አሜሪካ በኢራን በምታካሄደው ጦርነት እስካሁን ድረስ 29 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን አንድ ከፍተኛ የፔንታጎን ባለሥልጣን ማክሰኞ ዕለት አስታወቁ። ፔንታጎን አሁን ይፋ ያደረገው የገንዘብ መጠን ባለፈው ወር ከገመተው የ4 ቢሊዮን ብልጫ አሳይቷል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከ 27 ደቂቃዎች በፊትአሜሪካ በኢራን ጦርነት እስካሁን 29 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን ፔንታጎን አስታወቀአሜሪካ በኢራን በምታካሄደው ጦርነት እስካሁን ድረስ 29 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷን አንድ ከፍተኛ የፔንታጎን ባለሥልጣን ማክሰኞ ዕለት አስታወቁ።ፔንታጎን አሁን ይፋ ያደረገው የገንዘብ መጠን ባለፈው ወር ከገመተው የ4 ቢሊዮን ብልጫ አሳይቷል።ዲሞክራቶች ከስድስት ወር በኋላ ለሚካሄደው ምርጫ ድጋፍ እያገኙ ሲሆን ጦርነቱ የኑሮ ውድነትን አንሯል ሲሉ ጣታቸውን በሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት ላይ ቀስረዋል።ታዛቢዎች በምርጫው ሪፐብሊካኖች አብላጫውን የኮንግረስ ወንበር ሊያጡ ይችላሉ ሲሉ ተንብየዋል።ፔንታጎን ሚያዚያ 21 2018 ዓ.ም. በኢራን ጦርነት 25 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቱን ይፋ አድርጎ ነበር።የበጀት ጉዳዮችን የሚከታተሉት ጁለስ ሀርስት ለሕግ አውጪዎቹ አዲሱ የገንዘብ መጠን ጥገናን እና የምትክ መሣሪያዎችን እንዲሁም የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን የሚያካትት መሆኑን ተናግረዋል።ከመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ዳን ኬይን ጋር በመሆን ለምክር ቤት አባላት ሪፖርቱን ያቀረቡት ሃርስት “የበጀት እና የመከላከያ ቡድኖች በጋራ ጦርነቱ ምን ያህል እንደሚያስወጣ በቋሚነት ያሰላሉ” ብለዋል።ፔንታጎን በጀቱን 29 ቢሊዮን ዶላር አንዴት እንዳደረሰው ግልጽ አይደለም።በመጋቢት ወር ለሮይተርስ መረጃ የሰጡ አንድ ምንጭ የትራምፕ አስተዳደር በጦርነቱ የመጀመርያ ስድስት ቀናት ብቻ 11̄.3 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቱን ገምቷል።
  2. ከ 1 ሰአት በፊትከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር ወደ ቻይና የ17 የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያ ኃላፊዎች እንደሚጓዙ ተገለጸየአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቻይና ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያመሩ የ17 የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያ ኃላፊዎች አብረዋቸው እንደሚሄዱ ዋይት ሐውስ አስታወቀ።ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር በጀመሩት ጦርነት ምክንያት አራዝመውት የነበረውን የቻይና ጉብኝታቸውን የፊታችን ሐሙስ እና አርብ ዕለት ያካሄዳሉ።ከትራምፕ ጋር ወደ ቻይና ከሚሄዱት መካከል የቴስላ ባለቤት ኤለን መስክ እና የአፕል ኃላፊው ቲም ኩክ እንደሚገኙበት ታውቋል።የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በዚህ ሳምንት በቻይና በሚያደርጉት ጉብኝት ወቅት አብረዋቸው ከሚሄዱት ከፍተኛ የንግድ እና የቴክኖሎጂ ባለቤቶች መካከል የአፕሉ ሥራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ እና የቴስላ እና ስፔስ ኤክስ ባለቤቱ ኤለን መስክ እንዲሁም የሜታ፣ ቪሳ፣ ጄፒ ሞርጋን፣ ቦይንግ፣ ካርጊል፣ ብላክ ሮክ ኃላፊዎች ይገኙበታል ብሏል።ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዚህ ጉብኝታቸው ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በመገናኘት ኢራንን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።ከአስርት ዓመታት በኋላ አንድ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ወደ ቻይና ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያደርግ ትራምፕ የመጀመርያው ናቸው።ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ያለውን የንግድ ጦርነት ያረግባል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።ትራምፕ ወደ ቻእና ለማቅናት አቅደው የነበረው እአአ መጋቢት 31 ሲሆን፣ የካቲት 21 2018 ዓ.ም. አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ ዘግይቷል።በምላሹም ኢራን በባህረ ሰላጤው ውስጥ የእስራኤልንና የአሜሪካ አጋር አገሮችን በማጥቃት ለዓለም የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ዝውውር ቁልፍ የሆነውን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን በመዝጋቷ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ተፈጥሯል።ትራምፕ በኢራን ነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ የሆነችው ቻይናን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጫና እንድታደርግ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።ቻይና በኢራን ጦርነት ምክንያት የምታስቀባው የነዳጅ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን ጦርነቱ እንዲያበቃ በብርቱ ትፈልጋለች።ቻይና ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ክምችት እና የተለያዩ የኤነርጂ አቅርቦት አማራጮች አሏት።ትራምፕ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ዢን ጂንፒንግን በዋሽንግተን ዲሲ ተቀብለው ለማስተናገድ ቀጠሮ ይዘዋል።
