ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ምያንማር

ታትሟል26 ግንቦት 2026, 07:01 EAT

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ሚን፤ በምያንማር የሚገኘውን አነስተኛ ካፌውን እየከፈተ ነው። በፀሐይ ብርሃን የሚሠራውን መስመር እያስተሳሰረ የፕላስቲክ ወንበሮችን ይዘረጋል።

ሚን (ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ ተለውጧል) ደንበኞቹን ይጠባበቃል። በካፌው የሥጋ እና የአትክልት ዋጋ ዝርዝር ቀርቧል።

ደንበኞቹ ኢንተርኔት ለመጠቀም ሲሉ በካፌው ውስጥ ዘለግ ላለ ሰዓት እንደሚቆዩ ያውቃል።

በየቀኑ ቢያንስ 30 ደንበኞች ያስተናግዳል። ካፌውን የከፈተው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር።

በወቅቱ የኢንተርኔት ካፌዎች ብዙም ስላልተለመዱ በየቀኑ ከ300 እስከ 400 ሰዎች ያስተናግድ እንደነበር ያስታውሳል። “ያኔ ከፍተኛ ፍላጎት ነበር” ይላል።

በአውሮፓውያኑ 2021 በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው ምያንማርን የሚመራው ጁንታ የኢንተርኔት ገደብ ጥሏል።

ለአምስ ዓመት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ኢንተርኔት ለቀናት ወይም ለወራት ሲቋረጥ ነበር።

በ2022 የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ባወጡት መረጃ መሠረት የምያንማር መሪዎች ኢንተርኔት የሚያቋርጡት ተቃውሞ ይገጥመናል ብለው በሚያስቡት አካባቢ ነው።

ሚን ኢንተርኔት ላይ የተጣለውን ገደብ ማለፍ የሚቻልበት መንገድ ላይ አተኩሮ ይሠራል። የኤለን መስክ ስፔስኤክስ ኩባንያ የዘረጋውን ስታርሊንክ መጠቀም ዋነኛው መንገድ ነው።

በአገር ውስጥ ኢንተርኔት ቢዘጋም በስታርሊንክ አማካኝነት አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል።

ይሄንን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልገውን መገልገያ ከታይላንድ በጥቁር ገበያ ይገዛል። ከዚያም ወደ ምያንማር በድንበር በኩል በድብቅ ይገባል።

ሚን ንግዱ ለኪሳራ እንደዳረገው ይናገራል። በአንድ ሰዓት 1,000 ኪያት (የአገሩ ገንዘብ) ወይንም 0.25 ዶላር ያስከፍላል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እና ተፈናቃዮች ከዚህ በላይ መክፈል አይችሉም።

የኢንተርኔት ካፌ መክፈት ለአደጋ ያጋልጣል። እንዲህ ያለ ንግድ ክልክል ከመሆኑም በላይ ለእስራት ይዳርጋል። መገልገያዎችም ይወረሳሉ።

ካፌው በቀን ለሦስት ሰዓት ብቻ ክፍት ይሆናል። የመብራት አቅቦት ውስንነት አገልግሎቱን ይወስናል።

አካባቢውን የሚቆጣጠሩት የጁንታው ተቀናቃኞች ናቸው። ሆኖም መሪዎቹ የስታርሊንክ ዲሽ ወይም ከፀሐይ ኃይል ማመንጫ መስመርን አይተው ወደ ካፌው ሊሄዱ ይችላሉ።

በኩባያው ላይ የኢንተርኔት ዋጋ ተጠቅሷል
የምስሉ መግለጫ,በኩባያው ላይ የኢንተርኔት ዋጋ ተጠቅሷል

የካፌውን ቦታ ሁለት ጊዜ በድብቅ ቀይሯል። አሁንም ግን ልያዝ እችላለሁ ብሎ ይፈራል።

የዲጂታል መብት ተቋም የሆነው ምያንማር ኢንተርኔት ፕሮጀክት እንደሚለው ከጥር 2021 አንስቶ 450 ጊዜ ኢንተርኔት ተቋርጧል። ይህም ከ20 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ጫና አሳድሯል።

ተቋሙ በጁንታው የሚደርስ ጥቃትን ከኢንተርኔት መቋረጥ ጋር በማዛመድ መረጃ ይሰበስባል።

በተቋሙ የዲጂታል መብት ተንታኝ ኒያን (ስሟ ተለውጧል) “በጥናታችን መሠረት ወደ 90% የሚደርሰው የኢንተርኔት መቋረጥ ከጥቃት ጋር ይገናኛል። መረጃ እንዳይወጣ በማፈን አካባቢው ላይ ውድመት ያደርሳሉ” ይላሉ።

በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረጋል። የምያንማር ዜጎች ያለ መንግሥት ፈቃድ ቪፒኤን መጠቀምም ሆነ አገልግሎቱን ማቅረብ አይፈቀድላቸውም።

የተጠቃሚዎችን ቦታ እና አድራሻ በመሸሸግ ኢንተርኔት ለማግኘት የሚውለው ቪፒኤን ለብዙዎች ሁነኛ አማራጭ ነው።

በምያንማር ታጣቂ የመንግሥት ተቀናቃኞችም የኢንተርኔት አቅርቦትን ያስተጓጉላሉ።

በሚቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በስታርሊንክ ላይ ጊዜያዊ እገዳ ይጥላሉ። አንዳንዴም የግንኙነት መስመሮች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ።

ሚክ ካፌ በፀሐይ የሚሠራ ኃይል ማመንጫ ዘርግቷል
የምስሉ መግለጫ,ሚክ ካፌ በፀሐይ የሚሠራ ኃይል ማመንጫ ዘርግቷል

እየተባባሰ የመጣው የኢንተርኔት መዘጋት

የሚን ካፌ አነስተኛ ነው። ነገር ግን በመላው ዓለም በአምባገነን መሪዎች የተጣለ የኢንተርኔት እገዳን ለማለፍ የሚሞክሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

ለዲጂታል መብት የሚታገለው ዓለም አቀፍ ተቋም አክሰስ ናው እንደሚለው ከአውሮፓውያኑ 2020 ወዲህ ኢንተርኔትን መዝጋት እየተባባሰ መጥቷል።

በ2025 ከመቼው ዓመት በበለጠ የኢንተርኔት መቋረጥ ተመዝግቧል። በ52 አገራት 313 የኢንተርኔት መዘጋት ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ 95 የሚደርሰው በምያንማር ነው።

በ2025 ብቻ አክሰስ ናው በፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ቴሌግራም እና ኤክስ 94 የኢንተርኔት መቋረጥ መዝግቧል።

የኢንተርኔር መቋረጥን መመዝገብ ከጀመረበት 2016 አንስቶ ቁጥሩ በሦስት እጥፍ ጨምሯል።

ከምያንማር በአንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በማድሪድ የሚኖረው አንድሬዝ አዝፑራ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ቡድንን ይመራል።

አዥፑራ ተወልዶ ያደረገው ቬንዙዌላ ነው። የሚመራው ቡድን የኢንተርኔት መዘጋትን ማለፍ የሚችል መተግበሪያ ሠርቷል።

አዝፑራ በማድሪድ፤ በ2024
የምስሉ መግለጫ,አዝፑራ በማድሪድ፤ በ2024

የቬንዙዌላ መገናኛ ብዙኃን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የወደቁ ናቸው። ገለልተኛ ሚዲያ ላይ ከተጣለው ክልከላ ባሻገር እንደ ኤክስ እና ፌስቡክ ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲሁም እንደ ዋል ስትሪት ጆርናል ያሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም ዕገዳ ይጣልባቸዋል።

አዝፑራ የሚመራው ቡድን የሠራው ‘ኖቲሲስ ሲን ፊልትሮ’ የተባለው መተግበሪያ በቪፒኤን የሚሠራ ሲሆን፤ ገለልተኛ ለሆኑ የቬንዝዌላ እንዲሁም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ነጻ አገልግሎት ይሰጣል።

አዝፑራ እንደሚለው መተግበሪያው ቪፒኤን በቬንዙዌላ የተሻለ ተደራሽ እንዲሆን ይረዳል።

“መመዝገብ ወይም መክፈል ሳያስፈልግ ዜና ማግኘት ይቻላል” ሲል ያስረዳል።

በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2024 ከተካሄደው አወዛጋቢ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት ነበር መተግበሪያው ወደ ሥራ የገባው። መተግበሪያው 140 ሺህ ጊዜ ተጭኗል።

የዲጂታል መብት አቀንቃኙ ባለሙያ እስራትን በመሸሽ ከአገሩ ቬንዙዌላ የወጣው አምና ነው።

“ሊይዙኝ እየሞከሩ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ” ይላል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በአሜሪካ ከተያዙ በኋላ በቬንዙዌላ የፖለቲካ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብለው ያመኑ በርካቶች ደስታቸውን ሲገልጹ ታይቷል።

ሆኖም ሥልጣኑን የተረከቡት ደልሲ ሮድሪጌዝ የመገናኛ ብዙኃንን አፈና እንዳላስወገዱ አዝፑራ ይናገራል።

“መተግበሪያው የተሠራው በበጎ ፈቃደኞች እና በለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ ነው። መረጃ የማግኘት እና የንግግር ነጻነትን ጨምሮ ለሰብአዊ መብት መከበር ድጋፍ የሚሰጥ ነው” ሲል ይገልጻል።

