

አንዳርጋቸው አሰግድ
መግቢያ
አማረ ተግባሩ “ ” ከአዲስ አቤበነት እስከ ሉላዊነት በሚል ርዕስ ባሳተመው መፅሐፍ ውስጥ ስለእኔ ያወሳባቸውን ገጾች ተመለከትኳቸው። ራሴን በ መጀመሪያ የጠየቅኩት፣ አሁን ከርሱ ቅጥፈቶች ጋር መመላለስ ይገባኛል ወይ? በማለት ነበር። ቆየት ሲል፣ አማረ በቆርጦ ቀጥልነቱ ለመቀጠል የተዳፈረው፣ “ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ ” በተሰኝ ርዕስ ባሳተመው እና በብዙ ቅጥፈት በተመላው መፅሐፉ ላይ ሳንመለስበት በመቅረታችን ነው ብዬ ደመደምኩ።
እኔ በወቅቱ ያልተመለስኩበት፣ መ ፅሐፉን በቅጥፈት የተሞላ ሆኖ ስላገኘሁት ብቻ አልነበረም። አማረ የራሱን ማንነት በኃይሌ ላይ አንጠላጥሎ ለመካብ የጣረበት መፅሐፍ ሆኖ ስላገኘሁት ነበር። ወይንም፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎች በሆነ የታወቀ ሰው ላይ በመንጠላጠል ዝናን መሻት (seeking fame by proximity) የሚሉት ዓይነት መፅሐፍ ሆኖ ስላገኘሁት ነበር። አማረ አሁን ግን፣ ደግሞም በሌሎች ቅጥፈቶች የተሞላ ሌላ መፅሐፉን ለገበያ አዋለ። ይህንን፣ ግልፅ መልስ ለመፃፍ ወሰንኩ።
– Advertisement –

ለቅጥፈቶቹ ለመመለስ ሌላ ሰነድ ማገላበጥም ሆነ እማኝ መጥራት እንደማያስፈልገኝ ተረዳሁ። መልሴም ስለዚህ፣ የራሱን ሐተታዎች በመጥቀስ እና በማመሳከር ብቻ እንዲሆን ወሰንኩ። ካነሳቸው የጉዳዩ መነሻ አንስቼ እስከ የስዊድኑ ግኑኝነታችን እና ውሳኔው፣ ከድርጅት ስለመታገዱ እና ተመልሶ ስለመካተቱ፣ መልስ ስላላገኙት ደብዳቤዎቹ፣ የአዲስ ፋና መፅሔት አዘጋጅ ስለመሆኑ፣ ገረመኝ ስላለው ቃለ ምልልሴ እና በብሔር ማንነቱ ስለመከሰሱ ባነሳቸው ጉዳዮች ላይ ተመልሻልሁ። በመጨረሻው ክፍልም ውስጥ፣ በመጀመሪያው መፅሐፉ ውስጥ ያሰፈራቸውን ቅጥፈቶቹ አስታውሻለሁ። አንባቢ የራሱን መረዳት ሊያበጅ ይችላል።
አማረ በዚህ መፅሑፉ ውስጥ፣ በ1991 ዓ.ም. በታተመው መፅሐፌ ዝግጅት ወቅት ስለነበረው ድርሻው ከገፅ 345 እስከ ገፅ 350 ድረስ በሰፊው አትቷል። ያቀረባቸው ሃሳቦቹና አስተያየቶቹ በመፅሐፌ ውስጥ ባለመካተታቸው ያደረበትን ቅሬታ ገልጿል። በዚህ ጉዳይ ላይ በሁለት እሳቤዎች ምክንያት አልተመለስኩም።
የመፅሐፉን የመጀመሪያ ግርፍ በነሐሴ 1981 በቤልጂግ አገር ተደርጎ ለነበረው የመኢሶን ስብሰባ አቅረቤ፣ የስብሰባው ተሳታፊዎቹ የስጧቸውን እርማቶች እና አስተያየቶች ሰብስቤ ነበር። ከስብሰባው በኋላም፣ ከበርካታ የመኢሶን ወዳጆች እና ጓዶች ዘንድ ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን አሰባስቤአለሁ። ይሁንና፣ ሁሉንም ሃስብ እና አስተያየት አላካተትኩም። ሃስብ፣ አስተዋፅኦ እና አስተያየት መጠየቅ ተገቢ የነበረውን ያህል፤ መቀበል/አለመቀበል የእኔ መብት መሆኑ ይታወቃል። በተረፈው እና ዛሪም የመሰጠው መልስ፣ በአካል በተገናኝንበት ጊዜ አሳወቀኝ ካለው የተለየ መልስ አይደለም። ይህም፣ አማረ ራሱ በመፅሐፉ ገፅ 350 ውስጥ የገለፅው ነው።
“ እኔ የራሴን ተወጥቻለሁ። የፅሑፍ ችሎታ ያላችሁ አንተንና ነገደን የመሳሰላችሁት ደግሞ፣ በማትስማሙበት እና ጎደለ በምትሉት ላይ ልትፅፉ ትችላላችሁ። ”
– Advertisement –

መነሻው