  3. ከ 2 ሰአት በፊትበኢራን ጦርነት ወቅት እስራኤል ለዩኤኢ የመሣሪያ እና የባለሙያ ድጋፍ ማድረጓን የአሜሪካ አምባሳደር ተናገሩበእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ሃክቢ ማክሰኞ ዕለት በኢራን ጦርነት ወቅት እስራኤል ወደ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ሚሳዔሎችን ለመከላከል የሚያገለግለው ‘አይረንዶም’ ባትሪዎችን እና ባለሙያዎችን መላኳን ተናገሩ።ማይክ ሃክቢ ይህንን ያሉት በቴልአቪቭ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ መሆኑን ሲቢኤስ ዘግቧል።”ለመጀመሪያዋ የአብርሃም ስምምነት አባል ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ” ያሉት ሃካቢ “ጥቅሙን ተመልከቱ። እስራኤል የአይረን ዶም ባትሪዎች እና ማንቀሳቀስ እንዲችሉ ባለሙያዎችን ልካላቸዋለች” ሲሉ ተናግረዋል።ማይክ ሃክቢ እስራኤል ላከች ስላሉት መሣሪያም ሆነ ባለሙያዎች እስካሁን ድረስ አቡ ዳቢ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠችም።እስራኤል በዓለም ላይ ውጤታማነታቸው የተፈተኑ ናቸው ተብለው የሚታመኑ የሚሳዔል ጥቃት የመከላከያ ሥርዓት ያላት አገር ናት።ከእስራኤል የሚሳኤል ጋሻዎች መካከል በጣም የሚታወቀው “አይረን ዶም” ሲሆን፣ የአጭር ርቀት ሮኬቶችን ለመከላከል የሚያስችል ነው። ይህ መሳሪያ ሞርታሮችን እና ከሚሳዔል ማስወንጨፊያ የሚተኮሱ ከአራት እስከ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚጓዙትን ያከሽፋል።የኢራን ጦርነት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ ከተጀመረ በኋላ ቴህራን በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የእስራኤል እና የአሜሪካ አጋሮች ላይ ጥቃት ስትከፍት የሆርሙዝ ወሽመጥንም ዘግታለች።በጦርነቱ የተነሳ በኢራን ከ3300 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በሺህዎች የመቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል። ከዚህም በተጨማሪ 13 የአሜሪካ ወታደሮችም ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል።በፓኪስታን አደራዳሪነት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተኩስ አቁም ቢደረስም ኢዝላማባድ እስካሁን ድረስ ዘላቂ ሰላም በሁለቱ አገራት መካከል እንዲደረስ ማድረግ አልቻለችም።
  4. ከ 2 ሰአት በፊትየቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆርሙዝን “እንደ ጦር መሣሪያ” መጠቀም እንደማይገባ አስጠነቀቁየቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ማክሰኞ ዕለት ለቀጣናዊ መረጋጋትም ሆነ ለዓለም አቀፉ ምጣኔ ኃብት ሲባል ሆርሙዝን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም እንደማይገባ አስጠነቀቁ።ፊዳን ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ቢን አብዱራህማን ቢን ጃሲም አልታኒ ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “በባህረ ሰላጤው ላይ እያጋጠመን ያለው ችግር በምንም መልኩ የጋዛ ጉዳይ እንዲረሳ ሊያደርገው አይገባም” ብለዋል።ፊዳን የእስራኤል ተስፋፊነት በቀጣናው “መረጋጋት እና ደህንነት ላይ” ዋነኛ ስጋት ሆኗል ብለዋል።በኢራን ላይ የተካሄደው ጦርነት የዓለም የኢነርጂ እና የሸቀጦችን ገበያ አውኳል። አገሪቱ ለነዳጅ ጭነት ወሳኝ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋት ብቻ ሳይሆን ለማለፍ የሞከሩ ነዳጅ ጫን መርከቦች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓ የሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች የባሕር ወሽመጡን እንዲጠብቁ ጫና ለማሳደር ቢሞክሩም እስካሁን ድረስ አልተሳካላቸውም።አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደገና ለመክፈት የምታደርገውን ጥረት ካልደገፉ “የኔቶ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጣም መጥፎ” እንደሚሆን አስጠንቅቀው ነበር።በባሕረ ሰላጤው የተፈጠረው የመርከብ ጉዞ መስተጓጎል የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል።ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከነበረበት ከ70 የአሜሪካ ዶላር አሁን ከ100 የአሜሪካ ዶላር በላይ እንዲደርስ አድርጓል።
