
ከ 5 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ
በአሜሪካዋ ግዛት ሚኒሶታ የኢሚግሬሽን ሠራተኞች የሚያደርጉት አሰሳን ማጠናቀቃቸው ከተሰማ ወር ቢሞላውም አሁንም የፍርሃት ድባብ እንዳጠላ ነው።
ሁለት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በኢሚግሬሽን ባልደረቦች ከተገደሉ በኋላ በመላ አገሪቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተቀጣጥሎ፣ በተለይ ደግሞ በሚኒያፖሊስ የሚኖሩ የሶማሊያ ማኅበረሰብ አባላት በፍርሃት ውስጥ እየኖሩ ነው።
የ23 ዓመቱ አብዲ (*ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ ተቀይሯል) በፍርሃት ጥላ ስር ከሚኖሩ በርካታ የሶማሊያ ማኅበረሰብ አባለት መካከል አንዱ ነው።
ዛሬም መሣሪያዎችን ታጥቀው፣ ፊታቸውን በጭምብል ሸፍነው በከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የኢሚግሬሽን ሠራተኞችን የሚመለከታቸው በፍርሃት ነው።
“ገና አላበቃም” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል። በአንድ ቦታ ከአምስት ሌሊት በላይ እንደማያሳልፍ የሚናገረው አብዲ ወደ ሥራውም ሲሄድ ተደብቆ ነው።
አንዳንድ ጓደኞቹ እንደ እርሱ ጊዜያዊ ከለላ የሚያሰጣቸው ወረቀት (ቲፒኤስ) ቢኖራቸውም በቅርቡ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይናገራል።
ቲፒኤስ በግጭት፣ በአደጋ ወይም በድንገተኛ ሁኔታዎች ከተጎዱ አገራት የመጡ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ በአሜሪካ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ እንዲኖሩ እና እንዲሠሩ ያስችላቸዋል።
አብዲ ሶማሊያን ለቆ የወጣው የአልሻባብ ታጣቂዎች እርሱን ለመመልመል ከሞከሩ በኋላ በ2022 ነው።
ደብዛዛ ብርሃን ካለው የመኖሪያ አፓርትመንት ውስጥ ሆኖ ለስለስ ባለ ድምጽ “እዚህ ለመድረስ 15 ሺህ ዶላር ያህል አውጥቻለሁ። ቤተሰቤ ሁሉንም ነገር ሰጥቷል” ብሏል።
ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የኬንያ ፓስፖርት ገዝቶ ወደ ብራዚል በመብረር ወደ አሜሪካ የሚያደርገውን ረዥም ጉዞ ጀመረ።
ይህም በኮሎምቢያ እና በፓናማ መካከል ያለውን ጫካ እንዲሁም በዓለም ላይ ካሉት እጅግ አደገኛ የፍልሰት መንገዶች አንዱ እንደሆነ የሚታመነውን የዳሪየን ሸለቆ እና ረግረጋማ ስፍራ ማቋረጥን ያካተተ ነበር።
“በአንድ ወቅት አስከሬን ላይ ቆምኩ” ይላል ጉዞውን ሲያስታውስ።
የአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ከደረሰ በኋላ ወደ አሜሪካ ተሻግሮ የጥገኝነት ጥያቄ አቀረበ። የሕግ ምክር ካገኘ በኋላም እስከ 2029 ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ለመኖር እና ለመሥራት የሚያስችል የቲፒኤስ ማመልከቻ አቀረበ።
በአብዲ አስተሳሰብ ሁኔታው የኅልውና ቀውስ ሆኖ ቀጥሏል።
“ወደ ሶማሊያ ከመመለስ ይልቅ እዚህ ሕይወቴን ሙሉ ተደብቄ መኖርን እመርጣለሁ፤ ምክንያቱም ሕይወቴ አደጋ ላይ ይወድቃል።”
በአሜሪካ ውስጥ ወደ 260 ሺህ የሚጠጉ ትውልደ ሶማሊያውያን ይኖራሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአገሪቱ የተወለዱ ሲሆኑ፣ ብዙዎቹ ደግሞ ዜግነት አግኝተዋል ሲል የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ አስታውቋል።
የሶማሊያ ማኅበረሰብ መሪዎች እንደሚሉት በሕገ ወጥ መንገድ አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት ነው።
ብዙዎቹ ወደ አሜሪካ የመጡት በአውሮፓውያኑ 1991 መላውን ሶማሊያ የተቆጣጠረው መንግሥት ከፈረሰ በኋላ በነበሩት ዓመታት ነው። አገሪቱ ሥር የሰደደ ድርቅ ያጋጠማት ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዘላቂ ሰላም አላገኘችም።
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከእስልምና ታጣቂዎች በተለይም ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ካለው ከአልሻባብ ጋር ስትዋጋ ቆይታለች።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር እንደ አውሮፓውያኑ እስከ መጋቢት 17 ድረስ በአገራቸው ውስጥ ያለው የደህንነት ሁኔታ ተሻሽሏል በሚል ለሶማሊያ ስደተኞች የተሰጠው ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ (ቲፒኤስ) ለማገድ ጥሯል።
ይህም ወደ 2,500 የሚጠጉ ሰዎችን እንደሚጎዳ ይታሰባል። ሆኖም ግን የፌዴራል ዳኞች ለጊዜው ይህንን ማድረግ እንዳይችሉ የሚያደርግ ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ከዚህ ቀን በፊትም ቢሆን በሚኒሶታ የተሰማሩት 3,000 ተቆጣጣሪዎች ሰዎችን እያፈሱ ነበር፤ አንዳንዶቹም አስቀድመው ተባርረዋል።
ይህ ዘመቻ ትራምፕ ስለ ሶማሊያ ማኅበረሰብ ከሰጡት አንዳንድ የሚያዋርድ አስተያየት የተነሳ ዒላማ እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓል።

በኢሚግሬሽን እና ጉሙሩክ (አይስ) ባልደረቦች አሰሳ ወቅት ተይዘው የታሰሩት አንዳንድ ሰዎች ምንም እንኳን ዘመዶቻቸው ጋዜጠኛ ማነጋገር ቢፈሩም፣ የአሜሪካ እና የሶማሊያ ጥምር ዜግነት ያላቸው መሆናቸው ይነገራል።
አንዳንድ ቤተሰቦች ከፊሎቹ ወደ ሶማሊያ ተባርረው በመከፋፈላቸው ለመናገር ፍርሃት ውስጥ ናቸው።
አንድ ሰው ከተባረረ ወደ አሜሪካ እንዳይመለስ የ10 ዓመት ዕግድ ይጣልበታል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ገደብ ከዚህም የሚረዝም በመሆኑ ከኖሩበት አገር፣ ከልጆቻቸው ያቆራርጣቸዋል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት በሚኒሶታ የሚያደርገው ዘመቻ ለሕዝብ ደኅንነት ትልቅ ድል መሆኑን አስታውቋል።
“በሚኒያፖሊስ ፖለቲከኞች የራሳቸውን ሕዝብ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በምትኩ ወንጀለኞችን ለመከላከል በመነሳታቸው አሜሪካውያንን ሲገድሉ፣ ልጆችን ሲጎዱ እና ሽብር ሲያነግሱ የነበሩ ከ11,000 በላይ ሕገወጥ የውጭ ዜጎችን በቁጥጥር ስር አውለናል” ሲል ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ዶናልድ ትራምፕ ዳግመኛ ለመመረጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የሕገ ወጥ ስደተኞች ጉዳይ ዋነኛ የዘመቻቸው አካል ነበር።

ለሚኒያፖሊስ ከንቲባ ጃኮብ ፍሬይ እንዲህ ያሉ ፍርሃቶች የአሜሪካ ፖሊሲ ውስጥ ያለ ጉልህ መጣረስን ያመለክታሉ።
“የፌዴራል መንግሥት በዩናይትድ ስቴትስ ጊዜያዊ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ አካል አያስፈልግም ይላል፤ በተመሳሳይ ደግሞ አደገኛ ስለሆነ በማለት ሰዎች ወደ ሶማሊያ እንዳይጓዙ ያስጠነቅቃል” ሲሉ አለ ያሉትን ተቃርኖ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የትኛው ነው?”
በርካታ የስደተኞች ማኅበረሰቦች መኖሪያ በሆነችው በሚኒያፖሊስ አንዳንድ አካባቢዎች ቢቢሲ ሲዘዋወር፣ የአፈሳው ተጽእኖ አሁንም በጉልህ ይታያል።
ምንም እንኳን የዕለት ተዕለት ኑሮ ቀስ በቀስ ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለስ ቢጀምርም፣ ትምህርት ቤቶች እንደገና ቢከፈቱም የፍርሃት ደመናው ግን አሁንም በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ አለ።
ጥቂት ሱቆችና ምግብ ቤቶች አሁንም ዝግ ናቸው።
ከቻይናውያን ምግብ ቤት ውጭ ባለ የመኪና ማቆሚያ ቦታ አደጋ የገጠማቸውን መኪኖች የሚያነሳ መኪና ሹፌር ቆሟል።
“የዚህ ምግብ ቤት ባለቤት እና ሠራተኞች በአይስ እንደተያዙ ሰምቻለሁ፤ ለዚህም ነው የተዘጋው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
አንዳንድ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶቻቸው ለመመለስ በጣም ስለፈሩ ለቀናት እዚያው ቆመው እንደነበርም አክሏል።

“በጨለማ ውስጥ እየኖርን ነው” ሲሉ የሚኒሶታ ኮንግረስ አባል ኢልሃን ኦማር በቅርቡ በሚኒያፖሊስ በተካሄደ የዴሞክራቶች ጉባዔ ላይ ተናግረዋል።
ትውልደ ሶማሊያዊቷ ኢልሃን ኦማር ያለፉት ጥቂት ወራት ለሕፃናትም ጭምር አስከፊ እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“አሁንም ቢሆን ያስቆሙኝ ይሆናል፤ ወላጆቼን ያስቆሙ ይሆን የሚል ስጋት አለ። የጤና እንክብካቤ ማዕከሎቻችን እንኳን ተጎድተዋል።”
ትራምፕን በመተቸት የሚታወቁት የምክር ቤት አባሏ የዘመቻውን ስፋት እና አይስ የተጠቀመባቸውን ስልቶች ነቅፈዋል።
ከዚህ በፊት የነበሩ አስተዳደሮችም ቢሆኑ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ማባረራቸውን ያስታወሱት የምክር ቤት አባሏ፤ እርምጃቸው ከትራምፕ አስተዳደር በተለየ ሽብር የሚነዛ እንደልነበር ይገልጻሉ።
“የኦፕሬሽን ሜትሮ ሰርጅ የተካሄደበት መንገድ በጎዳናዎቻችን በጭምብል የተሸፈኑ፣ የማይለዩ፣ የጦር መሳሪያዎች ታጥቀው ብዙ ሰዎችን ማፈስ ነበር። እዚህ ያየነው የጦርነት ቀጣና ይመስል ነበር።”
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት (ዲኤችኤስ) በሕጋዊ መንገድ በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚፈሩት ነገር እንደሌለ እና የአይስ ወኪሎች ጭምብል የሚያደርጉት “በሽብርተኛ ደጋፊዎች እንዳይለዩ ለመከላከል” መሆኑን ይናገራል።
ትራምፕ ሶማሊያውያንን “ቆሻሻ” በማለት የሰጡት አስተያየት የበለጠ ውጥረቱን አባብሷል።
“በአገራችን እንዲኖሩ አልፈልግም፤ እውነቱን እነግራችኋለሁ… አገራቸው ጥሩ ያልሆነው ያለምክንያት አይደለም” ሲሉ ትራምፕ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በሚኒሶታ የሶማሊያ ማኅበረሰብን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወንጀል መፈጸማቸውን በተደጋጋሚ አጉልተው አሳይተዋል።
በኮቪድ-19 ወቅት ለልጆች ምግብ ለማቅረብ በሚል የሜኔሶታን መንግሥት አጭበርብረዋል የተባሉ ሰዎችን የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ከስሷል።
