ታትሟልከ 5 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 9 ደቂቃ
“ጦርነቱ ተጀምሯል” ይላሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት የሕገ መንግሥት ባለሙያው ዶ/ር አደም ካሴ የፌደራል መንግሥት እና ትግራይ ክልልን ሁኔታ ሲገልጹ።
ዶ/ር አደም እንደሚያረስዱት ቁርጡ ያልለየው “ተኩስ መቼ ጀመራል?” የሚለው ነው።
የሁለት ዓመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት የገታው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አደጋ ውስጥ የገባ ይመስላል።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስምምነቱ “ፈርሷል” የሚል አቋሙን አሳውቋል። ለዚህም ተጠያቂ ያደረገው ፌደራል መንግሥቱን ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እስካሁን በይፋ አስተያየት አልሰጠም።
ህወሓት ከስድስት ዓመት በፊት በተደረገው እና ለጦርነቱ እንደ አንድ ምክንያት በሚጠቀሰው ምርጫ የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ምክር ቤትም ወደ ሥራ መልሷል።
ምክር ቤቱ ደግሞ የህወሓትን ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በፕሬዝዳንትነት መርጧል።
ይህ እርምጃ የክልሉን ሥልጣን በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት ከተመሠረተው ጊዜያዊ አስተዳደር የነጠቀ ሆኗል።
መጋቢት መጨረሻ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሥልጣን ቆይታቸው የተራዘመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ በይፋ መውረዳቸው ባይገለጽም፤ የአስተዳደር ኃይሉን የተቀሙ ይመስላል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕጋዊነት እንዳበቃ የሚናገረው ህወሓት፤ በዚህ ምክንያት ከፌደራል መንግሥት ጋር የነበረው የግንኙነት “ገመድ ተበጥሷል” የሚል አቋም ይዟል።
በትግራይ ክልል ጉዳይ ‘ቀጥሎ ምን ይሆናል?’ የሚለው እስካሁን በውል አልለየም።
ሁኔታው ባለበት ይቀጥላል ወይስ ፌደራል መንግሥት እርምጃ ይወስዳል? ሥልጣን የተቆጣጠረው ህወሓትስ ወደ ወታደራዊ እርምጃ ይገባ ይሆን? ወይስ ሁለቱ አካላት አንዳች ስምምነት ላይ ይደርሳሉ?
እነዚህ አራት ቢሆኖች በተመለከተ ባለሙያዎችን አነጋግረናል።
“ጦርነት ሳይነሳ፤ ሰላምም ሳይመጣ ፍጥጫው ይቀጥላል”
ቀድሞውንም ፈተናዎች የነበሩትን የፕሪቶሪያ ስምምነት ይበልጥ አደጋ ውስጥ የከተተው የህወሓት እርምጃ ሦስት ሳምንት ገደማ ቢሆነውም እስካሁን ከፌደራል መንግሥት በኩል በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።
ዶ/ር ደብረጽዮን ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም. ካቤኒያቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰበሰቡበት ወቅት የጊዜያዊ አስተዳደሩ “ሥልጣን በጉልበት እየተያዘ” እንደሆነ የገለጹት ሌተናነት ጄነራል ታደሰ ከዚያ ዕለት በኋላ ድምጻቸው አልተሰማም።
ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የህወሓት ሊቀ መንበር እና ያዋቀሩት ካቤኒ በአንጻሩ ክልላዊ ውሳኔዎችን እያሳለፈ አመራርነቱን ቀጥሏል።