  5. ከ 3 ሰአት በፊትኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ሰፊ ወታደራዊ ቀጣና አድርጋ እንደምትመለከተው አብዮታዊ ዘቡ አስታወቀኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከጦርነቱ በፊት ከነበረው በተለየ ሰፊ ወታደራዊ ቀጣና አድርጋ እንደምትመለከተው አስታወቀች።የአብዮታዊ ዘቡ ባሕር ኃይል ከፍተኛ ባለሥልጣን ወሽመጡን ከዚህ በፊት ከነበረው ጠባብ መተላላፊያ በተለየ “ሰፊ ወታደራዊ ቀጣና” አድርገው እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።ከአሁን በኋላ ወሽመጡ በጥቂት ደሴቶች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ከወታደራዊ ጠቀሜታ አንጻር ሰፋ ተደርጎ እንደሚታይ የአብዮታዊ ዘቡ ባሕር ኃይል የፖለቲካ ምክትል ዳይሬክተር ሞሐማድ አክባርዛዴህ ለፋርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።ምክትል ዳይሬክተሩ ማክሰኞ ዕለት ለዜና ወኪሉ “ከዚህ ቀደም የሆርሙዝ ወሽመጥ በሆርሙዝ እና ሄንጋም ደሴቶች አካባቢ ያለ ጠባብ ስፍራ ተደርጎ ይታይ ነበር። አሁን ግን ይህ እይታ ተቀይሯል” ብለዋል።ሮይተርስ የኢራን ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት ለመግባት እንዲሁም ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን እና ኳታር ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩበት ዋነኛ መስመር ነው።አክባርዛዴህ ወሽመጡ አሁን ስትራቴጂካዊ ቀጣና ተብሎ የሚበየን መሆኑን ተናግረው በምሥራቅ በሲሪ ደሴት ከምትገኘው ጃስክ ከተማ እስከ ደሴቲቱ ደቡባዊ ክፍል ድረስ የሚሸፍን “ሰፊ ወታደራዊ አካባቢ” መሆኑን ተናግረዋል።አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት ካወጁ ወዲህ የሆርሙዝ ወሽመጥ ሰፊ አካባቢን አንደሚያካልል ሲገለጽ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።ግንቦት አራት የአብዮታዊ ዘቡ ባጋራው ካርታ ወሽመጡ እስከ የኦማን ባሕረ ሰላጤ ድረስ እንደሚሰፋ ያሳያል።ፋርስ እና ታስኒም የዜና ወኪሎች ማክሰኞ ዕለት የወሽመጡ ስፋት ከዚህ ቀደም ከ20 እስከ 30 ማይል ይገመት እንደነበር ጠቅሰው አሁን ግን ወደ 200 እና 300 ማይልስ ማደጉን ዘግበዋል።ታስኒም አክሎም የተጨመረው ቀጣና “የግማሽ ጨረቃ ቅርጽ” ይፈጥራል ሲል ዘግቧል።
  6. ከ 4 ሰአት በፊትአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ዕቅድ ላይ ስላልተስማሙ የነዳጅ ዋጋ ጨመረአሜሪካ እና ኢራን በሰላም ዕቅድ ላይ ባለመስማማታቸው የነዳጅ ዋጋ ሁለት በመቶ መጨመሩን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ላይ የሁለት ዶላር ጭማሪ ተደርጎ ዋጋው 106.21 ዶላር ደርሷል። የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱን ተከትሎ የነዳጅ ሽያጭ ቀንሷል።ነዳጅን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አገራት ማኅበር እንዳለው፤ በሁለት አሥርት ዓመታት ባልታየ ሁኔታ ባለፈው ሚያዝያ ወር ከፍተኛ የምርት መቀነስ ተስተውሏል።የነዳጅ ገበያው እስከ አውሮፓውያኑ 2027 ድረስ መረጋጋት ሳይታይበት ሊቆይ እንደሚችል የሳዑዲው አራምኮ ፕሬዝዳንት አሚን ናስር አስጠንቅቀዋል።የነዳጅ ምርት በአንድ ሳምንት ውስጥ እስከ 100 ሚሊዮን በርሜል መቀነሱ ተገልጿል።በሌላ በኩል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው አቻቸው ዢ ዢፒንግ ጋር የሚያደርጉትን ውይይት የነዳጅ ነጋዴዎች በንቃት እየተከታተሉ ነው።የአሜሪካ ግምጃ ቤት የኢራንን ነዳጅ ለቻይና የሸጡ ወይም ያዘዋወሩ ናቸው ባላቸው 12 ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታውቋል።
  7. ከ 5 ሰአት በፊትትራምፕ በኢራን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በድጋሚ ለመክፈት ማሰባቸው ተዘገበፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በድጋሚ ለመጀመር “አጥብቀው ማሰባቸውን” ሲኤንኤን ዘገበ።ሲኤንኤን ምንጮቹን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ መሠረት፤ ኢራናውያን ድርድሩን የያዙበት መንገድ አስቆጥቷቸዋል።ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች እንደገለጹት ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት እና በኢራናውያን ባለሥልጣናት መከፋፈል “ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ ነው።በኢራናውያን ባለሥልጣናት መካከል ያለው ክፍፍል ኒውክሌርን በተመለከተ የሚደረገው ንግግር ውጤታማ እንዳይሆን ማድረጉ ተጠቁሟል።ትራምፕ ኢራን የሰጠችውን ምላሽ “ፈጽሞ ተቀባነት የሌለው” ብለው አጣጥለዋል። አሜሪካ በቀጣይ የምትወስደውን እርምጃ በተመለከተ በዋሽንግተን ባለሥልጣናት ውስጥ የተለያየ አቋም መወሰዱን የሲኤንኤን ምንጮች ጠቁመዋል።የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ኢራን ላይ ጫና ለማሳደር ዒላማዎችን ለይቶ ጥቃት መሰንዘርን እንደ አማራጭ እንደሚወስድ ተገልጿል። በሌላ በኩል ለድርድር ዕድል የመስጠት ፍላጎት ያላቸውም እንዳሉ ተጠቅሷል።
