የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ አሜሪካ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ በቀጣናው የሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈርን መምታቱን አስታወቀ። አብዮታዊ ዘቡ የትኛውን የጦር ሠፈር እንደመታ አልገለጸም። ይሁን እንጂ የአሜሪካ ጦር ሠፈር ያለባት ኩዌት “ጠበኛ የሚሳዔል እና ድሮን ስጋቶችን” ማክሸፏን አስታውቃለች። ከዚህ አስቀድሞ የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የኢራን ድሮንን መትቶ መጣሉን እና በስትራቴጂካዊው የወደብ ከተማ ባንደር አባስ የሚገኝ ወታደራዊ ስፍራ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ከ 28 ደቂቃዎች በፊትአሜሪካ እና ኢራን ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረነዳጅ የሚቀዳ የማደያ ሠራተኛየፎቶው ባለመብት,Hindustan Times via Getty Imagesአሜሪካ እና ኢራን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ተኩስ አቁሙ ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት በመፍጠሩ፤ የነዳጅ ዋጋ በድጋሚ ጨመረ።በዛሬው ዕለት ሦስት ወር የሞላውን ጦርነት ሙሉ ለሙሉ ለመቋጨት የሚያስችል ስምምነት ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይደረሳል የሚል ተስፋ መፈጠሩን ተከትሎ ረቡዕ ዕለት የነዳጅ ቅናሽ አሳይቶ ነበር። የዛሬው ጭማሪ ትናንት የታየውን ቅናሽ ወደ ቦታው የመለሰ ሆኗል።ለዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በጠቋሚነት የሚወሰደው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ የአንድ በርሜል ዋጋ ሐሙስ ንጋት ላይ ዋጋው በ3.75 በመቶ ጨምሮ 97.83 ዶላር ገብቷል። የአሜሪካው ዌስት ቴክሳስ ኢንተርሚዲየት (WTI) ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋም የ4 በመቶ ዕድገት በማሳየት በበርሜል ወደ 92.22 ዶላር አሻቅቧል።የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት የሆነው ጥቃት የተፈጸመው ቴህራን እና ዋሽንግተን ጦርነቱን ለመቋጨት ንግግራቸውን በቀጠሉበት ወቅት ነው። የካቲት ላይ በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተከፈተባት ኢራን በምላሹ የሆርሙዝ ወሽመጥን መዝጋቷ የዓለም የኤነርጂ ገበያ እንዲቃወስ አድርጓል።ከዓለም ነዳጅ እና ወደ ፈሳሽነት የተቀየረ የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ 20 በመቶው ገደማው የሚተለላፈው በዚህ ወሽመጥ ነው።ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የዓለም የኤነርጂ ዋጋ መዋዠቁን ቀጥሏል። ከጦርነቱ በፊት በበርሜል 70 ዶላር ሲሸጥ የነበረው ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ፤ 120 ዶላር የደረሰበት ጊዜም ነበር።ያጋሩ, አሜሪካ እና ኢራን ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ
  2. ከ 3 ሰአት በፊትአሜሪካ፤ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስተዳደር በመሠረተችው አዲስ ተቋም ላይ ማዕቀብ ጣለችበሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዝ መርከብየፎቶው ባለመብት,Reutersየአሜሪካ ግምጃ ቤት ኢራን በሆርሙዝ በኩል የሚደረጉ የባሕር ጉዞዎችን ለመቆጣጠር በቅርቡ ባቋቋመችው “የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለሥልጣን” (Persian Gulf Strait Authority) ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።ግምጃ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ የዚህ መስሪያ ቤት መቋቋም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ከሚያልፉ መርከቦች ገቢ ለመሰብሰብ” የሚያደርገው ሙከራ አካል ነው ብሏል።በዚህም ምክንያት መስሪያ ቤቱ እና “ከተቋሙ ጋር የሚተባበሩ በሙሉ” የማዕቀብ ዝርዝር ውስጥ መግባታቸውን አስታውቋል።የተከፈተባትን ጦርነት ተከትሎ ሆርሙዝ ወሽመጥን የዘጋችው ኢራን፤ ይህንን ተቋም የመሠረተችው አሜሪካ ወደ ወደቦቿ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ እግድ ከጣለች በኋላ ነው።ተቋሙ በወሽመጡ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን የመቆጣጠር እና የማቀናጀል ሥልጣን አለው።ባለ ሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በቲውተር ገጹ ባወጣው ካርታ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኝ “የክትትል ዞን” አሳይቷል። በዚህ ዞን ውስጥ የሚደረግ ጉዞ ከተቋሙ ጋር “መቀናጀት እንደሚያስፈልገውም” አስታውቋል።በዚህ የወሽመጡ ክፍል በኩል ማለፍ የሚፈልጉ መርከቦች ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለሥልጣን ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸውም አሳስቧል።ባለፉት ቀናትም በዚህ የውሃ ክፍል የሚያልፉ መርከቦች በኢራን ኃይሎች ታጅበው እንዲጓዙ ወይም እንዲቆሙ እንደተደረጉ ዘገባዎች አመልክተዋል።ያጋሩ, አሜሪካ፤ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስተዳደር በመሠረተችው አዲስ ተቋም ላይ ማዕቀብ ጣለች
