ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ

ታትሟልከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ባለፉት ሦስት ዓመታት ቱርክ እና እስራኤል መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመፍጠር ወደ ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት እያመራ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል።

በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የቃላት ጦርነቱ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ወታደራዊ ግጭት የመከሰት ዕድል ይኖራል ወይ የሚል ጥያቄን እያስነሳ ይገኛል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ሚያዝያ ወር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን በኢራን የሚገኘውን “የሽብርተኝነት ሥርዓት” እንደረዱ እና “የራሳቸውን የኩርድ ዜጎች ጨፍጭፈዋል” ሲሉ ከሰዋቸዋል።

ከቀናት በኋላ ለቱርክ ፓርላማ ንግግር ያደረጉት ኤርዶዋን “በጋዛ በሚገኙ የ73 ሺህ ፍልስጤማውያንን በደም የተሸፈኑ እጆች እና ፊቶች ሳይመለከቱ፣ በኩርድ ወንድሞቻችን አማካኝነት አገራችንን ያለምንም እፍረት ይከሳሉ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከሰሞኑ ክስተቶች ጋር በተያያዘ ለቢቢሲ ሃሳባቸውን የሰጡ ባለሙያዎች እንደሚሉት በቱርክ እና በእስራኤል መካከል የሚፈጠር የግጭት አደጋ “ከመቼውም ጊዜ በበለጠ” ቢጨምርም ሁለቱም ወገኖች በተመሳሳይ ጊዜ ሊከሰት የሚችለውን ግጭትን ለመከላከል እየሞከሩም ነው።

“ከቀዝቃዛ ሰላም ይልቅ ቀዝቃዛ ፉክክር እየተመለከትን ነው”

መስከረም 26/2016 ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረ እና ቴል አቪቭ በጋዛ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች በኋላ በቱርክ እና በእስራኤል መካከል የቃላት ጦርነቱ ተጠናክሯል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተሰጡት ከባድ መግለጫዎች እና ክሶች በተጨማሪ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመፍጠር የሚደረገው ሂደቱም ቆሟል። ቱርክም ከእስራኤል ጋር ያላትን ንግድ ግንኙነት ማቋረጧን አስታውቃለች።

በቱርኩ ኢዝሚር ኬትብ ቻላቢ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ቶግሴ ኤርሶይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ሁኔታ ከዲፕሎማሲያዊ መርሆዎች በላይ የአገር ውስጥ ፍላጎቶች በመኖራቸው ምክንያት “የውጭ ፖሊሲው ለአገር ውስጥ ፖለቲካ ሰለባ ሆኗል” ብለዋል።

“ይህ የውጥረት መጨመር እና የቃላት ጦርነት የሁለቱንም ወገኖች የአገር ውስጥ ፖለቲካን እያቀጣጠለ ነው” ብለዋል።

“ኔታንያሁ ጠንካራ እና ለግጭት ወደኋላ የማይሉ መሆናቸውን የሚያሳይ ምሥል በመፍጠር በአገር ውስጥ ፖለቲካ ላይ ያላቸውን አቋም ለማጠናከር እየሞከሩ ነው። በቱርክ በኩል ደግሞ ከክልላዊ አመራርነት ጋር የተያያዘ ነው” ሲሉ አክለዋል።

“የእስራኤል፣ የፍልስጤማውያን እና የአይሁዶች የሚጋጩ ማንነቶች” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ኤርሶይ ቱርክ እና እስራኤል “የክልላዊ ሁኔታን የሚያናጉ ተዋናዮች” እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይመለከታሉ ብለዋል።

ስለአሁኑ የግንኙነት ሁኔታ ደግሞ “የቱርክ-እስራኤልን ግንኙነት ሁልጊዜም እንደ ‘ቀዝቃዛ ሰላም’ እንገልጸዋለን። አሁን ግን ‘ቀዝቃዛ ፉክክር’ እያየን ነው” ሲሉ አክለዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ ቱርክን እንደ ተቀናቃኝ አድርገው የገለጹበት አስተያየት “አደገኛ” እንደሆነ የቀድሞው የእስራኤል ዲፕሎማት አሎን ፒንካስ ተናግረዋል።

“በተለይም ኤርዶዋን ቀስቃሽ አስተያየቶችን በመስጠት ሁኔታውን ሲያባብሱት ይህ ዓይነቱ ንግግር በጣም አደገኛ ነው” ብለዋል ፒንካስ።

“የኔታንያሁ እና የኤርዶዋን የቃል ውዝግብ የግጭት አደጋን ይጨምራል”

በለንደን በሚገኘው የሴንት ጆርጅ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር አምኖን አራን እነዚህ የቃላት ጦርነቶች በአብዛኛው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያሉ መሆናቸውን ያምናሉ።

“ከቱርክ እና ከኤርዶዋን አንጻር የቃላት ግጭቱ ግብ የጀስቲስ እና የዲቨሎፕመንት ፓርቲ መሠረትን ማስደሰት ነው። ኔታንያሁም ተመሳሳይ ቃና በመጠቀም የቀኝ ዘመም ደጋፊዎችን ድጋፍ ለማግኘት እና አቋማቸውን ለማጠናከር የሚደረግ ነው” ብለዋል።