መኢሶን በነሐሴ 1969 ባደረገው የትግል ሥልት ለውጥ፣ የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ፅ/ቤት ይባል በነበረው ተቋም ውስጥ የነበረውን ተሳትፎ አቋረጠ። የተራዘመ የመሣሪያ ትግል ለመጀመር በወሰነው መሠረት፣ አንዳንድ አባላቱን በገጠር አካባቢ አሰማራ። ይሁንና፣ በጅባት እና ሜጫ ጥቁር እንጭኒ አካባቢ የተመደበው ቡድን በጥቂት ቀናት ውስጥ ተደረሶበት ሲሰዋ፣ አንድ አማረ ተግባሩ ብቻ ተርፎ ተገኘ። የመኢሶን ልሳን የነበረው የሰፊው ሕዝብ ድምፅ (ሰሕድ)፣ በወቅቱ እንደሚከተለው የዘገበው ጉዳይ ነው።
“ታኅሣሥ 20 ቀን 1967 ዓ.ም. አምቦ አካባቢ በደርግ የተረሸኑት 11 የመኢሶን አባሎች በሁለት ከሃዲዎችና በአንድ ተባባሪ አማካኝነት በተደረገው ጥቆማ ምክንያት ነበር” (ሰሕድ፣ ቁጥር 65፣ ጥር 21፣ 1970፣ ገፅ 7)።
የአማረ ብቻ መትረፍ ጥያቄዎችን ቀሰቀሰ። ከዚህም በተያያዘ፣ ሲራክ ተግባሩ የሚባለው ታናሽ ወንድሙ፣ በአማረ ተግባሩ መትረፍ ውስጥ ስለነበረው ሚና ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ተ ነሱ። በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ለመመለስ እና ለማጣራት የተሞከረው፣ አማረ ከእስር ተፈቶ ወደስዊድን አገር ከገባ በኋላ እና በዝያው ከተገናኘን በኋላ ነበር።
– Advertisement –
የስዊድኑ ግኑኝነታችንና እና ውሳኔው
ዓመተ ምሕረቱንና ወሩን ባላስታውስም፣ በስዊድን አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘን። በዚህም ጊዜ፣ ጥቁር እንጭኒ ስለደረሰው እየተከሰሰ መሆኑን አንስቼ ከተነጋገርን በኋላ አንደኛ፤ ራሱን የመከላከል መብት እንዳለው አስታውሼ፣ ክሶቹ በማስረጃ ተደግፈው ጥፋተኛ ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ ነፃ እንደሆነ ገልፅኩ። ሁለተኛ፤ በእርሱ በኩል ያለውን በሪፖርት መልክ ፅፎ እንዲያሰገባ ጠየቅሁ። አያይዤም፣ ከውሳኔ ላይ የምንደርሰው ፅሑፉ ለአገር ውስጥ አመራር ከተላከ በኋለ እና የነሱን አስተያየት ካገኝን በኋላ እንደሚሆን አመለከትኩ። ሦስተኛ እና በመጨረሻም፣ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ በስዊድን አገር በሚገኘው የድርጅቱ መዋቅር ውስጥ እንደማይካተት የተወሰነ መሆኑን ገልጬለት፣ ግኑኝነቱ ከድርጅቱ የውጭ አመራር አካል ጋር ብቻ እንደሚሆንና የደብዳቤ ልውውጦችም በእኔ በኩል ብቻ እንደሚሆን አሳውቄው ተለያየን።
አማረም ይህንኑ ስምምነታችንን በመፅሐፉ ገፅ 332 ውስጥ “ማንም ሰው ክሶች ቢቀርብበትም፣ ራሱን የመከላከል መብት ተሰጥቶት በመጨረሻ ጥፋተኛ ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ ነፃ” መሆኑ እንደተገለፀለት አስታውሶ ይነበባል። በገፅ 329 ውስጥም፣ “ከድርጅቱ መዋቅር ጋር ሳልደባለቅ ግኑኝነቴ ከድርጅቱ የውጭ አመራር አካል ጋር ብቻ እንደሚሆን ተነጋገርን” እያለ ያስታውሳል። ሆኖም ይህንኑ “መታገዱን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው” እኔ በመስከረም 2019 ለአርትስ ቲቪ ከሰጠሁት ቃለ ምልልስ እንደነበር እያተተ ይቀጥፋል ። ይቀጥፋል የምለው፣ ዕውነታዎቹ የሚከተሉት እንደነበሩ በራሱ ብዕር ጭምር ተገልፀው ስለሚገኙ ነው።
ከድርጅት ስለመታገዱ እና ተመልሶ ስለመካተቱ
