል” ብለዋል።የትራምፕን የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፍ ተከትሎ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በ1.2 በመቶ ቅናሽ በማሳየት በበርሜል 108.6 ዶላር መሸጥ ጀምሯል።ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢራን በሆርሙዝ ላይ የሚደረግን እንቅስቃሴ ልትቆጣጠር አይፈቀድላትም ሲሉ ተናግረዋል።ያጋሩ, ኢራን ከአሜሪካ ጋር “ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ማድረግ እንደምትፈልግ ገለጸች - 6 ግንቦት 2026የቻይና እና የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቤይጂንግ ተገናኝተው ተወያዩ
የፎቶው ባለመብት,Tasnimየቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረቡዕ ዕለት የኢራኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺን ተቀብለው ማነጋገራቸው ዢንዋ ዘገበ።አራግቺ አገራቸው ከአሜሪካ እና እስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ወዲህ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመርያቸው ነው።የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቤይጂንግ የተገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከመምጣታቸው ጥቂት ቀን ቀደም ብሎ ነው።የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዢንዋ አራግቺ በቤዢንግ የተገኙት በቻይና መንግሥት ግብዣ መሆኑን ተናግረዋል።አራጋቺ ቻይና ከገቡ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጀመሩትን ዘመቻ ለጊዜው መቆሙን ሲያስታውቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው አሜሪካ ዓላማዎቿን በማሳካቷ ኢራን ላይ የከፈተችው የማጥቃት ዘመቻ “አብቅቷል” ሲሉ ተናግረዋል።የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በሁለትዮሽ ጉዳዮች በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚወያዩ ተናግረዋል።ሁለቱ ሚኒስቴሮች የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሦስት ጊዜ በስልክ የተወያዩ ሲሆን ቤጂንግ በተደጋጋሚ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረስ እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ለንግድ መርከቦች ክፍት እንዲሆን ሲጠይቁ ቆይተዋል።ከጦርነቱ በፊት 20 በመቶ የዓለም ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ የሚያልፈው በወሽመጡ በኩል ነበር።ነገር ግን ከጦርነቱ በኋላ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ በእጅጉ ተስተጓጉሏል።ቻይና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ነዳጅ እና ጋዝ ከሚገዙ አገራት ግንባር ቀደሟ ናት።ያጋሩ, የቻይና እና የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቤይጂንግ ተገናኝተው ተወያዩ - 6 ግንቦት 2026ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ስላካሄዱት ‘ፕሮጀክት ፍሪደም” ምን እናውቃለን?
የፎቶው ባለመብት,Reutersፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መንቀሳቀሻ አጥተው የቆሙትን መርከቦች አጅበው ለማስወጣት ይዘውት የነበረውን ዕቅድ ለጊዜው ማቆማቸውን ተናግረዋል።ትራምፕ ዘመቻው ሰብዓዊ አላማ እንዳለው “ሰዎችን ነጻ ማውጣት፣ ኩባንያዎችን እና ምንም ጥፋት የሌለባቸውን አገራት ነጻ ማውጣት ማለት ው” ሲሉ ተናግረው ነበር።ኢራን መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፍ የሚችሉት በእርሷ ፈቃድ ብቻ መሆኑን ተናግራለች።ትራምፕ ይህንን ዘመቻ ይፋ አድርገው የነበረው እሁድ ዕለት ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የኢራን ጦር ወደ ወሽመጡ ለመግባት የሞከረ የአሜሪካ ጦር መርከብ ላይ መተኮሱን ሲናገር አሜሪካ በበኩሏ አነስተኛ ጀልባዎችን መትታ ማስመጧን ተናግራለች።አሜሪካ ይህንን ዘመቻ ይፋ ካደረገች ከሁለት ቀናት በኋላ፣ ማክሰኞ ዕለት ትራምፕ ከኢራን ጋር ከስምምነት ላይ መድረስ ይቻል እንደሆነ ለማየት በሚል ዘመቻው ለአጭር ጊዜ እንደሚቆም ተናግረዋል።የሆርሙዝ ወሽመጥ የተዘጋው እስራኤል እና አሜሪካ ከየካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ቴህራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ኢራን በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ ነው።ቴህራን የዓለም 20 በመቶ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነውን ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።አሜሪካ 22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች መንቀሳቀሻ አጥተው መቆማቸውን ትናገራለች።እነዚህ ባህረተኞች የ87 አገራት ዜጎች መሆናቸውን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አዛዥ አድሚራል ብራድ ኩፐር ተናግረዋል።ሰኞ ዕለት ሴንትኮም የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መሰማራቱን ገልጾ ነበር።ኢራን የአሜሪካ ዘመቻ ከመጀመሩ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብላ ማስጠንቀቂያ በማውጣት ወደ ወሽመጡ ለመግባት የሞከሩ የአሜሪካ መርከቦች ላይ ሁለት ሚሳዔሎችን መተኮሷን ተናግራለች።ሴንትኮም የኢራንን መግለጫ ወዲያውኑ ውድቅ አድርጓል። አክሎም ኢራን ወደ ጦር መርከብ እና የአሜሪካ ባንዲራ ወደምታውለበልብ የንግድ መርከብ ሚሳዔሎችን እና ድሮኖችን መተኮሷን እንዲሁም አነስተኛ ጀልባዎች በመጠቀም ጥቃት ለመፈጸም መሞከሯን ተናግሯል።ዩኤኢ ከኢራን በተተኮሱ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች ጥቃት እንደደረሰባት አስታውቃለች።በጥቃቱም የነዳጅ ማከማቻ ስፍራ መመታቱን ነገር ግን በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስታውቃች።በወሽመጡ በዩኤኢ አቅራቢያ የቆመ የደቡብ ኮሪያ የጭነት መርከብም ጥቃት እንደደረሰበት ተገልጿል።የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ሴንቲኮም አሜሪካ ሂሊኮፕተሮችን ስድስት አነስተኛ ኢራን ጀልባዎች መትተው ማስመጣቸውን አሰታውቋል። ኢራን ግን እህንን አስተባብላለች።ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ለማለፍ አገዛዙን ፈቃድ በማይጠየቁ ላይ “ወሳኝ እርምጃ እወሰዳለሁ” ስትል አስጠንቅቃለች።ይህ በእንዲህ አንዳለ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በሰጡት መግለጫ ላይ የተኩስ አቁሙ አለመክሸፉን ተናግረዋል።ያጋሩ, ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ስላካሄዱት ‘ፕሮጀክት ፍሪደም” ምን እናውቃለን? - 6 ግንቦት 2026ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ ዓላማዎቿን በማሳካቷ ኢራን ላይ የከፈተችው የማጥቃት ዘመቻ “አብቅቷል” አሉ
የፎቶው ባለመብት,EPAየአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ማክሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ በሰጡት መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ ዓላማዎቿን በማሳካቷ በኢራን ላይ የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ “መጠናቀቁን” ገለጹ።አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም የጀመረችው የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ነበር።