  3. ከ 4 ሰአት በፊትእስራኤል የደቡባዊ ሊባኖስ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አዘዘችየእስራኤል ድብደባ በሊባኖስየፎቶው ባለመብት,AFPየምስሉ መግለጫ,እስራኤል ረቡዕ ዕለት በደቡባዊ ጣይር ከተማ ድብደባዎችን ከፈፀመች በኋላ ወደ ሰማይ የሚጎን ጭስ ታይቷልየእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኝን ግዙፍ ክፍል “የግጭት ዞን” የሚል ምድብ ውስጥ እንዳስገባው በመግለጽ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጠ።የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ነዋሪዎች ከድንበር 40 ኪሎ ሜትር ገደማ በዛህራኒ ወንዝ ሰሜን አቀጣጫ እንዲጓዙ አሳስቧል።ጦሩ እጅግ ከባድ የሆነ የኃይል እርምጃ እንደሚወስድ ያስታወቀ ሲሆን፤ ሄዝቦላህ በተደጋጋሚ የተኩስ አቁሙን ጥሷል በሚል ከስሷል።የተኩስ አቁሙ ከታወጀ ከሚያዚያ መጀመሪያ ወዲህ 14 በመቶ የሚሆነውን የሊባኖስ ግዛት ከሚሸፍነው አካባቢ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ሲጠየቅ ይህ የመጀመሪያው ነው።ረቡዕ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ጣይር ከተማ ድብደባዎችን ፈፅማለች። እስራኤልን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ የሚከስሰው ሄዝቦላህ ተዋጊዎቹ ከእስራኤል ወታደሮች ጋር መጋጨታቸውን ተናግሯል።የረቡዕ ጥቃት የመጣው ሄዝቦላህ በሊባኖስ ግዛት በሚገኙ ወታደሮች እና በሰሜናዊ እስራኤል ንፁሃን ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የምድር ዘመቻቸውን እንደሚያስፋፉ ካስታወቁ በኋላ ነው።ባለፉት 24 ሰዓታት የእስራኤል ጦር ዘጠኝ የአካባቢውን ለቃችሁ ውጡ መመሪያዎችን አውጥቷል። ይህም በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ግዙፍ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት የደቀነ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችንም እንደሚያፈናቅል ተገምቷል።ያጋሩ, እስራኤል የደቡባዊ ሊባኖስ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
  4. ከ 4 ሰአት በፊትየኢራን አብዮታዊ ዘብ በአጸፋ እርምጃ ‘የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈርን’ መምታቱን አስታወቀየአብዮታዊ ዘቡ ፈጣን ጀልባየፎቶው ባለመብት,EPAአሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት ተከትሎ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወሰድኩት ባለው የአጸፋ እርምጃ “የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈርን” መምታቱን አስታወቀ።አሜሪካ ሌሊት ላይ በኢራን የወደብ ከተማ ባንዳር አባስ ውስጥ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ለአየር እና ለባሕር ኃይሏ ስጋት እንደሆኑ የገለጸቻቸውን ወታደራዊ ማዕከላት መምታቷን አስታውቃለች።የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥቃቱ ምንም ጉዳት እንዳላደረሰ በመጥቀስ በምላሹ የአሜሪካ የወረራ ጥቃት መነሻ ነው ባለው የአየር ኃይል ሰፈር ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢራን ዜና ወኪል ታስኒም ይዞት በወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።ይህ ጥቃት የተፈጸመበት ወታደራዊ ማዕከል የት እንደሚገኝ ግን በትክክል አልተገለጸም።የአብዮታዊ ዘቡ ጨምሮም “የጠብ ጫሪነት ጥቃቶች አጸፋ እንደሚሰጣቸው” በማመልከት ጥቃቶች የሚቀጥሉ ከሆነ “የበለጠ ከባድ” ምላሽ እንደሚኖር ገልጿል።ከአብዮታዊ ዘቡ ጋር ቅርብ የሆነው ታስኒም የዜና ወኪል ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ ሌሊት ላይ የፈጸመችው ጥቃት ምንም ነገር በሌለበት ቦታ ላይ መሆኑን እና ፍንዳታውም የተሰማው ከዚያ ጋር የተያያዘ መሆኑን አመልክቷል።ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የራዳር መከታተያውን አጥፍቶ ሊያልፍ የነበረ የአሜሪካ ነዳጅ ጫኝ መርከብን ማስቆሙን ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።ዘገባው እንዳመለከተው የአብዮታዊ ዘቡ ባሕር ኃይል በመርከቡ ላይ ተኩስ ከፍቶ ወደ መጣበት እንዲመለስ ማስገደዱንም ገልጿል።ያጋሩ, የኢራን አብዮታዊ ዘብ በአጸፋ እርምጃ ‘የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈርን’ መምታቱን አስታወቀ
  5. ከ 5 ሰአት በፊትአሜሪካ በሦስት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ኢራን ላይ ጥቃት ፈጸመችየአሜሪካ ተዋጊ ጄት ባህር ላይ ከሚገኝ የጦር መርከብ ተነስቶ ሲበርርየፎቶው ባለመብት,US Navy via Getty Imagesየአሜሪካ ጦር በኢራን ስትራቴጂካዊ የወደብ ከተማ ባንደር አባስ የሚገኝ ወታደራዊ ስፍራን ዒላማ ያደረጉ የአየር ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታወቀ።የአሜሪካ ኃይሎች “በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ ስጋት ደቅነው የነበሩ” አራት የኢራን ድሮኖችንም መትተው እንደጣሉ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ገልጿል።እንደ ሴንትኮም ገለጻ ባንደር አባስ ውስጥ የሚገኘው ወታደራዊ ስፍራ ጥቃት የተፈጸመበት አምስተኛውን ድሮን ለመተኮስ ሲዘጋጅ ነው። የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከከተማው በስተምስራቅ አቅጣጫ የፍንዳታ ድምፆች መሰማታቸውን ዘግበዋል።ጥቃቱ የተፈጸመው በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰው ጠንካራ ያልሆነ ተኩስ አቁም ተግባራዊ መሆን ባላቆመበት ነው።በሆርሙዝ ወሽመጥ ለሚደረግ የመርከብ ጉዞ መቆም እንዲሁም የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት የሆነውን ይህንን ሦስት ወር የሞላው ጦርነት ለማቆም የሚደረጉ ረጅም ድርድሮች እስካሁን መፍትሔ አላስገኙም።አሜሪካ ራሷን ለመከላከል እንደሆነ በመግለጽ ኢራን ውስጥ ባሉ ዒላማዎች ላይ ጥቃት ስትፈጽም ይህ በሦስት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። እንደአዲስ ጥቃቶች መድረሳቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱን አደጋ ላይ ጥሎታል።ሴንትኮም የተወሰደውን ወታደራዊ እርምጃ “የተመጠነ፣ በግልጽ ራስን የመከላከል የሆነ እንዲሁም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማስቀጠል ያለመ” ሲል ገልጾታል።አሜሪካ ሰኞ ዕለት ደቡባዊ ኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት የኢራንን የሚሳኤል ጣቢያዎች እና በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ፈንጂ ለማጥመድ የሞከሩ መርከቦች ዒላማ እንደተደረጉ ተገልጿል። ሴንትኮም እነዚህ ጥቃቶች የተወሰዱት “ወታደሮቻችንን ከኢራን ኃይሎች ከሚመጡ ስጋቶች ለመጠበቅ” ነው ብለዋል።