
ከ 3 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ
መሐመድ አሳሳ አባቱ ሁሴንን ቀብሮ ወደ ቤት ተመለሰ። ብዙም ሳይቆይ ብዙ ልጆች “ሠፋሪዎቹ መቃብሩን እየቆፈሩ ነው” ብለው እየጮሁ ወደ ቤቱ ገቡ።
ሁሴን የ80 ዓመት የዕድሜ ባለ ጸጋ ነበሩ። የሚኖሩት በዌስት ባንክ ጄኒን አቅራቢያ ነው። በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚከበሩ ሰው ነበሩ።
ከብት አርቢ የነበሩት የ10 ልጆች አባት በእስልምና አስተምሮ መሠረት ተቀበሩ። ከቤተሰቡ ቤት ጀርባ በሚገኝ አነስተኛ ኮረብታ ላይ ነበር ሥርዓተ ቀብሩ የተከናወነው።
ችግር እንዳይፈጠር የፈራው መሐመድ በአቅራቢያው ካሉት የእስራኤል ወታደሮች ለቀብር ሥነ ሥርዓቱ ፈቃድ ጠይቋል።
ከቀብሩ ከግማሽ ሰዓት በኋላ ግን ወደ ሥፍራው ለመመለስ ተገደደ። አይሁዳውያን ሠፋሪዎች የአባቱን መቃብር እየቆፈሩ ነበር። የተወሰኑት መሣሪያ ታጥቀዋል።
መጀመሪያ ሊያግባባቸው ሞከረ። ሰሚ ሲያጣ የአባቱ መቃብር ላይ ቆመ። የአባቱን አስከሬን ለማውጣት ተቃርበው ነበር።
“አስከሬኑን ሊያወጡት ነበር። ውሳኔዬ ቅጽበቱን የተከተለ ነበር” ይላል።
ሠፋሪዎቹ በቅርቡ የተደራጀው ሳ ኑር ሰፈራ አካል ናቸው። የሚኖሩት ከቀብር ሥፍራው በላይ ነው።
በፍልስጤም መሬት ላይ ያሉ ሰፈራዎች ባጠቃላይ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተቀባይነት የላቸውም። ሠፈራዎቹ ሕገ ወጥ ቢሆኑም እንኳን የቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት ሳ-ኑር የተባለ ይዞታን በቅርቡ ለሰፋሪዎች ሰጥቷል።
በቁጥጥር ሥር ባለችው ዌስት ባንክ የሠፋሪዎችን ይዞታ የማስፋፋት ሒደቱ ከፍተኛ ውዝግብ አስከትሏል።
ሰፋሪዎቹ “ወይ አስከሬኑን ታወጡታላችሁ ወይም እኛ እናወጣዋለን” ብለው የመሐመድን ቤተሰቦች ማስፈራራት ጀመሩ።
አማራጭ የሌላቸው የመሐመድ ቤተሰቦችም መቃብሩን መቆፈር ቀጠሉ። ይህም በሞባይል በተፈረጸ ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ ይታያል።
መሐመድ እና ወንድሞቹ የአባታቸውን አስከሬን አውጥተው ከኮረብታው በታች ወሰዱት። ሠፋሪዎቹ እዚያው ሆነው ይመለከቷቸው ነበር።
የእስራኤል መከላከያ ኋላ ላይ ባወጣው መግለጫ ጣልቃ ገብቶ የሰፋሪዎቹን መቆፈሪያ መሣሪያ እንደወሰደ እና ነገሩ እንዳይባባስ እንዳደረገ አስታውቋል።

የመሐመድ ቤተሰቦች በበኩላቸው ወታደሮች እዚያው ቆመው የአባትየው አስክሬን በአሳዛኝ እና አሳፋሪ ሁኔታ ተቆፍሮ ሲወጣ መመልከታቸውን ይናገራሉ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል “የሕዝብን ሰላም የሚያውክ፣ የሕግ የበላይነትን የሚገዳደር፣ በሕይወት ያሉም ይሁን የሞቱ ሰዎችን ክብር የሚያጓድል ድርጊት ያወግዛል” ሲል ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ቢሮ ድርጊቱ “አስቀያሚ እና መሬታቸው በይዞታ ሥር ያሉ ፍልስጤማውያን የሰውነት ክብር ማጣት ማሳያ ነው” ሲል አውግዟል።
የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር አጂታ ሱንጋይ “ማንም ሰው ከዚህ አያመልጥም። በሕይወት ቢኖርም፤ ቢሞትም” ብለዋል።
ሳ-ኑር የሰፈራ መንደር እንደ አዲስ ከተጀመረ ወዲህ ያለው ውጥረት ማሳያ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በሁሴን አሳሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከተገኙት አንዱ “እጅግ ያስቀይማል። መሬቱ ሁሉ ንብረታቸው ይመስላቸዋል። መልሰው አካባቢው ላይ መስፈር ይፈልጋሉ” ብለዋል።
“የሌሎች ዘመዶቻችን መሬትም በቅርቡ በሰፋሪዎች እና ወታደሮች ተወርሯል። ሁሉንም የወይራ ዘይት ዛፎች ያለ ምክንያት ነቅለዋል” ሲሉ የሀሰን ዘመድ ተናግረዋል።
ሰፋሪዎቹ ተንቀሳቃሽ ቤታቸውን ይዘው በሳ-ኑር እንዲሰፍሩ ተነግሯቸዋል። ቦታው ከእስራኤል መከላከያ ኃይል መቀመጫ አጠገብ ነው የሚገኘው።
አካባቢው “ዝግ ወታደራዊ ቀጣና” ተብሎ የተሰመ ነው።
ይህ ማለት ደግሞ የወይራ ዘይት ዛፎች፣ የእርሻ ቦታ እና የቀብር ሥፍራ በነዋሪዎች መንደር ውስጥ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ በአካባቢው ለሚደረግ እንቅስቃሴ ፈቃድ የሚሰጠው የእስራኤል መከላከያ ኃይል ነው። ከመከላከያ ኃይሉ በበለጠ ግን ሠፋሪዎች ቁጡ እና አስፈሪ መሆናቸውን ይገልጻሉ። መሣሪያ የሚታጠቁትም በአደባባይ ነው።
መላው ዓለም ትኩረቱ ሌሎች ጦርነቶች ላይ በሆበነት በአሁኑ ወቅት በዌስት ባንክ ከሠፋሪዎች ጋር የተያያዘ ግጭት እና ጥቃት እየተበራከተ መጥቷል።
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱበት ጊዜ አንስቶ በሰፋሪዎች በተፈጸመ ጥቃት 13 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ በቅርቡ ዘግቧል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በርካቶችም ከቤታቸው እንዲወጡ ተገድደዋል።
በኔታንያሁ መንግሥት ውስጥ ያሉ አክራሪ ሚኒስትሮች በሚሰጡት ድጋፍ እና መሣሪያ ምክንያት በግዳጅ ይዞታ ሥር ባሉ የፍልስጤም ግዛቶች የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ሕይወት አደጋ ውስጥ እንደወደቀ የሰብዊ መብት ተሟጋቾች ገልጸዋል።
ሁሴን አሳሳ ከተቀበሩበት ሥፍራ በግዳጅ አስክሬናቸው እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ በመንደሩ በሚገኝ ቦታ ተቀብረዋል።
አካባቢውን “ቤታችን” ብለው ከሚጠሩት ሰዎች ከተነሳው ውዝግብ በኋላ አስክሬናቸው አርፏል።
