ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ

ታትሟልከ 5 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ጋዛ ውስጥ የሚቆጣጠረውን የግዛት ስፋት ወደ 70 በመቶ እንዲያሳድግ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገለጹ።

ሐሙስ ዕለት በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አሁን ሀማስን እያስጨነቅን ነው። አሁን የሰርጡን 60 በመቶ ግዛት እንቆጣጠራለን፤ ይህንን ታውቃላችሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም “አሁን 50 [በመቶ] ላይ ነን፤ ወደ 60 እንሻገራለን። የሰጠሁት ትዕዛዝ ወደ” ብለው ንግግራቸውን ገታ ሲያደርጉ ከታዳሚዎቹ መካከል አንዱ ወደ “100” ብሎ መልሷል።

ኔታንያሁ ቀጥለውም፤ “ደረጃ በደረጃ እንሂድ። ከሁሉም በፊት 70 [በመቶ]፤ ከዚያ እንጀምር። በሁሉም አቅጣጫ እየገፋናቸው ነው፤ ከርዝራዦቹ ጋር እንጋፈጣለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

እስራኤል በጋዛ ያላትን ቁጥጥር ለማስፋት የምታደረግው እንቅስቃሴ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መሪነት በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ከተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የሚቃረን ነው።

ኔታንያሁ ይህንን እቅዳቸውን የተናገሩት፤ እስራኤል ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በተቃራኒ ጋዛ ውስጥ ጥቃት መፈጸሟን በቀጠለችነት ወቅት ነው። እስራኤል እና ሀማስ የትራምፕን የጋዛ የሰላም ዕቅድ ለማስቀጠል በአሜሪካ አሸማጋይነት በሚካሄደው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ዘላቂ መፍትሄ አላመጡም።

ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 738 ፍልስጤማውያን እንደተገደሉ የተባበሩት መንግሥታት እንደ ተአማኒ ምንጭ የሚቆጥረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ጥቅምት ላይ በአሜሪካ አደራደሪነት የተኩስ አቁም በተደረገበት ወቅት እስራኤል ጋዛ ውስጥ የሚኖራት ቁጥጥር 53 በመቶ እንደሚሆን ስምምነት ነበር። ከተኩስ አቁሙ ወዲህ የእስራኤል ጦር ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ያለውን ቁጥጥር ከ60 በመቶ በላይ እንዳደረሰ ኔታንያሁ በተለያዩ ይፋዊ ንግግሮቻቸው አረጋግጠዋል።

በስምምነቱ መሠረት የእስራኤል ጦር ‘ቢጫ መስመር’ ተብሎ ወደ ሚታወቀው መስመር ማፈግፈግ ነበረበት። ይህ ተግባራዊ ቢሆን እስራኤል ጋዛ ውስጥ ያላት ቁጥጥር በ53 በመቶ ይገደብ ነበር።

ባለ 20 ነጥቡ የሰላም እቅድ ያስቀመጠው ቀጣዩ ደረጃ ሀማስ ትጥቅ እንዲፈታ እና የእስራኤል ወታደሮች እንዲወጡ ማድረግ ነበር። ይሁን እንጂ በእስራኤል እና በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን መካከል የሚደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር ተገትቷል።

ረቡዕ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ፤ አገራቸው “የመስከረም 26ቱን [2018 ዓ.ም.] ጭፍጨፋ የመሩትን በሙሉ ለማጥፋት ቃል መግባቷን” በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አስታውቀዋል።

“ሀማስ በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር ጋዛን እንደማያስተዳድር ቃል ገብተናል” ሲሉም ጽፈዋል። በተጨማሪም “ከጋዛ በፈቃደኝነት የማፍለስ ዕቅድ” ሲሉ የጠሩት ሀሳብ “በትክክለኛው ጊዜ እና በትክክለኛው መንገድ” ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ቀኝ አክራሪዎቹ የእስራኤል ባለሥልጣናቱ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጊቪር እና የፋይናንስ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች ከዚህ ቀደም ፍልስጤማውያን “በፈቃደኝነት ማፍለስ” እና አይሁዳውያንን ማስፈር ሲሉ የገለጹትን ዕቅድ በይፋ ሲያቀነቅኑ ነበር።

ይህ አይነቱ ሲቪሎችን በግዳጅ የማፈናቀል ድርጊት የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል።

እስራኤል በዚህ ሳምንት ጋዛ ውስጥ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች አምስት ህጻናትን ጨምሮ 10 ሰዎች መገደላቸውን ሆስፒታሎች ተናግረዋል። ህጻናቱ የተገደሉት ረቡዕ ዕለት ጋዛ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሕንጻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ነው።

የእስራኤል ጦር ባወጣው አጭር መግለጫ “በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ሁለት ማዕከላዊ የሀማስ አሸባሪዎችን” መግደሉን ተናግሯል። ማንነታቸውን ግን አልገለጸም። የጥቃቱ ዒላማ የነበረው ከታዳጊ ሴት ልጁ ኢስራ ጋር የተገደለው የሀማስ እዝ አዛዥ ኢማድ አስሊም እንደሆነ ተገምቷል።