  8. ከ 6 ሰአት በፊትኢራን ጥቃት ከደረሰባት መሣሪያ መገንባት በሚያስችል መጠን ዩራኒየም ለማበልጸግ ዛተችኢራን በድጋሚ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ መሣሪያ ለመገንባት በሚያስችል የጥራት መጠን ዩራኒየም ማበልጸግ እንደምትጀምር ማስታወቋን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።በኢራን ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ኢብራሒም ራይዚ፤ ኢራን ጥቃት ከደረሰባት ዩራኒየም በ90 በመቶ ደረጃ እንደምታበለጽግ አስታውቀዋል።ቃል አቀባዩ በኤክስ ገጻቸው “ኢራን ሌላ ጥቃት ከተፈጸመባት እስከ 90 በመቶ ማበልጸግን አንድ አማራጭ አድርጋ ትወስዳለች። ጉዳዩን በምክር ቤት እንወያይበታለን” ብለዋል።
  9. ከ 7 ሰአት በፊትየኢራንን ነዳጅ ለቻይና ሸጠዋል የተባሉ 12 ግለሰቦች እና ተቋማት በአሜሪካ ማዕቀብ ተጣለባቸውየአሜሪካ ግምጃ ቤት የኢራንን ነዳጅ ለቻይና የሸጡ ወይም ያዘዋወሩ ናቸው ባላቸው 12 ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።የኢራን አብዮታዊ ዘብ በፈጠራቸው ወረቀት ላይ ብቻ የሚገኙ ኩባንያዎች (shell companies) አማካኝነት በድብቅ የነዳጅ ሽያጭ እንደሚያከናውን ተገልጿል።ብዙም ቁጥጥር በማይደረግባቸው ዘርፎች ውስጥ የሚፈጠሩት እነዚህ የይስሙላ ኩባንያዎች ነዳጅ እየሸጡ ለኢራን መንግሥት ገቢ እንደሚያስገኙ የአሜሪካ ግምጃ ቤት አስታውቋል።ከነዳጅ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለጦር መሣሪያ ምርት እና ኢራንን በእጅ አዙር ለሚደግፉ የውጭ አገራት ቡድኖች እንደሚውል ገልጿል።የአሜሪካ የግምጃ ቤት ጸሐፊ ስኮት ቤሴት “የኢራን ወታደራዊ ኃይሎች አቅማቸውን ለመገንባት እየሞከሩ ነው። እኛም የምጣኔ ሃብት ጫና ማሳደር እንቀጥላለን” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።“የኢራን መንግሥት የፋይናንስ ምንጮችን እንዘጋለን። የሽብር ድርጊቶችን በመደገፍ ዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብትን የሚያናጉበትን ትስስርም እንበጣጥሳለን” ሲሉም አክለዋል።
  10. ከ 8 ሰአት በፊት“የኢራናውያንን መብት ከማክበር ውጪ አሜሪካ ሌላ አማራጭ የላትም” አፈ ጉባኤ ጋሊባፍከስምምነት ላይ ለመድረስ አሜሪካ የኢራናውያንን መብት ከማክበር ውጪ ሌላ አማራጭ የላትም ሲሉ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገለጹ።አፈ ጉባኤው መሐመድ ባጊር ጋሊባፍ ለፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተያየት ምላሽ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ እንዳሉት ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም ባቀረበችው “ባለ14 ነጥብ ሃሳብ ላይ እንደተቀመጠው የኢራናውያንን መብቶች ከማክበር ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ የለም” ብለዋል።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ከኢራን በኩል በተሰጠው ምላሽ ደስተኛ አለመሆናቸውን በተመለከተ ሰኞ ዕለት የተኩስ አቁሙ “በቋፍ ላይ” መሆኑን ከተናገሩ በኋላ ነው አፈ ጉባኤው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የአገራቸውን አቋም ያስታወቁት።ጋሊባፍ በኤክስ ገጻቸው ላይ በእንግሊዝኛ እንደጻፉት “ሌላ የትኛውም መንገድ ተከታታይ ውድቀትን ከማስከተል ውጪ ምንም ዓይነት ውጤትን አያስገኝም። ነገሩ እየተራዘመ ሲሄድ ከአሜሪካውያን ታክስ ከፋዮች ኪስ የሚወጣውን ወጪን ይጨምራል” በማለት አሳስበዋል።የኢራን ምክር ቤት አፈጉበኤ ጋሊባፍ ከዚህ ቀደም ብሎ ባሠራጩት የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት ኢራን ለየትኘውም ሁኔታ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀው ነበር።
  11. ከ 9 ሰአት በፊትየኢራን ተኩስ አቁም “በቋፍ ላይ” መሆኑን ትራምፕ ተናገሩየአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት “በቋፍ ላይ” እንደሚገኝ ተናገሩ። የተኩስ አቁሙ ዘላቂነት “በማይታመን ሁኔታ ደካማ” መሆኑንም ገልጸዋል።ፕሬዝዳንቱ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ አንድ ወር ያስቆጠረው የተኩስ አቁም ስምምነት “በሕይወት ለመቆየት እየተንገዳገደ” ይገኛል።የትራምፕን አስተያየት ተከትሎ የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ መሐማድ ጋሊባፍ “ለማንኛውም ወረራ ምላሽ ለመስጠት እና ትምህርት ለማስተማር ዝግጁ ነን” ብለው በኤክስ ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።አሜሪካ ለኢራን ላቀረበችው የሰላም ዕቅድ ቴህራን የሰጠችው ምላሽ በዋሽንግተን ውድቅ ተደርጓል።ያለፈው እሑድ ኢራን ጦርነቱን ለማስቆም እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት ለአሜሪካ ያቀረበችው ዕቅድ ተቀባይነት አላገኘም። ፕሬዝዳንቱም “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው” እና “ቆሻሻ” ሲሉ ዕቅዱን አጣጥለዋል።