ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የመከላከያ አልባሳትን የለበሱ የጤና ባለሙያዎች

ታትሟል18 ግንቦት 2026

ተሻሽሏል ከ 6 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ባለፈው ሳምንት የዓለም ጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ አሳሳቢ ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ሲል አውጇል።

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ኢቱሪ ግዛት በሚገኙት ሞንግዋሉ እና ሩዋምፓራ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ እና ከ130 በላይ ሰዎች እንደሞቱ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በኡጋንዳ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ቫይረስ ሳይታወቅ ለበርካታ ሳምንታት ሲሠራጭ የቆየ ሊሆን እንደሚችል እና ከተነገረው በላይ በስፋት ሳይዛመት እንዳልቀረ የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንዳረጋገጡት በዲሞክራቲክ ኮንጎ 51 እንዲሁም ሁለት የወረርሽኙ ክስተቶች በኡጋንዳ ውስጥ ተግኝተዋል። በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ሲጠረጠር 139 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

በአውሮፓውያኑ 2025 በዲሞክራቲክ ኮንጎ ማዕከላዊቷ ካይሲ ግዛት 45 ሰዎች በኢቦላ ምክንያት ሞተዋል።

የኢቦላ ምርመራ

ኢቦላ ምንድን ነው?

ኢቦላ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ የሆነ ተላላፊ በሽታ ነው። መጀመሪያ ላይ የሚታዩት ምልክቶች ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ከፍተኛ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም እና ጉሮሮ መከርከር ናቸው።

ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ሲሠራጭ ማስመለስ እና ማስቀመጥ ይከሰታል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰውነታቸው ውስጥ እና ከሰውነታቸው ውጪ ደም ይፈስሳቸዋል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ምልክት የሚያሳዩት ከሁለት ቀናት እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ኢቦላ እንደ ወባ እና ታይፎይድ ካሉ ሕመሞች ጋር ተመሳሳይ ምልክቶች አሉት።

ሰዎች በኢቦላ መያዛቸው የሚረጋገጠው በቤተ ሙከራ በሚደረግ ምርመራ ብቻ ነው።

ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለይቶ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 1976 ሲሆን፤ በወቅቱ ወረርሽኙ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን ተስፋፍቶ ነበር።

በሽታው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች አንዱ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች የሚወጣ የሰውነት ፈሳሽ ጋር የሚኖር ንክኪ ነው። ይህም ደም፣ ምራቅ፣ የወንድ የዘር ፈሳሽ፣ ከሴት ብልት የሚወጣ ፈሳሽ፣ ሽንት፣ ሰገራ እና ላብን ይጨምራል።

ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ የነካቸው ቁሳቁሶችም በሽታውን ያስተላልፋሉ። ዐይን፣ አፍንጫ፣ አፍ እና አንዳች ስንጥቅ ያለው የቆዳ ክፍል በመንካት ቫይረሱ ይተላለፋል።

የሌሊት ወፍ፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጃርት እና ድኩላ በሽታውን የሚያስተላልፉ እንሰሳት ናቸው። ለምግብነት የሚታደኑ የዱር እንሰሳት ሥጋ ላይ ቫይረሱ ሊኖር ይችላል።

በኢቦላ ሳቢያ የሞቱ ሰዎችን አስከሬን መንካትም ለበሽታው ያጋልጣል።

ኢቦላ እንዴት እንደሚተላለፍ የሚያሳይ ግራፊክስ

በቅርቡ ኢቦላ የተከሰተው የት ነው?

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በከፍተኛ መጠን የኢቦላ ወረርሽኝ የተነሳው ከአውሮፓውያኑ 2018 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት ሲሆን 2,300 ገደማ ሰዎች ሞተዋል።

በ2022 በኡጋንዳ በተከሰተው የሱዳን ኢቦላ ዝርያ ወረርሽኝ ምክንያት 164 ሰዎች ለኅልፈት ተዳርገዋል።

በ2014 በጊኒ፣ በላይቤሪያ እና በሴራ ሊዮን የተነሳው የኢቦላ ወረርሽኝ ከምንጊዜውም በላይ የከፋ ሲሆን ከ11,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ሐኪም

ኢቦላን ማከም ይቻላል?

የኦቦላ ቫይረስ የተለያዩ ዝርያዎች አሉት። በዛየር ለሚገኘው የኢቦላ ዝርያ ክትባት ተገኝቷል።

የሱዳን የኢቦላ ዝርያን ጨምሮ ለሌሎችም የኢቦላ ዓይነቶች ክትባት ወይም መድኃኒት ለማግኘት ሳይንቲስቶች ምርምራቸውን ቀጥለዋል።

በሆስፒታሎች ውስጥ ሐኪሞች ለሕሙማን ድጋፍ ይሰጣሉ። የውሃ ጥምን መቁረጥ (rehydration)፣ እንደ ሶዲየም፣ ፖታሽየም፣ ካልሽየም እና ማግኒዥየም ያሉ ንጥረ ነገሮችን ማመጣጠን (electrolyte balance) እንዲሁም ደም በመለገስ በሕይወት የመትረፍ ዕድልን መጨመር ከሕክምናዎቹ መካከል ይገኙበታል።

ኢቦላን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የሌሊት ወፍ