ሩቢዮ በዋይት ሐውስ በሰጡት በዚህ መግለጫ “ኦፕሬሽን ኢፒክ ፉሪ ተጠናቅቋል። የዘመቻውን ዓላማዎቻችንን አሳክተናል፤ . . . የሰላም መንገድን እንመርጣለን። ፕሬዚዳንቱ ከስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።ሩቢዮ አሜሪካ ሰኞ ዕለት አዲስ የጀመረችው ዘመቻ ዓላማ የሆርሙዝ ወሽመጥን ማስከፈት መሆኑን ተናግረዋል።ይህ አነስተኛ መጠን ያለው ዘመቻ ከመጀመርያው ወታደራዊ ዘመቻ የተለየ መሆኑን በመግለጽ አሜሪካ “ካልተተኮሰባት በስተቀር” ወታደራዊ ምላሽ እንደማትሰጥ ተናግረዋል።አሜሪካ በኢራን ኣለይ ጦርነት የከፈተችበት አንዱ ምክንያት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳታመርት ለመከላከል ነው።አሜሪካ የኢራንን በከፍተኛ ደረጃ የበለጸገ 408 ኪሎ ግራም ዩራኒየም ማውጣት እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ማስደረግ እስካሁን ድረሰ አልቻለችም።
የፎቶው ባለመብት,Amirhosein Khorgooi/ISNA/WANA (West Asia News Agency) via REUTERSሩቢዮ በመግለጫቸው ላይ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ መንቀቀሳቀስ ላልቻሉ መርከቦች መንገዱን ለማስከፈት የተጀመረው ዘመቻ ከ87 አገራት የተውጣጡ የ23ሺህ ሰዎችን ሰቆቃ የሚያስቆም ነው ብለዋል። በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ባለው ግጭት ምክንያት እስካሁን ድረስ 10 ባህረተኞች መሞታቸውን ተናግረዋል።“ተነጥለው ነው ያሉት፤ እየተራቡ ነው፥ ተጋላጭ ናቸው። ቢያንስ 10 ባህረተኞች በዚህ የተነሳ ሞተዋል፤ ሲቪል ባህረተኞች” ብለዋል።ሩቢዮ ሞቱ ስላልዋቸው ባህረተኞች ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሩቢዮ ከበርካታ መርከቦች ጋር የሆርሙዝ ወሽመጥን አቋርጦ ስለመውጣት በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።ሩቢዮ አሁን ጊዜው ቴህራን “የሁኔታውን እውነታ የምትቀበልበት ነው” በማለት የአሜሪካ ልዑካን የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነር የዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ መፈለጋቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።ሩቢዮ አክለውም መፍትሄው ኢራን “የሆነ ስፍራ የደበቀችውን የኒውክሌር ቁስ ይመለከታል” ሲሉ ተናግረዋል”ፕሬዚዳንቱ የድርድር ሂደቱ አካል የበለጸገው [ዩራኒየም] ብቻ ሳይሆን የሆነ ስፍራ የቀበሩትን ቆፍረው ማውጣት ከቻሉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ ነው ” ብለዋል።ሩቢዮ በሁለቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ነው ስለሚባለው ውይይት ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።“ይህ በጣም ውስብስብ ነው፤ በጣም ቴክኒካዊ ነው። ነገር ግን እነሱ ለመደራደር ፍቃደኛ ስለሆኑባቸው ርዕሰ ጉዳዮች እና እነዚያን ንግግሮች ጠቃሚ ለማድረግ በግንባር ቀደምትነት ሊያደርጉት ስለሚችሉት መጠን በጣም ግልፅየሆነ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊኖረን ይገባል” ብለዋል።ያጋሩ, ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ ዓላማዎቿን በማሳካቷ ኢራን ላይ የከፈተችው የማጥቃት ዘመቻ “አብቅቷል” አሉ - 5 ግንቦት 2026ዶናልድ ትራምፕ ኢራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት አለባት” አሉ
የፎቶው ባለመብት,Reutersፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት የኢራን ጦር አቅምን አጣጥለው ቴህራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት” ነበረባት ግን ያንን ለማድረግ የቴህራን ባለሥልጣናት ትምክህት ይዟቸዋል አሉ።ትራምፕ በኦቫል ኦቪስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የኢራን ጦር ደካማ መሆኑን እና “የመጫወቻ ጠመንጃዎች” ይጠቀማሉ ሲሉ ተሳልቀዋል።ኢራን በአደባባይ የምትለው ሌላ ቢሆንም በምስጢር ግን ከስምምነት መድረስ ትፈልጋለች ሲሉም ተናግረዋል።