
ታትሟልከ 6 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ
በየካቲት ወር መጨረሻ ሳምንት ላይ የኢራን ጦርነት ሲቀሰቀስ ወላፈኑ የተሰማው በመካከለኛው ምሥራቅ ብቻ አልነበረም።
ግጭቱ የንግድ መርከቦች እና ሸቀጦች ፍሰትን ሲያስተጓጉል የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንዲንር እና የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር በማድረግ የዓለም ገበያን አናግቷል።
እንዲህ እርግጠኝነት በሚጠፋበት ወቅት የዓለማችን የናጠጡ ሃብታሞች አዋጭ ካልሆኑ ንግዶች ፊታቸውን ማዞር እንዲሁም ሃብታቸውን በዶላር ወደማስቀመጥ ይዞራሉ።
ይህ ደግሞ በበርካታ መገበያያ ገንዘቦች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ቀድሞ ይዋዥቁ የነበሩ አንዳንድ ገንዘቦች ዋጋቸው ሲያሽቆለቁል ጥቂቶች ደግሞ በነበሩበት ጸንተው ወይንም ጥንካሬያቸው ጨምሮ ይገኛል።
ብራዚላዊው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አንድሬ ፐርፌይቶ የነዳጅ ዋጋ “ሁሉንም በሚነካበት ወቅት የምንዛሬ ዋጋ መዋዠቅ የበለጠ ይከሰታል ወይም ይባባሳል” ይላሉ።
ስለዚህ ይህ ከሌሎች ኢኮኖሚውን ከሚጎዱ ጉዳዮች ጋር ሲደማመር ለአገራት እና ለዜጎች ምን ማለት ይሆናል?
በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱት

በርካታ እንደ ነዳጅ ያሉ የኢነርጂ ፍጆታቸውን ከውጪ የሚያስገቡ አገራት የገንዘብ የመግዛት አቅማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል።
ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ፊሊፒንስ፣ ታይላንድ እና ግብፅ በከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተጎዱ አገራት ናቸው።
ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ወደ ዶላር በሚቀይሩበት ወቅት የአገራቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም እየወደቀ ዕዳ በዶላር የሚከፈልበት መጠን እየጨመረ ይመጣል።
የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ በዶላር ግብይት የሚፈጸምባቸው ነዳጅ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ዋጋቸው እየጨመረ መጥቷል።
የአገራቱ ገንዘብ የመግዛት አቅም ሲዳከም ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ዋጋ እየጨመረ ከኢነርጂ እስከ ፕላስቲክ እነዲሁም ማዳበሪያ ድረስ ጭማሪ እያሳዩ ነው። ይህም በምግብ እና በሌሎች የፍጆታዎች ዕቃዎች ላይ ተጽዕኖው የከፋ ነው።
በሕንድ ከኢራን ጦርነት ጀምሮ የአገሪቱ ገንዘብ (ሩፒ) የመግዛት አቅም ከዶላር አንጻር ሲወዳደር በ5 በመቶ ቀንሷል።
የሕንድ መገበያያ ገንዘብ ከጦርነቱ በፊትም ቢሆን ደካማ የነበረ ሲሆን፣ ግጭቱ ደግሞ የበለጠ አባብሶታል።
የተወሰኑ ማዕከላዊ ባንኮች የወለድ ምጣኔያቸውን ከፍ በማድረግ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ የመጠባበቂያ ሰነዳቸውን በዶላር ሸጠው ጉድለታቸውን ለማካካስ ሞክረዋል።