አማረ ከድርጅቱ መዋቅር መታገዱን “ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው” በመስከረም 2019 እንዳልነበር ለማመልከት ሩቅ መሄድ አያስፈልገኝም። ከላይ የጠቀስኳቸው እና በራሱ ብዕርጭምር የተታወሱት የስዊድን አገሩ ስምምነቶቻችን በራሳቸው በቂ ማስረጃ ናቸው። ሁለተኛም፣ ተመልሶ በድርጅቱ መዋቅር ውስጥ እንዲካተት እንደተደረገ እርሱ ራሱ በመፅሐፉ ገፅ 336 ውስጥ እንደሚከተለው ተርኮታል።
“የድርጅቱ አመራር የነበረው አበራ የማነአብ ከሰሜን አሜሪካ ወደስዊድን ብቅ ብሎ … ስዊደን አገር ከሚገኙት የመኢሶን አባላት ጋር ስብሳባ ተደርጎ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ስብሰባ ላይ ተገኝቻለሁ። … አበራ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ባለሁበት ስዊድን አገር በሚገኘውድርጅታዊ መዋቅር በመካተት አብሬያቸው እንድሠራ መወሰኑን ለማስጨበጥ ቢሞክርም፤ እኔ ፈቃደኝ ሳልሆን በመቅረቴ ከድርጀቱ አመራር ጋር ብቻ አብሬ ለመሥራት በቅቻለሁ” (ገፅ 336)።
አንድ የድርጅት አባል በአንድ ድርጅት መዋቅር ውስጥ ተመልሶ እንዲካተት የሚደረገው በሆነ ምክንያት ከድርጅቱ ታግዶ ከቆየ በኋላ ብቻ እንደሆነ ማተቱ ትርፍ ነው። ስለዚህም፣ ተመልሶ እንዲካተት የተወሰነው በምን ምክንያት እንደነበር በአጭሩ አስታውሼ፤ ወደ ሌሎች ቅጥፈቶቹ አልፋለሁ።
አማረ የተጠየቀውን ሪፖርት ከረጅም ጊዜ በኋላ እስገባ። ሪፖርቱ ለአገር ውስጥ አመራር ተላክ። የአገር ውስጥ አመራር፣ አሁንም ከረጅም ጊዜ በኋላ በፀጥታ ምክንያት ወደአካባቢው ሄዶ ለማጣራት እንዳልቻለ ገለፀ። ይህ እንደታወቀ፣ በአንድ አበራ የማነአብ በተገኘበት የአመራር ስብሰባ ላይ ተወያየንበት። ያለበትን ክስ ራሳችን ለማጣረት ባልቻልንበት ሁኔታ አማረን ከድርጅቱ መዋቅር አግልሎ ማቆየት ተገቢ እንዳልሆነ ከተወያየን በኋላ፣ ሁኔታዎች ፈቅደው ያለበት ክስ እስኪጣራ ድረስ ተመልሶ በድርጅቱ መዋቅር ውስጥ የመካተት መብት እንዳለው ተስማማን። አበራ ወደስዊድን አገር ሄዶ ይህንኑ ፈፀመ። ይህም የተከናወነው በመስከረም 2019 ለአርትስ ቴሊቪዥን ቃለ ምልልስ ከሰጠሁት ብዙ ዓመታት በፊት፣ በሰማንያዎቹ ዓመት ውስጥ ነበር። ዓመተ ምሕረቱንና ወሩን ባላስታውስም፣ ወቅቱ፣ አበራ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ኃይሎች ቅንጅትን (ቅንጅት) ወክሎ ወደስዊድን ባቀናበት ወር ነው።
መልስ ስላላገኙት ደብዳቤዎቹ
አማረ የላካቸው ደብዳቤዎች ስለመድረስ/አለመድረሳቸው የተለዋወጥነውን አስታውሶ፣ እንደሚከተለው አትቷል።
“ አንዳርጋቸው በተሰጠኝ አድራሻ ለምልካቸው ደብዳቤዎች መልስ ስላላማገኘቴ ስናገር፣ በአገናኝን ጓድ በኩል እንጂ፤ ከርሱ ጋር ቀጥታ የደብዳቤ ልውውጥ እንድናደርግ የሰጠኝ አድራሻ እንደሌለ ካደ። እኔም የፎቶ ኮፒ ማስረጃዎችን ሳቀርብ፣ አንዳርጋቸው ከዚያ በላይ ለማስተበበል ባለመቻሉ ይህንን ጉዳይ ዘግተን፣ ከርሱ ጋር እጅግ አድርጎ ከመከራከር አልፎ እስከመካረርና ኃይለ ቃል እስከመለዋወጥ ወደ ደርስንባቸው ሁለት ጉዳዮች አለፍን” (ገፅ 331)።
“ኃይለ ቃል እስከመለዋወጥ ስለደርስንባቸው ሁለት ጉዳዮች” ዝቅ ብዬ እመለስባቸዋለሁ። የተሰጠውን አድራሻ በሚመለከተው የሰጠሁት መልስ ግን፣ እሱ ራሱ በመፅሐፉ ገፅ 483 ውስጥ ከጠቀሰው ደብዳቤዬ ያለፈ አልነበረም።
