
ታትሟልከ 6 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ
የዩናይትድ ኪንግደም እና ዩክሬን መሣሪያ አምራች ተቋም ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ ሮቦቶች ከሰው ልጆች በቁጥር በልጠው በዩክሬን ጦርነት የሚዋጉበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ዩክሬንም ሩሲያም በአየርም በየብስም የሚንቀሳቀሱ ሰው ሠራሽ መሣሪያዎች አሏቸው።
የዩክሬን ጦርነት የወታደራዊ ቴክኖሎጂን አካሄድ በፍጥነት እንደለወጠው ተንታኞች ይናገራሉ። በወደፊቱ ዓለም ጦርነት ምን ሊመስል ይችላል? የወታደሮች ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል? የሚሉ ጥያቄዎችንም አጭሯል።
ከወራት በፊት የወጣ ተንቀሳቃሽ ምሥል በዩክሬን የተሠሩ የሮቦት መሣሪያዎችን ያሳያል። ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ “የጠላት ይዞታን ተቆጣጥረናል” ሲሉም ይደመጣል።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ወታደራዊ እርምጃ የተወሰደው ሙሉ በሙሉ ሰው አልባ በሆኑ መሣሪያዎች ነው። ይህም ሮቦቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ያካትታል።
የዩክሬን ጦር ስለ ወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ከዚህ ኦፕሬሽን በፊት በየብስ ሮቦት አማካኝነት የሩሲያ ወታደሮችን የመስፋፋት እንቅስቃሴ ለ45 ቀናት መግታት እንደተቻለ ተገልጾ ነበር።
በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ ከዋሉ መሣሪያዎች የተወሰኑት የዩናይትድ ኪንግደም እና ዩክሬን ጥምር የጦር መሣሪያ አምራች በሆነው ‘ዩፎርስ’ በተባለ ተቋም የተሠሩ ናቸው።
ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ላላቸው ተቋማት የሚሰጠው ዩኒኮርን የተባለው ስያሜ ለመሣሪያ አምራቹ ተሰጥቷል።
የድርጅቱን የለንደን ቅርንጫፍ ቢቢሲ በጎበኘነት ወቅት ምሥጢራዊ እና ስያሜ ያልተሰጣቸው መሣሪያዎች ተመልክቷል። ይህም የሆነው የጦር መሣሪያዎቹን ከሩሲያ ለመታደግ እንደሆነ ተገልጿል።
ዜሌንስኪ ንግግር ሲያደርጉበት የሚታየው እና የዩክሬን የሮቦት መሣሪያን የተመለከተው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ የድርጅቱ ተወካይ አስተያየት ለመስጠጥ አልፈቀዱም።
ሆኖም የጦር መሣሪያ አምራቹ በባሕር እና በየብስ የሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች እንዳሉት ተገልጿል።

የተቋሙ የዩናይትድ ኪንግደም የስትራቴጂክ ጥምረት ዳይሬክተር ሪሃኖን ፓድሊ “የዩፎርስ የኦፕሬሽን ዝርዝሮችን መግለጽ አልችልም። ግን የሩሲያ ወረራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ድረስ 150 ሺህ ስኬታማ ዘመቻዎችን አካሂደናል” ብለዋል።
ሮቦቶች ከሌሎች ሮቦቶች ጋር ውጊያ የሚገጥሙበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ዳይሬክተሯ ይናገራሉ። ከሰዎች ወታደሮች ቁጥር የሮቦት ወታደሮች ቁጥር ከፍ እንደሚል ያስረዳሉ።
ሩሲያም ወደ በዩክሬን ግዛት ውስጥ ፈንጂ የሚያወስወግዱ ሮቦቶችን እየሠራች ነው።
በብሩኪንግስ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ሜላኒ ሲሶን “ዩክሬን ራስን ለመከላከል በሚረዱ መሣሪያዎች ግንባታ ሌሎችን ማስተማር የምትችል አገር ናት ብዬ አምናለሁ” ይላሉ።
ዩፎርስ ‘ኒዮ ፕራይም’ በሚል የሚታወቅ የመከላከያ ተቋማት ጥምረት አካል ነው። ቤይ ሲስተምስ፣ ቦይንግ እና ሎክሄድ ማርቲን የዚህ አካል ናቸው።
የአሜሪካው የመከላከያ ቴክኖሎጂ ተቋም አንዱሪል ከወራት በፊት ያለ አብራሪ የሚጓዙ ተዋጊ ጄቶች ሙከራ አከናውኗል።
አብዛኞቹ ድሮኖች አሁንም ድረስ በርቀት በሰዎች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። አንዱሪል እንዳለው ከሆነ ግን ያለው ሰው ዕገዛ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚዘወሩ መሣሪያዎች እየገነባ ነው።
የዩፎርስ የየብስ ድሮኖች ዒላማ ለማግኘት በመተግበሪያ የሚታገዙ ናቸው። አንዱሪል በበኩሉ እያጠናቀቃቸው ያሉት የተወሰኑ መሣሪያዎቹ ያለ ሰው ዕገዛ መንቀሳቀስ የሚችሉ እንደሆኑ ገልጿል።
የአሜሪካ መንግሥት መከላከያ ኃይሉ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እንዲተገብር በይፋ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት አሜሪካ “ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ቅድሚያ የሚሰጥ የውጊያ ኃይል” እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።
ቻይናም በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚመራ ወታደራዊ ሥርዓት እየዘረጋች እንደሆነ የአሜሪካ መከላከያ አስታውቋል።
ተንታኞች እንደሚሉት ለወደፊት ሮቦቶች ከሌሎች ሮቦቶች ጋር መዋጋታቸው የሚቀር አይደለም።
ራንድ ዩሮፕ የተባለው የባለሙያዎች ስብስብ (ቲንክ ታንክ) ባለሙያ ጃኮብ ፓራኪላስ “የዩክሬን እና ሩሲያ ድሮኖች አሁንም እርስ በርስ እየተዋጉ ነው። ይሄ ወደ የብስ ውጊያ የሚሻገርበት ዕድል ሰፊ ነው። ማስቀረት የሚቻል ነገር አይደለም” ብለዋል።