የኢንዶኔዢያ ባንክ በተደጋጋሚ ዶላር በመሸጥ የራሱን ገንዘብ በመግዛት ፍላጎቶችን ለመጨመር ሞክሯል።
የወለድ ምጣኔ ሲጨምር ሰዎች ላስቀመጡት ገንዘብ ከፍ ያለ ገንዘብ ያገኛሉ፤ ነገር ግን የመኖሪያ ቤት ግዢ ብድር እና ሌሎች ብድሮች ላይም ከፍተኛ የክፍያ መጠን ያስከትላል።
የገበያ መዋዠቅ እና ጭማሪ ማሳየት

አንዳንድ ገንዘቦች በሁለት አቅጣጫ መዋዠቅ አሳይተዋል።
እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኮሎምቢያ፣ ቺሊ እና ሜክሲኮ ያሉ አገራት በዚህ ምድብ ውስጥ ይወድቃሉ።
እነዚህ ገንዘቦች ብዙውን ጊዜ ለዓለም አቀፍ ገበያ ጠንካራ ምላሽ ይሰጣሉ። ባለሀብቶቻቸው ወደ ዶላር ሄደው ሲሸሸጉ ይዳከማሉ፤ ነገር ግን የሸቀጦች ዋጋ ሲጨምር ወይም ለአደጋ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት ሲኖር በፍጥነት አቅማቸው ሊሻሻል ይችላል።
ብራዚልን እና ማሌዢያን ጨምሮ አንዳንድ የኢነርጂ ላኪዎች በከፊል ከነዳጅ ዋጋ መጨመር ተጠቃሚ ሆነዋል። ይህም ከኤክስፖርት የሚገኝ ገቢን ከፍ ሲያደርግ የባለሀብቶችን ፍላጎት አግዟል።
ባንኮች፣ ጎልድማን ሳክስ እና ባንክ ኦፍ አሜሪካን ጨምሮ በሚያዝያ ወር ለደንበኞች በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ የብራዚል የመንግሥት ቦንዶች እና የኩባንያ አክሲዮኖች ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።
ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም የላቲን አሜሪካ ምርምር ኃላፊ ማርቲን ካስቴላኖ እንደሚሉት፣ ከፍተኛ የኢነርጂ ዋጋ በብራዚል የዋጋ ግሽበትን ሊያባብስ፣ የወለድ መጠን ቅነሳን ሊያዘገይ እና የካፒታል ፍሰትን ሊጎዳ ይችላል።
ብራዚል እንደ ቤንዚን እና ናፍጣ ያሉ ምርቶችን ከውጭ ስለምታስገባ የነዳጅ ዋጋን በአገር ውስጥ እንዲጨምር አድርጓል።

የብራዚል የኢንቨስትመንት አስተዳደር ኩባንያ፣ ኤክስፒ ኢኮኖሚስት ሉዊዛ ፒኔዝ በቅርቡ ባወጡት ሪፖርት ላይ በተጨማሪም በጥቅምት ወር ከሚካሄደው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት የፖለቲካ አለመረጋጋት “የምንዛሪ ተመን ላይ ያለውን ዋጋ ይጨምራል” ሲሉ ጽፈዋል።
የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በተለያዩ ምክንያቶች የበለጠ ጠንካራ ሆነው ቆይተዋል።
የቻይና ምንዛሪ በከፊል በካፒታል ቁጥጥር እና በከፍተኛ መዋዠቅን በሚገድቡ የፖሊሲ ጣልቃ ገብነቶች ድጋፍ ስለተደረገለት በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ሆኖ ቀጥሏል።
እነዚህም ወደ አገር ውስጥ እና ወደ ውጭ በሚዘዋወር ገንዘብ ላይ የተጣሉ ገደቦችን እና የአገሪቱ ገንዘብ የምንዛሪ ተመንን በቅርበት ለማስተዳደር ማዕከላዊ ባንክ ቀጥታ ጣልቃ መግባቱን ያካትታሉ።
የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ከዶላር ጋር ባለው የምንዛሬ ተመን ጥንካሬን ካሳዩ ገንዘቦች መካከል የሩሲያ ገንዘብ (ሩብል) አንዱ ነው።
ይህም ከፍተኛ የነዳጅ ምርቶችን በመላክ የሚገኝ ገቢ እና በጥብቅ የካፒታል ቁጥጥር የተነሳ የተገኘ ሲሆን፣ ላኪዎች ከወጪ ንግድ ያገኙትን ገቢ ወደ ሩብል እንዲቀይሩ እና የገንዘብ ፍሰትን ከአገሪቱ እንዲገድቡ የሚጠይቁ እርምጃዎችን ያካተተ ነው።
ምጣኔ ሃብታቸው ጠንካራ የሆኑ አገራትስ?

