Ethiopia Election

ኢሰመኮ የምርጫ ጣቢያዎች በመጠጥ ቤት፣ በመከላከያ እና ፖሊስ ጣቢያዎች ጭምር መቋቋማቸውን በክትትል እንዳረጋገጠ ገለጸ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በዛሬው ዕለት ሚያዚያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በምርጫ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ያዘጋጀውን የሰብዓዊ መብቶች ግኝት ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ወቅት እንደገለጸው፣ ምንም እንኳን አብዛኛው የመራጮች እና የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት “በመልካም ጎኑ የሚታይ ቢሆንም” የተለያዩ ጉድለቶች መታየታቸውንም ይፋ አድርጓል። ሪፖርቱ በተለይም የምርጫ ጣቢያዎች በሕግ ባልተፈቀዱ አካባቢዎች መቋቋሙን መታዘቡን አሳውቋል።

የኮሚሽኑ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ዳይሬክተር መቅደስ አመኑ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ክልክል በሆኑ በመከላከያና በፖሊስ ጣብያዎች እንዲሁም በመጠጥ ቤቶች መቋቋማቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በጋምቤላ ክልል ላሬ በሚባል የምርጫ ጣቢያ “የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ ዘግይቶ በመድረሱ ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ለሦስት ቀናት ብቻ ተከናውኗል” ብለዋል።

የሪፖርቱን ይፋ መሆን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ነዋይ በተከለከሉ ቦታዎች የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሟል በሚል ለቀረበው ወቀሳ መልስ ሲሰጡ፣ “የፖሊስ አባላት ልብስ የሚቀይሩበት እና የሚያርፉበት ቦታ” የተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን አምነው፣ “ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ” የተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች የሉም ብለው ተከራክረዋል።

ኮሚሽኑ አክሎም በሚዛን አማን ከተማ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ዜጎች “ስብሰባ እና ሰልፎች ላይ ተሳትፎ እንዲያርጉ” አስገድዷል ብሏል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ተግዳሮች እንደገጠማቸው በክትትሉ እንደተደረሰበት ተነግሯል።

በቅድመ ምርጫ ክትትሉ ላይ የዕጩዎች ምዝገባን፣ የመራጮች ምዝገባን፣ የምርጫ ቅስቀሳ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አካባቢ ያለውን የመራጮች ምዝገባ ሂደትን አካቷል። ኮሚሽኑ ይህንን ሥራ ለመሥራት 55 የሚሆኑ የክትትል ቡድኖችን በማቋቋም የቅድመ ምርጫ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን ተመልክቷል።

ኢሰመኮ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ምልከታ ማድረጉን ገልጾ፣ በ150 የምርጫ ክልሎች ክትትል እንዳደረገም አሳውቋል። በተጨማሪም ክትትሉ በ1,007 የምርጫ ጣብያዎች እና በ47 ልዩ የምርጫ ጣብያዎች በተለይም በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ክትትል መደረጉን ገልጿል።

በሪፖርቱ 886 ቃል መጠይቆችን እና 405 የቡድን ውይይቶች መደረጋቸውንም ሪፖርቱን ያቀረቡት መቅደስ አመኑ ተናግረዋል።
በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ይታከልበታል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection 

See less