
ታትሟልከ 3 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከግለ ታሪክ ፀሐፊያቸው ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ይፋ እንዳይሆን ለማገድ የፌደራል መንግሥቱ ላይ ክስ መሠረቱ።
ጆ ባይደን ቃለ ምልልሱ “ግላዊ መረጃ” እንደሆነ በመግለፅ፤ ሊያሳፍሩ የሚችል ዝርዝሮችን ይዞ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ባይደን የሚስጢራዊ ሰነዶች አያያዛቸውን በሚመለከት ምርመራ በተከፈተባቸው ወቅት የድምፅ ቅጂ እና የቃለ ምልልስ ፅሑፍ ተገኝቷል።
ምርመራውን የደረጉት ሮበርት ኸር ባይደን ሰነዶችን ያላግባብ መያዛቸውን ጠቁመው ክስ መመስረት ግን አላስፈላጊ አይደለም ብለው ነበር።
ከሁለት ዓመታት በፊት ይፋ የተደረገ ምርመራው፤ ባይደን ለፕሬዝዳንትነት ኃላፊነት ብቁ መሆናቸው ላይ ጥያቄ አስነስቷል።
የፍትሕ መስሪያ ቤቱ የባይደን የአዕምሮ ጤና እያሽቆለቆለ እንደነበር የሚያሳውን “የድምፅ ቅጅ ለመደበቅ” ሞክሯል በሚል የቀድሞውን አስተዳደር ወቅሷል።
የተወካዮች ምክር ቤት የሪፐብሊካን እና ወግ አጥባቂዎች የባለሙያዎች ኮሚቴ በ2024 የግለ ታሪክ ቃለ ምልልሱን ቅጅ ለማግኘት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ የፍትሕ መስሪያ ቤቱም ቅጂውን በሚቀጥለው ወር ይፋ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
ባይደን በ2017 ‘ፕሮሚስ ሚ ዳድ’ በተባለው ግለ ታሪካቸው፤ ከጋራ ፀሐፊው ማርክ ዝወኒትዘር ጋር ከሁለት ዓመት አስቀድሞ ስለሞተው የመጀመሪያ ልጃቸው እና በዚያ ሰሞን ስለነበሩ ክስተቶች አውርተዋል።
ከፀሐፊው ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ዋቢ ወስደው በሪፖርቱ ያካተቱት ሮበርት ኸር፤ በወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እያሉ ባይደን ሚስጢራዊ ሰነዶችን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ሪፖርቱን የተመለከተው ልዩ ኮሚቴ የባይደን ትውስታ ጉልህ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ጠቅሷል። ከፀሐፊው ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ሁነቶችን ለማስታወስ በጣም ሲቸገሩ እና አንዳንድ ጊዜ ማስታወሻ ደብተራቸውንም ለማንበብ ሲከብዳቸው እንደነበር ተጠቅሷል።
ይህ ሪፖርት በዋሽንግተን ውዝግብ የፈጠረ ሲሆን የባይደን ጤና እና እድሜ ላይ ትኩረት እንዲደረግበት አስገድዷል። በ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክር ባሳየቱ አቅም ፓርቲያቸው ስጋቱ በማንሳቱ ምክንያት ከዳግም የምርጫ ዘመቻቸው ራሳቸውን አግልለዋል።
ሪፐብሊካኖች ደግሞ ባይደንን ተጠያቂ ለማድረግ ሞክረዋል። ሕግ አውጪዎች ለሦስት ጊዜ ያህል የድምፅ ቅጂው እንደ ማስረጃ ሆኖ እንዲመዘገብ ጠይቀዋል።
የፍትሕ መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ቃለ ምልልሱ በግላዊ መብት ምክንያት ይፋ እንደማይሆን ተቃውሟል። ነገር ግን በፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር መስሪያ ቤቱ አቋሙን ቀይሯል።
የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ናታሊ ባልዳሳር “የጆ ባይደን ፍትሕ መስሪያ ቤት ከ2016 ጀምሮ የእውቀት አዕምሯቸው እያሽቆለቆለ እንደነበር በግልፅ የሚያሳውን የድምፅ ቅጂ ደብቋል” ብለዋል።
“እነዚህን ቅጂዎች የአሜሪካ ሕዝቦች እንዲሰሟቸው ለማድረግ እንፋለማለን። እናም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፕሬዘዳንት ከመሆናቸው በፊት የአዕምሮ ብልሃታቸውን ደረጃ ራሳቸው አይተው እንዲደመድሙ እናደርጋለን” ብለዋል።
የባይደን ጠበቆች ባቀረቡት ክስ ላይ ቃለ ምልልሱ ግላዊ እና ሚስጢራዊነት ያለው ነው ብለዋል። የድምፅ ቅጂዎቹ የሕግ ከለላ እንዳላቸው መከራከሪያ ያቀረቡም ሲሆን፤ የፍትሕ መስሪያ ቤቱ የአስተዳደር ሕግ እየጣሰ ነውም ሲሉ መከራከሪያ አቅርበዋል።
የፍትሕ ቢሮው የፕሬዝዳንት ባይደንን የግላዊ መረጃዎች ይፋ ለማድረግ የሐሰት መከራከሪያ እያቅበ ነው ሲሉም ከስሰዋል።
