

በጃርሶ ረታ
አገራችን ካለችበት እጅግ አደገኛ ሁኔታ እንድትላቀቅ እና ሕዝቡ በሰላም፥ በደህንነት፥ በብልጽግና እና በአንድነት እንዲጓዝ የመንግሥት መለወጥ እና የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት መወገድ ብቸኛ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። ከአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ለለውጡ ዕውን መሆን የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የተሻለ ግንዛቤ እንደተገኘበት ይታመናል። ይሁንና ሀገራችን የተጋረጠባትን የህልውና ጠንቅ ለማስወገድና ሕዝባችንን ከክፍፍል፥ ከስደት፥ ከግድያ እና በአጠቃላይ ከጉስቁልና ኑሮ ለማላቀቅ የሰመረና የተቀናጀ የትግል ዘዴ እና ስልት ያስፈልጋል።
የትግሉ ዘዴና ስልት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ መስፈርቶች መካከል የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ በሚገባ መገንዘብ፥ የአገር እና የሕዝብ ጠላቶችን ለይቶ ማወቅ፥ የትግል አካሄድ ድክመቶችን ማጤን እና የትግል አቅጣጫውንና አሰላለፍን በውል መረዳት ያስፈልጋል። ለለውጥ ስኬት ወሳኙ ትልም ለውጥ ፈላጊውና ታጋዩ ሁሉ በግል እና በቡድን ወይም በማሕበረሰብ ደረጃ የሚጠበቅበትን ለመወጣትና ለመስዋዕትነት መዘጋጀት ግድ ይላል።
ከዚህ አኳያ በዚች አንስተኛ ጽሑፍ በዝርዝር ማቅረብ ባይቻልም ለትግሉ ስምረት አንዳንድ ሀሳቦችን ማንሳት መልካም ነው። እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ እንዴት ለውጡን ተግባራዊ እናድርገው? የሚለው ነው። ለዚህ ሙሉ ምላሽ ከመስጠት በመለስ አሁንም እንደትናንቱ በብዥታ ውስጥ መገኘታችንን ማንሳቱ ተገቢ ነው። ቀደም ሲል ጀምሮ በአጋራችን የፖለቲካ ውጥንቅጦች ለሽግግር መንግሥት የሚያበቁን በርካታ ሁኔታዎች አልፈውናል። ለምን ቢባል መልሱ ብዙ ምርምርን የሚጠይቅ አይደለም። ለትግላችን መጠማዘዝና ፈሩን ይዞ ያለመሄድና በእልህ አስጨራሽ አካሄድ እንደተፈለገው ካለረጅም ጉዞ ለድል አለመብቃት በርካታ ምክንያቶች አሉ። ሁሉም ምክንያቶች ከአመለካከት፥ ከድርጅታዊ አሠራር እና ከግለሰቦች አቋም አንጻር ሊታዩ ይችላሉ።
የለውጥ ትግልን በሰመረ ሁኔታ ለመምራት መጀመሪያ አደናቃፊ ችግሮችን ነቅሶ ማየት እና የመፍትሄ ዘዴዎችን መትለም ተገቢ ነው። በመሆኑም፥ በለውጥ አራማጆች ሆነ ፈላጊዎች ከጉጉትም ሆነ በቅጡ ያለማጤን ከተስተዋሉት የትግል አደናቃፊ ችግሮች መካከል ጥቂቶችን ለማየት እንሞክር።
– Advertisement –

1.አገራዊ አመለካከት – አገራዊ አመለካከት ከግል ጥቅም ይልቅ ለአገርና ለሕዝብ ልዕልና መቆም፥ ለአገር አንድነትና ነጻነት ቀናዒ መሆን፥ የአገርና የሕዝብን ታሪክ፥ ትሩፋትና እሴቶች በክብር መጠበቅ፥ ከባንዳዊ አቋም መራቅ እና በአጠቃላይ አገራዊ ራዕይ መላበስ ማለት ነው። አንደኛው የአገራችን ትልቁና ግዙፍ ችግር በጎሳ አስተሳሰብ ተተብትቦ ሚዛናዊ አስተያየት መስጠት ያለመቻል ነው። አገራዊ አመለካከት ተኮላሽቷል። አገራዊ ራዕይ በጎደፈ ጸረ-ሕዝብ አቋም ተጠርንፏል። ንጹህ እና የጸዳ አገራዊ ፍቅር ተፍቋል። የጎሳ ፖለቲካው ኢትዮጵያውያን እንዳይተማመኑ አድርጓል፥ እርስ በርስ አጋድሏል። በጎሳ አሰላለፍ ምክንያት የቆየ ጓደኝነት፥ ጉርብትና፥ አብሮ መሥራት እና ረጅም ዕውቅና ተሸርሽሮ የጋራ ራዕይ፥ የጋራ ጥቅም፥ የጋራ አገር እና ኢትዮጵያዊነት ለይስሙላ ሆነዋል። እንደፖለቲካዊ አደራጀታተቸው ዜጎች የሚኖሩት በአስመሳይነት እና በገሀድ ወይም በድብቅ በለየለት የጠላትነት ስሜት ውስጥ ነው። ይህ ሁኔታ ለጋራ አገራዊ እና ሕዝባዊ ትግል ስምረት ትልቁ ደንቃራ ሆኗል።
2.ውጤት ከሌላው መጠበቅ እና የተስፋ መቁረጥ ምልክቶች-በእርግጥ የትግል ውጤት ከሁሉም
የሚጠበቅ አይደለም። ይሁንና አነሰ ባዛ እያንዳንዱ ዜጋ ከራሱ በአስተሳሰቡ እና በተግባሩ የትግሉ ተሳታፊ የሚሆንበት ሁኔታ የተሟጠጠ አይሆንም። ታጋዮች በሰላማዊ ሆነ በትጥቅ ትግል ለውጤት መብቃት የሚችሉት የተቀረው ሕዝብ ቢይንስ ቢያንስ ለለውጡ ደንቃራ ሳይሆን ሲቀር ነው። ባለአቅም አገርና ሕዝብን ከሚያደሙ መራቅ፥ በሞራልም ሆነ በሌላ መልኩ አጋዥ ሆኖ ያለመገኘት በራሱ የትግል አስተዋጽኦ ነው። በሌላ መልኩ ይህን ለማደረግ የተሳነው መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን በተሎ ያለመድረስ “ዝም ብለው ነው!” በሚል ስሜት በተስፋ ቢስነት ለማንቋሸሽ መሞከር አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ለትግሉ አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው።
በዚህ ረገድ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በትጥቅ ትግል የተሳተፉትን የፖለቲካ ፐሮግራም የላቸውም ወይም ካለም አይረባም በሚል የሚሰጡት ትችት በይዘት ገንቢነት ሊኖረው ቢችልም፥ አቀራረቡ ግን አፍራሽነቱን አጉልቶ ያሳያል። እንዲህ አድርጉ ብሎ ሀሳብን መስጠት ሲቻል በማንቋሸሽ የሚቀርብ ትችት የፈለገውን ያህል ዕውነትነት ይኑረው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። የጎደለን መሙላት፡ የሌለን መስጠት ሲቻል ነቀፋዊ ትችት ማዥጎድጎድ ለጠላቶች እና ለተጠርጣሪዎች ጥይት ከማቀበል የተለየ አይደለም። መሆን የሚገባው ገንቢ አስተያየትን በአግባቡ ማቅረብ ካልሆነ የጠላት ወገን ከመሆን የሚለየው አይሆንም።
– Advertisement –

3.ሕዝብን መንቀፍ – ለአንድ ሀገራዊ የለውጥ ትግል የጠራ አገራዊ አመለካከት፥ጠንካራ አመራር
ለለውጥ የሚያበቁ ነባራዊ እና ተጨባጭ ሁኒታዎችን ያገናዘበ የዳበረ ንቃተ ህሊናና መስዋዕትነትን በአግባቡ እና በጥንቃቄ የመቀበል ዝግጁነት መኖር አስፈላጊ ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ከድርጅታዊ አሰላለፍ እና ከሕዝብ ቅቡልነት እና ከግለሰቦች ምንነት አኳያ መቃኘት ተገቢ ነው። ከዚህ አንጻር ባለፉት የመከራና የስቃይ፥ የትግልና የመስዋዕትነት ጉዟችን ከድርጅታዊ አሠራር ደካማነት ምክንያት የተከሰቱ ችግሮች በርካታ ናቸው።