“አድራሻ ልኬልህ እንደነበር በዕውነቱ አላስታወስኩም ነበር። በኛ በኩል (ስለግኑኝነት ጉዳይ) ውሳኔ ስናደርግ (ያ አድራሻ እንዲሰጥህ መወሰኑን) ሁለታችንም (ማለትም ነገደ እና እኔ) ልናስታውስ አልቻልንም። የሆነው ሆኖ፣ (ባቀረብካቸው የፎቶ ኮፒ ማስረጃዎች “ ”) ማስረጃዎችህን አቅርበሃል። በኛ በኩል ጥፋት አለ ማለት ነው። ነገር ግን ብታምንም/ባታምንም፣ ዕውነቴን ነው የምልህ፤ ሀ) በዚያ አድራሻ ልከኸው የደረሰ አንድም ደብዳቤ የለም። … እኔ የማምነው፣ ያንተን የላኪውን አድራሻ በትክክል አስቀምጠህ እንደሁ፣ (ደብዳቤው) ወደ አንተው ተመልሷል ብዬ ነው። ለ) የፖስት ሣጥኑ ከተዘጋ ቆይቷል። ያም ሆነ ይህ፣ በተንኮል የተደረገብህ ጉዳይ እንዳልሆነ እንድትገነዘብ እጠይቅሃለሁ” (ገፅ 483)።
ይህንን በዚሁ ልተወው እና፤ ኃይለ ቃል ተለዋወጥንባቸው እያለ የሚያነሳው “ ” አንደኛ፣ የአዲስ ፋና መፅሔት አዘጋጅ ስለመሆኑ ነው። ሁለተኛም፣ ስላስገረመው የአርትስ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልሴ ነው።
የአዲስ ፋና መፅሔት አዘጋጅ ስለመሆኑ
አማረ የአዲስ ፋና መፅሔት አዘጋጅ ስለመሆኑ የሚከተለውን አትቷል።
“(አንዳርጋቸው) ለጀርመን ራዲዮ (ዶውቼ ቬሌ) የአማርኛ ፕሮግራም ቀርቦ ከጋዜጠኛ ይልማ ኃይሌሚካኤል ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩ። በዚህ ቃለ ምልልስ አንዳርጋቸው የመኢሶን ሕጋዊ መፅሔት የነበረችው የአዲስ ፋና አዘጋጅ ነበርኩ በማለት መናገሩ፣ በድርጅቱ ውስጥ የነበረኝን ሚናም ሆነ የከፈልኩትን መስዋዕትነት እስከመከለስና ዋጋ እስከማሳጣት እንደደረሰ ያህል ተሰማኝ። ከዚህ የተነሳ አንዳርጋቸው አሰግድ መፅሔቷን በሕጋዊ ባለቤትነት ከማስመዝገቡ ያለፈ አንድም ጊዜ በእርሱ አዘጋጅነት የወጣ የመፅሔት ዕትም እንዳልነበርና፣ ድርጅቱ የሚያውቀው የመፅሔቷ ዋና አዘጋጅ እኔ እንደነበርኩ በአደባባይ አስተባበልኩ”(330)።
በጀርመን ራዲዮ (ዶውቼ ቬሌ) የአማርኛ ፕሮግራም ላይ ቀርቤ ከጋዜጠኛ ይልማ ኃይሌሚካኤል ጋር ስለአዲስ ፋና መፅሔት ይቅር እና ስለሌላ ሌላም ጉዳይ ያደረኩት አንድም ቃለ ምልልስ የለም። ይህ ዕውነታ ከራሱ ከዶውቼ ቬሌ መሥሪያ ቤት መዝገብ ቤትም ሆነ ከይልማ ኃይሌሚካኤል ዘንድ ሊጣራ የሚችል ጉዳይ ነው። ስለዚህም፣ በወቅቱ የነበረውን ድርጅታዊ አሠራር አስታውሼ አልፈዋለሁ።
አዲስ ፋና መፅሔትን በሕጋዊ ባለቤትነት ወደማስመዝገብ ያቀናሁት፣ በአንድ በ1968 ዓ.ም. በተደረገ የመኢሶን አመራር ስብሰባ ላይ፣ በአራት ነጥቦች በተዘረዘረ መመሪያ ላይ ከተስማማን በኋላ ነበር። እነዚህም አንደኛ፣ መፅሔቱ የመኢሶን መሆኑ በምንም ዓይነት ሕጋዊ ማስረጃ ውስጥ እንዳይጠቀስ። ሁለተኛ፣ የመፅሔቱ ሕጋዊ ባለቤት እና አዘጋጁ እኔ እንደሆንኩ እንዳይመለከት። ሦስተኛ አዝጋጁ፣ አሳታሚው እና አከፋፋዩ አዲስ ፋና በሚለው ስም ብቻ እንዲመዘገብ። አራተኛ፣ ፅሑፎች ለዕትማት ከመሰጣተቸው በፊት በመኢሶን የመፅሔት ቦርድ እንዲታዩ።
መፅሔቱ በመመሪያው መሠረት ተመዘገበ። ለመጀሪያዎቹ ቁጥሮች የሚሆኑ ፅሑፎችን ማሰባሰብ እና ማዘጋጀት ጀመርኩ። ይሁንና፣ ከጥቂት ወራት በኋላ የመፅሔት ዝግጅት የሚጠይቃቸውን ሥራዎች ሁሉ በሙሉ ጊዜ ልከታተል እና ልፈፅም አለመቻሌን ለመፅሔት ቦርዱ አሳወቅኩ። በውይይታችን ወቅት፣ መፅሔቱ በእኔ ስም የተመዘገበ በመሆኑ እና ሕጋዊ ተጠያቂውም እኔ ስለሆንኩ፣ እኔ በዋና አዘጋጅነት እንድቀጥል ተስማማን። ከዚያም እኔ ባቀረብኩት አማራጭ መሠረት፣ አማረ ተረክቦኝ የመፅሔቱን ሥራዎች እንዲቀጠል ተወሰነ። አማረም ይህንኑ፣ “ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ” በተሰኘው የ2010 መፅሐፉ ገፅ ሁለት ውስጥ፣
