ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ኢራን ውስጥ በጎዳና ላይ እግረኞች ሲንቀሳቀሱ ይታያል

ከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሜሪካ ከኢራን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ማቆሟን እየተናገረች ነው።

በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ከተደረገ ከሳምንታት በኋላ ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ “ኢፒክ ፊውሪ’ በማለት የተጠራው ዘመቻ ማብቃቱን ተናግረዋል።

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በተደረገው ጦርነት ማን አሸነፈ?

መልሱ የሚወሰነው ይህንን የጦርነት ታሪክ እንደሚናገረው ወገን የሚወሰን ይሆናል።

በኢራን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የዓለም ኃያላንን የጦርነት ጥምረት መቋቋማቸውን እና ማሸነፋቸውን ዘግበዋል።

በአሜሪካ በኩል ደግሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና አስተዳደራቸው ዓላማቸውን እንዳሳኩ እና ድል እንደተቀዳጁ ይናገራሉ።

ነገር ግን በአደባባይ ከሚነገሩ አስተያየቶች እና ከሚወጡ መግለጫዎች ባሻገር ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረጉ ድርድሮች ከጦርነቱ ባልተናነሰ ወሳኝ እየሆኑ መጥተዋል።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ግቦቿን ማሳካቷን በመግለፍ በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ማብቃቱን ተናግረዋል
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው ግቦቿን ማሳካቷን በመግለፍ በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ማብቃቱን ተናግረዋል

ከአክሲዮስ፣ ከሮይተርስ እና ከሌሎች የአሜሪካ ሚዲያዎች የተገኙ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ዋይት ሐውስ ከኢራን ጋር ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም መቃረቡን ያምናል።

ሰነዱ በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም፣ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ እና በሰፊው የቀጣናው ውጥረቶች ላይ ቀጣይ ድርድር ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ ይፈጥራል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገሪቱ ዕቅዱን እየገመገመች መሆኑን እና ምላሽዋን በፓኪስታን በኩል እንደምታሳውቅ ተናግረዋል። ነገር ግን አንዳንድ ከፍተኛ የኢራን ፖለቲከኞች አስቀድመው በይፋ ውድቅ አድርገውታል።

“አሜሪካውያን ከተሸነፉበት ጦርነት ምንም አያገኙም” ሲሉ የኢራን ፓርላማ የብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮሚሽን ቃል አቀባይ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈው፣ “የአሜሪካ ፍላጎት” በማለት ውድቅ አድርገውታል።

እስካሁን ይፋ በሆኑት የዕቅዱ ዝርዝር ሃሳቦች መሠረት፣ ኢራን የኒውክሌር ግንባታዋን ለ20 ዓመታት ማገድ፣ ከፍተኛ የበለፀገ የዩራኒየም ክምችቷን ማስረከብ እና ሰፊ ዓለም አቀፍ ቁጥጥር እንዲደረግ መፍቀድ ይኖርባታል።

ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ስምምነቱ ኢራን የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ እንደገና እንድትከፍት ዋስትና እንድትሰጥ ያስገድዳል።

በምላሹም አሜሪካ ቀስ በቀስ ማዕቀቦችን ታነሳለች፣ የታገደ የኢራን ሀብትን ትለቅቃለች እና የስምምነቱ ጊዜ ካበቃ በኋላ ኢራን የተወሰነ ዩራኒየም ማበልጸግ እንድትጀምር ትፈቅዳለች።

ነገር ግን በኢራን ውስጥ ላሉ ብዙዎች እነዚህ ቃላት ከስምምነት ይልቅ እንደ እጅ መስጠት ተቆጥረዋል። ክርክራቸው ቀላል ነው። አሜሪካ ወሳኝ ውጤቶችን ማግኘት ስላልቻለች ‘ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉዩሪ’ን አቋርጣለች ብለው ያምናሉ።

አሜሪካ የሆርሙዝን የባሕር ወሽመጥ እንደገና ለማስከፈት የጀመረችው ዘመቻ በድንገት ተቋርጧል።

ኢራን በአካባቢው ያሉትን የአሜሪካ የጦር ሠፈሮች እና የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ዒላማ ብታደርግም፣ ከባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል አንዳቸውም በቀጥታ ወደ ጦርነቱ አልገቡም።

የቀድሞውን የኢራን ጠቅላይ መሪ የሚያሳይ ግዙፍ ቢል ቦርድ
የምስሉ መግለጫ,የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እስራኤል እና አሜሪካ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጦርነቱን ሲጀምሩ በፈጸሙት ጥቃት ተገድለዋል

ከሁሉም በላይ ደግሞ ምንም እንኳ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በርካታ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች እና ከፍተኛ የደኅንነት መሪዎች በጦርነቱ ቢገደሉም ሥርዓቱ ባለበት ቀጥሏል። የኢራን የፖለቲካ እና የወታደራዊ ሥርዓት መሥራቱን ቀጥሏል፤ ተተኪዎችንም በፍጥነት ሾሟል።

ከጦርነቱ በፊት አንዳንድ የምዕራባውያን ባለሥልጣናት እና ተንታኞች ፈጣን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፍተኛ የኢራን መሪዎች እና አዛዦች መግደል አዲስ ተቃውሞዎችን ሊያስነሳ እና ምናልባትም ሥርዓቱን ሊጥል እንደሚችል ያምኑ ነበር።

ያ ግን አልሆነም።

ከጦርነቱ በፊት በነበሩት ወራት ኢራንን ያናወጡት ተቃውሞዎች በአብዛኛው ከጎዳና ላይ ጠፍተዋል። የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥራቸውን አጠናክረዋል። እስሩም ጨምሯል። አንዳንድ የሞት ቅጣቶችም ተፈጽመዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በበርካታ ከተሞች መንግሥትን የሚደግፉ ሠልፎችን በተደጋጋሚ ሲካሄዱ አሳይተዋል።

የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ ሞሐማድ ባጋር ጋሊባፍ
የምስሉ መግለጫ,የኢራን ዋነኛ ተደራዳሪ ሞሐማድ ባጋር ጋሊባፍ “በዚህ መልኩ መቀጠል ለአሜሪካ የሚያዋጣ እንዳልሆነ እናውቀዋለን፤ እኛ ግን ገና አልጀመርንም” ሲሉ ተናግረዋል

የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ እና ዋነኛ ተደራዳሪ መሐመድ ባጊር ጋሊባፍ በቅርቡ “አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል ለዩናይትድ ስቴትስ አዋጭ አለመሆኑን በሚገባ እናውቃለን፤ እኛ ግን ገና አልጀመርንም” ሲሉ ተናግረዋል።

ለኢራን አመራር በሕይወት መትረፍ ብቻ ድል ሊሆን ይችላል። በተለይም ቴህራን በአካባቢው እና በእስራኤል እንዲሁም በአሜሪካ ጦር ሠፈሮች እና በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ያደረሰችውን ጉዳት ስትመለከት ድሏን ታላቅ እንደሆነ ልታውጅ ትችለላች።

ለዚህም ነው ቴህራን ሌላ ዙር ጦርነት ቢመጣ ግድ እንደማይሰጣት እና ዝግጁ መሆኗን እየገለጸች ያለችው።

የኢራን ባለሥልጣናት ከተቃዋሚዎቻቸው ይልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ጫናን እንዲሁም የተራዘመ ጦርነትን የበለጠ የመቋቋም አቅም እንዳላቸው ያምናሉ።

ሦስት ሰዎች በባህር ዳርቻ አካባቢ ተቀምጠው
የምስሉ መግለጫ,ኢራን አሁን የሆርሙዝን እንደገና መክፈት እንደ ስምምነት ሳይሆን እንደ የመደራደሪያ መሳሪያ አድርጋ ትመለከተዋለች

በተጨማሪም የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ መዘጋት ኢራን አሁንም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንዳሳደረች ያሳያል ብለው ያምናሉ። ወሽመጡ ከዓለም ነዳጅ እና ጋዝ መተላለፊያ በላይ መሆኑ ተረጋግጧል።

የአካባቢው ፀጥታ መደፍረስ የመርከብ ጭነትን፣ የምግብ አቅርቦትን፣ የኢንሹራንስ ወጪን እና ሰፊውን ዓለም አቀፍ ንግድ አስተጓጉሏል።

ኢራን አሁን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደገና መክፈት እንደ ስምምነት ሳይሆን እንደ መደራደሪያ መሳሪያ አድርጋ ትመለከተዋለች።

ይህ ለቀጣናው ሰፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ኢራን ከግጭቱ በኋላ ጠንካራ ትወጣ ይሆን፤ በተለይም በጦርነቱ ወቅት የአሜሪካን የጦር ሠፈሮች ያስተናገዱ ወይም በተዘዋዋሪ የአሜሪካን እና የእስራኤልን ዘመቻዎች የደገፉ ጎረቤት አገራት ላይ ክንደ ብርቱ ሆና ልትወጣ ትችላለች።

በቴህራን የፈራረሰ የመኖሪያ ቤት
የምስሉ መግለጫ,ኢራን በጦርነቱ ከፍተኛ የጦር አዛዠቿን አጥታለች፤ በርካታ መሠረተ ልማቶቿ ወድመዋል

ይህ ማለት ኢራን የፈለገችውን ሁሉ አሳካች ማለት አይደለም። አገሪቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፤ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናትን እና ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን አጥታለች። እንዲሁም ተቃውሞዎችን ሊያቀጣጥል የሚችል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ ትገኛለች።

አሜሪካ እና እስራኤል በተራቀቁ የጦር መሳሪያዎች እና የስለላ አቅማቸው ኢራን ውስጥ ዘልቀው በመግባት መምታት እንደሚችሉ አሳይተዋል።

ነገር ግን ጦርነቶች ሁልጊዜ የሚወሰኑት በጦር ሜዳ ብቻ አይደለም። ይህ ግጭት በመጨረሻ በጦርነቱ በራሱ ሳይሆን ለማስቆም በተደረገው ድርድር ውጤት ሊመዘን ይችላል።

አሜሪካ ኢራንን ወደ ወሳኙ የኑክሌር ስምምነት እንድትገባ ካስገደደች፣ አሜሪካ ስኬታማ ትሆናለች። ቴህራን በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ካስጠበቀች እና የኒውክሌር መረሃ ግብሯን በቋሚነት መቀጠል ከቻለች ኢራን በምትኩ ድል ትነሳለች።

ይህ ግጭት በመጨረሻ በጦርነቱ ሳይሆን ያንን ለማስቆም በተደረገው ድርድር ውጤት ሊፈተሽ ይችላል።

ለጊዜው ሁለቱም አገራት ለሕዝባቸው በጦነርቱ ማሸነፈቸውን እየተናገሩ ነው። ትክክለኛው መልስ ግልጽ የሚሆነው ግን ሁለቱም ወገኖች ወደ ጠረጴዛው መጥተው እስከ መጨረሻው ድረስ በመደራደር ከስምምነት መድረስ ሲችሉ ብቻ ነው።