የሕገ መንግሥት እና የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር አደም ካሴ እንደሚናገሩት አሁን በትግራይ ያለው “ሰላምም፣ ጦርነትም ያልሆነ” ሁኔታ የፌደራል መንግሥቱን እና የክልሉን አስተዳደር ግንኙነት ያወሳስበዋል።
ፌደራል መንግሥቱ “አቋቁሜዋለሁ እውቅና እሰጠዋለሁ” የሚለው ጊዜያዊ አስተዳደር ከፈረሰ፤ “በምን ዓይነት መልኩ ከትግራይ ክልል ጋር እንደሚገናኝ አይታወቅም” ይላሉ።
ይህ መሆኑም ቀድሞውኑ “በተወሰነ ደረጃ” ብቻ ወደ ክልሉ የሚደርሱት “ነዳጅ እና የተለያዩ መሠረታዊ ሸቀጦች” ወደ ክልሉ መግባት የመቀጠላቸውን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባው አስረድተዋል። የፌደራል ድጎማ በጀት ጉዳይም በተመሳሳይ የሚነሳ ሌላኛው ነጥብ መሆኑን አክለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፈው ሚያዝያ ላይ የፌደራል ድጎማ በጀት በምን ያህል መጠን እንደተቆራረጠ የሚዘረዝር ደብዳቤ ለገንዘብ ሚኒስቴር ጽፎ ነበር። ደብዳቤው እንደሚያስረዳው ከጥቅምት አንስቶ ወደ ክልሉ መድረስ ከነበረበት 17.1 ቢሊዮን ብር ውስጥ የደረሰው 8.5 ቢሊዮን ብር ያህል ብቻ ነው።
ቢቢሲ ወደ ክልሉ የሚላክ የድጎማ በጀትን በተመለከተ ከገንዘብ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ያደረጋቸው ተደጋጋሚ ጥረቶች አልተሳኩም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን ባለፈው ጥቅም ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት “የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚመድበው በጀት ለልማት ሳይሆን ለታጣቂ እየዋለ ነው” በማለት ከስሰው ነበር።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ደብዳቤ መጋቢት ላይ መድረስ ከነበረበት በጀት ውስጥ 50 በመቶው መላኩን ጠቅሷል። አሁን ፌደራል መንግሥት እውቅና ለማይሰጠው የዶ/ር ደብረጽዮን ካቤኒ የድጎማ በጀት ይልካል? የሚለው ጥያቄ ያስነሳል።
የፖለቲካ ተንታኙ እና በካናዳ ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ፌደራል መንግሥት “በጀት በመከልከል እስኪ እንደ ፍጥርጥራቸው ብሎ ለተወሰነ ጊዜ ሊተዋቸው ይችላል” ሲሉ ግምታቸውን ይናገራሉ።
እንደ ዶ/ር ጌታቸው ትንተና ከሆነ ግን ይህ የፌደራል መንግሥት ዝምታ እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ ሳይሆን ሁኔታዎች እስከሚሟሉ “ጊዜ የሚጠብቅ” ነው።
ዶ/ር ጌታቸው አሁን ለሚታየው ዝምታ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ከሚጠቅሷቸው ጉዳዮች መካከል፤ ሊካሄድ አንድ ሳምንት የቀረው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ እና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው መንግሥት ምሥረታ ይገኙበታል።
መጪው ጊዜ ክረምት መሆኑን እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ግጭትም ፌደራል መንግሥት የአጸፋ እርምጃቸውን ለማዘግየቱ ከግምት ውስጥ ያስገቧቸዋል።
ዶ/ር አደምም በተመሳሳይ “አሁን ያለው ሰላምም ያልሆነ፣ ጦርነትም ያልሆነ ሁኔታ መቀጠሉ ምናልባት ለትንሽ ጊዜ ነው እንጂ ዘላቂ ነው ብዬ አላስብም” ይላሉ።
ፌደራል መንግሥት እውቅና የሚሰጠው አስተዳደር ሥልጣን ላይ ባለመሆኑ “በበጀት እና በሌሎች ዋና ዋና እቃዎች ላይ ያለውን ቁጥጥር እንደሚያጠብቅ” የሚናገሩት ዶ/ር አደም፤ ይህ ደግሞ ህወሓት እነዚህ ጉድለቶች ለማሟላት “ሙሉ በሙሉ ከውጪው ዓለም ጋር ግንኙነት” እንዲፈጥር ሊያደርገው እንደሚችል ያስረዳሉ።
