ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መግለጫ እየሰጡ
የምስሉ መግለጫ,ትራምፕ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጋር ያላቸውን ግንኙነት “አስደናቂ” ብለው አሞካሹ

ታትሟልከ 8 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተለመደው ዲፕሎማሲ አካሄድ ውጪ በሆነ አካሄድ ስለ ጦር መሣሪያ ሽያጭ ከታይዋን ፕሬዝዳንት ላይ ቺንግ-ቲ ጋር ሊነጋገሩ መሆኑን ገለፁ።

ዋሽንግተን ለቻይና መንግሥት እውቅና በመስጠት ከታይዋን ጋር ያላትን ይፋዊ ግንኙት ካቋረጠችበት የአውሮፓውያኑ 1979 ወዲህ የአሜሪካ እና ታይዋን መሪዎች በቀጥታ ተነጋግረው አያውቁም።

ቻይና ታይዋንን የግዛቷ አካል አድርጋ የምታይ ሲሆን፤ ከአንድነትን ለማምጣት ልትከተል ከምትችላቸው አማራጮች መካከል አንዱም በኃይል መጠቅለል ነው።

እ.አ.አ በ2024 ወደ ሥልጣን የመጡት የታይዋን ፕሬዝዳንት ባለፉት ዓመታት ከታዩ እና የደሴቲቷን መከላከያ የማጠናከር ጠንካራ አቋም ካላቸው መሪዎች መካከል ናቸው።

አሜሪካ ለረጅም ዓመታት ታይዋንን የደገፈች ሲሆን በሕግ ራሷን ለመከላከል የሚያስችላትን መሣሪያ እንድታቀርብ ትገደዳለች። ነገር ግን ይህን ስታደርግ ከቻይና ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አመዛዝና መሆን አለበት።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት የጦር መሣሪያ ሽያጭ ላይ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ከፕሬዝዳንት ላይ ጋር ለመነጋገር መወጠናቸውን ሲጠየቁ፤ “አነጋግረዋለሁ። ከሁሉም ሰዎች ጋር እናገራለሁ። … በታይዋን ችግር ዙሪያ እኛ እንሰራለን” ብለዋል።

ከቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጋር ያላቸውን ግንኙነት “አስደናቂ” ብለው አሞካሽተዋል። ትራምፕ ይህን አስተያየት የሰጡት ባለፈው ሳምንት በቤጂንግ ያካሄዱትን የሁለት ቀናት ጉብኝት ተከትሎ ነው።

እ.አ.አ 1979 አሜሪካ ‘የታይዋን ግንኙነት ሕግ’ አፅድቃለች። ይህ ሕግ ለታይዋን የመከላከያ መሣሪያዎችን ማቅረብ እንዳለባት ይዘረዝራል። ሕጉ እስካሁን ድረስ ለታይዋን መሣሪያ እንድትሸጥ የሚያደርግ ምክንያት ነው።

ትራምፕ ፀረ ድሮን እና የአየር መቃወሚያ ሚሳዔል ስርዓቶችን የሚያካትተውን እንዲሁም 14 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣን የጦር መሣሪያ ጥቅል ለታይዋን ለመሸጥ እስካሁን እንዳልወሰኑ ተነግሯል።

እንደ ፋይናንሻል ታይምስ ዘገባ ቤጂንግ ትራምፕ ሽያጩ ላይ ውሳኔ እስኪያሳልፉ ድረስ የፔንታጎን ከፍተኛ የፖሊሲ ሹም ኤልብሪጅ ኮልቢን ጉብኝት አዘግይታለች።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ከፕሬዝዳንት ዢ ጋር ተገናኝተው ሲመለሱ ስለ ለታይዋን የመሣሪያ ሽያጭ ተመሳሳይ ጥያቄ ሲቀርብላቸው “በአጭር ጊዜ ውስጥ እወስናለሁ” ብለው ነበር።

ትራምፕ በቤጂንግ በነበራቸው ጉብኝት ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ከትልቅ ጉዳዮች አንዱ የታይዋን ነገር መሆኑን በግልጽ አቅርባለች።

ፕሬዝዳንት ዢ ጉዳዩ በአግባቡ ካልተከናወነ በሁለቱ ኃያላን ኃይሎች መካከል “ግጭት” ሊፈጠር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ ግን በደሴቱ ምክንያት በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ግጭት ሊፈጠር የሚችልበትን እድል አጣጥለዋል። “እኔ ለሁለቱም ወገኖች ምንም ቃል አልገባሁም” በማለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ከትራምፕ እና ዢ ንግግር በኋላ የታይዋኑ ፕሬዝዳንት አገራቸው “ሉዓላዊ፣ ነፃ ዲሞክራሲያዊ አገር” ናት በማለት፤ በታይዋን ወሽመጥ አካባቢ ያለው ሰላም ” በመስዋዕት ወይም በንግድ ልውውጥ አይተካም” ብለዋል።