“ ከእኔ በፊት አዲስ ፋናን በግል ባለቤትነትና ዋና አዘጋጅነት በሕግ አስመዝግቦ እኔ ወደአገር ስመለስ የዋና አዘጋጅነቱን ሥፍራ ለኔ የለቀቀውና ወደ የየካቲት 66 የፖለቲካ ት/ቤት በአስተማሪነት የተዛወረው አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ .።”
እያለ ተርኮት ይነበባል። ከዚህ በኋላ የኔ ተሳትፎ በዕውነትም፣ አማረ አሁኑ በ2018 ባሳተመው መፅሐፉ ገፅ 214 ውስጥ እንደሚከተለው ካስታወሰው ያለፈ አልነበረም።
“ አብዛኛውን ጊዜ እነኚህን (የመፅሔቱን) ሥራዎች አብሮኝ በመካፈልና አንዳንድ ጊዜ ራሴ በማዘጋጀው ርዕሰ አንቀፅም ሆነ በሌሎች በምፅፋቸው ፅሑፎች ላይ የሚታየውን የጦዘ ርዕዮተ ዓላማዊ አንድምታ በማስከን፣ በማረምና በማስተካከል የሚረዳኝ አንዳርጋቸው አሰግድ ሲሆን፤ አልፎ አልፎም ኃይሌ ፊዳ ይህንን የመሰለ እርዳታ ያበረክት ነበር። ”
“ ” ገረመኝ ያለው ቃለ ምልልሴ
አማረ ለደረጀ ኃይሌ ከሰጠሁት ቃለ ምልልሴ ውስጥ የገረመው ምን እንደሆነ በመፅሐፉ ገፅ 350 የግርጌ ማስታወሻ ቁጥር 143 ውስጥ እንደሚከተለው አትቷል።
“በዚህ ቃለ ምልልስ የገረመኝ ይላል፣ ” “(አንዳርጋቸው) ስለጅባት እና ሜጫ ስለፃፍኩት መቶ ገፅ ገደማ ሪፖርት ይዘት ሲጠየቅ፤ ለጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ የሰጠው መልስ ‘ስለሪፖርቱ የምትጠይቀኝ መሆኑን ቀድሜ ባወቅ ኖሮ አንብቤ እመጣ ነበር’ የሚል መሆኑን ስሰማ ዕውነት ያደመጥኩት የማውቀውን አንዳርጋቸው አሰግድን ሳይሆን፣ ሌላ የማላቀውን አንዳርጋቸውን ብዬ እስከማለት አድርሶኛል።”
ከመልሴ ያስገረመው ምን እንደሆነ ባይገባኝም፣ ለጥያቄው የሰጠሁት ሙሉ መልስ፣ “አስቀድመህ ብትነግረኝ ኖሮ አንብቤው እመጣ ነበር። የዛሬ ሠላሳ አመት ስለሆነ ነገር (ስላነበብኩት ሪፖርት) ዛሬ አሁን መዘባረቅ አልፈልግም” (https://www.youtube.com/watch?v=RTLcjTTaEeg)፣ ከ24፡55 እስከ 36፡54)
በተረፈው፣ አማረ በመፅሐፉ ገፅ 480 እና 481 ውስጥ ታናሽ ወንድሙበወቅቱ ለእናታቸው እና በኋላም ለርሱ ለራሱ ስለክሱ የሰጣቸውን መልሶች አቅርቧል። አንባቢዎቹ የታናሽ ወንድሙን የተለያዩ መልሶች በማገናዝብ የየራሳቸውን አመላካከት ለማብጀት ስለሚችሉ፣ የእኔ መታከል አስፈላጊ አይደለም።
አማረ በዚሁ የታናሽ ወንድሙ ጉዳይ ሌላም፣ አንዳርጋቸው በተጠቀሰው ቃለ ምልልስ ውስጥ፣ “(ታናሽ ወንድሜ) የመኢሶን ካድሬ ሆኖ ጅባት እና ሜጫ መመደቡን ገና ኅቡዕ ከመግባታችን በፊት የሚያውቀውን እንደማያውቅ የተናገረው ጨርሶ ሀሰት እንደሆነ እዚህ ላይ ማሳወቅ እወዳለሁ እያለ ” አትቷል (የግርጌ ማስታወሽ ቁጥር 138፣ ገፅ 333)።
ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ የጠየቀኝ የአማረ ታናሽ ወንድም “የመኢሶን ካድሬ ሆኖ ጅባት እና ሜጫ ስለመመደብ/አለመመደቡ አልነበረም። ተስፋዬ መኮንን ይድረስ ለባለታሪኩ በተባለው መፅሐፉ ውስጥ ” “ ” ወደጅባት እና ሜጫ ስለወጣው የመኢሶን ቡድን መገደል እና የአማረ ታናሽ ወንድም ስለነበረው ሚና የተረከበትን ክፍል አስታውሶ፣ የምሞግተው ሃሳብ እንዳለ ነበር የጠየቀኝ ። የሰጠሁት መልስ የሚከተለው ነበር።
