ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ከ 4 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአውሮፓ ህብረት በአሜሪካ ላይ የጣለውን ግብር እስከ ሐምሌ 4 ድረስ ወደ ዜሮ ካላወረደ በህብረቱ ላይ “በጣም ከፍ ያሉ” ታሪፎችን እንደሚጥሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠነቀቁ።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ጋር የስልክ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው።

እንደ ትራምፕ ገለጻ ህብረቱ እስከ የአሜሪካ “250ኛ ዓመት የልደት በዓል ድረስ ጊዜ እንደተሰጠው እና ይህ ካልሆነ ግን የሚጣልባቸውን ታሪፍ በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር” ከኮሚሽነሯ ጋር ተስማምተዋል።

ቮን ደር ሌየን በበኩላቸው ህብረቱ የትራምፕ የቀነ ገደብ ከማብቃቱ በፊት “በታሪፍ ቅነሳ ላይ ጥሩ ለውጥ እያሳየ ነው” ብለዋል።

ይህ ከሆነ ከሰዓታት በኋላ የአሜሪካ የንግድ ፍርድ ቤት ትራምፕ በበርካታ አገራት ላይ የጣሉት የ10 በመቶ ታሪፍ በአሜሪካ የንግድ ሕግ መሠረት ትክክል እንዳልሆነ የሚገልጽ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ ውሳኔ ወደፊት የፍርድ ቤት ክርክሮች እንዲደረጉ ሊያደርግ ይችላል።

ቮን ደር ሌየን እና ትራምፕ የንግድ ስምምነት የተፈራረሙት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ነበር። ረቡዕ ዕለት በአውሮፓ ህብረት ሕግ አውጪዎች እና መንግስታት መካከል የተደረገው ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ግን ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ተስተጓጉሏል።

“ሁለታችንም ለተግባራዊነቱ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኞች ነን” ሲሉ ቮን ደር ሌየን ሐሙስ ዕለት ኤክስ ላይ ጽፈዋል።

በስምምነቱ መሠረት ከአውሮፓ ህብረት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶች 15 በመቶ ታሪፍ ይጠብቃቸዋል። ትራምፕ በአውሮፓ ምርቶች ላይ 30 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ዝተዋል።

ስምምነቱ በመጋቢት ወር ከአውሮፓ ፓርላማ በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ይሁንታ አግኝቷል። አብዛኛዎቹ ህግ አውጪዎች ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ህግን ቢደግፉም አሜሪካ የስምምነቱን እንድትጠብቅ ለማድረግ የታለሙ በርካታ አንቀጾችን አክለዋል።

የፓርላማ አባላት በብረት እና በአሉሚኒየም የተሰሩ የአውሮፓ እቃዎች ትራምፕ በብረት ምርቶች ላይ ከጣሉት 50 በመቶ ታሪፍ ውጭ ከሆኑ ብቻ በአሜሪካ ምርቶች ታሪፉን ዜሮ እንደሚያደርጉ ድምጽ ሰጥተዋል።

ሀሳቡ በፓርላማው ቢጸድቅም ስምምነቱ በ27ቱ አባል አገራት ጭምር መጽደቅ ይኖርበታል።

የአውሮፓ ፓርላማ ዋና ተደራዳሪ በርንድ ላንጅ የትራምፕ የማህበራዊ ሚዲያ መግለጫ ከመውጣቱ በፊት እንዳሉት፤ ሕግ አውጪዎች እና መንግሥታት በድርድሩ ዙሪያ ጥሩ ለውጥ እያሳዩ ቢሆንም “አሁንም የሚቀረን መንገድ አለ” ብለዋል።

ተደራዳሪዎቹ ግንቦት 19 በስትራስቡርግ ሌላ ዙር ውይይት ለመገናኘት ተስማምተዋል።

“ለአውሮፓ ህብረትም ሆነ ለአሜሪካ ዜጎችንና ኩባንያዎችን የሚጠቅሙ ተጨማሪ ዋስትናዎችን ለማቅረብ የፓርላማውን ሥልጣን ለማስከበርና ለመከላከል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በቁርጠኝነት እንቀጥላለን” ሲሉ ላንጅ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ህብረትን “የተስማማንበትን የንግድ ስምምነት ሙሉ በሙሉ አላከበረም” ሲሉ ከስሰዋል። በዚህም በጭነት ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለውን የታሪፍ ጭማሪ ወደ 25 በመቶ እንደሚያሳድጉ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው የታሪፍ እና የንግድ ስምምነት የተደረሰው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በተርንቤሪ፣ ስኮትላንድ በሚገኘው የቅንጦት ሪዞርታቸው የጎልፍ ጨዋታ ካጠናቀቁ በኋላ ነበር።

በንግድና በታሪፍ ስምምነቶች ላይ የሚደረጉ ድርድሮች በቀጠሉበት በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንቱ ሰፊ የታሪፍ ውሳኔዎቻቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማስቀጠል ተቸግረዋል።

ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ የንግድ ፍርድ ቤት የትራምፕ 10 በመቶ ዓለም አቀፍ ታሪፎች በአሜሪካ የንግድ ሕግ መሠረት ሕጋዊ አይደሉም ሲል ወስኗል።