ታትሟልከ 4 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
ከዩናይድ ኪንግደም የስለላ ተቋማት ትልቁ የሆነው ‘ጂሲኤችኪው’ (GCHQ) ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከከፈተችበት የአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ 500,000 ሺህ ገደማ ወታደሮቿ ተገድለውባታል አለ።
የተቋሙ ዳይሬክተር አን ኪስት በትለር ይህንን ቁጥር የገለጹት ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉ ይፋዊ ንግግር ነው። በዚህ ንግግራቸው ዩናይትድ ኪንግደም ላይ ስለተደቀኑ ስጋቶች እና ስጋቶቹን ለመጋፈጥ መወሰድ አለባቸው ብለው የሚያምኑባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የስለላ ኃላፊዋ ሩሲያ በመላው ዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን “ያለ ማቋረጥ ዒላማ እያደረገች” መሆኑን ገልጸው፤ ብሪታኒያ “ከባድ ጊዜ” ላይ እንደምትገኝ አስጠንቅቀዋል።
በብሪታኒያ ግዛት ውስጥ ለተፈጸሙ ተከታታይ የስለላ ሴራዎች እንዲሁም በቅርቡ በዩኬ እና በሌሎች የኔቶ አገራት ለተከፈተው በግልጽ ያልታወጀ “ድብልቅ ጦርነት” የሩሲያ መንግሥትን ተጠያቂ አድርገዋል።
ኪዬቭ እና ሞስኮ አንዳቸው የሌላኛቸው ወገን ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በተመለከተ በተከታታይ ቁጥሮችን ሲገልጹ ቆይተዋል። በራሳቸው ወታደሮች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ግን ይፋ አላደረጉም።
ይሁን እንጂ የካቲት ላይ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ፤ አገራቸው ከ2022 አንስቶ 55,000 ወታደሮችን እንዳጣች ተናግረዋል።
የቢቢሲ የሩሲያኛ ቋንቋ አገልግሎት፤ ‘ሜዲያዞና’ ከተሰኘው ገለልተኛ የዜና ምንጭ እና ከበጎ ፈቃደኞች ቡድን ጋር በመሆን ከየካቲት 2022 ወዲህ ሩሲያ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ቆጥሯል።
በተሰበሰበው ዝርዝር ላይ መሞታቸው በይፋዊ መረጃዎች፣ ጋዜጣዎች፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በመቃብር ስፍራዎች አማካኝነት የተረጋገጡ ሰዎች ስም ተመዝግቧል።
ቢቢሲ እስካሁን በዩክሬን ለሩሲያ ሲዋጉ የተገደሉት የ223,539 ወታደሮች እና መኮንኖችን ስም ማረጋገጥ ችሏል። ትክክለኛው የሞት ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ይታመናል።
ቢቢሲ ያማከራቸው ወታደራዊ ባለሙያዎች በመቃብሮች፣ በጦርነት መታሰቢያዎች እንዲሁም ከሰው ሕልፈት በኋላ በታተሙ የህይወት ታሪኮች አማካኝነት የተሰበሰው የቢቢሲ መረጃ ከጠቅላላው የሞቾች ቁጥር ውስጥ የሚወክለው ከ45-65% ያህሉን ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
የስለላ ኃላፊዋ ኪስት በትለር በንግግራቸው፤ “ወሳኝ መሠረተ ልማቶች፣ ዴሞክራሲያዊ ሂደቶች፣ የአቅርቦት ሰንሰለቶች እና የሕዝብ አመኔታን ዒላማ አድርጋለች” ያሏትን ሩሲያን ወቅሰዋል። የሩሲያ መንግሥት እነዚህን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጓል።
ኃላፊዋ አክለው ሩሲያ እና ቻይና ህዋ ላይ ለሰላማዊ እና ወታደራዊ ዓላማዎች ሲባል በከፍተኛ መጠን ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የስለላ መስሪያ ቤቱ፤ የሳይበር ጥቃቶችን ለማስወገድ እንዲሁም “ግድየለሽ የማሰናከል እና የግድያ ሙከራዎች” ሲሉ የገለጿቸውን ድርጊቶችን ለመመከት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