የቀድሞው የሜኔሶታ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መርማሪ ኬሽ ሜጋን እንዳሉት፤ በዚህ የማጭበርበር ክስ ብዙ ሶማሊያዊ ስደተኞች ስማቸው ተነስቷል። ተፈጽሟል በተባለው ማጭበርበር የሜኔሶታ ግዛት በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ማጣቱም ተገልጿል።
በማጭበርበሩ ስማቸው የተነሳው ሰዎች ከአጠቃላዩ የሚኒሶታ ሶማሊያዊ ነዋሪዎች አንጻር ውስን ቁጥር ነው ያላቸው።

የሚኒሶታ ሴኔት የሪፐብሊካን አባል የሆኑት ጂም አቤለር የአይስ ስልቶችን ተችተዋል። ነገር ግን ይህ ችግር መጠገን የሚያስፈልጋቸው ጥልቅ የፖሊሲ ውድቀቶችን እንደሚያመለክት ይሰማቸዋል።
“ይህ የፓርቲ ጉዳይ ነው ብዬ አላስብም። የብሔራዊ የኢሚግሬሽን ፖሊሲያችን ድብልቅልቁ የወጣ ነው። ለአስር ዓመታት የሁለት ወገን ውድቀት ሆኖ ቆይቷል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የትራምፕ ስድብ በሚኒሶታ ሶማሊያውያን ዘንድ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ በኋላ አግኝተውት የነበረውን ድጋፍ አሳጥቷቸዋል።
የሚኒያፖሊስ ነዋሪዋ ፉስ አቤ “ለትራምፕ ድምጼን ሰጥቻለሁ፤ እና ያንን በማድረጌ ተጸጽቻለሁ” ካለች በኋላ “እኔ ባልመርጠው ኖሮ ‘ቆሻሻ’ ብሎ ሊጠራን አይችልም ነበር” ስትል ትጸጸታለች።
ኦፕሬሽን ሜትሮ ሰርጅ ያደረገው አንድ ነገር ቢኖር ሰዎችን ባልተጠበቀ መንገድ ማሰባሰብ ነው።
ይህም የሶማሊያ አሜሪካዊ ኢማም ሻሪፍ መሐመድን እና በአሜሪካ የኢቫንጀሊካል ሉተራን ቤተክርስቲያን ፓስተር የሆኑትን ጄን ቡክሌይ ፋርሊን ያካትታል።
ኢማሙ “የአይስ ወረራ የበለጠ ቅርበት እና የበለጠ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን ፈጥሯል” ብለዋል።
ፓስተሯም “አፈሳው ሲካሄድ ሰዎች አንድ ላይ ተሰበሰቡ እና እርዳታ የት እንደሚያስፈልግ እና እንዴት ምላሽ እንደምንሰጥ ጠየቁ” ብለዋል።
የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት በአቅራቢየው በሚገኙበት ጊዜ ነዋሪዎችን ለማስጠንቀቅ አንድ ላይ ሆነው መደበኛ ያልሆነ የማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን መሥርተዋል፤ ይህም ለፍርሃታቸው ምላሽ የሚሰጥ ነው።

ከእነዚህ በጎ ፈቃደኞች መካከል ሬኔ ጉድ እና አሌክስ ፕሬቲ በጥር ወር በተካሄደው አፈሳ ወቅት በፌዴራል የኢሚግሬሽን ሠራተኞች የተገደሉ ሁለት የአሜሪካ ዜጎች ናቸው።
ሌሎቹ በጎ ፈቃደኛ የሆኑት ጡረተኞቹ ሊሳን እና ባለቤቷ ሲሆኑ፣ የኢሚግሬሽን ሠራተኞች በአካባቢው ካሉ ነዋሪዎች እንዲጠነቀቁ ፊሽካን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ።
“ዝም ያሉ ናቸው ግን ደግሞ የበለጠ ተንኮለኛ ናቸው። ከነዋሪው ጋር ስለሚቀላቀሉ ለመለየት አስቸጋሪ ነው” ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።
አብዲ ተስፋ እንደቆረጠ ቢናገርም የእነዚህ የበጎ ፈቃድ ማኅበረሰቦች የተወሰነ መረጋጋት ሰጥተውታል።
“በአሜሪካ ተስፋ ነበረን። ሕልማችን ተንኮታኩቷል” ብሏል።