“ ሲራክ ተግባሩ የገጠሩ እና የከተማው አገናኝ ሆኖ መመደቡን የሚያወራው ተስፋዬ መኮንን ነው። ከየት አመጣው? እኔ ስለዚህ አላውቅም። ዕርግጠኛ ነኝ፤ ዶ /ር ከበደን የሚያክል ሰው፣ እነ ዳንኤል ታደሰ፣ እነ መስፍን ካሡ ማን ማንን እንደሚያገናኝ በደንብ መዝነው የሚሠሩ ሰዎች ናቸው ” (ከላይ የተመለከተው ቪድዮ)።
በብሔር ማንነቱ ስለመከሰሱ
አማረ “ዕውነት ይሁን ” “ አይሁን ለማረጋገጥ ባልችልም እየለ ቢሆንም ቅሉ፤ (አንዳርጋቸው) በመኢሶናዊነት ከመቆም ይልቅ የኦሮሞ ብሔረተኝነት ያሸነፋቸውን ወገኖች አግኝቶ ተናገረ የተባለው ነገር አሳዝኖኛል እያለ፤ ” በእኔ እና የኦሮሞ ብሔረተኝነት ያሸነፋቸው ወገኖች ባላቸው የመኢሶን አባላት መካከል ተከሄዶ ነበር “ ” ስለሚለው ልውውጥ የሚከተለውን ይተርካል።
“ የኦሮሞ ብሔረተኝነት ያሸንፋቸው ወገኖች፣ አማሮች በመሆናችን ከሞት እንደተረፍን እና የቀሩት በሙሉ ደግሞ ኦሮሞዎች በመሆናቸው እኛ (እሱና ወንድሙ) አሳልፈን እንደሰጠናቸው አድርገው ሲያቀርቡ፤ አንዳርጋቸው የእነርሱን ክስ የሚጋራ መስሎ ተናገረ የሚል ዜና ሰምቻለሁ (ገፅ 329)። … በአንዳርጋቸው በኩል ተሰጠን የሚሉት ምላሽ፣ እኔም በእናቴ በኩል ኦሮሞነት አለብኝ የሚል፣ ‘ ’ ለእነርሱ ክስ የልብ ልብ የሚሰጥ እና እኔን አሳልፎ ከመስጠት ያልተመለስ (መልስ) ሆኖ እንዳገኝሁት ምንም ሳልሸፋፍን ተናገርኩ (ገፅ 331)።
በዚህ፣ አማረ ራሱ ዕውነት ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ባልችልም እየለ በተረከው አሉ ቧልታ ላይ መመለስ “ ” የኔ ፈንታ አይደለም። በአጭሩ ለማመልከት ያህል ፣ አማረ የኦሮሞ ብሔረተኝነት ያሸንፋቸው ያላቸው “ ” የመኢሶን አባላት በጅባት እና ሜጫ /ጥቁር እንጭኒ የተሰውት ጓዶች በመኢሶንነታቸው እንጂ፤ በብሔር ማንነታቸው እየተለዩ እንዳልተገደሉ የሚያውቁ ነበሩ። እንደዚያ ዓይነቱን የወረደ አመለካከት ያኔም ይሁን ዛሬ የሚያንፅባርቁ አይደሉም። በተረፈው፣ የመኢሶን አባላት ከነበሩት ኦሮሞች ጋር እንደምገናኘው ሁሉ፤ የመኢሶን አባላት ከነበሩት የአማራ፣ የትግራይ፣ የሲዳማ፣ የሃድያ … ጓዶች ጋር ያኔም ይሁን ዛሬ እገናኛለሁ። በእናቴ በኩል የኦሮሞ ደም እንዳለብኝ አወሳለሁ። የብሔር ማንነት የደም ጉዳይ እንዳልሆነ አትታለሁ። ይህ የትላንትናም ይሁን የዛሬ አመለካከቴ ነው።
ሌሎች ቅጥፈቶቹ
በመግቢያው ውስጥ፣ አማረ አሁን በ2018 በቆርጦ ቀጥልነቱ ለመቀጠል የተዳፈረው፣ በ2010 “ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ” በተሰኝ ርዕስ ባሳተመው መፅሐፉ ላይ ሳንመለስበት በመቅረታችን ምክንያት ጭምር እንደሆነ አመልክቼ ነበር። በዚህኛው መፅሐፉ ላይ በወቅቱ ያልተመለስኩበት አንድም፣ መፅሐፉን አማረ የራሱን ማንነት በኃይሌ ላይ አንጠላጥሎ ለመካብ የጣረበት መፅሐፍ ሆኖ ስላገኘሁት እንደነበርም አስታውሻለሁ።
እያደር ግን፣ መፅሐፉ ተጠቃሽ እስከመሆን እና አንዳንዶችም፣ ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች በቂ የታሪክ “ ግብዓት መሆን የሚችል ነው ብዬ አምናለሁ እስከማለት ድረስ ሄደው እንዳስተዋወቁት ተመለከትኩ። ” ሌሎችም፣ “Haile Fida: A Socialist Visionary Betrayed by His Own Revolutionary Ideals” በሚል ርዕስ አንድ ሰፊ መጣጥፍ እስከመድረስ እንደሄደ ተገነዘብኩ (Birhanu Lenjiso, Horn Review, October 2025)። በዚህ ፅሑፍ ውስጥ፣ አማረ በሕይወት የሌለው ኃይሌ እንዲህ እና እንዲያ አለኝ እያለ “ ” በተረካቸው ጉዳዮች ላይ አልመለስም። ምክንያቱም፣ በሚተረካቸው ጉዳዮች ውስጥ ሁሉ አልተሳተፍኩም። የተሳተፍኩባቸው ጊዜዎች ከነበሩም፣ አማረ በተረካቸው ዓይነት መካሄድቸውን አላስታውስም። ፅሑፌ ስለዚህም፣ አማረ ቅጥፈቶቹን ተዓማኒ ለማድረግ ያጎላቸውን ትርክቶች በማመልከት ላይ ብቻ የተወሰነ ነው። አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።
