”ታማኝ ሆይ! መከፋትህ የሁላችንም መከፋት ቢሆንም የከፈልከው ዋጋ ግን ከንቱ ሆኖ አይቀርም”

ከሰሞኑን በአንድ የሽልማት መድረክ ላይ አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የተናገረው ንግግር፣ የአንድን ታላቅ ሰው የግል ስሜት ብቻ ሳይሆን ፣ ብዙ ነገራችንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው ። “24 ሰዓት እኔ ከተኛሁ ኢትዮጵያ አንድ ነገር ትሆንብኛለች የሚል ስስት ነበር ያለኝ… ለዚህ ያተረፍኩት ቁስል ብቻ ነው” ሲል ቃላቱ በደም እንደተጠመቁ ይሰማሉ። ይህ ንግግር ለሀገር የኖረ ሰው “በቃኝ” ሲል የሚሰማው የመጨረሻው የልብ ስብራት ድምፅ ነው።

ታማኝ ለዘመናት የገዛ ምቾቱን፣ ቤተሰቡንና ዝናውን መስዋዕት አድርጎ ሲደከም የኖረው ለዝና አልነበረም። እሱ የፈለገው ኢትዮጵያን ነበር ፤ ያተረፈው ግን በመርዝ የተለወሰ የክህደት ምላሽ ነው። ለሀገሩ ሲል የልጆቹን ፍቅር በጊዜ ያልተካፈለ፣ ዛሬ ላይ ቆሞ “ቅድሚያ ልጆቼን መውደድ ብቻ ነው” ብሎ እንዲያዝን የተገደደው፣ የቆመላት ሀገርና የደከመለት ህዝብ በባለጌዎች ስድብና በሴረኞች ዘመቻ ልቡን ስላደሙት ነው።

ታማኝ ሆይ! መከፋትህ የሁላችንም መከፋት ቢሆንም የከፈልከው ዋጋ ግን ከንቱ ሆኖ አይቀርም። አንተ ስለ ኢትዮጵያዊነት የዘመርከው ዜማ፣ ያፈሰስከው እንባህና የደከምክበት ድካም በብዙዎች ልብ ውስጥ የጽናት ዘር ሆኖ ይኖራል ፣ ይበቅላል !

“በህዝባዊ በዓል መገኘት ያመኛል” እስክትል ድረስ የቆሰልክበት ያ የቅንነት መንገድ ታሪክ በወርቅ ቀለም የሚመዘግበው እንጂ በባለጌዎች ስድብ የሚረክስ አይደለም። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ጩኸት መሬት ላይ ያለውን እውነት አይቀይረውም።

ውለታህን የማይረሳ ላንተ ጥልቅ አክብሮት ያለው ብዙ ሰው ከጎንህ አለ፤ የተሰበረው ልብህ የሚጠገንበት የለፋህላት ኢትዮጵያ ከፍ ብላ የምትታይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። እስከዚያው ግን ለልጆችህ የምትሰጠው ፍቅር ካሳ ይሁንህ 🙏

በይድነቃቸው ከበደ

See less