ጥቃቶቹን “ትልቅ የተሰስ አቁም ጥሰት” ስትል ያወገዘችው ኢራን፤ “የትኛውም ጠበኛ ድርጊት ምላሽ ሳይሰጠው እንደማያልፍ” ዝታለች።የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ ድሮንን መትቶ መጣሉን እንዲሁም ወደ ኢራን የአየር ክለል የገቡ ተዋጊ ጄት እና ድረኖን ላይ ተኩስ መክፈቱን ገልጿል። እነዚህ እርምጃዎች የተወሰዱት መቼ እንደነበር ግን አልተጠቀሰም።ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ትናንት በተካሄደ የካቢኔ ስብሰባ ላይ፤ ኢራን “በንዴት እየተደራደረች ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። አክለውም በመጪው ህዳር የሚካሄደው የአጋማሽ ጊዜ የሥልጣን ዘመን ምርጫ የጦርነት ስትራቴጂያቸው ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ተናግረዋል።ያጋሩ, አሜሪካ በሦስት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ኢራን ላይ ጥቃት ፈጸመች
  6. 27 ግንቦት 2026ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረገው ድርድር “እስካሁን አልተሳካም” አሉትራምፕየፎቶው ባለመብት,Reutersየአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ድርድር “እስካሁን አልተሳካም” አሉ።ድርድሩ “ገና ደስተኛ አላደረገንም” ያሉት ትራም “ነገር ግን [ደስተኛ] እንሆናለን” ብለዋል።ትራምፕ በአስተዳደራቸው ሥር ካሉ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ “መሆን ያለበት በዚህ መንገድ ነው፤ አለበለዚያ ግን እንጨርሰዋለን” ሲሉም ገልጸዋል።የኢራን ባለሥልጣናት ድርድሩን እያካሄዱ ያሉት “ደካማ ሆነው ነው” ብለዋል።“ምን እንደሚሆን እናያለን። ተመልሰን ሥራውን መጨረስ ይኖርብን ይሆናል። ወይም አይኖርብንም” ሲሉም አክለዋል።የኢራን መሪዎች “ስምምነት ላይ ለመድረስ ይፈልጋሉ” ሲሉም ትራምፕ ተደምጠዋል።የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉ ገልጸው “ካልተሳካ ግን ፕሬዝዳንቱ አማራጭ አላቸወ” ብለዋል።በሌላ በኩል ኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ድርድር፤ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ፣ ይፋዊ ያልሆነ፣ የመግባቢያ ሰነድ ማዕቀፍ ረቂቅ እንደደረሳት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቡም ዋይት ሀውስ ግን ይሄንን “ፍጹም ፈጠራ” ሲል አስተባብሏል።ያጋሩ, ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረገው ድርድር “እስካሁን አልተሳካም” አሉ
  7. 27 ግንቦት 2026ኢራን “የመግባቢያ ሰነድ ረቂቅ” ደርሶኛል ብትልም አሜሪካ አስተባበለችኢራንየፎቶው ባለመብት,EPAኢራን ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ድርድር፤ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚገኝ፣ ይፋዊ ያልሆነ፣ የመግባቢያ ሰነድ ማዕቀፍ ረቂቅ እንደደረሳት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቡም ዋይት ሀውስ ግን ይሄንን “ፍጹም ፈጠራ” ሲል አስተባብሏል።የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ “ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደተናገሩት ድርድሩ እየተሻሻለ ነው። [ፕሬዝዳንቱ] ቀይ መስመሮቻቸውን በግልጽ አስምረዋል” ብለዋል።የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ቴህራን በአንድ ወር ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያለውን የጉዞ መጠን ከጦርነቱ አስቀድሞ ወደነበረው ትመልሳለች። በምላሹ አሜሪካ ወታደሮቿን ከኢራን ዙርያ ታስወጣለች፤ በባሕር ኃይሉ ላይ የጣለችውን ማዕቀብም ታነሳለች።የመርከቦችን ጉዞ ማስተዳደሪያ መንገድ የሚወሰነው በኢራን እና ኦማን እንደሆነ ተገልጿል።ነገር ግን “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለአሜሪካ ሕዝብ የሚጠቅም እና ኢራን መቼም ቢሆን ኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት የሚያግድ ስምምነት ብቻ ነው የሚቀበሉት” ብለዋል።የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ምክትል ዳይሬክተር አሊ ባግሪ፤ ቴህራን ከዋሽንግተን ጋር እያደረገችው ባለው ድርድር የዩራኒየም ጉዳይ በአጀንዳነት እንዳልቀረበ ተናግረዋል።በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን በማስተዳደር ረገድ ኢራን እና ኦማን ሚና እንዲኖራቸው እየተደራደሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።“በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የማለፍ ሁኔታ እና አካሄድ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ከነበረው ፈጽሞ የተለየ ይሆናል” ብለዋል።“ሁሉም ነጥቦች ላይ ካልተስማማን በስተቀር ስምምነት ላይ ደርሰናል ብለን አናምንም” ሲሉም አክለዋል።ያጋሩ, ኢራን “የመግባቢያ ሰነድ ረቂቅ” ደርሶኛል ብትልም አሜሪካ አስተባበለች
  8. 27 ግንቦት 2026ኢራን በዩራኒየም ይዞታዋ ላይ እንደማትደራደር አስታወቀችአሊ ባግሪየፎቶው ባለመብት,Reutersየምስሉ መግለጫ,አሊ ባግሪኢራን ከአሜሪካ ጋር እያደረገችው ባለው ድርድር የዩራኒየም ጉዳይ በአጀንዳነት እንዳልቀረበ በኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ እና የዓለም አቀፍ ደኅንነት ምክትል ዳይሬክተር አሊ ባግሪ ተናገሩ።ባለሥልጣኑ ይህንን ያሉት በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ እየተካሄደ ባለው 14ኛው ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት ስብሰባ ወቅት በተጓዳኝ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ቀደም ሲል የዳበረው የኢራን ዩራኒየም ክምችት፤ በሚደረስ ስምምነት ወደ አሜሪካ ተወስዶ ወይም በሌላ ስፋራ ላይ እንዲወድም እንደሚደረግ ተናግረው ነበር።የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ ለወራት ያለመቋጫ እየተካሄደ ያለው የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር ወደ ስምምነት መቃረቡን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ባለፉት ቀናት ሲናገሩ ቆይተዋል።የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዋነኛ መነጋገሪያ ቢሆንም አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኗን እና የድርድሩ ቀይ መስመር መሆኑን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ነበር።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ የቀረበላትን ሃሳብ የማትቀበል ከሆነ ሌላ ዙር ከባድ ጥቃት እንደሚጠብቃት እያስጠነቀቁ ነው።ያጋሩ, ኢራን በዩራኒየም ይዞታዋ ላይ እንደማትደራደር አስታወቀች
