ከ 4 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በእስር ላይ የነበረችው ኢራናዊቷ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ናግረስ ሞሐመዲ በገጠማት የጤና እክል ምክንያት ወደ ቴህራን ሆስፒታል ተዛወረች።

የኢራን ባለሥልጣኖች ናግረስ “በከፍተኛ ዋስትና አማካኝነት ከእስር እንድትወጣ” መወሰናቸውን ቤተሰቦቿ የከፈቱት ተቋም አስታውቋል።

ናግረስ በዓመቱ መባቻ በገጠማት ሁለት ተከታታይ የልብ ድካም ምክንያት እስር ቤት ልትሞት እንደምትችል ቤተሰቦቿ እና ደጋፊዎቿ ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቀው ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2023 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆነችው ናግረስ፤ በኢራን የሴቶችን ጭቆና በመቃወም እና ለሰብአዊ መብት በመታገል ትታወቃለች።

ናግረስ ሞሐመዲ ፋውንዴሽን “የቤተሰቦቿን ተማጽኖ ተከትሎ በራሷ የሕክምና ቡድን ለመታከም ወደ ቴህራን ፓርስ ሆስፒታል ተዘዋውራለች” ብሏል።

በእስራት ላይ ሳለች በሰሜን ኢራን በሚገኘው ዛንጃን ለ10 ቀናት ሆስፒታል ቆይታለች።

ፓሪስ የሚኖረው ባለቤቷ “ያለችበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም” ብሏል።

በእስር ላይ ሳለች ወደ 20 ኪሎግራም የሰውነት ክብደቷ መቀነሱ ተገልጿል።

መናገር እንደሚያስቸግራት እና ማንነቷን ለመለየት እስከሚያስቸግር መጎሳቆሏን ጠበቃዋ ቺሪን አርዳካኒ ተናግረዋል።

“መንግሥትን የሚጻረር ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት እና ከመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ጋር በመጋጨት” ክሶች በአውሮፓውያኑ 2021 ላይ የ13 ዓመታት እስር ተፈርዶባታል።

ክሶቹን ያስተባበለች ሲሆን፤ በ2024 በጤና እክል ምክንያት ከአደገኛው የኢራን ኢቪን እስር ቤት እንድትወጣ ተወስኖ ነበር።

ባለፈው ታኅሣሥ በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ “ቀስቃሽ ንግግር” በማድረግ የኢራን መንግሥት ወንጅሏት በቁጥጥር ሥር ውላለች። ስትታሰር በመደብደቧ ወደ ሆስፒታል መወሰዷን ቤተሰቦቿ ገልጸዋል።

ጥር ላይ የኢራን አብዮታዊ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ሰባት ዓመት ተኩል እስራት ፈርዶባታል።

ጠበቃዋ እንዳሉት የቀረበባት ክስ “ለፕሮፓጋንዳ እንቅስቃሴ መሰብሰብ እና መመሳጠር” ነው።

የመብት ተሟጋቿ ወንድም ሐሚድረዛ እንደተናገረው እህቱ ዛንጃን እስር ቤት ውስጥ በገጠማት የልብ ድካም ሳቢያ ራሷን ስታ ተገኝታለች።

የቤተሰቧ ተቋም “ከእስር መውጣት ብቻውን በቂ አይደለም። ቋሚ እና ልዩ ክትትል ያስፈልጋታል። ወደ እስር ቤት ተመልሳ የተፈረደባትን 18 ዓመታት እንድትጨርስ መደረግ የለበትም” ሲል መግለጫ አውጥቷል።

“ክሶቿ ባጠቃላይ ውድቅ ተደርገው ያለ ቅድመ ሁኔታ ነጻነቷ እንዲከበር ማድረግ ያለብን አሁን ነው። ማንኛውም ሰው ወይም የሴቶች መብት ተሟጋቾች በሰላማዊ ሥራቸው ምክንያት መታሰር የለባቸውም” በማለትም መግለጫው ያሳስባል።