ታትሟልከ 2 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ኬንያ በርካታ ሰዎችን ለገደለው አደገኛ የኢቦላ ቫይረስ የተጋለጡ አሜሪካውያንን ለይቶ ማቆያ የሚሆን ማዕከል በግዛቷ ውስጥ እንዲቋቋም መፍቀዷን ተከትሎ አንድ ማኅበር ባቀረበው ክስ ዕቅዱ በጊዜያዊነት ታገደ።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኡጋንዳ ውስጥ በርካታ ሰዎችን የገደለው እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መያዛቸው የተጠረጠረበት ይህ በሽታ እጅግ ከፍተኛ የሕብረሰተሰብ ጤና ስጋት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ያወጀው ከአንድ ሳምንት በፊት ነው።

በዚህም የተነሳ አሜሪካ ከዜጓቿ ውጪ የሆኑ እና ባለፉት 21 ቀናት ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኡጋንዳ ወይም ደቡብ ሱዳን ውስጥ የነበሩ ሰዎች ወደ አገሯ እንዳይገቡ አግዳላች።

በሽታው ወደ ግዛቷ እንዳይገባ እርምጃ እየወሰደች ያለችው አሜሪካ በተጨማሪም ለኢቦላ ተገላጭ የነበሩ ዜጎቿ በቀጥታ ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ ለማድረግ ኬንያ ውስጥ የለይቶ ማቆያ ማዕከል ለማቋቋም ከኬንያ መንግሥት ጋር ተስማምታለች።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ሁለት ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ኬንያ በማዕከላዊ ክፍሏ ውስጥ በሚገኘው ላይኪፒያ ግዛት ውስጥ የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከሉ እንዲከፈት ፈቅዳለች።

ማዕከሉ በአሜሪካ የሕብረተሰብ ጤና አገለግሎት ባለሙያዎች፣ በአሜሪካ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የሰብዓዊ አገልግሎት ተቋማት አማካይነት የሚመራ እንደሚሆን ተነግሯል።

ይህ ዜና መሰማቱን ተከትሎ በውሳኔው ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ እየተሰማ ነው። ኬንያውያን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየሰጡት ባለው አስተያየት በከፍተኛ ደረጃ በሚዛመተው እና አደገኛ ለሆነው ኢቦላ በሽታ አሜሪካ ለምታቋቁመው የለይቶ ማቆያ ማዕከል መንግሥት ፈቃድ መስጠቱ አስቆጥቷቸዋል።

ረቡዕ ዕለት የኬንያ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የኢቦላ በሽታን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ከአሜሪካ እና “ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች” ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ቢገልጽም፤ የአሜሪካ ለይቶ ማቆያ መዕከል ለማቋቋም ስላለው ዕቅድ ግን በቀጥታ ምንም ያለው ነገር የለም።

በሽታው በተከሰተበት አካባቢ ቆይታ ያደረጉ ዜጎቿ በቀጥታ ወደ ግዛቷ መመለሳቸው ያሰጋት አሜሪካ ለኢቦላ ተጋላጭ ያለቻቸውን ሰዎች ከድንበሯ ውጪ ለማቆየት የሚያስችላትን ዕቅድ በማዘጋጀት ከኬንያ ጋር ስምምነት ላይ ደርሳለች።

በዓለም ላይ በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ የጤና ስጋት የሆነውን ኢቦላን ለመከላከል አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ሲሆን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም በበሽታው የተያዘ ማንኛውም ሰው ወደ አገራቸው እንዲገባ እንደማይፈቅዱ አስታውቀዋል።

በሽታው ከተከሰተባቸው አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኡጋንዳ ጎረቤት የሆነችው ኬንያ ምንም እንኳን በግዛቷ ውስጥ በሽታው ባይገኝም አሜሪካ ለተጋላጭ ሰዎች የለይቶ ማቆያ ማዕከል በአገራቸው ውስጥ ማቋቋሟ ዜጎች ስጋት ፈጥሮባቸዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኬንያ ሲቪል ማኅበረሰብ ቡድን የሆነው ካቲባ ኢኒስቲቲዩት አሜሪካ ወይም የትኛውም የውጭ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ለማቋቋም ያላቸውን ዕቅድ እንዲያስቆምለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርቧል።

ክሱ በተጨማሪም ፍርድ ቤት የኬንያ ጤና ሚኒስቴር በአገሪቱ ውስጥ የኢቦላ ወረርሽን ቢከሰት ያለውን ዝግጁነት፣ የበሽታ ቅኝት ሥራ እና የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሥርዓቱን በዝርዝር የሚያሳይ ዕቅዱን በ24 ሰዓታት ውስጥ እንዲያርብ ጠይቋል።

እንዲሁም መንግሥት የለይቶ ማቆያ ማዕከሉን ለማቋቋም ከአሜሪካ ጋር የደረሰውን ስምምነት ዝርዝር ወይም ስለማዕከሉ፣ ስለአካባቢ ጥበቃ የተደረጉ ድርድሮች፣ ፓርላማው የጸደቀ ስምምነት እና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎች ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ ተጠይቋል።

ይህንንም ተከትሎ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአሜሪካ የሚቋቋመውን የኢቦላ ለይቶ ማቆያ ማዕከል ሥራን በጊዜያዊነት የሚያግድ ውሳኔ አሳልፏል።

ክሱን የተመለከቱት ዳኛ ፓትሪሺያ ንያውንዲ የጉዳዩን አስቸኳይነት በመቀበል ተጨማሪ የችሎት ስሚ እስኪካሄድ ድረስ ማዕከሉን ከማቋቋም እና ሥራ ከማስጀመር ጋር የተያያዘ የትኛውም ዕቅድ ተግባራዊ እንዳይሆን ዕግድ ጥለዋል።

ውሳኔው በተጨማሪም ከአሜሪካ ወይም ከሌላ አገር ጋር በተያያዘ የትኛውም የመንግሥት ተቋም ወይም ባለሥልጣን ከኢቦላ ጋር የተያያዘ ለይቶ ማቆያ ወይም የሕክማና ማዕከል “የሚያቋቁም፣ ሥራ የሚያስጀምር፣ የሚያመቻች፣ የሚያጸድቅ ወይም የሚፈቅድ” ውሳኔ እንዳያሳልፍ አግዷል።

ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ዕቅድ ያወጣው ካቲባ ኢኒስቲቲዩት የአሜሪካ የኢቦላ ላይቶ ማቆያ ማዕከል በኬንያ ውስጥ የማቋቋም ዕቅዱ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሳይደረግበት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ለዜጎች ሕይወት አደጋ ነው የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የሕዝብ ጥቅም የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ቀጣይ የችሎት ስሚ እስኪካሄድ ድረስ ቅድሚያ ሰጥቶ ጊዜያዊ ዕግድ ማስተላለፉን አስታውቋል።

በችሎቱ ውሳኔ መሠረት ከሳሽ በይፋ ጥያቄውን በ24 ሰዓታት ውስጥ ለመንግሥት ማቅረብ ያለበት ሲሆን፣ መንግሥትም በ48 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ መስጠት አለበት። ይህንንም ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ውሳኔ ለመስጠት በመጪው ማክሰኞ ይሰየማል።

በአሁኑ ጊዜ በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኡጋንዳ ውስጥ የተያዙ ሰዎች የተገኙበት የተለየ የኢቦላ ቫይረስ አስካሁን 1,077 ሰዎች መያዛቸው ሲጠረጠር 246 ሰዎች በቫይረሱ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተዘግቧል።