
ታትሟልከ 8 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
መካከለኛው ምሥራቅ በኢራን ጦርነት የተነሳ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ቢሆንም፤ ከመላው ዓለም የተወጣጡ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለዓመታዊው የሐጅ ጉዞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገቡ።
1.51 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ከሳዑዲ ውጪ ከሆኑ አካባቢዎች መምጣታቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል።
ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ11,000 ይጨምራል። ሙስሊሞች ለሃይማኖታዊው ጉዞ ወደ ሳዑዲ የደረሱት ሦስት ወር ሊደፍን የተቃረበው የአሜሪካ፣ እስራኤል እና ኢራን ጦርነት በድጋሚ ሊጀምር ይችላል የሚል ስጋት በቀጣናው ባረበበበት ወቅት ነው።
ደካማ የሆነው ተኩስ አቁም ባለፈው ወር ተግባራዊ መሆን ከመጀመሩ በፊት፤ ኢራን በርካታ ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት አስወንጭፋለች። ቴህራን እነዚህ ጥቃቶች የፈጸመችው አሜሪካ እና እስራኤል ላደረሱባት አየር ድብደባ በአጸፋ ምላሽነት ነው።
ኢራን መጋቢት ላይ በፕሪንስ ሱልጣን አየር ኃይል ጦር ሰፈር አቅራቢያ በፈጸመችው ጥቃት ከሜሪካ ወታደሮች በተጨማሪ ሁለት ንጹኃን ተገድለዋል።
የሳዑዲ መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ በለቀቀው ቪዲዮ፤ ከቅድስት ከተማዋ መካ ወጣ ያለ አካባቢ ላይ የአየር መከላከያ መሣሪያዎች መስፈራቸውን አሳይቷል።
“የአየር መከላከያ ኃይሎቹ የቅዱስ ስፍራዎችን ሰማይ በመጠበቅ እንዲሁም ሁሉንም የአየር ስጋቶች በመመከት የእንግዶችን ደኅንነት እና የአዕምሮ ሰላም የማረጋገጥ ኃላፊነት አላባቸው” ብሏል።
ከተጓዦቹ መካከል የሆነው በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኛው ግብጻዊው ሞሐመድ ቻሃዳ አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለው።
“ኢራን ውስጥ ያለው ጦርነት መላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።ማንም ሰው በሌሎች አገራት እና ሕዝቦች ላይ ጦርነት ወይም ጉዳት እንዲደርስ አይፈልግም” ሲሉ ለዜና ወኪሉ ኤኤፍፒ ተናግሯል።
ሌሎች ተጓዦች በበኩላቸው ለወራት ከዘለቀ እርግጠኝነት ማጣት፣ የአየር በረራ መቋረጥ እና የጉዞ ዋጋ መናር በኋላ ሳዑዲ አረቢያ መግባት በመቻላቸው ደስተኛ ናቸው።
የ68 ዓመቱ ሞሮኳዊ ጄሪሽ ሞሐመድ በበኩላቸው “በሕይወቴን በሙሉ ለ40 ወይም 50 ዓመታት ይህንን ጉዞ ለማድረግ ስፈልግ ነበር። በዚህ ዓመት ሕልሜ እውን ሆነ” ብለዋል።
ሐጅ ከእስልምና አምስት አምዶች መካከል አንዱ ሲሆን የሚደረገውን በእስልምና የጨረቃ ካላንደር መሠረት በ12ተኛው ወር ነው።
የገንዘብ አቅም እና አካላዊ ብቃት ያለው እያንዳንዱ አዋቂ ሙስሊም በሙሉ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ ሊያደርገው የሚገባ ተግባር ነው።
የዘንድሮ ሐጅ አድራጊዎች በጉዞው የመጀመሪያ ቀን በመካ ወደሚገኘው ታላቁ መስጊድ በሚያመሩበት እንዲሁም ካዕባን ሰባት ጊዜ በመዞር ሃይማኖታዊ ስርዓት በሚፈጽሙበት ጊዜ የአገሪቱን 45 ዲግሪ ሴልሺየስ ሙቀት ለመቋቋም ተገድደዋል።
ቀጥሎም 5 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ሚና የተጓዙ ሲሆን በዚያም ምሽቱን ድንኳን ውስጥ ያሳልፋሉ። ቀጣዩ መዳረሻ ነቢዩ መሐመድ የመጨረሻ ትምህርታቸውን እንደሰጡበት የሚነገረው አረፋት ተራራ ነው። በተራራው ላይ ለአንድ ቀን የሚደረገው ጸሎት የሐጅ ጉዞ ማጠቃለያ ተደርጎ ይወሰዳል።
