ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ነዳጅ የሚቀዳ እጅ

ታትሟልከ 4 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ሦስተኛ አገራት ውስጥ ተጣርቶ ወደ ናፍጣ እና የአውሮፕላን ነዳጅ የተቀየረ የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ የጣለውን ማዕቀብ አላላ። ይህ የዩኬ ውሳኔ ከረቡዕ ዕለት ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል።

እርምጃው አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የጀመሩትን ጦርነት ተከትሎ ወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋቱ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ምን ያህል ስጋት እንደተፈጠረ የሚያንጸባርቅ ነው።

ከዚህ ቀደም ወደ ፈረሳሽነት በተቀየረ በሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ጉዞ ላይ ተጥለው የነበሩ የተወሰኑ ማዕቀቦችም እንዲነሱ ተደርጓል።

የተጣሉት ማዕቀቦች እየጠነከሩ መምጣታቸውን የገለጸው የአገሪቱ መንግሥት፤ ተለዋዋጭ አካሄድ የሚከተል ተጨማሪ አሰራር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። ከጦርነቱ መነሳት በኋላ አሜሪካም ተመሳሳይ እርምጃ ተግባራዊ አድርጋ ሰፊ ትችት ደርሶባታል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ አውሮፓ ውስጥ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ ታይቷል። በአሁኑ ሰዓት ዋጋው በፊት ከነበረበት በግማሽ ጨምሮ እየተሸጠ ነው። ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥም የነዳጅ ዋጋ ማሻቀቡን ቀጥሏል።

በዩኬ እና በመላው ዓለም የሚንቀሳቀሱ በርካታ አየር መንገዶች ጣሪያ በነካው የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ ምክንያት በረራዎቻችን ሰርዘዋል አልያም የትኬት ዋጋቸውን ጨምረዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም ለዓመታት ሞስኮ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ስትመራ ቆይታለች።

ማክሰኞ ዕለት እንኳ ሩሲያ ላይ “ከባድ ዋጋ” ለመጣል “የማይናወጥ ቁርጠኝነት” እንዳለ የተገለጸበት የቡድን 7 መግለጫ ላይ ፊርማዋን አኑራለች።

https://www.bbc.com/amharic/articles/c3328v5078eo#:~:text=%E1%8B%A9%E1%8A%AC%20%E1%8A%AB%E1%88%88%E1%8D%88%E1%8B%8D%20%E1%8C%A5%E1%89%85%E1%88%9D%E1%89%B5,%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%B2%E1%8C%88%E1%8B%AB%E1%8A%99%20%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8B%AB%E1%88%B5%E1%89%BD%E1%88%8D%20%E1%8A%90%E1%8B%8D%E1%8D%A2