አማረ እንደሚለው፣ ከኃይሌ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘው በየካቲት 1965 (1972) ነበር (ገፅ 1)። ለመገናኘት የበቃውም፣ ወደ ፈረንሳይ አገር ለመሄድ ሲነሳ የኢሕአፓው ፀጋዬ ገ /መድህን (ደብተራው) በሰጠው ገለፃ እና መመሪያ መሠረት እንደነበር፣ በመፅሐፉ ገፅ 18 ውስጥ እንደሚከተለው ይተርካል።
“ ኃይሌ ፊዳ የሚባል እንደብርሃነ መስቀል ረዳ ሁላችንም እንደመሪያችን የምናየው ሰው ፈረንሳይ አገር አለና እሱን እንድትገናኝ። ከአገር የወጣህበት ምክንያትና ማን ወደእርሱ እንደላከህ (ለኃይሌ) በሌላ በኩል ይደርሰዋል። የመጣህበት ምክንያት፣ (ኃይሌ) ከኩባና ከቻይና መንግሥታት ጋር በቶሎ ግኑኙነት ፈጥሮ ወደዚያ እንዲልክህና በፈንጂ ክህሎት እንድትሰለጥን ሲሆን፣ ስልጠናውን ከጨረስክ በኋላ ለማይቀረው የገጠርና የከተማ አመፅና ሽምቅ ትግል በቂ ሆነህ ስትገኝ ወዴትና እንዴት እንደምትመለስ በጌታቸው ማሩ በኩል መልዕክት ይደርሰዋል ” (ገፅ 18)።
ይህንን የአማረ ትርክት የሚያነብ ሰው በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥያቄ፣ ኃይሌ በሚያዚያ 1965 ከፀጋዬ ገ/መድህን ይገናኝ ነበር ወይ ? የሚለውን ጥያቄ እንደሆነ እገምታለሁ። መልሱ አጭር እና ግልፅ ነው። አንደኛ፣ ኃይሌ ከመኢሶን የአገር ውስጥ አካል ጋር የሚገናኘው በዶ/ር ወርቁ በኩል ብቻ ነበር። ስለነበረም፣ ከዶ/ር ወርቁ ውጭ የተላከን የድርጅታዊ ጉዳይ መልዕክት የሚያስተናግድ አልነበረም። ሁለተኛም፣ ወቅቱ በአንድ በኩል ጥቂት ወጣቶችን ይዞ ለመሣሪያ ትግል በተነሳሳው የአልጄሪያው የብርሃነ መስቀል ቡድን እና፤ በሌላው በኩል ለነቃ እና ለተደራጀ ሕዝባዊ ትግል በቆመው መኢሶን መካከል የነበሩት ልዩነቶች በገሃድ
የሚነገሩበት ወቅት ነበር። ልዩነቱን ያውቅ የነበረው ፀጋዬ ገ /መድህን፣ አማረን ለፈንጂ ክህሎት ሥልጠና ወደ ኩባም ሆነ ቻይና ላከው የሚልን መልዕክት አስይዞ ወደኃይሌ አይልከውም። ኃይሌም የሰጠው መልስ፤ “ ጥቂት ፋኖዎች በፈንጂ ሥልጠናም ሆነ፣ በመሳሰለው የመሣሪያና የሽምቅ ውጊያ ስልጥነው ገጠርና ከተማ በመግባት የገጠርም ሆነ የከተማ ትግል ለመጀመር ሕዝቡን ተክተው ነፃ ያወጡታል ብለን አናምንም። የሕዝቡ ነፃ አውጪራሱ ሕዝቡ ነው። … አንተም ገና ልጅ ነህ። የኢትዮጵያን ሕዝብ ነፃ አውጭነቱን ጉዳይ እርግፍ አድርገህ ከጭንቅላትህ አውጥተህ፣ በቅድሚያ ትምህርትህን መቀጠል አለብህ”
አማረ ግን ሌላም ያክላል። ኃይሌ “ንቅናቄም ብንሆን፣ የፖለቲካ ድርጅት አይደለንም” (ገፅ 19) በማለት ጭምር ነግሮት እንደነበር ያወሳል። ዕርግጠኛ ነኝ፤ ኃይሌ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ለተገናኘው አንድ ወጣት፣ የመኢሶንን ህልውና የመግለፅ ያህል የሚያክልን ጉዳይ አይናገርም። አማረ ከገፅ 29 ላይ ሲደርስ ደግሞ፣ መኢሶንን ከጌታቸው ማሩ ስለማገናኘቱ፣