“ጨዋታ ይጫወታሉ። ነገር ግን አንድ ነገር ልንገራችሁ፤ ከስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ። ጦሩ ሙሉ በሙሉ ከወደመበት ማን የማይፈልግ አለ” ብለዋል።የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ኢራን ምንም አማራጭ የላትም” በማለት የቴህራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር ሲነጋገሩ እና ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርቡ የተለያየ ነገር ይናገራሉ ሲሉ ተችዋቸዋል።“ምንም አማራጭ የላትም፤ ኖሯትም አያውቅም” በማለት የኢራን ጦር መሸነፉን ዳግም ተናግረዋል።የኢራን ጦር ባሕር ኃይል፣ አየር ኃይል ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲኖራቸው አንፈቅድም” ሲሉ አስተየየታቸውን ሰጥተዋል።አሜሪካ “ኢራንን ክፉኛ ደቁሳታለች” ያሉት ትራምፕ “በጠመንጃ ብቻ ጥቂት ጀልባዎችን መቀነስ ችለናል” ብለዋል።ሰኞ ዕለት አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የነበሩ የኢራን ጀልባዎችን መምታቷን አስታውቃለች።ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ በኢራን በመዘጋቱ መውጫ አጥተው የቆዩ መርከቦችን እንደሚያስወጡ የተናገሩት ትራምፕ፤ “ሰባት ትንሽ ጀልባዎችም ወይም እነሱ ‘ፈጣን’ ጀልባ የሚሏቸውን መትተናል። የቀሯቸው እነሱ ብቻ ነበሩ” ብለዋል።ትራምፕ በኦቫል ኢፊስ በሰጡት መግለጫ ኢራን በጦርነቱ መጀመርያ ወቅት 159 መርከቦች እንደነበሯት ገልጸው “ያሏቸው እያንዳንዱ መርከብ ከባሕር ወለል በታች ነው የሚገኙት’ ሲሉ ተናግረዋል።በባሕር ኃይላቸው ምንም ዓይነት መርከብ የላቸውም ያሉት ትራምፕ ከዚያ ይልቅ ስምንት “ትንሽ ጀልባዎች” ነበሩ እነርሱም “ሁሉም ወድመዋል” ብለዋል።አክለውም “ከእኛ ታላቅ ባሕር ኃይል ጋር ለመገዳደር ትንንሽ ጀልባ እየፈለጉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የፎቶው ባለመብት,REUTERSኢራን የተኩስ አቁሙን ጣሰች የሚባለው ምን ስታደርግ ነው ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ “ስለምነግራችሁ ታውቁታላችሁ” በማለት መልሰዋል።“በጣም አስፈላጊው ነገር ምን ማድረግ እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው ያውቃሉ” ብለዋል።ኢራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት አለባት” ያሉት ትራምፕ “ይህ መደበኛ ውጊያ ቢሆን ኖሮ ይሄኔ አቁመውት ነበር” ብለዋል።አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ማገዷን በተመለከተም ሲናገሩ አንድም መርከብ ማለፍ እንዳልቻለ አብራርተዋል።አንድ መርከብ ለማለፍ ሲሞክር ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው በኋላ የአሜሪካ ጦር “በአንድ ተኩስ ሞተሩን መትቶታል” ብለዋል።ትራምፕ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር “ትልልቅ ስምምነቶችን” እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቻይና በሚጓዙበት ወቅት ከፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋርም መልካም ንግግር ይኖራል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።ትራምፕ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ ጣለችው እገዳ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ቴህራን “ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች” ብለዋል።“ጨዋታ ይጫወታሉ። የምነግራችሁ ነገር ግን ከስምምነት መድረስ ይፈልጋሉ” ብለዋል።ያጋሩ, ዶናልድ ትራምፕ ኢራን መሸነፏን አምና “እጇን መስጠት አለባት” አሉ - 5 ግንቦት 2026የሆርሙዝ ወሽመጥ ለእንቅስቃሴ ክፍት መሆኑን አሜሪካ አስታወቀች