  9. 27 ግንቦት 2026የኮንጎ ግጭት ኢቦላን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዳሰናከለ ዶ/ር ቴድሮስ ገለጹየኢቦላ ምርመራየፎቶው ባለመብት,Reutersበዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው ግጭት የኢቦላን ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ላይ ጫና ማሳደሩን የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ገለጹ።በአገሪቱ “ግጭት እና አደገኛ በሽታ” መደራረባቸውን የተናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ፤ በኢቱሪ ግዛት በሽታውን የመከላከል እንቅስቃሴ ማድረግ መስተጓጎሉን አክለዋል።ኃላፊው በኤክስ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ የዓለም ጤና ድርጅት “ቦምብ እየዘነበ የማኅበረሰቡን እምነት ማግኘት ወይም ታማሚዎችን መለየት አይችልም”ዶ/ር ቴድሮስ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር የማዋል ጥረቱን ለመምራት ዛሬ ኮንጎ እንደሚገቡ ተገልጿል። በኢቦላ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 220 ደርሷል።የአገሪቱ መንገዶች አመቺ ባለመሆናቸው የእርዳታ ሠራተኞች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት ተቸግረዋል። ግጭት እና መፈናቀልም የጤና ሥርዓቱን አናግተዋል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ እርዳታ ተቋርጧል።ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት ኢቱሪ ግዛት ከአውሮፓውያኑ 2021 አንስቶ በወታደራዊ አስተዳደር ሥር ናት።ያጋሩ, የኮንጎ ግጭት ኢቦላን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት እንዳሰናከለ ዶ/ር ቴድሮስ ገለጹ
  10. 27 ግንቦት 2026ኢራን እና አሜሪካ ልዩነቶቻቸውን ያጠብባሉ ብላ ተስፋ እንደምታደርግ ቻይና ገለጸችየቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪየፎቶው ባለመብት,Reutersየቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የኢራን ጦርነት ተፋላሚ ወገኖች የተኩስ አቁሙን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ሆነው እንደሚቀጥሉ እና ልዩነቶቻቸውን ያጠብባሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገለጹ።አሜሪካ በደቡብ ኢራን የመከላከል ያለችውን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ቴህራን ማክሰኞ ዕለት ዋሺንግተንን የተኩስ አቁሙን በመጣስ ከስሳለች።ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር “የተወሰነ ቀናት ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።ዋንግ በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በተገኙበት ወቅት “ሰላም በተቻለ ፍጥነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲመለስ ተፋላሚ አካላት የተኩስ አቁምን ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚቆዩ እና ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ ግማሽ መንገድ እንደሚገናኙ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።ዋንግ አክለውም ሁሌም እንደምንለው ሰላም እና መፍትሄ ለማምጣት ጊዜ ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ “ለረዥም ጊዜ የቆዩ ችግሮች ቶሎ አይፈቱም” ብለዋል።“ይሁን እንጂ በድርድሩ የሚደረግ እያንዳንዱ እርምጃ የበለጠ ተስፋን ይሰጣል፤ እንዲሁም ግጭቱ ቶሎ በተቋጨ ጊዜ የሰላማዊ ዜጎችን ጉዳት መቀነስ ይቻላል” ብለዋል።ያጋሩ, ኢራን እና አሜሪካ ልዩነቶቻቸውን ያጠብባሉ ብላ ተስፋ እንደምታደርግ ቻይና ገለጸች
  11. 27 ግንቦት 2026የዩኬ የደህንነት ተቋም ሩሲያ ወሳኝ የመሠረተ ልማቶችን እና ዲሞክራሲን “ያለመታከት ዒላማ እያደረገች” ነው ሲል ወነጀለየሩሲያ ባንዲራየፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየዩናይትድ ኪንግደም የስለላ፣ ደህንነት እና ሳይበር ኤጀንሲ ሩሲያ ያለ መታከት ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን ማጥቃት በመቀጠሏ አገሪቱ አሳሳቢ እና ወሳኝ ጊዜ ላይ እንደምትገኝ ገለጸ።የዩኬ የስለላ ተቋም ኃላፊ የሆኑት አኔ ኪአስት በትለር ረቡዕ ዕለት የሩሲያ እርምጃ ለዩናይትድ ኪንግደም የሚኖረውን ስጋት በሚመለከት እንዲሁም እንዴት መመከት እንዳለባት የሚገልጽ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።ከኃላፊዋ ንግግር ተቀንጭቦ የተጋራው መልዕከት ላይ ሩሲያ “ወሳኝ የሆነ መሠረተ ልማቶችን፣ የዲሞክራሲ ሂደቶችን፣ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን እና የሕዝብ እምነትን ዒላማ አድርጋለች” ብለዋል።ሩሲያ በብሪታኒያ ግዛት ውስጥ የአገር ክህደት ወንጀልን በማበረታታት የምትወቀስ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዩኬ እና የኔቶ አባል አገራት ላይ በይፋ ያልታወጀ ‘የተቀናጀ ጦርነት’ ከፍታለች በሚል ትከሰሳለች።ክሬምሊን ውንጀላውን ያስተባብላል።