በአገሪቱ ጠንካራ ድርጅታዊ አመራር ባለመኖሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለተለያዩ ድክመቶች ተዳርጓል። በዋናነት ከሚነሱ ድክመቶች መካከል ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል – በአፈጮሌ ግለሰቦች መታለል፡ ከአምክኖያዊ አስተሳሰብ ይልቅ በስሜት መነዳት፥ በመንግሥት ጭካኔያዊ እርምጃዎች ተሸማቆ ተስፋ መቁረጥ፥ መንግሥትን ከመጠን በላይ መፍራት፥ ከድህነት እና ከፍርሃት ብሎም ከማሕበራዊ፥ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውጥረት ለመውጣት ግልጽ እና ተስፋ ሰጭ ትግል ለማድረግ አቅም ማነስ በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።
ለእነዚህ ድክመቶች መሠረቶች የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች ናቸው። የፖለቲካ ድርጅቶች ማለትም በተቃዋሚነት ደረጃ የተመሠረቱ ፓርቲዎች በአብዛኛው የፓርቲነት መስፈርትን የማያሟሉ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በተለይ አብዛኞቹ ወይም ሁሉም ማለት ይቻላል ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት የሚያቀነቅኑ ናቸው። አብዛኞች ለፖለቲካ ሥልጣን እና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ተቋዳሽ ለመሆን የተሰባሰቡ ከገዥው ፓርቲ አቋም መሠረታዊ ልዩነት የሌላቸው ናቸው። ጥቂቶች አገራዊ አንድነት አለን የሚሉት የመስዋዕትነት ትንፋሽ የሌላቸው በአስመሳይነት በተደላደለ መልኩ ለፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የተኮለኮሉ ናቸው። በግለሰብ ሆነ በፖለቲካ አደረጃጀቶች ውስጥ የሰፈነው ራስ ወዳድነት፥ ሆድ አደርነት፥ አስመሳይነት፥ ግዴለሽነት፥ ካለኔ አዋቂ ለአሳር ባይነት፡ ፍጹም ባንዳነት፥ በሌላው መስዋዕትነት ለመወጣጣት መሻት፡ የሌሎችን መስዋዕትነት እና ድሎች ማንቋሸሽ፡ ግልጽ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ያለመኖር፡ እና የመሳሰሉት ባህርያት ሕዝቡንና የትግል ሂደቱን ጠርንፈውና ቀይደው ይዘውታል።
– Advertisement –
እውነታው ይህ ሁኖ ሳለ፥ የሕዝብ የትግል አካል የሆኑ የማሕበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ አንቂዎች፥ አንዳንድ ፖለቲከኞች እና ግለሰቦች የኢትዮጵያ ሕዝብ ተኝቷል፥አይንቀሳቀስም ሲሉ ይደማጣሉ። ዛሬ በቴዲ አፍሮ ዘፈን ግልብጥ ብሎ እንዲወጣ፡ በኑሮው ተማሮ በሰልፍ እንዲያጥለቀልቅ ይፈለጋል። እንደምሳሌ ጎረቤት አገር ኬኒያ በተቃውሞ ሰልፍ ትነሳለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቴዲን ለመታደግ መነሳት እንዴት ያቅተዋል እየተባለም ነው። አልፎ አልፎ በተከሰቱ የሕዝብ ትግል አካል በሆኑ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ለምሳሌ የጤና ባለሙያዎች ጠንካራ ትግል ባደረጉበት ወቅት ሕዝብ ድጋፉን በሰላማዊ ሰልፍ ባለማሳየቱ የደረሰበት ትዝብትና ነቀፋ በቀላሉ አይታይም። በዚህ ዓይነት በሕዝብ ላይ የሚቃጣ አስተያየት ትክክል አይመስለኝም። ሕዝብ በዘፈቀድ በግልፍተኝነት ግልብጥ ብሎ አይወጣም። ከውስጥ የሚቀሰቅሰው የሚያደራጀው፥ የሚያስታጥቀው፥ የሚመራው ኃይል ያስፈልገዋል። ዛሬ የረባ የፖለቲካ ፓርቲ በሌለበት፥ ሠራተኛው በጎሳ ፖለቲካ ተወጥሮ መንቀሳቀስ ሳይችል በረሃብ እያለቀ ባለበት ሁኔታ፥ ሰው ሆድ እና ጀርባ በሆነብት ጊዜ የሕዝብን ግልብጥ ብሎ የተቃውሞ ሰልፍ መጠበቅ አንድም የዋህነት አልያም የፖለቲካ ትግልን አካሄድ በአግባቡ ያለማጤን ነው።