“የእስራኤል የውጭ ፖሊሲ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ጀምሮ” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ለሆኑት አራን በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ከ2010 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ከነበረው ከማቪ ማርማራ ቀውስ ወዲህ በጣም የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። አክሎም “በእኔ አስተያየት ኔታንያሁም ሆነ ኤርዶጋን በንግግራቸው በጣም ኃላፊነት በጎደለው መንገድ እየሠሩ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ንግግር በሁለቱ አገሮች መካከል ግጭት የመፍጠር ዕድልን ይጨምራል” ብለዋል።

ኔታኒያሁ በወታደራዊ ልብስ

ሶሪያ፣ ቆጵሮስ እና ምስራቅ ሜዲትራኒያን

ለቢቢሲ ሃሳባቸውን የሰጡ ባለሙያዎች እንደሚሉት በቱርክ እና በእስራኤል መካከል ሊኖር የሚችል ማንኛውም ግጭት ሁለቱ አገራት ለራሳቸው የተፅዕኖ ወሰን በሚገናኙባቸው ነጥቦች ሊከሰት ይችላል።

“በቱርክ እና በእስራኤል መካከል የግጭት አደጋ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከፍ ብሏል” ሲሉ ኤርሶይ ተናግረዋል።

ወደ ሁሉን አቀፍ ጦርነት የማምራት ዕድሉ ዝቅተኛ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት በተለይም በሶሪያ፣ በቆጵሮስ እና በምስራቅ ሜዲትራኒያን እየጨመረ የመጣውን ውድድር ጠቁመዋል። “እዚህ ላይ ደጋፊ ቡድኖችን ለመፍጠር የሚደረገውን ሙከራ እያየን ነው። ሁለቱ አገሮች አብረዋቸው የሚቆሙ የጂኦፖሊቲካል ጋሻ ለመፍጠር እየሞከሩ ነው ማለት እንችላለን” ብለዋል።

ኤርሶይም እንዲህ ብለዋል: “በእስራኤል ስትራቴጂካዊ ሰነዶች ውስጥ ቱርክ አሁን እንደ ጠላት ተመድባለች። ይህ እውነታ ነው።”

አምኖን አራንም በበኩላቸው “ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የወታደራዊ ግጭት ዕድሉ ጨምሯል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን አሁንም ማስወገድ ይቻላል።”

እአአ በ2025 በአዘርባጃን ሪፐብሊክ የቱርክ እና የእስራኤል ወታደራዊ ልዑካን በወቅቱ በአገራቱ መካከል ያለውን ውጥረት ለመከላከል ኣደረጉትን ስብሰባ ጠቅሰዋል። “እኔ እስከማውቀው ድረስ ቢያንስ በወታደራዊ ደረጃ ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ማናቸውም ክስተቶችን ወይም የተሳሳቱ ስሌቶችን ለመከላከል ጥረቶች እየተደረጉ ነው” ብለዋል።

አራን በእስራኤል ስለቱርክ ስላለው አመለካከትም “ቱርክ ቀስ በቀስ በእስራኤል መንግስት እና ጦር ሰራዊት ውስጥ ባሉ የፖለቲካ እና የወታደራዊ ልሂቃን ዘንድ እንደ ጠላት እና አደገኛ ኃይል እየተታየች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አሎን ፒንካስ ይህንን አደጋ ለማሳየት ምሳሌ አስቀምጠዋል። “ቱርክ ወደ ጋዛ ወይም ሊባኖስ የሚያመሩ የእርዳታ መርከቦችን አጅባለች እንበል። የእስራኤል የባህር ኃይል መርከቦች ይህንን መርከብ ለማጥቃት ቢሞክሩ እና የቱርክ መርከቦች የአጸፋ ተኩስ ቢከፍቱ እስራኤል ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች። ይህም የተወሰነ ጦርነት ሊፈጠር ይችላል። ግን ያ ይሆናል ብዬ አላስብም” ብለዋል።

አሎን ፒንካስ በበኩላቸው የቱርክ እና የእስራኤል ወታደሮች ከሁለቱ አገራት ፖለቲከኞች ጋር በተነጻጻሪነት “በምክንያታዊነት” እንደሚሠሩ ያምናሉ።

ሆኖም በሶሪያ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳጋጠመው ሁሉ የሁለቱ አገራት የተውጣጡ የጦር ጄቶች እርስ በእርስ ሊጋፈጡ የሚችሉበት “ውድመት” ሊያስከትል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

“ስለዚህ ምንም መረጃ ባይኖረኝም ግን ሞሳድ እና የቱርክ ወታደራዊ እንዲሁም የውጭ የስለላ አገልግሎቶች ያለማቋረጥ ግንኙነት እንዳላቸው ቢነግሩኝ ምንም አልገረምም” ብለዋል።

ኤርዶዋን የወታደር ልብስ ለብሰው

“አዲሷ ኢራን”

አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ከከፈቱት ጦርነት ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ቱርክ “አዲሷ ኢራን” መሆኗን ተናግረዋል።