እንዲህ አይነቱ ግንኙነት “ፌደራል መንግሥቱን ሌላ ቁጣ ውስጥ እና ሌላ እርምጃ ውስጥ ሊያስገባው ይችላል” ሲሉ የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።
ፌደራል መንግሥት እርምጃ ይወስዳል
ዶ/ር አደምም ሆነ ዶ/ር ጌታቸው ፌደራል መንግሥት እንደ ሁለት ዓመቱ የትግራይ ጦርነት ዓይነት መጠነ ሠፊ ግጭት ውስጥ የመግባት ዕድሉ ጠባብ መሆኑን ይናገራሉ። አንዳች ግጭት መነሳቱ ግን አይቀሬ መሆኑን ይገምታሉ።
ዶ/ር አደም “ፌደራል መንግሥቱ መጠቀም ከፈለገ ብዙ ጡንቻ አለው” ባይ ናቸው። “ወደ ጦርነት ሳይገባ ጫና ማድረግ ከፈለገ፤ በተለይ በጀትን በተመለከተ ብዙ ጫና” ማሳደር እንደሚችል ያምናሉ።
ጦርነት የሚጀመር ከሆነ፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ባሉ ግጭቶች የተነሳ “ጫና ውስጥ” ያለው ፌደራል መንግሥት፤ “ወታደሩን ከተለያዩ ቦታዎች እየወሰደ ጦር ሜዳ ማስገባት” እንደሚኖርበት ያስረዳሉ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባሉ ክልሎች ጭምር “አሁን ያሉ ግጭቶች ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ግጭቶች የመከሰት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው” ይላሉ።
ጥር መጨረሻ ላይ መከላከያ ሠራዊት ከደቡብ ጎንደር ዞን በወጣበት ወቅት በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የፋኖ ኃይሎች እንደ ደብረ ታቦር ባሉ ከተማዎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፍተው ነበር። ኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥም የመከላከያ እንቅስቃሴን ተከትሎ ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸማቸው ተዘግቧል።
ዶ/ር አደም በሁለተኛነት የሚጠቅሱት ምክንያት ጦርነት ከተጀመረ “ኢትዮጵያ እያደገች ነው የሚለውን ትርክት ያፈርሳል” የሚል ነው።
“ሁለተኛ [ጦርነት መጀመሩ] ‘ኢትዮጵያ እየታደሰች ነው፣ እያደገች ነው፣ እየተቀየረች ነው’ የሚለውን ትርክት በጣም የሚያቋርጥ ነው። እና [ፌደራል መንግሥት] ጦርነቱን ይፈልገዋል ብዬ አላስብም” ይላሉ።
“ምናልባት በህወሓት እና በኤርትራ፣ በህወሓት እና በሱዳን በኩል የተቀናጀ … ዓይነት ነገር ከተፈጠረ ምናልባት ያንን ነገር ለማስወገድ ወደ ጦርነት ሊገባ ይችላል” ሲሉ ፌደራል መንግሥት የመከላከል እርምጃ ሲወስድ ግጭት ሊፈጠር የሚችለበት ዕድል መኖሩን አመልክተዋል።
ዶ/ር አደም ፌደራል መንግሥት ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ቢያምኑም፤ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ “የባሕር በርን የማስመለስ ዕድል ይፈጥራል” የሚል ስሌትን ሊይዝ እንደሚችል ያነሳሉ።
ከ2016 ዓ.ም. አንስቶ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ በይፋ እያነሳ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት፤ በመገናኛ ብዙኃኑ በኩል አሰብ የኢትዮጵያ የግዛት አካል እንደነበር የሚገልጽ ትርክት እያቀነቀነ ነው።