ትራምፕ ይህንን ካሉ በኋላ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢስማኤል ባጊ የቴህራን ዕቅድ “ኃላፊነት የተሞላው” እና “ቸር” መሆኑን ተናግረዋል።የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ “በ14ቱ ነጥቦች እንደተመለከተው የኢራናውያንን መብት ከማክበር ውጭ አማራጭ የለም። ሳይቀበሉት በዘገዩ ቁጥር የአሜሪካውያን ግብር ከፋዮች ገንዘብ ይባክናል” ብለዋል።በኢራን እና አሜሪካ መካከል የተወሰኑ ግጭቶች ቢኖሩም የተኩስ አቁም ስምምነቱ አንድ ወር አስቆጥሯል።ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ “የተኩስ አቁም ስምምነቱ በሕክምና እርዳታ እንደሚተነፍስ ታማሚ ነው። ሐኪሞች መጥተው ‘ጌታዬ የሚወዱት ሰው በሕይወት የመቆየት ዕድሉ 1 በመቶ ነው’ የሚሉት ዓይነት ነው” ብለዋል።
  12. 11 ግንቦት 2026ሆርሙዝ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ካልተከፈተ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ ይጋለጣሉ ተባለየሆርሙዝ ወሽመጥ በቶሎ ተከፍቶ የማዳበሪያ ምርት በባሕረ ሰላጤው መተላለፍ ካልቻለ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ እጥረት እና ረሃብ እንደሚገጥማቸው አንድ የተበባሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ተናገሩ።ባለሥልጣኑ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደተናገሩት ወራት ባስቆጠረው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምክንያት በሆርሙዝ በኩል የሚደረገው የመርከቦች እንቅስቃሴ መስተጓጎሉ ለእርሻ ምርት አስፈላጊ የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት አደናቅፎታል።ስለዚህም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሆርሙዝ ወሽመጥ ተከፍቶ የአፈር ማዳበሪያ ምርት እና ግብዓት እንዲያልፍ ካልተፈቀደ የምግብ ምርት መስተጓጎል እና ረሃብ ሊያስከትል እንደሚችል የመንግሥታቱ ድርጅት የፕሮጀክቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ዮርግ ዳ ሲልቫ ተናግረዋል።ባለሥልጣኑ “ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ሊሆን የሚችለውን ችግር ለመቀልበስ ያሉን ጥቂት ሳምንታት ብቻ ናቸው” ሲሉ ለዜና ወኪሉ ገልጸዋል።አክለውም በጦርነቱ ሰበብ የአፈር ማዳበሪያ ምርቱ አቅርቦት በመስተጓጎሉ “ተጨማሪ 45 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጨማሪ ሰዎችን ለምግብ እጥረት እና ለረሃብ የሚዳርግ ቀውስ ሊገጥመን ይችላል” ብለዋል።ባለፈው የካቲት ወር ማብቂያ አካባቢ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ኢራን እና አሜሪካ በወሳኙ የባሕር መተለላፊያ የሆርሙዝ ወሽመጥ የጭነት መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ እገዳ ጥለዋል።
  13. 11 ግንቦት 2026ስለ አሜሪካ የጦር መሣሪያ ክምችት የተናገሩት ሴናተር ምርመራ እንደሚደረግባቸው መከላከያ ሚኒስትሩ ገለጹየአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት፣ መሥሪያ ቤታቸው ዴሞክራቱ ሴናተር ማርክ ኬሊ ስለ አገሪቱ የጦር መሣሪያ ክምችት የሰጡትን አስተያየት እንዲመረምር ጠየቁ።ሴናተሩ “ቴሌቪዥን ላይ” ቀርበው ምሥጢራዊ ስለሆነ የፔንታጎን መረጃ “ዘላብደዋል” ያሉት ሄግሴት፤ “በድጋሚ… መሐላውን ጥሷል?” ሲሉ ኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ጠይቀዋል።ሴናተሩ ኬሪ ወቀሳ ያስነሳባቸውን ንግግር ያደረጉት ከሲቢኤስ ኒውስ ‘ፌስ ዘ ኔሽን’ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው። ፕሮግራሙ ላይ ቀርበው በኢራን ጦርነት ምክንያት ስለ አሜሪካ የጦር መሣሪያ ክምችት የተሰማቸው ስጋት ገልጸው ነበር።የጦር መሣሪያዎችን የሚዘረዝር የፔንታጎን ማብራሪያም በማጣቀስ የመሣሪያ ክምችቱ ምን ጥቅም ላይ እንደዋለ መረዳታቸው “አስደንጋጭ” እንደሆነ ተናግረዋል።ኬሊ፤ ከዚህ ቃለ መጠይቅ በኋላ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ለቀረበባቸው ክስ በሰጡት ምላሽ ምሥጢራዊ መረጃ አውጥተዋል መባሉን አስተባብለዋል። ስለዚህ ጉዳይ “ከሳምንት በፊት ይፋዊ ውይይት ላይ ተነጋግረናል” ሲሉ ጉዳዩ ምሥጢር እንዳልነበረ ተከራክረዋል።የአሪዞናው ሴናተር በኤክስ ገጻቸው በሰጡት ምላሽ፤ “ከእነዚህ ክምችቶች የተወሰኑትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ‘ዓመታት’ ተናግረሃል” ሲሉ መረጃው የመጣው ከመከላከያ ሚኒስትሩ ንግግር እንደሆነ ገልጸዋል። ባለፈው ወር የነበረውን የሴኔት ስብሰባ የሚያሳይ ቪዲዮም ለጥፈዋል።”ይህ ምሥጢራዊ መረጃ አይደለም፤ የአንተ ንግግር ነው። ይህ ጦርነት ከፍተኛ ዋጋ እያስወጣ ነው፤ አንተ እና ፕሬዝዳንቱ እስካሁን ድረስ [የጦርነቱ] ግብ ምን እንደሆነ ለአሜሪካ ሕዝብ አላብራራችሁም” ሲሉ ወቅሰዋል።የመከላከያ ሚኒስትሩ ሄግሴት ሴናተር ኬሊ ላይ ምርመራ እንዲደረግ የጠየቁት ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር ምክንያት የተነሳው ውዝግብ ባልተቋጨበት ወቅት ነው። ሴናተሩ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ወታደሮች ሕገ-ወጥ ትዕዛዞችን እንዳይቀበሉ ሲናገሩ ተደምጠው ነበር።መከላከያ መሥሪያ ቤቱ በዚህ ንግግራቸው ምክንያት ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድባቸው ያቀደ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት ግን የፌዴራል ይግባኝ ሰበር ችሎት የፔንታገንን እርምጃ ውድቅ ሊያደርግ እንደሚችል ተሰምቷል።