ባለሀብቶች ደኅንነትን ሲፈልጉ ገንዘባቸውን የሚያስቀምጡባቸው የውጭ ምንዛሪዎች በቀውሱ መጀመሪያ ላይ ተጠናክረዋል።
የአሜሪካ ዶላር እና የስዊዝ ፍራንክ ሁለቱም ከጦርነቱ በኋላ ጭማሪ አሳይተው የነበረ ሲሆን፣ በኋላም ወደነበሩበት በመመለስ ተረጋግተዋል።
እንደ ኖርዌይ ክሮነር ያሉ ከነዳጅ ዘይት ጋር የተገናኙ ገንዘቦች ከድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይተዋል።
የጃፓን ገንዘብ የን ግን አገሪቱ ከውጭ በምታስገባው ኢነርጂ ላይ በጣም ጥገኛ ስለሆነች ተዳክሟል።
የካናዳ እና የአውስትራሊያ ዶላር እንደ ድፍድፍ ዘይት፣ ጋዝ፣ ብረት፣ እና የድንጋይ ከሰል ያሉ ምርቶችን ወደ ውጭ ስለሚልኩ የበለጠ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ ሆነዋል።
ዩሮ እና የብሪታኒያ ፓውንድም የራሳቸው የሆነ መዋዠቅ አጋጥሟቸዋል፤ ይህም ከፍተኛ የኢነርጂ ወጪ፣ የዋጋ ግሽበት እና በአውሮፓ ውስጥ ያለው የእድገት መቀዛቀዝ ያስከተለው ስጋት ነው።
ቀጥሎ ምን ይሆናል?
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት በኢራን ላይ የተሰነዘረው የመጀመሪያው የአየር ጥቃት ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ወደ ጠንካራ የውጭ ምንዛሪዎች እንዲቀይሩ በማድረግ ዶላርን አጠናክሯል።
ነገር ግን የአሜሪካ ምንዛሪ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተዳክሟል፣ ይህም በማደግ ላይ ያሉ ገበያዎችን ሊያግዝ ይችላል።
“ገንዘብ መበደር ይቀላል፤ እንዲሁም የፋይናነስ ጫናዎችን ይቀንሳል። በማደግ ላይ ያሉ አገራት ምጣኔ ሃብታቸውን ለመደገፍ የወለድ ምጣኔያቸውን ይቀንሳሉ፣ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ አይፈሩም፤ በማደግ ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች ምቹ ሁኔታ ይኖራቸዋል” ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደ ም (ዩኬ) ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ድርጅት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በቅርቡ ባወጡት ሪፖርት ይፋ አድርገዋል።
የበርካታ ታዳጊ አገራት ዕዳ በአሜሪካ ዶላር በመሆኑ እና ዋና ዋና ሸቀጦችም በዶላር ዋጋ ስለሚሸጡ የዶላር ሚና ማዕከላዊ ሆኖ ቀጥሏል።
ይሁን እንጂ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በሚያዝያ ወር በኢራን ጦርነት ምክንያት የሚፈጠሩ መስተጓጎሎች ዓለም አቀፉን ኢኮኖሚ ወደ “መጥፎ” ሁኔታ እየገፋ መሆኑን አስጠንቅቋል፤ ይህም የደካማ እድገት እና የከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ጥምረት ነው።
በዚህ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ሆኖ ስለሚቀጥል፣ የዋጋ ግሽበት ስለማይረጋጋ የዓለም አቀፍ ዕድገት ወደ 2.5 በመቶ ሊወርድ ይችላል፤ የዋጋ ግሽበትም ወደ 5.4 በመቶ ሊጨምር ይችላል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የዓለም የምጣኔ ሀብት እድገት ወደ 2.0 በመቶ የሚወርድበት እና የዋጋ ግሽበት ከ6 በመቶ የሚበልጥበትን ከባድ ሁኔታ ዘርዝሯል። ይህንንም በሐምሌ ወር ትንበያው ላይ እንደገና እንደሚያስተካክል ይጠበቃል።