ወደ ታይላንድ በድብቅ የገባው ስታርሊንክ
የምስሉ መግለጫ,ወደ ታይላንድ በድብቅ የገባው ስታርሊንክ

የቻይና የመረጃ ክልከላ

ኢኮ (ስሙን ተለወጧል) በቻይና የተጣለውን ሁለንተናዊ የመረጃ እገዳ ከሚታገሉ አንዱ ነው።

ግሬት ፋየርዎል ቻይና (Great Firewall of China) በሚል ስያሜ የሚታወቀው እገዳ የቻይና መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚገድብበት ነው።

በቻይና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች እና መረጃ ማሰሻ መተግበሪያዎች ታግደዋል።

ቻይና ውስጥ መጠቀም የሚቻለው መንግሥት የሚቆጣጠራቸው መተግበሪያዎች (ዊቻት እና ዌቦ) ነው።

የቀድሞው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ኢኮ ከቻይና ከወጣ 10 ዓመት አልፏል።

ቻይና ያሉ ሰዎች እገዳ የተጣለባቸውን እንደ ጉግል፣ ዩቲዩብ እና ፌስቡክ ያሉ ገጾች መጠቀም የሚችሉበት መተግበሪያ ሠርቷል።

ቻይና ከሚገኝ አጋር ተቋም ጋር የሚሠራ ሲሆን፣ እንቅስቃሴው እንዳይታወቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል።

“ቻይና ውስጥ ሰዎች ኢንተርኔትን በነጻነት እንዲጠቀሙ ማገዝ የሚያሳስር ተግባር ነው” ይላል።

የኢኮ መተግበሪያ የሚሠራው በነጻ ነው። ወጪውን ለመሸፈን መተግበሪያውን በክፍያ የመጠቀም አማራጭ ዘርግቷል።

በቻይና ሳንሱር ዋነኛው ፈተና እንደሆነ ይናገራል። እንደ እሱ ያሉ መተግበሪያ ሠሪዎች አንዳንዴ ቢሳካላቸውም የሚሰናከሉበትም ጊዜ እንዳለ ያስረዳል።

ካለፈው ታኅሣሥ አንስቶ የኢንተርኔት አቀርቦት በተቋረጠባት ኢራን ውስጥም አገልግሎቱን ይሰጣል።

በሕዝባዊ አመጽ ምክንያት የተዘጋው ኢንተርኔት አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት በከፈቱበት ወቅትም ቀጥሏል።

ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው ‘አርቲክል 19’ የመብት ተሟጋች ቡድን እንደሚለው ኢራን የቴክኖሎጂ አፈና ለማድረግ ቻይና የምትከተለውን አሠራር ተግብራለች።

የምያንማር፣ ቬንዙዌላ እና ቻይና መንግሥታት ስለ ኢንተርኔት ገደብ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም። ከዚህ ቀደም ግን የደኅንነት እና አለመረጋጋት ጉዳይን እንደ ምክንያት አቅርበዋል።

የምያንማር ጁንታ በ2021 ፌስቡክን ሲያግድ “ሐሰተኛ መረጃን ለመግታት ነው” ብሏል።

ማዱሮ በበኩላቸው አንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያዎች “ጥላቻን ለማሠራጨት” እየዋሉ ነው ብለዋል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ደግሞ “የኢንተርኔት ምስቅልቅል ሕዝብን ይጎዳል” ሲሉ ተናግረዋል።

በምያንማር የሚንን ካፌ ከሚጠቀሙ አንዷ የሆነች የ27 ዓመት ሴት “ኢንተርኔት ሲቋረጥ ሁሉም የሕይወት ዘርፍ ላይ ጫና አለው። የዕለት ከዕለት ሕይወት፣ ምጣኔ ሃብት እና የቤተሰብ ትስስርን ጨምሮ” ብላለች።

ኢንተርኔት ሲቋረጥ የስልክ አገልግሎት አስተማማኝ ባልሆነበት ቦታ ከሚኖሩ ዘመዶቿ ጋር መገናኘት አለመቻሏን ትናገራለች።

“ግንኙነታችን በአጠቃላይ ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ” ትላለች።

ኢንተርኔት ለማግኘት አንድ ሰዓት መጓዝ ይጠበቅባታል።

ሌላዋ የ25 ዓመት ሴት ስታርሊንክ ያለበትን ካፌ ለማግኘት እስከ 2 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንዳለባት ትገልጻለች።

“እኛ ወጣቶች አገራችንን ማሳደግ ቢጠበቅብንም ኢንተርኔት ሲቋረጥ ምንም መሥራት አንችልም። እንደ እኔ ያሉ ወጣቶች የወደፊት ሕይወታችን ወደ ጨለማ እየተገፋ ነው።”