“በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች 97% ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አለ መባሉን አንቀበለውም” — ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት
አዲስ አበባ — «ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት» ጥምረት ዛሬ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ-ሂደት ላይ በርካታ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ይፋ አደረገ።
ጥምረቱ ባወጣው ባለ 11 ነጥብ መግለጫ መንግሥትን በበርካታ ጉዳዮች የገመገመ ሲሆን፣ የታሰሩ ፖለቲከኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱና ለሀገራዊ አንድነት እንዲሠራ ጥሪ አቅርቧል።
መግለጫውን በንባብ ያቀረቡት የትብብሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፤ በክልሎቹ የተንቀሳቀሰው የምርጫ አስቻይነት አጣሪ ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት አጥብቀው ተችተዋል።
ኃላፊው፦ “በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ለምልከታ የተጓዘው የምርጫ አስቻይነት አጣሪ ቡድን በክልሎቹ 97 በመቶ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አለ ማለቱን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ ሕዝብ ውድቅ እንዲያደርጉት ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል። በትብብሩ ግምገማ መሠረት ይህ ሪፖርት የተዛባና አሳሳች ነው።
ጥምረቱ ባወጣው ዝርዝር መግለጫ፣ ገዢው ፓርቲ እያደረገው ያለው አፈና እና ወከባ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ መቀጠሉን ጠቅሷል። ከእስርና ከአፈና ባሻገር “የቴክኖሎጂ ሲስተም” በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ትልቅ መዋቅራዊ ተግዳሮት መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና አካባቢ በዚሁ የሲስተም ችግር ምክንያት 15 የትብብሩ ዕጩዎች ሳይመዘገቡ መቅረታቸውን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም በዕጩዎች ላይ የማወከብና የግድያ ማስፈራሪያ መደረጉን ገልጿል።
የጥምረቱ ዕጩ የነበሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ወልዳይ ከቀናት በፊት ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ጥምረቱ ዕጩዎቹ “ከዕጩነት እንዲለቁ ወይም ምርጫ ክልል እንዲቀይሩ” ከባድ ዛቻና ሥነ-ልቦናዊ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑን አረጋግጧል።
በተጨማሪም ምርጫ ካርድ ባልወሰዱ ዜጎች ላይ የሚደረገው የማዳበሪያና የአገልግሎት ክልከላ፣ የመራጮች መረጃ ምንተፋ፣ የ1 ለ 5 ጥርነፋ እና የሴፍቲኔት እርዳታን ለፖለቲካ መጠቀሚያ የማድረግ ተግባራት በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥምረቱ ጠይቋል።
በማጠቃለያው፣ መንግሥት የገባውን የለውጥ ቃል እንዲያከብር፣ በአስቸኳይ ጦርነት እንዲያቆም፣ የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ እና ለሀገራዊ አንድነት ሲባል ከሁሉም አካላት ጋር በጋራ እንዲሠራ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፤ ይህ ካልሆነ ግን ጥምረቱ በምርጫው የመሳተፍ ጉዳዩን እንደገና ለመገምገም እንደሚገደድ በጥብቅ አስታውቋል።
#ኢትዮጵያ#ዜና#ምርጫ2018#ትብብርለኢትዮጵያአንድነት#ጌትነትወርቁ#የምርጫቦርድ#የፖለቲካምኅዳር#ሀገራዊአንድነት
See less