በኋላም ተመሳሳይ ሃሳቦች በእስራኤል እና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተስተጋብተዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ በአንድ ፅሑፋቸው ላይ ቱርክ ኢራንን እንደምትደግፍ ጠቅሰው ከሰዋል።

“እስራኤል ከኢራን በኋላ ጠላት ሳይኖራት መኖር ስለማትችል አጀንዳ ለመፍጠር ተገድዳለች” ሲሉ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ባለፈው ወር ለአገራቸው የዜና አገልግሎት አናዶሉ ተናግረዋል። “የኔታንያሁ መንግሥት ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ተቃዋሚዎቹም ቱርክን በፖለቲካ ቋንቋ እንደ አዲስ ጠላት ለማስተዋወቅ እየሞከሩ እያየን ነው።”

የቀድሞው ዲፕሎማት አሎን ፒንካስ እንደገለጹት ከኢራን በተለየ መልኩ ቱርክ “እስራኤልን ለማጥፋት አልዛተችም” በእስራኤል ላይ የምትጠቀመው ወታደራዊ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማዘጋጀት ያለመ ግብም የላትም።

“ኤርዶጋን ስለእስራኤል ከሚናገሩት ጋር የማይስማማ ሰው እንኳን ቱርክ ጠላት አገር እንዳልሆነች ያውቃል። በማስፈራራት ረገድ ቱርክ ከኢራን ጋር እኩል እንደሆነች የሚያስብ ማንኛውም ሰው በግዴለሽነት እና በአደገኛ ሁኔታ እየሠራ ነው” ብለዋል።

አምኖን አራንም ቱርክ “አዲሷ ኢራን” አይደለችም ይላሉ። “እኔ እንደማስበው የእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናት ይህንን በእውነት ያምናሉ ብዬ እንኳን አላስብም። ምክንያቱም ቱርክ የኔቶ አባል ስለሆነች፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ስላላት እና አብዛኛውን የንግድ ልውውጧን ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ስለምታደርግ።

አራን አክለውም የዚህ አመለካከት መነሻ በአንዳንድ የእስራኤል ባለስልጣናት እና ተንታኞች ዘንድ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን እና አንካራ በእስራኤል ላይ ከነበራቸው ጨካኝ አቋም ጋር የተያያዘ ነው ብለው ያምናሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ከሆነ ይህ የሆነው ኤርዶዋን ኔታንያሁን ከሂትለር ጋር በማነጻጸራቸው እና የቱርኩ ፕሬዝዳንት ከዚህ ቀደም በእስራኤል ላይ በሰነዘሩት ትችት ምክንያት ነው።

ቱግሴ ኤርሶይም “ቱርክ አዲሷ ኢራን እንዳልሆነች ግልፅ ነው” ሲሉ ተናግረው፤ “ይህ ሃሳብ የተዘጋጀው ቱርክን ከምዕራባውያን ለመለየት እና ለማግለል በማሰብ ሊሆን ይችላል። በተለይም በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የሚታተሙት የእስራኤል ደጋፊ ትንታኔዎች የታቀዱ እና አድልዎ ያላቸው ናቸው ብዬ አምናለሁ። እነዚህን ሆን ተብሎ የተሰጠ መግለጫ እና ዓላማ አድርገን ልንቆጥራቸው እንችላለን” ብለዋል።

“በአጭር ጊዜ ውስጥ መሻሻል አንጠብቅም”

የግጭት አደጋ ባንዣበበት ሁኔታ በሁለቱ አገራት መካከል መተማመንን እንደገና መገንባት ይቻላልን?

“ኔታንያሁ ሥልጣን ሲለቁ ነገሮች ይሻሻላሉ ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን እንደተጠቀስውም ናፍታሊ ቤኔት ከቢቢ ኔታንያሁ የበለጠ ጠንከር ያለ አቋም ይዘዋል” ሲሉ አሎን ፒንካስ ገልጸዋል።

እስራኤል በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት መብቂያ ላይ አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ አቅዳለች። በቀድሞዎቹ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ናፍታሊ ቤኔት እና ያይር ላፒድ የሚመራው ጥምረት ከቤንያሚን ኔታንያሁ ጥምረት ጋር እንደሚፎካከር ይጠበቃል።

በቱርክ እና በእስራኤል ግንኙነት ዙሪያ የሚመጣ ለውጥ ካለ አሁን ካሉት መንግሥታት ሳይሆን ተተኪዎቻቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሊሆን እንደሚችል አምኖን አራን ያምናሉ።

ቱግሴ ኤርሶይም “በአጭር ጊዜ ውስጥ የተሻለ ለውጥ መጠበቅ የለብንም” ሲሉም አክለዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በታሪክ ውስጥ “ፍፁም ስምምነት የሞላው ሆኖ አያውቅም” በማለትም አፅንዖት ሰጥተዋል።

“የቱርክ እና የእስራኤል ግንኙነት ወደ መልሶ ግንባታ መስመር እንዲገባ አዲስ የደኅንነት ሥርዓት ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር የጋራ መተማመን እንደገና መመሥረት አለበት” ብለዋል።