በየትኛውም መስፍርት ይህ ዓይነቱ አመለካከት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥን አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎሳዊ ሽንቁር ተተብትቦም ቢሆን ከመታገል እና መስዋዕትነት ከመክፈል አልቦዘነም። በመላ አገሪቱ ትግል እየተካሄደ እንዳልተካሄደ መቁጠር ትክክል አይደለም። በ1997ዓ.ም ምርጫ ወቅት በገጠሩ ሆነ በከተማው የለውጡ መዘውሩና ሞተሩ ሕዝቡ ነበር። የጥቂቶች ብቅ ማለት ተስፋ አለመለመና ሕዝቡ ከጫፍ ጫፍ ተነሳ። ትግሉ የሕዝብ ነበር። መስዋዕትነት የከፈለው ቤት ይቁጠረውና ከፖለቲከኞች በላቀ ሁኔታ ትልቁን መስዋዕትነት የከፈለው ሕዝቡ ነው። ዛሬም መራራ ጽዋን እየከፈለ ነው። ግና ሕዝብ ያለመሪ መራመድ ከባድና አስቸጋሪ ነው። በመሪነት ያያቸው የደገፋቸውና የሞተላቸው ከዱት። አደሙት። ገደሉት። እንዲያም ሆኖ ዛሬስ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተዋጋ፡ እየተዋደቀ አይደለምን? የተፈለገው እንዲሆን የሚፈለገው ቅድመ ሁኔታ ሊሟላ ይገባል።
አጠቃላይ የአገራችን ችግር ዕይታ
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ክፍተቶች ይበልጥ ተወሳስበው እና ተጠላልፈው የሕዝብን ትግል ውል አልባ ያደረገው ሕውሀት ከቅኝ ገዥዎች የወረሰውን የጎሳ ፓለቲካ ስለሰነቀረብን ነው። ይህ የአገር ከፋፋይ መርዝ በቅኝ ገዥዎች የተጠነሰሰ እና በባንዳዎች ሲሽከረከር የቆየ ነው። ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን፥ እስያን እና ላቲን አሜሪካን ሲቀራመቱ እና እርስ በርሳቸውም በእራሳቸው አሕጉር እና በተጠቀሱት ክፍላተ ዓለም ሲተራመሱ የተከተሉት ዘዴ አንዱን ጎሳ ከሌላው ማናከስ፥ በነጻነት ሽፋን ሕዝቡ እርስ በርስ እንዲከፋፈሉ ማድርግ እና በግርግር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ አገሮችን በቁጥጥር ስር ማድረግ እና የበላይነታቸውን በማንገስ የሀገራትን አንጡራ ሀብት መዝረፍ ነው።
ጣሊያን በኢትዮጵያን ዳግም ወረራ በፈጸመች ጊዜ የፖለቲካ ሴራው ያጠነጠነው የጎሳ እና የሀይማኖት ጥላቻ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እንዲሰነቀር ማድረግ ነበር። ያነጣጠረውም በአማራ እና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ላይ ነበር። ይህ የቅኝ ገዥዎች ዕኩይ ሴራ በአያት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ተጋድሎ ከሸፈ። ሰንኮሉ ግን ከነጭራሹ ባለመነቀሉ ጊዜውን ጠብቆ ያኔ ድል የራቃቸው ባንዳዎች እንደገና አንሰራርተው የገዥዎቻቸውን ዓላማ አሳኩ። አባባሉ ዕውነት እንጂ ማጋነን አይደለም። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እንክብካቤ ሲያገኙ የነበሩ ባንዳ ወገኖቻችን በቀዝቃዛው ጦርነት መወገድ ጋር በለስ ቀንቷቸው በዓለማችን ኢትዮጵያን የመጨረሻዋ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እንድትወደቅ አስችለዋል። ማሳየዎች ወይም ማረጋገጫዎች ፍንትው ብለው ይታያሉ።
እነዚህን በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፥-
- ከሁሉም በላይ ለአገራችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ዓለማችንን የማይመጥን የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት በሕገ መንግሥት ተደንግጎ ኢትዮጵያ እንድትከፋፈል እና የጥንቱ የቅኝ ገዥዎች እና የባንዳዎች ዓላማ እና ፍላጎት እንዲሰምር ተደርጓል።
- የአንድነት ጸር የሆነው የፖለቲካ ሥርዓት አገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አሳጥቶ በጦርነት እንድትታመስ ሆኗል። ሕዝቡ በፍትህና ርትዕ ዕጦት ተወጥሮ ለስደት፥ ለመከራና ለጉስቁልና ኑሮ ተዳርጓል።
- ዛሬ ኢትዮጵያ በነጻነት አርአያነት ያበቃትን እና አብዛኝ የአፍሪካ አገራት፥ መላው ጥቁር ሕዝብ እና የሕዝቦችን ነጻነት ፈላጊ ኃይሎች የሚያደንቋትን አረንጓዴ፡ ቢጫ ፥ቀይ ሰንደቅ ዓላማ አዋርዳዋትና አርክሰዋት ይገኛሉ።
- በዓለም ካሉት የራሳቸው ፊደላት ካለቸው 8 ቋንቋዎች መካከል የታሪክ እና የሥልጣኔ መሠረት የሆነውን ብሔራዊ ቋንቋችን ከብሔራዊ ስሜት እንዲላቀቅ በማድረግ ‘የሥራ ቋንቋ’ ተብሎ በሕገ መንግሥት ተደንግጓል። ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የዓለም ቋንቋዎች የተሻለ እና አማራጭ የሌለውን የግዕዝ/አማርኛ ፊደላት ከመጠቀም ይልቅ ለከፋፋይ ቅኝ ገዥዎች ታዛዥነትን ለማረጋገጥ በላቲን መጠቀምን አምጥተዋል። ዛሬ ዘመናዊ ሆነች በተባለች አዲስ አበባ በኦፊሴል በየመንገዱ እና በየአደባባዩ ጥቅሶችና ስያሚዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ በማድረግ ኢትዮጵያዊነትን የመፋቅ ተግባር እየተሠራ ነው።
- በአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ሰነድ አንደኛው ቋንቋ የነበረው አማርኛ የአፍሪካ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን በኢትዮጵያዊያንና የውጭ ዜጎች የቀረበ ጥያቄ በኢትዮጵያ መንግሥትን ድጋፍ አላገኘም።
- በቅኝ ግዛት ትግል በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ጉልህ ሚና ያሳዪትን ማሳየት ይቅርና ዓለም አቀፋዊ ዝናና ክብር ያገኙትን የሚኒሊክን ስም በጊዜ ሂደት ለማጥፋት የሚኒሊክ ቤተ መንግሥትን በአንድነት ፓርክ ስም፥ የአድዋ ድል በዓል በሚኒሊክ አደባባይ ይደረግ የነበረውን በአድዋ ሙዚየም ውስጥ እንዲከበር በማድረግ የሚኒሊክን ስም በማደብዘዝ የቅኝ ገዥዎች መንፈስ እየታደሰ ነው።
- ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥታት እና የሕዝቡ አይበገሬነት ምልክት አንበሳ ከሚኒሊክ ታላቁ ቤተ መንግሥት ተወግዶ በአገራችን በማትታወቅና ለመንግሥት ሆነ ለሕዝብ የማትመጥን በሽቅርቅርነቷ ልዩ ትርጉም ባላት እንስሳ ተለውጧል። ታሪክ መግደል ስሜት ማጥፋት መንገዱ ብዙ ነው።
- ኤርትራ ከእናት አገሯ እንድትገነጠል አብሮ የመታገል ውጤቱ ሆኖ አገሪቱ ከነጭራሹ ወደብ አልባ እንድትሆን ተደርጓል።
የዚህ ሁሉ ሂደት ውጤት አሌ የማይባል ሀቁ በቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‘ዳስ ጣል’ እና ሌሎች ዜማዎች ተገልጸዋል። ስምን አምላክ ያወጣዋል እንዲሉ ስሙ ከእነአባቱ ቴዎድሮስ ካሳሁን – የሚገርም ነው። ከለጋ ዕድሜው ጀምሮ እንደአጼ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ አንድነት ልቡ የተቃጠለ- ኢትዮጵያን የካሰ እና እየካሰ ያለ ወጣት ጀግና ነው። ኢትዮጵያ ከእርሱ በፊት ሆነ ከእርሱ ጊዜ ጅምሮ የኢትዮጵያ ህመም ያመማቸው ብሶቷን ያሰሙ፥ ያነቡ ወደ እስር ቤት የተወረወሩ፥ የቆሰሉ፥ የሞቱ ብርቅየ ጀግኖችን አፍርታለች። በዜማዊ ኪነት ዓለም ጥላሁን ገሠሠ በአገራችን የደረሰውን የረሀብ ሰቆቃ በተመለከተ “ወይ እማማ ወይ አባባ” የሚለውን ጣዕመ ዜማ ከሚያዥጎደጉደው እንባ ጋር ያሳየው ጥበብ ፥ “አልቻልኩም መረረኝ እኔን” እና “ወደፊት በሉለት ” የሚሉት ጣዕመ ዜማዎች ፥ አለማዬሁ እሸቴ “እኔ ልኮማተር እኔ ከሰል ልምሰል’’ የሚለው፥ ጠለላ ከበደ ከገጠሬው ዕረኛ አሳምራ ያቀረበችው “ሎሚ ተራ፥ተራ! እምየን አደራ” እና በዘመናችን እነሻምበል በላይነህ፥ ዳኜ ዋለ፥ ፋሲል ደሞዝ እና ሌሎችም ያወጧቸው ቀስቃሽ ዜማዎች እና በስተጀርባ የነበሩና ያሉ ጠበብት የመስዋዕትነት ትግሎች መገለጫዎች ናቸው።
ዛሬ ቴዎደሮስ ካሳሁን በጀግንነት ለአገሩ መዳን እና መካስ ያደረገው ጥረት ዘመናትን ተሻጋሪ አኩሪ ሥራ ነው። በጥበብ ኃይሉ የኢትዮጵያን እና የሕዝቧን ብሶትና ጉስቁልና አጉልቶ ያወጣው እጅግ ድንቅ ውጤት የዓለም ማሕበረሰብን አድናቆት አስገኝቶለታል። ዘፈኑ እንዳይሰማ የተደረገውና እየተደረገ ያለው ጥረት አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የአገራችን ተጨባጭ ሁኒታዎች ጉልህ ማሳያ ነው።
የመፍትሄ አቅጣጫ
የአገራችን ጉዞና ተጨባጭ ሁኔታ በአጭሩና በጥቅሉ የቴዲ ‘ኢትዮ-ሪካ’ ቁልጭ አድርጎ አቅርቦታልና በዚሁ እንቋጨው። ትልቁና ወሳኙ ቁም ነገር እንዴት እና በምን ሁኔታ አዲሲቷን ጀምበር እናምጣ ነው። በዚች አጭር ጽሑፍ የትግል ሂደቶችን በዝርዝር ይቅርና በጥቅሉም ቢሆን ማቅረብ ያዳግታል። ቢሆንም በንድፍ መልኩ የሚከተለውን ማቅረብ ይቻላል።
ሀ. የፖለቲካ አቋም
- ከሁሉም በላይ የአገራችን ችግር በዘለቄታ ሊፈታ የሚችለው የቅኝ ገዥዎችን እና የባንዳዎችን የጎሳ ፖለቲካ በማስወገድ እና ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን በማንገሥ ብቻ እንደሆነ የትግሉ ተካፋዮች ማመን ይኖርባቸዋል። ይህም የሕገ መንግሥቱ መቀየር አንደኛውና ዋናው የለውጡ መሠረትና ምሰሶ ነው።
ለ. የትግል ዘዴ