በትለር ተቋማቸው “ግድየለሽነት የተሞላበት” ያሉትን የሳይበር ጥቃቶች ለመመከት እንዲሁም “የግድያ ሙከራዎችን” ለመከላከል ያለ እረፍት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።አክለውም “በእንዲህ ዓይነት ጠብ አጫሪት እና ግርግር ውስጥ ተቋማችን ያለመታከት ከደህንነት እና መከላከያ አጋሮቻችን ጋር በመሆን የሩሲያን ስጋት ለመቀነስ ይሰራል” ብለዋል።ክሬምሊን የኬጂቢ ባልደረባ የነበረውን አሌክሳንደር ሊትቪኔንኮን በለንደን ሆቴል ውስጥ ሳለ በጠጣው ሻይ ውስጥ መርዛማ ኬሚካል በመጨመር ለመግደል ሙከራ አድርጓል መባሉን አስተባብሏል።እአአ በ2018 የቀድሞው የሩሲያ ወታደራዊ ደህንነት ባልደረባ የነበረውን ሰርጌይ ስክሪፓልን ለመግድል ሙከራ በማድረግ ተከስሷል።ሩሲያ እአአ በ2022 ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም ከኪየቭ ጎን በመቆሟ በምዕራባውያን አገራት ላይ “የተቀናጀ ጦርነት” በመክፈት ትወነጀላለች።ያጋሩ, የዩኬ የደህንነት ተቋም ሩሲያ ወሳኝ የመሠረተ ልማቶችን እና ዲሞክራሲን “ያለመታከት ዒላማ እያደረገች” ነው ሲል ወነጀለ
  12. 27 ግንቦት 2026በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አዲስ አበባ ገባየቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታየምስሉ መግለጫ,የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታበመጪው ሰኞ ሰባተኛውን አጠቃላይ ምርጫን የሚታዘቡ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች አዲስ አበባ መግባታቸውን ኅብረቱ አስታወቀ።በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራው የኅብረቱ ታዛቢዎች ከ37 አገራት የተውጣጡ እና 73 አባላትን የያዘ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተገልጿል።ይህ አምባሳደሮችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች፣ የምርጫ ባለሙያዎች፣ የሰብኣዊ መብት፣ የሥርኣተ ፆታ፣ የወጣቶች እና የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮችን ያከላተተ መሆኑ ተገልጿል።የአፍሪካ ኅብረት ማክሰኞ ግንቦት 18/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫው ዕለት የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን እና ቆጠራን ለመታዘብ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሰማሩ መሆኑ አስታውቋል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመላ አገሪቱ ሰኞ ግንቦት 24 የሚደረገው ሰባተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ከአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች በተጨማሪ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ታዛቢዎች እንደሚገኙ አስታውቋል።የአፍሪካ ብረት እና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ መሠረት መሆኑን የምርጫ ቦርድ እና ኅብረቱ አስታውቀዋል።የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ግምገማውን በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ፣ በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም አስፈላጊ በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ በተቀመጡ መስፈተርቶች ላይ በመመሥረት ግምገማውን እንደሚያደርግ ተገልጿል።ታዛቢዎቹ ከምርጫ ቦርድ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከዕጩዎች፣ ከመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ከሌሎች የምርጫ ታዛቢዎች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።ታዛቢ ቡድኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ግንቦት 26/2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፋ የሚያደርግ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመጨረሻ ሪፖርቱን ደግሞ ከምረጫው በኋላ በሁለት ወር ውስጥ ያቀርባል ተብሏል።የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለመታዘብ ከ500 በላይ የሚሆኑ የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን ማሰማራታቸውን አስታውቀዋል።ያጋሩ, በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አዲስ አበባ ገባ
  13. 27 ግንቦት 2026እስራኤል በጋዛ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት አዲሱን የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ መግደሏን አስታወቀችጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በርካታ ሰዎች ተሰብሰብው ታይተዋልየፎቶው ባለመብት,Reutersእስራኤል ማክሰኞ ዕለት በጋዛ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት በዲሱን የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ መግደሏን አስታወቀች።የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ በተጨናነቀ የገበያ ስፍራ በሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻ ላይ በፈጸመው ከፍተኛ የአየር ድብደባ ቢያንስ ሦስት ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የሕክምና ባለሙያዎችና የዓይን እማኞች ተናግረዋል።ጥቃቱ የኢድ አል-አድሃ በዓል ከመከበሩ በፊት ጎዳናዎች በገበያተኞች ተጨናንቀው ባለበት ወቅት በጋዛ ከተማ መሃል በሚገኘው የአል-ካያሊ ሕንፃ የላይኛውን ሦስት ፎቅ ዒላማ ማድረጉ ተገልጿል።የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ ቀደም ሲል የእስራኤል ጦር የሐማስን የጦር ክንፍ አዛዥ መሐመድ ኦዴህን ዒላማ እንዳደረገ አስታውቋል። ይህም የቀድሞው የጦር አዛዥ በተመሳሳይ ጥቃት ከተገደለ ከጥቂት ቀናት በኋላ የተፈጸመ ነው።