  14. 11 ግንቦት 2026የቴህራን ጎዳናዎችን የሞሉት የኢራን መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ሥዕሎችየካቲት ላይ የተጀመረው የኢራን ጦርነት መቋጫ ሳያገኝ ወደ ሦስተኛ ወር እያመራ ነው። ሁለቱ አገራት ስምምነት የመፈጸማቸው ጉዳይ እስካሁን ተጨባጭ የሚባል ሁኔታ ላይ አልደረሰም።ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን መንግሥት ዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ የሚያስቀምጣቸው የፕሮፖጋንዳ ቢልቦርዶች እና የግድግዳ ሥዕሎች እየጨመሩ መጥተዋል።የከተማዋ ነዋሪዎች በአንጻሩ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲገታ ባደረገው ተኩስ አቁም ጥላ ስር ሆነው የዘውትር ሕይወታቸውን ቀጥለዋል።የቴህራን ነዋሪዎች እንቅስቃሴ እና የጎዳና ላይ ሥዕሎቹን የሚያሳዩትን ምሥሎች ይመልከቱ
  15. 11 ግንቦት 2026ኢራን ለአሜሪካ የስምምነት ዕቅድ የሰጠሁት ምላሽ “ምክንያታዊ እና ለጋስ” ነው አለችየኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቴህራን በአሜሪካ ለቀረበው የድርድር ዕቅድ የሰጠችው ምላሽ “ምክንያታዊ እና ለጋስ” እንደሆነ በመግለጽ፤ አሜሪካን ግን “ለአንድ ወገን ያደላ እና ምክንያታዊ ያልሆነ” አቋም ላይ ጸንታለች የሚል ክስ አቀረቡ።ኢራን ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ለቀረበው የድርድር ዕቅድ በአሸማጋይዋ ፓኪስታን በኩል ምላሽ መስጠቷን ያሳወቀችው ትናንት እሁድ ነበር። የቴህራን ምላሽ ያላስደሰታቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው” በማለት ውድቅ አድርገውታል።የኢራን ዜና ወኪል ዘገባ እንደሚያሳየው ቴህራን የሰጠችው ምላሽ በሁሉም ግንባሮች የሚካሄዱ ውጊያዎች እንዲቆሙ እና አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው እገዳ እንዲነሳ ይጠይቃል። ወደፊት ኢራን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም ዋስትና የመስጠት ጉዳይም ምላሹ ውስጥ ተካትቷል።ዛሬ ሰኞ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ኢስማኢል ባጋኢ፤ ቴህራን “ከሕጋዊ መብቶቿ” ውጭ የሆነ ጥያቄ እንዳላቀረበች ተናግረዋል።እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ የኢራን ምላሽ “በቀጣናው የሚደረገው ጦርነት እንዲያበቃ”፣ “የባሕር ላይ እገዳ ተብሎ የሚገለጸው በኢራን መርከቦች ላይ የሚፈጸመም የባሕር ላይ ውንብድና እንዲቆም” እንዲሁም “በውጭ ባንኮች የታገደውና የኢራን ሕዝብ ንብረት የሆነው ሀብት እንዲለቀቅ” የሚጠይቅ ነው።ቃል አቀባዩ “እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አስተማማኝ የባሕር ጉዞ እንዲኖር ያቀረብነው ሐሳብ ከመጠን ያለፈ ጥያቄ ነውን? ሊባኖስን ጨምሮ በመላው ቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን መጠየቅስ እንዴት ከልክ ያለፈ ጥያቄ ሆኖ ሊታይ ይችላል?” በማለት ጠይቀዋል።በዕቅዱ ውስጥ የተካተቱት ነጥቦች “ምክንያታዊ እና ለጋስ” መሆናቸውን የተናገሩት ባጋኢ፤ በአንጻሩ ግን አሜሪካ “ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥያቄዎችን” እያቀረበች ነው ሲሉ ከስሰዋል።ፓኪስታን ውስጥ በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ድርድር ሁለቱን አገራት ያላስማማቸው ዋነኛ ጉዳይ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ነበር።ከዚህ ቀደም ኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ለጊዜው ወደ ጎን ተደርጎ በቅድሚያ ጦርነቱን ማቆም እና ሆርሙዝን መክፈት የተመለከተ ንግግር እንዲደረግ የሚጠይቅ ዕቅድ አቅርባ የነበረ ቢሆንም፤ አሜሪካ አልተቀበለችውም።
