ከዚያ በኋላም በአሜሪካ ቺካጎ ማራቶን የብር ሜዳሊያ፣ በቻይና ሻንጋይ፣ በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ እንዲሁም በአሜሪካ ሂዩስተን ማራቶኖች ላይ ተሳትፋ አሸንፋለች።
በፈረንሳይ ፓሪስ ግማሽ ማራቶን ሁለት ጊዜ ያሸነፈችው የብርጓል፣ በፖርቱጋል ሊዝበን የግማሽ ማራቶንም አሸናፊ እንደነበረች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
አሠልጣኝ ዳዊት የሕመም ስሜት ስላላት ለውድድር የምታደርገውን መደበኛ ልምምድ ማቋረጧን፣ ነገር ግን ማክሰኞ ማለዳ ባለቤቷ “ካልሄድኩ” ብላው እንደወጣች እንደነገራቸውም ገልጸዋል።
ለልምምድም ስትወጣ መደበኛ ልምምድ ሳይሆን ዝግ ያለ ቀላል እንቅስቃሴ እደያረገች ሳለ ነው ለኅልፈት ያበቃት ችግር የገጠማት።
የብርጓል ጃንሜዳ ልምምድ በምታደርግበት ወቅት ስትወድቅ ወዲያውኑ አብረዋት የነበሩ ሰዎች ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል እንደወሰዷት አሠልጧኟ ተናግረዋል።
የዛሬ ዓመት በባርሴሎና ማራቶን ሁለተኛ መውጣቷን ያስታወሱት አሠልጣኟ ከውድድሯ በኋላ በግል ልምምድ በምታደርግበት ወቅት “በድንገት የመውደቅ ነገር ጀምሯት ነበር” ብለዋል።
ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር በኋላ ለስምንት ወር ያህል የሕክምና ክትትል ላይ እንደነበረች ያስታወሱት አሠልጣኝ ዳዊት፣ በተለያዩ የሕክምና ተቋማት የልብ፣ የነርቭ እና ሌሎች ተያያዥ ምርመራ አድርጋ በሽታዋ አለመታወቁን ገልጸዋል።
“ልምምድ በምታደርግበት ወቅት ትወድቃለች. . .ከዚያም አንዳንዴ እስከ አምስት ደቂቃ ድረስ ራሷን ስታ ትቆያለች” ብለዋል።
የብርጓል በምን ምክንያት ሕይወቷ እንዳለፈ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አሠልጣኟ ጨምረው ተናግረዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የአጥንት መሰንጠቅ አጋጥሟት ሕክምና ላይ እንደነበረች ያስረዱት አሠልጣኟ ከዚያ በኋላም በወሊድ ምክንያት ከውድድር ሜዳ ርቃ ቆይታለች።
“ከወሊድ በኋላ ሴዑል፣ በርሊን፣ ባርሴሎና ማራቶኖችን ከሮጠች በኋላ አሁን እግሯን ስላለመማት የኦቶዋ ማራቶንን ለመሰረዝ” መገደዷን ይገልጻሉ።
የተለያዩ ሕመሞች እየገጠሟትም ራሷን ብቁ ለማድረግ እና ወደ ውድድር ለመመለስ የምታደርገውን ጥረት አሠልጣኟ ሲናገሩ “ታታሪ፣ ሥነ ምግባር እና ለስፖርቱ ፍቅር ያላት” በማለት የበለጠ ውጤታማ ልትሆን የምትችል አትሌት እንደነበረች በቁጭት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከወሊድ በኋላ በዚያው ሳትጠፋ ወደ ውድድር ለመመለስ የፈለገችው ለስፖርቱ ፍቅር ስላላት እንዲሁም ሜዳሊያ በማምጣት አገሯን ማስጠራት ስለምትፈልግ እንደነበር አሠልጣኝ ዳዊት ህሉፍ ተናግረዋል።
አትሌት የብርጓል ጥሩ ሰዓት አምጥታ በዓለም ሻምፒዮና አገሯን ለመወከል ነበር የምትጥረው ያሉት አሠልጣኙ፤ ይህንን ለማሳካት ሚኒማ ለማሟላት በምትዘጋጅበት ወቅት ሕይወቷ ማለፉን አሠልጣኟ በሐዘን ገልጸዋል።
የአትሌት የብርጓል መለሰን ድንገተኛ ኅልፈትን ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን “መራር ሐዘን” እንደተሰማው በመግለጽ ለቤቸሰቦቿ፣ ወዳጆቿ እና ለመላው ለስፖርት ቤተሰቡ መፅናናትን ተመኝቷል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌት የብርጓል መለሰ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ሐዘን በመግለፅ ለመላው የስፖርት ቤተሰብ መፅናናትን ተመኝቷል።