መንግሥት የባሕር በር ማግኘት የሚፈልገው በሰላማዊ እና በንግድ ዘዴ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ ኤርትራ በዚህ ሽፋን ጦርነት ይከፍታል የሚል ክስ ታሰማለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ጫና ሲመጣ ጫናውን መመለስ ብቻ ሳይሆን አማራጮችን የማየት” ዝንባሌ እንዳላቸው የሚያነሱት ዶ/ር አደም፤ “ይህ ነገር ከመጣ እንዲያውም ‘አጋጣሚውን ተጠቅመን የባሕር በር እናገኛለን’ የሚል ስሌት ሊኖር ይችላል” ብለዋል።
የካልጋሪ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ዶ/ር ጌታቸው በበኩላቸው፤ ፌደራል መንግሥት ወታደራዊ እርምጃ ይወስዳል ወደሚለው ድምዳሜ እንደሚያዘነብሉ ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት ወደ ሥራ በተመለሰበት ዕለት ከፕሪቶሪያ ስምምነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በመቀለ ሰማይ ላይ ተዋጊ ጄቶች መታየታቸውን ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
መጠነ ሠፊ ጦርነት የመከፈት ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ጌታቸው፤ በአንጻሩ “የተመረጡ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎችን ዒላማ ያደረገ እርምጃ ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።
“በአፋር ክልል አለ የሚባለውን ታጣቂ [ቡድን] መጠቀም፣ እነርሱን መደገፍም ሊሆን ይችላል” ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።
ከትግራይ ኃይሎች በወጡ ወታደራዊ አዛዦች የተመሠረተው “የትግራይ ሰላም ኃይል” የተባለው ታጣቂ ቡድን በአፋር ክልል እና በደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል። ቡድኑ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተኩስ ልውውጥ ያደረገባቸው ጊዜያትም ነበሩ።
የዚህ ታጣቂ ቡድን አባላት የትግራይ “የሰላም እና የለውጥ ምክር ቤት” የተባለው እንቅስቃሴ ግንቦት 9 ቀን በአዲስ አበባ ሲመሰረት ታዳሚ እንደነበሩም ተገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ጌታቸው ረዳን ጨምሮ የተለያዩ የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት ይህ እንቅስቃሴ “በመፈንቅለ መንግሥት ትግራይን የተቆጣጠረውን ኃይል ማስወገድ” ዓላማ እንዳለው ገልጿል።
ዶ/ር ጌታቸው ፌደራል መንግሥት ከግጭት ውጪ እንደ በጀት ያሉ አቅርቦቶችን ሙሉ በሙሉ የሚያቋርጥ ከሆነም ተጽዕኖው “ከወታደራዊ እርምጃ የማይተናነስ” እንደሚሆን ገልጸዋል።
“ህወሓት እርምጃ ይወስዳል”
ዶ/ር ጌታቸው ህወሓት “ወታደራዊ እርምጃ ይወስዳል ብዬ አላምንም” ይላሉ። እንደ ተንታኙ ገለጻ ግን ህወሓት ይህንን አማራጭ የማይወስደው “ካለመፈለግ ሳይሆን ምናልባት ፕራግማቲክ ከመሆን አንጻር” ነው።
ተንታኙ፤ የህወሓት አመራሮች ወታደራዊ እርምጃ ውስጥ የማይገቡበት አንዱ ምክንያት “ከኤርትራ መንግሥት ጋር” ያላቸው ግንኙነት ነው የሚል ግምገማ አላቸው።
በህወሓት በኩል እርምጃ የሚወሰድ ከሆነ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ሥር በተዋቀረው አስተዳደር እጅ ወደሚገኙት የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ሊያመሩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙት ተንታኙ፤ ይህ ጉዳይ “ከኤርትራ መንግሥት ጋር” ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያወሳስበው ይጠቅሳሉ።
ህወሓት ከፕሪቶሪያ ስምምነት አለመፈጸም ጋር በተያያዘ በአጽንኦት ከሚያነሳቸው ጉዳዮች መካከል የአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች እና ከስፍራዎቹ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች አለመመለስ ነው።
ባለፈው ጥር ላይ በፌደራል እና ትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት የተነሳው የትግራይ ኃይሎች ወደ ጸለምቲ አካባቢዎች እንዲቀሳቀሱ በመደረጉ እንደሆነ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ተናግረው ነበር። ሌተናንት ጄነራል ታደሰ እንደሚገልጹት የትግራይ ኃይሎች በጸለምቲ አካባቢ እንዲቀሳቀሱ የተደረገው የተፈናቃዮች ጉዳይ “ዳግም አጀንዳ ሆኖ እንዲነሳ” ለማድረግ ነበር።
የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር ጌታቸው ግን ከህወሓት አመራሮች ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚገለጸው “የአሥመራ መንግሥት፤ በፍጹም ምዕራብ ትግራይ ተመልሶ፣ ከሱዳን ጋር መገናኘት የሚለውን የሚፈልገው ሴናሪዮ አይደለም” ይላሉ።
የህወሓት አመራሮችም “ሻዕቢያ የፈለገውን ይበል እኛ ይሄንን እናደርጋለን ብለው የሚሄዱ አይመስለኝም” ሲሉ ምልከታቸውን ገልጸዋል። ከፌደራል መንግሥት ጋር “የገቡበት ችግር አለ፤ ችግራቸውን መንቀስ የሚፈልጉ ይመስለኛል” ሲሉም ተጨማሪ ምክንያት ይጠቅሳሉ።
የሕገ መንግሥት እና የፖለቲካ ባለሙያው ዶ/ር አደም ምልከታ ከዚህ የተለየ ነው። የህወሓት አመራሮች “ወደ ጦርነት እንዲገቡ በሱዳን እና በግብፅ ምናልባት በኤርትራ በኩልም ጫና ሊሆንባቸው ይችላል” ይላሉ።
የህወሓት አመራሮች ከእነዚህ አገራት ጋር ግንኙት እንዳላቸው በይፋ አልገለጹም። ይሁን እንጂ የህወሓት ኃይሎች እና የኤርትራ መንግሥት “ጽምዶ” በሚል በሚጠራው ጥምረት አማካኝነት ቅንጅት መፍጠራቸው ከሁለቱም አካላት ጋር ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን እና ደፊዎቻቸው ይናገራሉ።
በቅርቡ ደግሞ በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖችን እንደወከሉ የተገለጹ ግለሰቦች በተገኙበት በዚሁ “ጽምዶ” በሚል ስያሜ ሱዳን ውስጥ ዝግጅት ተካሂዷል። ከሱዳን እና ኤርትራ እንደሆኑ የተገለጹ ግለሰቦች ፖርት ሱዳን ውስጥ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ንግግር አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ ይህንን ጥምረት “‘ወደ መሬት እናወርዳለን’ ብለው ስንዝር እንቅስቃሴ” የሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።
ዶ/ር አደም እንደሚናገሩት የአወዛጋቢዎቹ ግዛቶች ጉዳይ እንቅፋት ሊሆን ቢችልም፤ የህወሓት አመራሮች ከፋኖ ኃይሎች ጋር “ቅንጅት ሊፈጥሩ” የሚችሉበት ዕድል ዝግ አይደለም።
ህወሓት የክልሉን ሥልጣን የመቆጣጠር እርምጃ የወሰደው “በቆየን ቁጥር ድክመታችን እየሰፋ ነው፤ ነገሮች መለወጥ አለባቸው” ከሚል አቋም እንደሆነ ዶ/ር አደም ያስረዳሉ።
“የመተኮስ ጫናው ያለው ህወሓት ላይ ነው። ምክንያቱም በበጀትም፣ በነዳጅም፣ በመሬቱም ጉዳይ በሁሉም ቦታ፣ በፍትሕ ጉዳይም [በሰላማዊ መንገድ] ‘አመጣለሁ’ የሚለው ነገር ሊሆን አይችልም። በምንም በምንም መልኩ ፌደራል መንግሥቱ የሚፈልገውን በፈቃደኝነት የሚያደርግለት አይመስለኝም” ብለዋል።
“ድርድር ይደረጋል፤ ስምምነት ላይ ይደረሳል”
