
ታትሟልከ 3 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጽንስ ማቋረጫ የሆነው ሚፌፕሪስቶን የተሰኘው ክኒን በፖስታ ቤት በኩል መላክ እንዲቀጥል ወሰነ።
ክኒኑን የሚያመርቱ ሁለት አምራቾች የታችኛው ፍርድ ቤት በሚፌፕሪስቶን ስርጭት ላይ ከፍተኛ ገደቦችን ካስቀመጠ በኋላ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሐሙስ ዕለት ባስተላለፈው ትዕዛዝ ክሱ በሚታይበት ወቅት የተጣሉት ገደቦች እንዲነሱ አዟል። በጉዳዩ ዙሪያ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ክኒኑን ማግኘት ይችላል። ውሳኔው በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት ሊሰጥ ይችላል ተብሏል።
ክኒኖቹ በአሜሪካ ውስጥ በተለይም ጽንስ ማቋረጥ በተከለከሉባቸው ግዛቶች እርግዝናን ለማቋረጥ በጣም ከተለመዱት ዘዴዎች መካከል ነው። ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወግ አጥባቂ ዳኞች ክላረንስ ቶማስ እና ሳሙኤል አሊቶ ውሳኔውን ተቃውመዋል።
እአአ በ2023 የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) ዶክተሮች ታካሚዎችን በአካል ሳያዩ ክኒኖቹን እንዲልኩ ፈቅዷል። ይህም ሴቶች ክኒኖቹን በፖስታ ወይም በቴሌሜዲሲን አማካኝነት ከፋርማሲ እንዲያዙ አስችሏቸዋል።
ሚፌፕሪስቶን እንዳይላክ ለመከላከል በማሰብ የሉዊዚያና ግዛት ባለፈው ጥቅምት ወር ኤፍዲኤን ከሳለች።
ሉዊዚያና በመላ አገሪቱ የመድኃኒቱ በፖስታ መላኩ የግዛቱን የጽንስ ማቋረጥ እገዳ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል ብላ ተከራክራለች።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለክሱ ምላሽ የሰጠው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የጽንስ ማቋረጫ ክኒኖች ለማግኘት በአካል መገኘትን የሚያስገድደውን መስፈርት ለጊዜው እንደገና አጽንቶታል።
“በኤፍዲኤ እርምጃ ምክንያት እያንዳንዱን ጽንስ ማቋረጥ የሉዊዚያናን የሕክምና ጽንስ ማቋረጥ እገዳ ይሰርዛል። ‘እያንዳንዱ ያልተወለደ ሕፃን ከተጸነሰበት ጊዜ ጀምሮ ሰው ነው ስለዚህም ሕጋዊ ሰው ነው’ የሚለውን ፖሊሲም ያዳክማል” ሲል የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ጽፏል።
ሁለት የማይፌፕሪስቶን አምራቾች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ሐሙስ ዕለት የወጣው ውሳኔ የፍርድ ቤቱ የአደጋ ጊዜ ውሳኔ አካል ሲሆን ምንም ምክንያት ሳይኖረው የተሰጠ ነው። ዳኞቹ የአምራቾቹን ጉዳይ መስማት አለመስማታቸውን እስኪወስኑ ድረስም ይቆያል።
ቶማስ በተቃውሟቸው ላይ እንደጻፉት ሚፌፕሪስቶንን በፖስታ መላክ በሉዊዚያና ሕገ-ወጥ ስለሆነ የመድኃኒት አምራቾች “በወንጀል ድርጊታቸው ትርፍ ላይ ተመስርተው” የፍርድ ቤት ትዕዛዝን የማገድ መብት የላቸውም።
ሚፌፕሪስቶን እርግዝናን ለማቋረጥ በኤፍዲኤ የሚመከር የመጀመሪያው ክኒን ነው። ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊ በሆነባቸው ግዛቶች በስፋት ይገኛል።
ኤፍዲኤ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሚፌፕሪስቶን ለማግኘት በአካል የመቅረብን መስፈርትን እንደሚያነሳ መግለጹን ተከትሎ የመድኃኒቶቹ አቅርቦት ጨምሯል።