“በእኔ (አማረ) አማካኝነት በተፈጠረው ድርጅታዊ መስመር በአብዮት መሪ ጌታቸው ማሩና የመኢሶን አመራር አባል በነበረው ዳንኤል ታደሰ መካከል ለውህደት ይደርሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ውይይት ሲካሄድ ቆይቶ፤ ጌታቸው ማሩ ምክንያቱን ሳያሳውቅ ደርጅቱን ከኢሕአፓ ጋር አድርጓል።”
እያለ እና፤ ዕልፍም ሳይል፣
“ከአብዮቱ በፊትም ሆነ ከፈነዳም በኋላ የእነ ጌታቸው ማሩ ቡድን ከዶ/ር ወርቁ ፈረደ ጋር በነበረው ግኑኝነት ከመኢሶን ጋር የጋራ ፅሑፍ እስከማውጣት ተደርሶ እንደነበር፤ ወርቁ ፈረደ “ዕድገት ብሎ ውድቀት” በሚል ርዕስ በ1990 በፃፈው መፅሐፍ ውስጥ ይገኛል።
እያለ ይተርካል። መአሶን በ1966 አብዮት ወቅት ‘የተራማጆች ኅብረት ይባል የነበረውን ጋዜጣ በወቅቱ ’ በኅቡዕ ከነበሩ ተራማጅ ቡድኖች ጋር በመተባበር ያወጣ ነበር። አማረ በዚያን ወቅት እንኳን መኢሶን እና ጌታቸው ማሩን ያገናኘ ሰው ሊሆን ቀርቶ፣ ስለመኢሶን መኖር /አለመኖር የሚያውቅ አልነበረም። ከመኢሶን በኩል ጌታቸው ማሩን ይገናኝ የነበረው ዳንኤል ታደሰ እንደነበርም፣ በ1992 በታተመው መፅሐፌ ውስጥ ተገልጦ ይገኛል። አማረ እንደዚሁም ኃይሌ፣
“ “ ” ስለኤርትራ ጉዳይ፤ ተገቢ አጀማመር፣ ሕዝባዊ አመራር (በሚል ርዕስ የተደረሰውን ፅሑፍ ) በቀለ ወርዶፋ በሚል (የብዕር ስም) የፃፈው ማን እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም፣ እኔ ነበርኩ ሲል መለሰልኝ”
በማለት ይተርካል (ገፅ 41)። ይሁንና በዚያን ወቅት አንደኛ፣ ማን የትኛውን ፅሑፍ እንዳበረከተ የሚገለፅ አልነበረም። ሁለተኛም፣ “ ” ኃይሌ እኔ እኔ እያለ ራሱን የሚክብ እና ራሱን መካብ የሚያስፈልገው ሰው አልነበረም። ሦስተኛም፣ በቀለ ወርዶፋ በሚል የብዕር ስም የተደረሰው ያ ፅሑፍ በኃይሌ የተፃፈ እንደነበር በ1992 በታተመው መፅሐፌ ውስጥ ተገልፆ የሚገኝ ነው። አማረ ግን ቀጥሎ ይተርካል፣
“ ‘ ’ ኃይሌ በሃምቡርግ ከተማ ሳለ የኢትዮጵያ አብዮት እና የደርጉ አረማመድ በሚል ርዕስ ይፅፋቸው ለነበሩት የትግላችን መፅሔት ቁጥሮች የሚያስፈልጉትን ዜናዎች በካርድ ላይ በመፃፍ እይሰጠሁት ይጠቀምባቸው ነበር ” (ገፅ 82)።
ይህም ሌላው ቅጥፈቱ ነው። ምክንያቱም፣ ኃይሌ ለፅሑፉ ዝግጅት ሲጠቀም የነበረው ሰነድ ዮሐንስ ኅሩይ Developments in Ethiopia በሚል ርዕስ ያዘጋጅ የነበረውን እና በትግላችን ዜና መፅሔት ላይ ይወጡ የነበሩትን የአብዮቱ ዜና መዋዕልን እና BBC Monitoring በየዕለቱ ያወጣቸው የነበሩትን ዕትሞች ነበር።
ማጠቃለያ
መልሴ የራሱን የአማረን ሐተታዎች በመጥቀስ እና በማመሳከር ላይ ብቻ እንደሚሆን በመግቢያው ውስጥ አመልክቼ ነበር። ቃሌን አክበሬ/አላከበርኩ እንደሁ ማገናዘብ የአንባቢው ፈንታ ነው።
“የግል ትዝታ” ሆነ የግለ ታሪክ ወይንም ባጠቃላይ የታሪክ ተዓመኒነት የሚመዘነው በዕውነታ ላይ የተመሠረቱ (fact based) የሆኑትን ያህል ነው።
አማረ ራሱን የመከላከል መብት አለው። ይሁንና፣ የመዋሸት መብት እና ውሸቶቹን በቃልም ሆነ በፅሑፍ እየረጨ አንባቢዎቹን፣ ተቺዎቹን እና ተመራማሪዎችን የማሳሳት መብት የለውም። ይህ መልስ ለአንባቢዎቹ ሆነ፣ ለተቺዎቹ እና ለተመራማሪዎች ጠንቀቅ እንዲሉ በቂ ማሳሰቢያ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ።
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
