ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ታጋቾች እና ቤተሰቦቻቸው
የምስሉ መግለጫ,ሪፖርቱ በሐማስ እና ሌሎች ቡድኖች የተፈፀሙ ወሲባዊ ትቃቶች ስልታዊ ነበሩ ብሏል

ታትሟልከ 3 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በእስራኤል የተደረገ ገለልተኛ ምርመራ ሐማስ እና ሌሎች የፍልስጤም ቡድኖች መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በፈፀሙት ጥቃት በታጋቾች ላይ “ስልታዊ እና ሰፊ” ወሲባዊ ጥቃቶችን መፈፀማቸውን የሚያሳይ ዝርዝሮችን የሚያሳይ ሰነድ ይፋ አደረገ።

300 ገፆች ያለው ምርመራ አስገድዶ መድፈር፣ ወሲባዊ ትንኮሳ እና ወሲባዊ ስቅየት “ህመም እና ስቃይን ከፍ” ለማድረግ ታልመው ጥቅም ላይ መዋላቸውን ያጠቃልላል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እና ሌሎች ተቋማት1,200 ሰዎች በተገደሉበት እና 251 ሰዎች በታገቱበት ጥቃት ወቅት የተፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን ቢያወጡም የአሁኑ ምርመራ ግን ሁሉን አቀፍ ሰፊ ሪፖርት መሆኑ ተገልጿል።

ምርመራው ከተጎጂዎች እና ከእማኞች ጋር 420 ቃለ ምልልሶችን፣ በአጥቂዎች የተቀረፁ ከ10 ሺህ በላይ ፎቶግራፎችን እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን እንዲሁም ይፋዊ ሰነዶችን እና ከጥቃት ስፍራዎች የተገኙ ማስረጃዎች መርምሮ የወጣ ነው።

ሐማስ አግቶ በያዛቸው ሰዎች ላይ ወሲባዊ እና ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈፀሙን በተደጋጋሚ አስተባብሏል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በግጭቶች ወቅት የሚፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን የሚመረምረው ልዩ ልዑክ በቡድን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ወሲባዊ ጥቃቶች ስለመፈፀማቸው አሳማኝ ማስረጃዎች እንዳገኘ አስታውቋል።

ከሐማስ ጥቃት በኋላ ወሲባዊ ጥቃት ስለመፈፀማቸው የእማኞች ቃል ወዲያው የተሰማ ሲሆን፣ ይህም የእስራኤል መንግሥት የፍትሕ አካላትን የያዘ ‘ሲቪል ኮሚሽን’ እንዲያቋቁም አድርጎታል።

ሐማስ ጥቃት በፈፀመበት እና 370 ሰዎች በተገደሉበት በኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ የነበሩ እማኞች በቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ሲፈፀሙ ማየታቸውን እና መስማታቸውን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

አንድ ወንድ ተጎጂ አጥቂዎቹ “እንደ ወሲባዊ አሻንጉሊት” ሲጠቀሙት እንደነበር ምስክርነት ሰጥቷል።

አብዛኞቹ የአስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች የደረሱባቸው ተጎጂዎች በጥይት ግንባራቸውን ተመትተው መገደላቸውም ተገልጿል።

የሙዚቃ ፌሲቲቫሉ በተሰናዳበት ስፍራ እና በወታደራዊ ካምፖች የተገደሉ ሴቶች ካለ የውስጥ ሱሪ ብልታቸው ላይ ጉዳት ደርሶ አስከረናቸው እንደተገኘ የሚያመላከቱ ተደጋጋሚ የእማኝ ቃሎች ተገኝተዋል።

“የከፋ ዓይነት” ወሲባዊ እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ለረጅም ጊዜ ታግተው በቆዩ በሴቶች እና በወንዶች ላይ መፈፀሙንም የሲቪል ኮሚሽኑ ሪፖርት ጠቁሟል።

የምርመራ ሪፖርቱ ጥቃቶቹን “ወሲባዊ ጥቃትን እንደ መሣሪያ” መጠቀም ሲልም ገልጿቸዋል።

አንዳንድ የቀድሞ ታጋቾች ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው በይፋ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች ተጎጂዎች ስለደረሰባቸው ወሲባዊ ጥቃት በምሥጢራዊነት ለሕክምና ባለሙያዎች፣ የሥነ አእምሮ አማካሪዎች እና መሪማሪዎች ተናግረዋል።

ሪፖርቱ ሁለት ዘመዳሞች ወሲባዊ ድርጊቶችን እንዲፈፅሙ በአጋቾቻቸው መገደዳቸውን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ እና አስደንጋጭ ዝርዝሮችንም ይዟል።

እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶችን ሪፖርቱ የቤተሰብ አባላት ዒላማ ያደረገ እና ቤተሰባዊ ግንኙነትን ለማሸበር እንደ መሣሪያ የመጠቀም የተለየ የጥቃት አዝማሚያ አድርጎ ገልፆታል።

ሲቪል ኮሚሽኑ በግኝቱ የተፈፀሙ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ሕግ “እንደ ጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል እና የዘር ፍጅት ድርጊት” ተብለው የሚቆጠሩ እንደሆነ አስታውቋል።