
ታትሟልከ 3 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
ልጅ መስለው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት የሚሞክሩ አዋቂ ስደተኞችን ለመቆጣጠር የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሣሪያ ሊተገበር መሆኑ ተገለጸ።
በሚቀጥለው ዓመት በዩኬ ድንበር ላይ የሚዘረጋው የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሣሪያ የሰዎችን ገጽታ መለየት የሚችል ነው።
ጥገኝነት ጠያቂዎችን ፎቶ በማንሳት ዕድሜያቸውን የሚለየውን ኤአይ የሚሠራው መተግበሪያ አምራች ኩባንያ መሣሪያውን እንዲሞክር ፈቃድ ተሰጥቶታል።
የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ቴክኖሎጂው “ሥርዓቱን ለመበዝበዝ የሚሞክሩ አዋቂ ስደተኞችን” መለየትን ቀላል ያደርጋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራዎችን ኤአዩ “ውጤታማ” መሆኑን እንዳሳዩ ተገልጿል።
ሂውማን ራይትስ ዋች በበኩሉ “ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ቴክኖሎጂ” መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት አሠራሩን እንዲሰርዝ አሳስቧል።
የጥገኝነት ጥያቄያቸው መታየት ያለበት ለአደጋ የተጋለጡ ሕጻናትን የተባባሰ ችግር ውስጥ የሚከት እንደሆነም አስጠንቅቋል።
ብቻቸውን የሆኑ ታዳጊ ስደተኞች ጉዳያቸው የሚታየው በጥገኝነት ጠያቂዎች መሥሪያ ቤት ሳይሆን ለሕጻናት እንክብካቤ በሚሰጥ ተቋም አማካኝነት ነው።
ኢንግሊሽ ካናልን የሚያቋርጡ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ አንጻር መተግበሪያው አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል።
እስከ ሰኔ 2025 ድረስ 111,084 ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ዩኬ የገቡ ሲሆን፤ ከዚያ በፊት ከነበረው ዓመት 14% ጭማሪ ታይቷል።
በ2026 እስከ ሚያዝያ ድረስ ልጆች መሆናቸውን የገለጹ ስደተኞች ቁጥር ከ6,400 በላይ መሆኑ ተገልጿል። ከእነዚህ መካከል 43% የሚሆኑት አዋቂ ሆነው ተገኝተዋል።
የዩኬ መንግሥት ገለልተኛ መርማሪ እንዳለው ከሆነ፤ አምና ልጆች ተብለው ከተፈረጁ ስደተኞች መካከል አዋቂዎች የተገኙ ሲሆን፤ ሕጻናት ሆነው ሳለ በስህተት በዕድሜ የገፉ ዝርዝር ውስጥ የገቡም አሉ።
“ምርመራ ባለመደረጉ አንዳንድ የዕድሜ ፍረጃዎች የተሳሳቱ ናቸው። ይህም አስጊ ነው፤ በተለይ ሕጻናት የሚገባቸውን ከለላ ሳያገኙ መቅረታቸው ያሳስባል” ይላል ሪፖርቱ።
የዩኬ መንግሥት መፍትሔ አድርጎ ያቀረበው በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠራ ገጽታ መለያ መሣሪያ (AI facial recognition) መጠቀምን ነው።
ኤአዩ የሚገነባው አክተር ኮምፒውተርስ ሊሚትር በተባለ ኩባንያ ሲሆን፤ ቴክኖሎጂው በ2027 አጋማሽ ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል።
ለኩባንያው በሦስት ዓመታት ውስጥ 322,000 ፓውንድ እንደሚከፈለው ተገልጿል።
የድንበር ደኅንነት እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ሚኒስትር አሌክስ ኖሪስ “ራሳቸውን ልጅ አስመስለው የሚያቀርቡ አዋቂ ስደተኞች ለሕጻናት መድረስ ያለበትን አስፈላጊ ድጋፍ አሰናክለዋል” ብለዋል።
“ሥርዓቱን የሚበዘብዙትን በአፋጣኝ ለይቶ ለማስወገድ” ቴክኖሎጂው አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።
የዩኬ የአገር ውስጥ መሥሪያ ቤት የተለያዩ አገራት ዜጎችን ፎቶ በማንሳት ሙከራ ማድረግ ጀምሯል።
ሆኖም በምርመራ የተገኘውን መረጃ ተጠቅሞ እስካሁን ውሳኔ አላስተላለፈም።
በቀጣዩ ዓመት በዶቨር ከተማ በሚገኘው ‘ዌስተርን ጀት ፎይል’ የጥገኝነት ጠያቂዎች ማዕከል ቴክኖሎጂው እንደሚተገበር ተገልጿል።
እስካሁን የስደተኞችን ዕድሜ የሚለዩት ባለሙያዎች ናቸው። ሰነዶችን ከማመሳከር በተጨማሪ የኤክስሬይ እና ኤምአርአይ ምርመራ ያደርጋሉ።
አጠራጣሪ ሁኔታ ሲገጥም ባለሙያዎች ዕድሜ ለመለየት ከሚያደርጉት ግምገማ በተጨማሪ ኤአይ ጥቅም ላይ ይውላል።
የዩኬ መንግሥት ቴክኖሎጂውን “ወጪ ቆጣቢ” ቢለውም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተችተውታል።
በሂውማን ራይትስ ዋች የኤአይ ተመራማሪ አና ባሲራሊ “ስደተኛ ልጆችን ለመለየት የተዘረጋውን እጅግ የተበላሸ አካሄድ መንግሥት መሰረዝ አለበት” ብለዋል።
“ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ከለላ ለመስጠት ያልተረጋገጠ ቴክኖሎጂ መጠቀም ሕሊና ቢስነት እና ጭካኔ ነው” ሲሉም አክለዋል።
የገጽታ ልየታ ቴክኖሎጂው ውጤታማነቱ እንደማይታወቅ ጠቅሰው፤ለአደጋ የተጋለጡ ሕጻናትን ኢ-ሰብአዊ ለሆነ ሒደት ማጋለጥ መብታቸውን የሚጋፋ እንደሆነም ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በመደብሮች እና መጠጥ ቤቶች ጥቅም ላይ እንደሚውል የተናገሩት የኤአይ ተመራማሪዋ “በስደተኞች ማዕከላት መተግበር ከሥነ ምግባር ያፈነገጠ ነው” በማለት ኮንነዋል።