- ትግላችን በደፈናው በሰላማዊ ትግል እና በአንድነት በሚል አባባሎች ከመታጀል መቆጠብ ያስፈልጋል።
- ሰላማዊ ትግል አስቻይ ሁኒታዎች ሲኖሩ የሚተገበር ሲሆን፥ አስቻይ ሁኔታ ከሌለ ግን የሰላማዊ ትግል ቅንቀና ለትጥቅ ትግል ዕውቅናን በመስጠት ድጋፍ ሰጭ ሚና ያለው ሆኖ መቅረብ አለበት።
- በአንድነት ለአንድነት መታገል ትልቁ የትግል ዘዴ ነው። ሆኖም፥በአንድነት መታገል እንዲሁ በግለሰቦችና በተለያዩ ድርጅቶች መሰባሰብ የሚከወን አይደለም። ጥርት ያለ ፖለቲካዊ አቋም ካልያዙ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ጋር መቀላቀል አደጋው የከፋ ይሆናል። አብይን – ብልጽግናን በደፈናው የጋራ ጠላት አድርጎ መሰባሰብ ሩቅ አይስኬድም። ትናነት የኦነግ መሥራቾች እነሌንጮና ዲማ ነገዎ በ30 ዓመት ትግላቸው ውጤት በማጣታቸው የመሠረቱትን ኦነግ ትተው የሚያዋጣን በኢትዮጵያ ጥላ ሥር መታገል ነው ብለው ወሰኑ። በአሜሪካ ከነበሩ ኢትዮጵያዊነትነ ከሚያራምዱ 3 ድርጅቶች ጋር ተሰለፉ። እሰየ ተባለ። እኒህ ግለሰቦች ሕውሀት በኦሮሞ መንግሥት ሲተካላቸው ሁለተኛውን ክህደት ፈጸሙ። ዛሬ የመንግሥት አማካሪዎች በመሆን ለኦሮሞ ነጻ መሆን እያሴሩ ነው። በተመሳሳይ በሥልጣን ሽኩቻ ተጣልተው ዛሬ ጸረ-አብይ አቋም የያዙት ትክክለኛ አቋማቸው ምን እንደሆነ ማረጋገጫ ሳይኖር ከእነሌንጮ ዓይነቱ ጋር ግጥም ማለት አደጋ አለው። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ካላማከለ ግለሰብ ሆነ ድርጅት ጋር በደፈናው የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በማለት መሰባሰቡ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።
- በተፎካካሪነት እና በጥርጣሬ ብሎም ከጠላትነት ባላነሰ የሚተያዩ ኃይሎች የኢትዮጵያ መከፋፈል መጨረሻው የአገርን ሕልውና ማጣት፥ ሕዝብን ለባርነት መዳረግ እና የውጭ ኃይሎች መፈንጫ መሆንን ሊረዱ ይገባል። አገራዊ ራዕይ ሳይዙ የጋራ ጠላትን ማስወገድ ቢቻልም፥ አገርን እና ሕዝብን ካዙሪት ድህነት፥ መከራና ስቃይ እንደማያወጣ የጋራ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል። ይህንን ሀቅ ተረድተው በስውርና በገሀድ እየተገናኙ ያለፈውን ወደጎን ትተው ለአገር እና ለሕዝብ የሚበጀውን ለማድረግ መነጋገር፥ መግባባት እና መተማመን ይኖርባቸዋል። የሁሉን አቋም ጠንቅቆ ማወቅ አስፈላጊ ነውና።
- ሁሉም ለአገራችን ለውጥ መገኘት እና ለሽግግር መንግሥት መፈጠር ቀጥታ ተሳታፊ ሆነ ደጋፊ በጋራ ትግሉ ለመሳተፍ የሚሹ ኃይሎች – ድርጅቶች ሆኑ ግለሰቦች – ቢያንስ በሚከተሉት ላይ ካላንዳች ማሽሞንሞን ወይም ብዥታ ግልጽ አቋማቸውን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።
- አሁን ስላለው የአገራችን የፖለቲካ ሥርዓት
- ወደፊት ስለሚያራምዱት የፖለትካ ሥርዓት
- በየትኛውም የአገራችን ክፍሎች ስለሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች ያላቸው አቋም
- ስለሽግግር መንግሥት ምሥረታ ዓላማ፥ሂደት እና ይዘት
- ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ሊኖሩ ስለሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች ወ.ዘ.ተ
- በትጥቅ ትግል የተሰማሩ ኃይሎች በትግሉ ግምባር ቀደም ተፋላሚዎችና የሕይወት መስዋዕትነት ከፋዮች ስለሆኑ የሚከተሉትን የፖለቲካ ሥርዓት በማብራራት
- ለኢትዮጵያ ሕዝብ፥
- የአገር ድምበርን የመጠበቅ ኃላፊነትን ወደጎን ትተው ወገኖቻቸውን በመውጋት በታሪክ እና በሕዝብ ተጠያቂ ለሆኑት የመከላከያ ኃይል አባላት፥
- በራስ ጥቅም በመታወር ለተወሰነ ቡድን ሥልጣን ማራዘም ወገኖቻቸውን ለሚጨርሱና ለሚያስጨርሱ የየክልሉ የአስተዳደር ኃላፊዎችና ሠራተኞች፥ የልዩ ጥበቃ፥ የሚሊሽያ እና የፖሊስ አካላት እና
- በአገር ውስጥ እና በውጭ ላሉ ደጋፊ እና ተቃዋሚ ኃይሎች አሰባሳቢ አገራዊ ጥሪ ቢያቀርቡ ይመረጣል።
- በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ አገራት የሚኖሩ የተቃዋሚ ኃይሎችም ግልጽ የፖለቲካ አቋማቸውን በግልጽ እና በማያሻማ ሁኔታ ማሳወቅ እና እርስ በርስ በሰለጠነ መንገድ መፈታተሽ ይጠበቅባቸዋል።
በአጭሩ ለዘላቂ የአገራችን ችግር መፈታት በመሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ጋር ተመሳሳይ አቋም ይዞ መገኘት የትግሉ ዋንኛ ቁልፍ ነው። መፍትሄው በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እጅ ነው። የግድ በሁሉም ባይባልም በተለይ በእርግጠኝነት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት በቆሙት ልጆቿ ነው። ስለዚህ ሁሌም በዙሪያ ከመሽከርከር ወደ ጥርጊያው ትግል ለመግባት የቁርጥ ልጆች ድርጅታዊ ሥራዎች እንዲሠሩ ማድረግና መደገፍ እና ማገዝ ያስፍልጋል። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስፈልገው የሚኖርበትን መከራውን መግለጽ እና ለምን ሰልፍ አትወጣም ከማለት በፖለቲካ ድርጅቶች፡ በሰላማዊ ድርጅቶች፡ በመንግሥት ድርጅቶች እና በግል ድርጅቶች ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ለማታገል በድርጅታዊ መልኩ ማዘጋጀትና ትክክለኛውን የትጥቅ ትግል-አይምሯዊ እና አካላዊ – ኃይል መርጦ ከጎኑ መሰለፍ ያሻል። ያለድርጅታዊ ሥራ ፎቀቅ ማለት አንድ እርምጃ ለመጓዝ አይቻልም።
ምንጊዜም ሕዝብ ያሸንፋልና ትግሉንና መስዋዕትነቱን ሳናኳስስ እኛው የትግሉ አካል እንሁን። ለትግል መሪን ማውጣት ግድ ይላልና በእኔ እምነት ወደኢትዮጵያዊነት ማማ ለመውጣት ቆራጥ ትግል ለሚያደርገውና ከአማራዊነት ወደኢትዮጵያዊነት ለሚገሰግሰው ፋኖ እና ተመሳሳይ አቋም ያነገቡ ኃይሎች ካሉም ዕውቅና ሰጥቶ እነሱኑ በአንድነት እንዲሰባሰቡ ማድረግ ትኩረት ይሰጠው። እነዚህን ኃይላት የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅፈውና ደግፈው እንዲቀበሏቸው በሁሉም ጥረት ይደረግ። ለድርጅታዊ ሥራ በውጭም በአገር ውስጥም ቅድሚያ ትኩረት ይሰጥ።
እግዚእብሔር ኢትዮጵያን ይባር!!!`
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