  16. 11 ግንቦት 2026ሦስት ድፍድፍ ነዳጅ የጫኑ ግዙፍ መርከቦች መከታተያቸውን በማጥፋት የሆርሙዝ ወሽመጥን ማቋረጣቸውን ሮይተርስ ዘገበባለፈው ሳምንት ሦስት ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ራሳቸውን ከኢራን ጥቃት ለመከላከል የመከታተያ መሣሪያቸውን በማጥፋት ወሽመጡን ማቋረጣቸውን ሮይተርስ ዘገበ።ሮይተርስ የመርከቦች እንቅስቃሴን ከሚከታተሉት ኬፕለር እና ኤልኤስኢጂ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ እንደዘገበው ሁለት ግዙፍ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ሆርሙዝን ያቋረጡት ትናንት እሁድ ነው።አንዱ መርከብ ግን ከአምስት ቀን በፊት ማቋረጡን የመርከቦችን እንቅስቃሴ የሚከታተሉትን ድርጅቶች ጠቅሶ ዘግቧል።አጊዮስ ፋኖውሪየስ I እና ኪያራ ኤም የተሰኙት መርከቦች እያንዳንዳቸው ሁለት ሚሊየን በርሜል ነዳጅ መጫናቸው ተግለጿል።አጊዮስ ፋኖውሪየስ I ወደ ቬይትናም የሚያመራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከዚህ ቀደም ሁለቴ ወሽመጡን ለማቋረጥ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።አጊዮስ ፋኖውሪየስ I የሚያስተዳድረው ኢስተርን ሜዲትራኒያን ማሪታይም ስለመርከቡ ጉዞ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።እሁድ ዕለት ወሽመጡን ያቋረጠው ሌላው ነዳጅ ጫኝ መርክ ኪያራ ኤም የጫነውን ነዳጅ ወዴት እንደሚያጓጉዝ አልታወቀም። መርከቡን የሚያስተዳድረው መቀመጫውን ሻንጋይ ያደረገው ኩባንያ ሲሆን ስለ መርከቡም ሆነ ስለ ጭነቱ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይመልስ መቅረቱን ሮይተርስ ዘግቧል።ቀደም ብሎ ከአቡዳቢ ብሔራዊ የነዳጅ ኩባንያ 2 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫነ መርከብ እአአ ግንቦት 6 የመከታተያ መሣሪያውን በማጥፋት አቋርጧል።አሜሪካ እና ኢራን ከሁለት ወር በፊት የገቡበት ጦርነትን ተከትሎ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ የነዳጅ፣ ጋዝ፣ ፔትሮል፣ ፕላስቲክ እና የምግብ ዋጋ ንሯል።
  17. 11 ግንቦት 2026ከኢራን ጦርነት በቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያገኙት እነማን ናቸው?የካቲት መጨረሻ የተጀመረው የኢራን ጦርነት በመላው ዓለም ተጽዕኖው ተሰምቷል። በአንጻሩ ጦርነቱ በረከት የሆነላቸው ኩባንያዎች እና ዘርፎችም አሉ። የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በዚህ ጦርነት ትርፍ ካጋበሱት መካከል ናቸው።ከዓለም የነዳጅ እና የጋዝ ጭነት አንድ አምስተኛ ያህሉ የሚጓጓዝበት የሆርሙዝ ወሽመጥ፤ ከየካቲት መጨረሻ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተዘግቷል።ይህንን ተከትሎ የአውሮፓ የነዳጅ ኩባንያዎች ከፍተኛ ትርፍ አጋብሰዋል። በወሽመጡ መዘጋት ምክንያት የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ከፍተኛ የሚባል ትርፍ አግኝተዋል።’ቢፒ’ የተባለው የብሪታኒያ የነዳጅ ኩባንያ በ2026 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ትርፉ ከእጥፍ በላይ አድጎ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።ሌላኛው የነዳጅ ኩባንያ ‘ሼል’ ደግሞ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 6.92 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ተንታኞች ከጠበቁት በላይ ትርፍ አስመዝግቧል።ግዙፉ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ‘ቶታል ኤነርጂስ’፣ በነዳጅ እና በኢነርጂ ገበያ ዋጋ መናር ምክንያት ትርፉ በአንድ ሦስተኛ ገደማ ጨምሯል። በሦስት ወራት ውስጥ ያገኘው ትርፍም 5.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ አስታውቋል።በአንጻሩ የአሜሪካዎቹ ኩባንያዎች ‘ኤክሶንሞቢል’ እና ‘ቼቭሮን’ በመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ምክንያት ገቢያቸው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ብሎ ቢታይም፤ ያገኙት ትርፍ ከባለሙያዎች ግምት የበለጠ ነው።የነዳጅ ዋጋ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከነበረው በእጅጉ የጨመረ በመሆኑ፤ የሁለቱም ኩባንያዎች ትርፍ እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል።የዓለምን ኢኮኖሚ ካናጋው የኢራን ጦርነት ቢሊዮኖች እያተረፉ ያሉት ኩባንያዎች
  18. 11 ግንቦት 2026ኔታንያሁ እስራኤልን ከአሜሪካ ድጋፍ ማላቀቅ እንደሚፈልጉ ለሲቢኤስ ተናገሩየእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸውን ከአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ለማላቀቅ እንደሚፈልጉ ተናገሩ።ኔታንያሁ እሁድ ዕለት ከሲቢኤስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ከባሕረ ሰላጤው አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ከአሜሪካ የሚያገኙትን ወታደራዊ ድጋፍ ለመቀነስ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።ኔታንያሁ ለሲቢኤስ ኒውስ “60 ደቂቃ” ፕሮግራም እንደተናገሩት “የአሜሪካን የገንዘብ ድጋፍ፣ ባለን ወታደራዊ ትብብር ላይ ያለው የገንዘብ ድጋፍን፣ ወደ ዜሮ ማውረድ እፈልጋለሁ” ብለዋል።ኔታንያሁ እንዳሉት እስራኤል በዓመት 3.8 ቢሊዮን ዶላር የአሜሪካን ወታደራዊ እርዳታ ታገኛለች። ዩናይትድ ስቴትስ እአአ ከ2018 እስከ 2028 በድምሩ 38 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ለእስራኤል ለመስጠትተስማምታለች።የዩናይትድ ስቴትስ እና የእስራኤል የገንዘብ ድጋፍ ትብብር ለመለወጥ “ፍጹም” ትክክለኛው ጊዜ ነው ሲሉ ኔታንያሁ ተናግረዋል። ቀጣዩ ምክር ቤት እስኪመጣ ድረስ “መቆየት አልፈልግም” ያሉት ኔታንያሁ፣ “አሁን መጀመር እፈልጋለሁ” ብለዋል።እስራኤል ለረዥም ዓመታት በሁለቱም ፓርቲዎች የሥልጣን ዘመን ጠንካራ ወታደራዊ ድጋፍ ስታገኝ ቆይታለች። ነገር ግን በ2016 ዓ.ም. የጋዛ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ከአሜሪካ ሕግ አውጪዎች እና ሕዝብ የሚገኘው ድጋፍ እየቀነሰ መትቷል።በመጋቢት ወር የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው 60 በመቶ አሜሪካውያን ለእስራኤል አሉታዊ አስተያየት ያላቸው ሲሆን፤ 59 በመቶ ዎቹ በቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