ይህ እስራኤል ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረገች በኋላ በጋዛ የተፈጸመ የቅርብ ጊዜ ከባድ ጥቃት ነው።ኦዴህ በጥቃቱ መገደሉን በተመለከተ የእስራኤል መንግሥት ሲያስታውቅ ሐማስ ግን ምንም አስተያየት አልሰጠም።የነፍስ አድን ሠራተኞች በስፍራው ሲደርሱ በአካባቢው በደረሰው ከባድ ጉዳት እና በነበረው መጨናነቅ ምክንያት ወደ ላይኛው ፎቅ ለመውጣት ተቸግረዋል።የዓይን እማኞች ቢያንስ አምስት ሚሳኤሎች ሕንፃውን ከተለያየ አቅጣጫ በተመሳሳይ ጊዜ መምታታቸውን ተናግረዋል።አንድ ነዋሪ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የሄሊኮፕተር ድምፅ መስማቱን ተናግሯል።ከቦታው የተገኘ ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው አምቡላንሶች እና የሲቪል መከላከያ ሠራተኞች በተመታው ሕንፃ ውስጥ የተረፉ ሰዎች ካሉ ሲፈልጉ የሚያሳይ ሲሆን በአቅራቢያው በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ነበር።የኔታንያሁቢሮ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት “ካቀነባበሩ ሰዎች መካከል አንዱን” መሐመድ ኦዴህን ዒላማ እንዳደረገውአስታውቋል።“ኦዴህ በበርካታ የእስራኤልዜጎችን እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ግድያ፣ ጠለፋ እና መቁሰል ተጠያቂ ነው” ሲል መግለጫውአክሏል።የቡድኑ ታጣቂ ክንፍ አዛዥ የነበሩት ኢዝ አድ-ዲን አል-ሃዳድ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ በእስራኤል የአየር ጥቃት ተገድለዋል።ይህ ጥቃት በአንድ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ቢያንስ ሦስት ሰዎችን ገድሏል ሲሉ የዓይን እማኞች እና የአካባቢው ምንጭ ተናግረዋል።እስራኤል የተኩስ አቁም ከተደረሰበት እአአ ከጥቅምት 10 ጀምሮ በጋዛ ዙሪያ ጥቃቶችን ስትፈጽም ቆይታለች።ሐማስ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እና ሲቪሎችን በማጥቃት በተደጋጋሚ ሲከስ ቆይቷል።የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በተኩስ አቁም ስምምነቱ ወቅት በእስራኤል በተሰነዘረው ጥቃት ከ800 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።ያጋሩ, እስራኤል በጋዛ ከተማ በፈጸመችው ጥቃት አዲሱን የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ መግደሏን አስታወቀች
  14. 27 ግንቦት 2026እስራኤል በሊባኖስ በተከታታይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸየእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በምሥራቅ ሊባኖስ በሚገኘው ቤካ ሸለቆ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ጥቃት በመክፈት ሄዝቦላህን እየመታ መሆኑን ይናገራል።እስራኤል በተከታታታይ በምሥራቃዊ እና ደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።የእስራኤል ጦር በሊባኖስ የሚፈጽመውን ከባድ ጥቃት የቀጠለው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሄዝቦላህ ላይ የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃ እንዲጠናከር ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነው።የእስራኤል መከላከያ ከ100 በላይ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶችን እና ተዋጊዎችን ዒላማ አደርጎ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።ኔታንያሁ ሰኞ ምሽት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፤ እስራኤል “ከሄዝቦላህ ጋር ጦርነት ላይ” እንደሆነች ተናግረው ሠራዊቱ “አድቃቂ ምት” እንዲፈጽም ማዘዛቸውንም ገልጸዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እስራኤል በከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ “ከ600 በላይ አሸባሪዎች” መገደላቸውንም ተናግረዋል። “አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ጥቃቱን ማጠናከር እና ጥንካሬውን ይበልጥ መጨመር ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።ኔታንያሁ ማክሰኞ ዕለት በደህንነት ካቤኔ ስብሰባቸው ላይ “በሊባኖስ የምናካሄደውን ዘመቻ እያሰፋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።“የእስራኤል ጦር በምድር ከፍተኛ ኃይል አሰማርቶ ዘመቻ እያካሄደ እና ገዢ መሬቶችን እየተቆጣጠረ ነው” ብለዋል።አክለውም በሰሜን እስራኤል የሚገኙ እስራኤላውያንን ከሄዝቦላህ ጥቃት ለመከላከል “የደህንነት ቀጣናዎች እየመሰረተ ነው” ብለዋል።በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በተደጋጋሚ ተጥሷል።እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በየዕለቱ የአየር ድብደባ የምትፈጽም ሲሆን ሄዝቦላህም ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ይተኩሳል።የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በምሥራቅ ሊባኖስ በሚገኘው ቤካ ሸለቆ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ጥቃት በመክፈት ሄዝቦላህን እየመታ መሆኑን ይናገራል።የተወሰኑ ጥቃቶች በተባበሩት መንግሥታት በቅርስነት የተመዘገበ እና የ900 ዓመት እድሜ እንዳለው የሚገመት ቤተ መንግሥት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።ያጋሩ, እስራኤል በሊባኖስ በተከታታይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች ቢያንስ 31 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
  15. 26 ግንቦት 2026በኢራን ለሦስት ወራት ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ተጀመረበኢራን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧልየፎቶው ባለመብት,Anadolu via Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,በኢራን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧልበኢራን ለሦስት ወራት ያህል ተቋርጦ የቆየው የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም መጀመሩን የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት አስታወቁ።ሞሃማድ ሬዛ አረፍ ማክሰኞ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ “ነጻ እና ቁጥጥር የሚደረግበት የኢንተርኔት አገልገሎት ለመስጠት የመጀመርያ እርምጃ ወስደናል” ብለዋል።ኔትብሎክስ እና ኬንቲክ የተባሉ የዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ግንኙነትን የሚከታተሉ ተቋማት በኢራን ዛሬ ከምሳ ሰዓት ጀምሮ “በከፊል” የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩን ተናግረዋል።በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም. በአገሪቱ ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ነበር።የኢራን ባለሥልጣናት በጦርነቱ ወቅት ኢንተርኔት የተዘጋው ከደኅንነት ጋር በተያያዙ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። ይህንን በማድረግ ክትትል፣ ስለላ እና የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል እንዳሰቡ ጠቁመዋል።በቴህራን የሚገኝ አንድ ግለሰብ ዛሬ የዋይፋይ አገልግሎት መጀመሩን ለቢቢሲ ተናግሯል።ኔትብሎክስ የኢንተርኔት አገልግሎት “የሚቀጥል” ስለመሆኑ “ግልጽ አይደለም” ብሏል።ያጋሩ, በኢራን ለሦስት ወራት ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ተጀመረ
  16. 26 ግንቦት 2026እስራኤል በሊባኖስ መንደሮች ላይ በፈጸመችው ጥቃት አስራ አንድ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸእስራኤል ሰኞ ዕለት በደቡባዊ ሊባኖስ ናቤታህ መንደር የፈጸመችው ጥቃትየፎቶው ባለመብት,Reutersእስራኤል በሄዝቦላህ ላይ የምትወስደውን ወታደራዊ እርምጃ እንደምታጠናክር ከገለጸች በኋላ በደቡብ እና ምሥራቃዊ ሊባኖስ በርካታ ድብደባዎችን መፈጸሟ ተገለጸ።የእስራኤል ጦር ከ100 በላይ የሄዝቦላህ መሠረተ ልማቶችን እና ተዋጊዎች ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን ተናግሯል።በሚያዚያ ወር አጋማሽ ላይ በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል በአሜሪካ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ተደርሷል።የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በቤካ ቫሊ በሚገኝ ማሽጋሃራ በተሰኘ መንደር በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።የእስራኤል ጦር ግን “የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ” በታየበት አካባቢ ጥቃት መፈጸሙን ተናግሯል።የእስራኤል ጦር ጥቃቱን አጠናክሮ የቀጠለው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሄዝቦላህ ዒላማዎች ላይ “ጠንከር ያለ ጥቃት” እንዲፈጸም ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ነው።በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በተደጋጋሚ ተጥሷል።እስራኤል በተለይ በደቡባዊ ሊባኖስ በተደጋጋሚ የአየር ድብደባ የምትፈጽም ሲሆን ሄዝቦላህም ሮኬቶችን እና ድሮኖችን በሰሜን እስራኤል ወደሚገኙ አካባቢዎች ይተኩሳል።ያጋሩ, እስራኤል በሊባኖስ መንደሮች ላይ በፈጸመችው ጥቃት አስራ አንድ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
  17. 26 ግንቦት 2026ኢራን፣ አሜሪካ የፈጸመችው አዲስ ጥቃት የተኩስ አቁሙን የጣሰ ነው አለችኢራንየፎቶው ባለመብት,REUTERSአሜሪካ ራስን መከላከል በሚል አዲስ ጥቃት በደቡባዊ ኢራን ከፈጸመች በኋላ ቴህራን ዋሺንግተን የተኩስ አቁሙን ጥሳለች ስትል ከሰሰች።የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር “ጥቂት ቀናት ሊወስድ ይችላል” ብለዋል።የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ሆርሞዝጋን አውራጃ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቆ የተኩስ አቁሙ “ግልጽ ጥሰት ነው” ሲል ተናግሯል።የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አሜሪካ “ጠብ አጫሪ እና ተቀባይነት ለሌለው ድርጊቷ” ተጠያቂ ትሆናለች ብሏል።አሜሪካ ጥቃት የፈጸመችበት ሆርሞዝጋን ክልል ከሆርሙዝ ወሽመጥ ጋር የሚዋሰን ነው።ኢራን በመግለጫው “ያለምንም ጥርጥር የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ምላሽ ሳይሰጥ የሚተወው ምንም ክፋት የለም እንዲሁም የኢራን ዜጎችን ከመከላከልም ወደ ኋላ አይልም” ብላለች።ሁለቱ አገራት እስከ ትናንት ሰኞ ድረስ በመግባቢያ ሰነዱ ዙሪያ የሚደረገው ንግግር ለውጥ ማሳየቱን ሲናገሩ ነበር።አሜሪካ እና ኢራን የሚያደርጉት ንግግር በስምምነት ከተቋጨ ለሦስት ወር የዘለቀውን ጦርነቱን ያስቆማል፣ የሆርሙዝ ወሽመጥን ያስከፍታል እንዲሁም የተኩስ አቁሙን በ60 ቀናት ይራዘማል ተብሎ ነበር።የአሜሪካ ጦር በደቡብ ኢራን የሚገኙ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና ፈንጂ የሚጥሉ ጀልባዎችን ዒላማ በማድረግ አዲስ ዙር ጥቃት መክፈቱን አስታወቋል።የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ “ራስን መከላከል” እንደሆነ አስታውቋል። ዓላማውም “በኢራን ኃይሎች ስጋት የተጋረጠባቸው ወታደሮቻችንን መከላከል ነው” ብሏል።ያጋሩ, ኢራን፣ አሜሪካ የፈጸመችው አዲስ ጥቃት የተኩስ አቁሙን የጣሰ ነው አለች
  18. 26 ግንቦት 2026የኢራኑ ጠቅላይ መሪ “ባሕረ ሰላጤው ከዚህ በኋላ የአሜሪካ ጦር ሰፈር መጠለያ አይሆንም” አሉየኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒየፎቶው ባለመብት,AFP via Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒየኢራኑ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ለኢድ አል አድሃ በዓል ባስተላለፉት መልዕክት እስራኤልን “አደገኛ” በማለት ከዚህ በኋላ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ አካባቢ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች መቀመጫ አይሆንም ሲሉ ገለጹ።ጠቅላይ መሪው በጽሁፍ ባስተላለፉት እና በመንግሥት ቴሌቪዥን በተነበበው መልዕክታቸው ላይ እስራኤልን “በቀጣናው አደገኛ እና ገዳይ ህመም” በማለት “መወገድ ይገባታል” ማላታቸውን ኢራኑ ዜና ወኪል ታስኒም ዘግቧል።ሞጅታባ የአባታቸው መገደል ተከትሎ የጠቅላይ መሪነቱን ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ እስካሁን ድረስ ለሕዝብ በይፋ ያልታዩ ሲሆን፣ መልዕክታቸውን በጽሁፍ ሲያስተላልፉ ቆይተዋል።በአሁኑ መልዕክታቸው በኢራን ላይ ጦርነት ከተከፈተ በኋላ ነገሮች እየተቀያየሩ መሆናቸውን በማንሳት የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች በባሕረ ሰላጤው አገራት ውስጥ ቦታ እንደማይኖራቸውን ገልጸዋል።ጠቅላይ መሪው “ጊዜን ወደ ኋላ መመለስ እንደማይቻል እርግጥ እንደሆነው ሁሉ፤ በቀጣናው ያሉ አገራት እና መሬት ከዚህ በኋላ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች መጠለያ አይሆኑም” ሲሉ የአሜሪካ ሚና በአካባቢው እንደማይኖር አመለክተዋል።ጨምረውም “በቀጣናው ለክፉ ተግባር መጠለያ የሆኑት ጦር ሰፈሮች አይኖሩም እንዲሁም ተጨማሪ ወታደራዊ ሰፈሮች አይመሠረቱም” በማለት “አሜሪካ ከቀን ወደ ቀን ከዚህ በፊት ከነበረችበት ደረጃ እየወረደች ነው” ብለዋል።ጠቅላይ መሪው ባለፉት ወራት በተካሄደው ጦርነት አሜሪካ እና እስራኤል ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው በመጥቀስ “በኢራን ከባድ ምት እስራኤል አቅመ ቢስ” እንደሆነች እና አሜሪካም “ከባድ ጥፊ እንደቀመሰች” ገልጸዋል።ያጋሩ, የኢራኑ ጠቅላይ መሪ “ባሕረ ሰላጤው ከዚህ በኋላ የአሜሪካ ጦር ሰፈር መጠለያ አይሆንም” አሉ
  19. 26 ግንቦት 2026ኢራን “የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ተገቢ እና የማይቀር” መሆኑን ገለጸችየኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብየፎቶው ባለመብት,EPAየኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ፤ በአሜሪካ ጦር ለሚፈጸም ማንኛውም የተኩስ አቁም ጥሰት “የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ተገቢ እና የማይቀር” እንደሆነ አስታወቀ።እስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ አሜሪካ በደቡብ ኢራን የከፈተችውን ጥቃት ሳይጠቅስ በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል ባወጣው መግለጫ “የአሜሪካ ጦር በቀጣናው ጣልቃ ገብነቱን እና ጠብ ጫሪነቱን ቀጥሎ በፐርዥያ ባሕረ ሰላጤ ወደ ኢራን የአየር ክልል እና ወደ እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መከላከያ ሰፈር ገብቷል” ብሏል።“በጥንቃቄ የደኅንነት ቅኝት ካደረግን በኋላ የግዛት ሉዓላዊነታችንን ለመከላከል ኤምኪው-9 ድሮን መትተን ጥለናል” ሲልም አክሏል።አርኪው-4 ድሮን እና ኤፍ-35 ተዋጊ ጄት እንደመታ እና እርምጃው “በውሃ የተሸፈነውን አካባቢ ጥለው እንዲሸሹ እንዳስገደዳቸው” አስታውቋል።እነዚህ ጥቃቶች መቼ እና የት እንደተፈጸሙ በግልጽ አላስቀመጠም።የአሜሪካ ጦር ባወጣው መግለጫ በደቡብ ኢራን የሚገኙ የሚሳዔል ማከማቻዎች እና ፈንጂ የሚጥሉ ጀልባዎችን ዒላማ በማድረግ አዲስ ዙር ጥቃት መክፈቱን ይፋ አድርጓል።የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጥቃቱ “ራስን መከላከል” እንደሆነ ገልጾ፤ ዓላማውም “በኢራን ኃይሎች ስጋት የተጋረጠባቸው ወታደሮቻችንን መከላከል ነው” ብሏል።የኢራን መገናኛ ብዙኃን ትናንት ምሽት በባንደር አባስ የወደብ ከተማ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ ፍንዳታ መሰማቱን ዘግበዋል።ያጋሩ, ኢራን “የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ተገቢ እና የማይቀር” መሆኑን ገለጸች
  20. 26 ግንቦት 2026ኳታር ለኢራን 12 ቢሊየን ዶላር ልትሰጥ ነው መባሉን አስተባበለችየኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርየፎቶው ባለመብት,Reutersየምስሉ መግለጫ,የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር ከስምምነት እንድትደርስ ለማድረግ 12 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ሃሳብ አቅርባለች መባሉን መሠረተ ቢስ በማለት ኳታር አስተባበለች።የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማጂድ አል እንሳሪ በኤክስ የሶሻል ሚዲያ መድረክ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የአገራቸው ዲፕሎማሲያዊ ሚና በግልጽ የሚታወቅ መሆኑን በመጥቀስ የወጡ ዘገባዎች ያላትን “ታማኝ ዓለም አቀፍ የሰላም ጥረቶች አመቻችንት የሚያጠለሽ ነው” ብለዋል።ይህ የሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው በርካታ ከፍተኛ የኢራን ባለሥልጣናት ከአሜሪካ ጋር የሚደረገውን ድርድር ለመቋጨት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኳታርን እየጎበኙ ባለበት ጊዜ ነው።ኢራን ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር በኳታር ያለውን ጨምሮ በውጭ አገራት እንዳይንቀሳቀስ የታገደባት ሃብቷ እንዲለቀቅ እየጠየቀች ነው። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት አገሪቱ በኳታር ውስጥ 12 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ታግዶባታል።በኒውክሌር መረሃ ግብሯ ምክንያት ከምዕራበባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር በገባችው እሰጣ ገባ ተደራራቢ ዕቀባ የተጣለባት ኢራን ባለፈው የካቲት ወር በአሜሪካ እና በእስራኤል በተከፈተባት ጥቃት ጦርነት ውስጥ ገብታለች።ለጥቂት ወራት የዘለቀው ጦርነት በተኩስ አቁም ጋብ ብሎ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ድርድር እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ ኢራን ከስምምነት ለመድረስ በቅድመ ሁኔታ ካቀረበቻቸው ነጥቦች መካከል በውጭ ያለው ሃብቷ እንዲለቀቅላት የሚጠይቀው ይገኝበታል።ያጋሩ, ኳታር ለኢራን 12 ቢሊየን ዶላር ልትሰጥ ነው መባሉን አስተባበለች