ሁለቱም ተንታኞች ‘ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል’ የሚለውን ሙሉ በሙሉ ከግምት ውጪ ባያደርጉትም፤ የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው የሚል ግምገማ አላቸው።
የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎችን ጦርነት በገታው የፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ተደራዳሪዎቹ አካላት ፖለቲካዊ ንግግር እንዲያደርጉ ይጠበቅ ነበር። አሁን በድጋሚ ለድርድር የሚቀመጡ ከሆነ ህወሓት “ፈርሷል” ባለው በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ሊካሄድ ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ የሚነሳበት ነጥብ ነው።
በራሳቸው ለድርድር ይቀመጣሉ ወይስ አሸማጋይ ይኖራል? የሚለውም ሌላኛው ጥያቄ ነው። ከፕሪቶሪያ ስምምነት አደራዳሪዎች አንዱ የነበሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ኅብረት “በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፉ” ግንቦት 6 ቀን ተሹመዋል።
ዶ/ር ጌታቸው ግን የንግግር ጉዳይ የሚነሳ ከሆነ “አሜሪካ ነች የምታደራድረው ብዬ ነው የማምነው” ይላሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘም ከሰሞኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞትዮስ ወደ አሜሪካ ያደረጉት ጉብኝት ጠቅሰዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ግንቦት 3 ቀን ዶ/ር ጌዲዮን ጋር በተገናኙነት ወቅት፤ “ኢትዮጵያ በመላው ምሥራቅ አፍሪካ ግጭቶችን ለመፍታት እና ለማርገብ ስላላት ወሳኝ ሚና” መነጋገራቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል።
ዶ/ር ጌታቸው ከአሜሪካ ጋር የተደረጉት ግንኙነቶች “ታሳቢ የሚያደርጉት የቀጣናውን መረጋጋት ነው” ብለዋል።
ከአሜሪካ በኩል እየመጣ ያለው “አንድ መልዕክት ብቻ አይደለም፤ ብዙ በጣም የተዘበራረቀ ነው” የሚሉት ዶ/ር አደም በአንጻሩ የዋሽንግተን አሸማጋይነት ላይ ብዙም ተስፋ የላቸውም።
“ሁለቱም አካላት ለአንዱ ሊሰጡት የሚችሉት፤ እስካሁን ድረስ ያላደረጉት ነገር የለም” ሲሉም ስምምነት ሊደረስ የሚችልበት መንገድ “ግራ አጋቢ” መሆኑን ይገልጻሉ።
ዶ/ር አደም፤ “ስምምነት ከተባለ ቢያንስ ቢያንስ ህወሓትን [በፓርቲነት] መመዝገብ እና በፌደራል በኩል በጀቶችን የመልቀቅ ነገር መኖር ይኖርበታል። ህወሓትም ደግሞ በተለይ ከኤርትራ እና ከሌሎች አካላቶቻቸው ጋር የሚያደርገውን ነገር መቀየር ይኖርበታል” ይላሉ።
አሁን በሁለቱ አካላት መካከል ያለው “የእምነት ማጣት” ግን ይህንን ለማድረግ የማስቻል ዕድሉ “ዝቅተኛ” መሆኑ ያነሳሉ።
ዶ/ር ጌታቸው በበኩላቸው አሁን የትግራይ ክልል ሥልጣንን የተቆጣጠረው ህወሓት “የሚፈልገውን” ስላደረገ፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲቀበለው እና እንዲያጸድቅለት” ይፈልጋል የሚል እምነት አላቸው። “የፌደራል መንግሥት ወደ ድርድር የሚገባ ከሆነ ደግሞ [የህወሓትን ፍላጎት] እንዳለ ይቀበለዋል ብዬ አላስብም” ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ጌታቸው ገለጻ ድርድር የመካሄዱን ጉዳይ የሚወስነው “እነ አሜሪካ ትግራይን በተመለከተ እስከምን ድረስ ነው የሚሄዱት?” በሚለው ላይ ነው።