  19. 11 ግንቦት 2026ቻይና ቴህራን ላይ የሚጣል ማዕቀብ ኩባንያዎቼን ይጎዳል በሚል ተቃወመችአሜሪካ መቀመጫቸውን ቻይና ባደረጉ ሦስት ኩባንያዎች ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ቤይጂንግ ተቃወመች።ቤይጂንግ ተቃውሞዋን ያሰማችው ኩባንያዎቹ የኢራንን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ደግፈዋል በሚል ውንጀላ ከቀረበባቸው በኋላ ነው።ሰኞ ዕለት ጠንካራ ተቃውሞዋን የገለጸችው ቤይጂንግ ማዕቀቦቹን ሕገ ወጥ እና የአንድ ወገን ውሳኔ ብላ ጠርታዋለች።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት ጉኦ ጂያኩን “ምንጊዜም የቻይና ኩባንያዎችን ሥራቸውን በሕግ እና መመሪያዎች መሠረት እንዲያከናውኑ እናደርጋለን፤ እንዲሁም የቻይና ኢንተርፕራይዞችን ሕጋዊ መብቶች እና ጥቅሞች በጽኑ እንጠብቃለን” ሲሉ ተናግረዋል።”ሌሎች አገራትን በስህተት ከመኮነን እና ከመተቸት አንገብጋቢው እና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ጦርነቱ ዳግም እንዳይጀመር መከላከል ነው” ብለዋል።የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዢ ጂንፒንግ ጋር ለመገናኘት በዚህ ሳምንት ወደ ቻይና ያመራሉ። ከግንቦት 5 እስከ 7 2018 ዓ.ም. የሚቆየው ይህ ጉብኝት በአስር ዓመታት ውስጥ አንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ወደ ቻይና የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉዞ ይሆናል ተብሏል፡፡
  20. 11 ግንቦት 2026ትራምፕ የኢራንን የሰላም ዕቅድ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ለአሜሪካ የሰላም ዕቅድ የሰጠችውን ምላሽ ውድቅ ካደረጉ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ።ቴህራን ምላሹን የሰጠችው በአደራዳሪዋ ፓኪስታን በኩል ሲሆን ግጭቱ ወዲያውኑ እንዲቆም እንዲሁም ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ጥቃት እንደማይፈጸምባት ማረጋገጫ እንዲሰጣት መጠየቋን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።ሰኞ ዕለት ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በእስያ ገበያ በበርሜል የ4.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 105.50 ዶላር ተሸጧል።የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መተላለፊያ የሆነው ሆርሙዝ ከየካቲት የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት በመቀስቀሱ ዝግ ሀኗል።ጦርነቱ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣ ሲሆን የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል።የዓለም አንድ አምስተኛው ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተዘጋ በኋላ ቴህራን ለማቋረጥ የሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም በመግለጽ አስጠንቅቃለች።ጦርነቱ ከተጀመረበት የካቲት 21/ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማቋረጥ የሞከሩ 26 የነዳጅ እና ኮንቴይነር ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተገልጿል።መርከቦቹ ላይ ጥቃት የደረሰው በተወንጫፊዎች፣ በአነስተኛ ጀልባዎች፣ በቦምብ ሲሆን አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ከኦማን የባሕር ዳርቻ ወጣ ባለ ስፍራ እንዲሁም የዩኤኢ ፉጃይራህ ወደብ አቅራቢያ ነው።ዓለም አቀፉ የባሕር ላይ ትራንስፖርት ድርጅት በሆርሙዝ ወሽመጥ ከ1500 እስከ 2000 መርከቦች እንዲሁም 20 ሺህ ባህረተኞች መንቀሳቀሻ አጥተው መቆማቸውን አስታውቋል።ዋና ዋና የኢነርጂ ኩባንያዎች የዓለም የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ትርፋቸው መጨመሩን ይፋ አድርገዋል።እሁድ ዕለት አራምኮ ባለፉት ሦስት ወራት ያገኘው ትርፍ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ጭማሪ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።ባለፈው ወር እንዲሁ ቢፒ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ትርፉ ከእጥፍ በላይ መጨመሩን የገለጸ ሲሆን ሼል ደግሞ ባለፈው ሳምንት ትርፉ ከፍ ማለቱን ተናግሯል።