የፎቶው ባለመብት,Reutersየአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት እና የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን በጋራ በመሆን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት መሆኑን ተናገሩ።የመከላከያ ሚኒስትሩ አሜሪካ “ጦርነት አትፈልግም” ያሉ ሲሆን ነገርግን ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታ እንድትቀመጥ እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።ሚኒስትሩ አክለውም የ’ፕሮጀክት ፍሪደም’ ግብ “ገለልተኛ የሆኑ የንግድ መርከቦችን ከኢራን ጥቃት መከላከል” መሆኑን ተናግረዋል።ሄግሴት አክለውም ሁለት የአሜሪካን ባንዲራ የሚያውለበልቡ መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፋቸውን ገልጸው “መስመሩ ነጻ ነው” በማለት ኢራናውያን “ተዋርደዋል” ሲሉ አስታውቀዋል።የተኩስ አቁሙ “አልፈረሰም” ያሉት ሄግሴት ኢራን ዳግም ግጭቱን ላለመጀመር “እንድትጠነቀቅ” አሳስበዋል።
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው መንቀሳቀሰሻ አጥተው መቆማቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን በበኩላቸው ኢራን የተኩስ አቁሙ ከተጀመረ አንስቶ አስር ጊዜ ያህል የአሜሪካ ጦር ላይ ጥቃት ፈጽማለች ሲሉ ከስሰዋል።አክለውም እነዚህ ጥቃቶች “በአሁን ሰዓት” ጦርነቱን ለመጀመር “ከመስፈርቱ በታች” ናቸው ብለዋል።ኬን ኢራንን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ያለውን የዓለም አቀፉን የአቅርቦት ሰንሰለት “እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም” የወነጀሏት ሲሆን የመላው ዓለም ምጣኔ ሃብትን “አግታ ለመያዝ ጥረት አድርጋለች” ብለዋል።22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው መንቀሳቀሰሻ አጥተው መቆማቸውንም ጄነራሉ በመግለጫቸው ላይ ተናገረዋል።ያጋሩ, የሆርሙዝ ወሽመጥ ለእንቅስቃሴ ክፍት መሆኑን አሜሪካ አስታወቀች - 5 ግንቦት 2026የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ከኢራን ጋር የተገባው የተኩስ አቁም ስምምነት “አልፈረሰም” አሉ
የፎቶው ባለመብት,Reutersየአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር በሆርሙዝ ወሽመጥ ጥቃት ቢቀጥልም አገራቸው ከኢራን ጋር የገባችው የተኩስ አቁም ስምምነት “አልፈረሰም” አሉ።የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አሜሪካ እና ኢራን ሰኞ ዕለት ጥቃት መፈጸማቸውን ቢቀጥሉም የተኩስ አቁሙ ባለበት መሆኑን ተናግረዋል።የተኩስ አቁሙ “አልፈረሰም” ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ አሜሪካ ሰኞ ዕለት በወሽመጡ የጀመረችውን ዘመቻ “የተለየ፣ የተናጠል ፕሮጀክት ነው” ብለዋል።ኢራን ዳግም ግጭቱን ላለመጀመር “እንድትጠነቀቅ” አሳስበው “አሁን የተኩስ አቁሙ ባለበት” መሆኑን ተናግረዋል።የአሜሪካ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን በበኩላቸው ኢራን ዘጠኝ ጊዜ የንግድ መርከቦች ላይ መተኮሷን ተናግረዋል።ቴህራን ሁለት የጭነት መርከቦችን መቆጣጠሯን የገለጹት ጄነራሉ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጀመረ ጀምሮ 10 ጊዜ የአሜሪካ ጦር ላይ ጥቃት ፈጽማለች ሲሉ ወንጅለዋታል።ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ዳን ኬን ኢራን ላይ ሙሉ በሙሉ ጥቃት ለመጀመር አሁን ጊዜው አይደለም ያሉት ሲሆን፣ የቴህራን ሚሳዔሎች፣ ድሮኖች እና አነስተኛ ጀልባዎች በትናንትናው ዕለት በአሜሪካ ጦር ላይ የፈጸሙት ጥቃትን መመከታቸውን ተናግረዋል።22,500 ባህረተኞች እና 1,550 የንግድ መርከቦች በባሕረ ሰላጤው መንቀሳቀሰሻ አጥተው መቆማቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።ያጋሩ, የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ከኢራን ጋር የተገባው የተኩስ አቁም ስምምነት “አልፈረሰም” አሉ
