ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የጨረቃ ሰሜን ንፍቀ ክበብ ላይ ቅኝት የሚያደርግ መሣሪያ

ታትሟልከ 4 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ናሳ በጨረቃ ወደፊት ለሚገነባው ቋሚ የምርምር ማዕከል የሚያገለግሉ ሮቦቶችን እና ማሽኖችን ይፋ አደረገ።

መሣሪያዎቹን ለመገንባት ከተመረጡት መካከል የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ የኅዋ ኩባንያ ‘ብሉ ኦሪጅን’ አንዱ ነው።

የአሜሪካ ኅዋ ተመራማሪዎች ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እአአ በ2029 ከሥልጣን ከመነሳታቸው በፊት ወደ ጨረቃ ዳግም መመለስ ይፈልጋሉ።

ነገር ግን ናሳ ወደ ጨረቃ ለመመለስ ከቻይና ጋር ፉክክር እያደረገ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።

ቻይና እአአ በ2030 ጠፈረተኞቿን ጨረቃ ላይ ለማሳረፍ አቅዳ እየሰራች ነው።

ሰኞ ዕለት ቻይና ሼንዙ-23 የተባለ መንኮራኩር ወደ ቲያንጎንግ የኅዋ ጣቢያ ጠፈረተኞችን ይዞ የተጓዘ መንኮራኩርን ይፋ አድርጋለች።

በመጋቢት ወር ናሳ እአአ በ2032 በጨረቃ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በኒውክለር እና የፀሀይ ኃይል የሚታገዝ ቋሚ ሠፈር ለመገንባት የ20 ቢሊዮን ፕሮግራም ይፋ አድርጎ ነበር።

የናሳ አስተዳዳሪ ጃሬድ አይዛክማን ማክሰኞ ዕለት የዕቅዱን ይፋ መሆን አስመልከትው ሲናገሩ አሜሪካ “ጨረቃ ላይ ዳግም ተስፋ አትቆርጥም” ብለዋል።

ሠፈሩ አሜሪካ ሳይንሳዊ ሙከራዎቸን በተለይ ደግሞ ጠቃሚ የማዕድናት ሃብቶችን ፍለጋ የምታካሄድ ሲሆን እንዲሁም ወደ ማርስ የሚደረገውን ጉዞ የበለጠ ቀላል ያደርገዋል ተብሏል።

ነገር ግን በርካታ ባለሙያዎቸ የናሳ የጊዜ ሰሌዳን ከእውነታው ጋር ይጣረሳል ሲሉ ተችተዋል።

በሚያዚያ ወር ከፍሎሪዳ የተነሳው መንኮራኩር ለ24 ሰዓታት በምሕዋር ዙሪያ ሲሽከረከር ቆይቶ ወደ ጨረቃ ስኬታማ ጉዞ አድርጓል።

የአርቴሚስ 2 ተልዕኮ (Artemis II mission) የሰው ልጆችን ከአፖሎ 17 (Apollo 17) ወዲህ ወደ ጨርቃ መልሶ በመውሰድ ታሪካዊ ጉዞ ተብሏል።

አራት የናሳ ጠፈርተኞችን የያዘው ይህ መንኮራኩር ከፍሎሪዳ ሲነሳ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በርካታ ሰዎች ተከታትለውታል።

በኦፕን ዩኒቨርስቲ የኅዋ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሳይመን ባርበር የሰው ልጅን ጨረቃ ላይ ለማስቀመጥ የሚረዳ መሣሪያ ላይ ያለውን ክፍተት ግምት ውስጥ በማስገባት “ቻይና ቀድማ እዚያ ብትደርስ አልገርምም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የናሳ ወደ ጨረቃ የሚያደርገው ጉዞ በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው።

የሰው ልጅ ወደ ጨረቃ ከመጓዙ በፊት ናሳ አስቀድሞ የአካባቢው አስቸጋሪ መልክዓ ምድር ለመፈተሽ ሮቦቶችን መላክ ይፈልጋል።

ሳይንቲስቶችን እና የተለያዩ ሳይንሳዊ መሳሪያዎችን የሚሸከሙ ተሽከርካሪዎችንም የመላክ ሃሳብ አለ።

ማክሰኞ ዕለት ብሉ ኦሪጅን፣ ኢንቲውቲቭ ማሺን እና አስትሮቦቲክ የተባሉ ከባንያዎች ናሳ ወደ ጨረቃ ለመሄድ የሚያስለፍጉትን ማሽኖች እንዲገነቡ ኮንትራት ተሰጥቷቸዋል።

ከዚህ ቀደም የኤለን መስክ ኩባንያ ስፔስኤክስ ወደ ጨረቃ ለመጓዝ የሚያገለግሉ ማሽኖችን እንዲገነባ ቢደረግም በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውታል።