
Harun media ሃሩን ሚዲያ ·Follow
የትግራይ ሲኖዶስ አክሱምን “ቅድስት ከተማ” ማለቱ ለከተማው ሙስሊሞች ከባድ ስጋትና ቅሬታ ፈጠረ!
• ሀሩን ሚዲያ | ሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ል
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ (መንበረ ሰላማ) አክሱም ከተማን “ቅድስት ከተማ አክሱም ጽዮን” በማለት መሰየሙ እና ለአፄ ዮሐንስ 4ኛ የሰማዕትነት እውቅና መስጠቱ ከፍተኛ ትችት እያስነሳ ይገኛል።
ሲኖዶሱ ውሳኔውን ያሳለፈው አክሱም የሕገ-ልቦና፣ የኦሪት እና የክርስትና እምነት መሠረት መሆኗን በመጥቀስ ቢሆንም፤ ይህ እርምጃ ከሀገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ የሴኩላሪዝም መርህ ጋር የሚጋጭና የከተማዋን ሙስሊም ነዋሪዎች መብት የሚጋፋ ነው ተብሏል።
የሕግ ባለሙያዎች እና የመብት ተሟጋቾች እንደሚያስረዱት፣ አክሱምን የአንድ ሃይማኖት ብቻ “ቅድስት ከተማ” አድርጎ መሰየም፣ አስተዳደራዊ መዋቅሩን ከሃይማኖት ጋር በማቀላቀል የሌሎች እምነት ተከታዮችን በተለይም ሙስሊሙን ማህበረሰብ ያገልላል።
ይህ ዓይነቱ ውሳኔ የከተማዋ ሙስሊሞች የመስጊድ ግንባታ፣ የመቃብር ቦታ እና ሂጃብን የመሰሉ ሃይማኖታዊ መብቶቻቸውን ይበልጥ እንዲገደቡ ከማድረጉም በላይ፤ ለዘመናት በከተማዋ የኖረውን ማህበረሰብ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንዲታይ የሚያደርግ ስጋት ደቅኗል።
በሌላ በኩል ሲኖዶሱ ለአፄ ዮሐንስ 4ኛ የሰጠው “የሰማዕትነት” እውቅና የታሪክ ምሁራንን እና ሙስሊሙን ማህበረሰብ በእጅጉ አስቆጥቷል። አፄ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ታሪክ ሙስሊሞችን “ተጠመቁ ካልሆነ ሀገር ለቃችሁ ውጡ” በማለት ያስገደዱ፣ የእስልምና መጻሕፍትን ያቃጠሉ እና አሻፈረኝ ያሉትን ያስጨፈጨፉ መሪ መሆናቸውን ታሪክ ይመሰክራል።
ይህ ጥቁር የታሪክ ጠባሳ እያለ መሪውን በሰማዕትነት ማወደስ፣ በወቅቱ የተፈጸመውን ግፍ እንደመደገፍ የሚቆጠርና በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተፈጸመውን ታሪካዊ በደል የሚዘነጋ አድራጎት መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ባለፈው ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ል በአክሱም ሹቅ መስጊድ ውስጥ ዱዓ ላይ በነበሩ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ሲኖዶሱ የሰጠው ማብራሪያ ሌላው አነጋጋሪ ነጥብ ሆኗል።
በተጨባጭ ሸይኽ ሙሐመድ አወልን ጨምሮ በርካታ ምዕመናን ተደብድበው ሆስፒታል መግባታቸው እየታወቀ፤ ሲኖዶሱ በመግለጫው ተበዳይ ሙስሊሞችን “በጸብ አጫሪነት” መክሰሱ የፍትሕ መዛባትና የጋራ አብሮነትን የሚጻረር ነው በሚል ተወግዟል።
በአጠቃላይ የሲኖዶሱ ውሳኔዎች አድሎአዊ እና የዜጎችን እኩልነት የሚጥሱ በመሆናቸው፤ አክሱም የሁላችንም ከተማ መሆኗ ቀርቶ የአንድ እምነት ተከታዮች ብቻ ተደርጋ መታሰቧ በቀጣይ ለሃይማኖት ግጭት መንስኤ እንዳይሆን ስጋት አጭሯል። በመሆኑም መንግሥት የዜጎችን እኩልነት እና የሃይማኖት ነጻነት የማስከበር ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
ዙል-ቂዕዳ 20 ቀን 1447 ዓ.ሂ
© ሀሩን ሚዲያ
See less

