
ታትሟል31 ግንቦት 2026, 08:01 EAT
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ዘገባ የወሲባዊ ይዘት አለው
ልዩ መርማሪው ግሬግ ስኳየር እና ቡድኑ ‘ሉሲ’ ሲሉ ስያሜ ያወጡላትን የወሲባዊ ጥቃት ተጎጂ ለማዳን ያደረጉት ጥረት እክል ገጥሞታል።
የሉሲ ምሥሎች ማንነት ሊደረስበት በማይችለው እና በልዩ ሶፍትዌር ብቻ በሚገናኘው ምሥጢራዊ የበይነ መረብ (ኢንተርኔ) መድረክ ላይ እየተጋሩ ነበር።
መርማሪው ግሬግ ኢንተርኔቱ በዚህ መጠን ምሥጢራዊነት ያለው ቢሆንም አጥቂውን ምሥሎቹ ላይ መለየት የሚያስችሉ የማንኛውንም ምልክቶች “ዱካ ለማጥፋት” ተጠቅሟል ይላል። ሉሲ ማን እንደሆነች፣ የት እንዳለች፣ ማን እንደነበረች ለማወቅ አይቻልም ነበር።
በኋላ ላይ የ12 ዓመቷን ልጅ አድራሻ ለማወቅ የሚያስችለው ፍንጭ ዐይኑን አፍጥጦ በግልጽ ዕይታ ውስጥ እየታየ መሆኑን ደረሰበት።
ግሬግ በአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ልዩ ቡድን ውስጥ ነው የሚሠራው። ቡድኑ ወሲባዊ ጥቃት ውስጥ ያሉ ሕፃናትን የሚለይ ነው።
የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ቡድን ግሬግን እና ሌሎች የፖርቹጋል፣ የብራዚል እና የሩሲያ መርማሪዎችን በማሰልጠን አምስት ዓመታት ቆይቷል። በእነዚህ ዓመታት መርማሪዎቹ ከአፈና ጀምሮ በምሥጢራዊ ኢንተርኔት ወሲባዊ ይዘት ያላቸውን ምሥሎች በስፋት የሚያሠራጩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ይህ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት በአብዛኛው እንዴት እንደሚደረስበት ያሳያል። መዝገቦቹ መፍትሔ የሚያገኙት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሳይሆን በሚጋሩ ምሥሎች ወይም የመልዕክት ለውውጦች ላይ የሚገኙ ጥቃቅን ፍንጮችን በመከተል ነው።

ግሬግ ሥራውን ሲጀምር የያዘው የሉሲ መዝገብ የረጅም ዘመን ቁርጠኝነቱ መነሻ እንደሆነ ይጠቅሳል።
ሉሲ የሴት ልጁ ዕኩያ መሆኗ በጣም እንዲረበሽ አድርጎታል። በመኝታ ክፍሏ እንዳለች ጥቃት ሲፈጸምባት የሚያሳይ አዲስ ፎቶግራፍ በተደጋጋሚ እየተጋራ ነበር።
ቡድኑ በፎቶዎቹ ከሚታየው የኤሌክትሪክ ሶኬት ዓይነት በመነሳት ሉሲ ሰሜን አሜሪካ ውስጥ እንደሆነች አውቀዋል።
በወቅቱ ማኅበራዊ የትስስር መድረኮችን ተቆጣጥሮ የነበረውን ፌስቡክ ከተለጠፉ የቤተሰብ ፎቶዎች ውስጥ ሉሲ ትገኝ እንደሆነ ለማወቅ እርዳታ ጠየቁ። ይሁን እንጂ ፌስቡክ ምንም እንኳ ፊት መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ያለው ቢሆን ይህንን ግን ማድረግ አልቻለም።
ስለዚህ ግሬግ እና ባልደረቦቹ በሉሲ በነበረችበት ክፍል ውስጥ ማየት የቻሉትን ፍንጮች ሁሉ ትኩረት ሰጥተው አጠኑ ። ሊያግዝ ይችላል ብለው ያሰቡትን ማንኛውንም ቁስ አንሶላውን፣ ልብሶቿን፣ አሻንጉሊቶቿን ተነተኑ።
እናም አነስተኛ ፍንጭ አገኙ። ቡድኑ በአንዳንድ ምሥሎች ላይ የሚታየው ሶፋ በመላው አገሪቱ ሳይሆን በአንዳንድ ግዛቶች ውስጥ እንደሚሸጥ ደረሱበት። ሶፋው የተወሰነ የሽያጭ ሥርጭት ያለው ነው።
እንዲያም ሆኖ ግን 40 ሺህ ገዢዎች አሉት።
“በዚህ የምርመራ ወቅት በአሜሪካ 29 ግዛቶችን እየተለመከትን ነበር። ይህም በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አድራሻዎችን የሚመለከት ነው። እና ይህም በጣም አስፈሪ ተግባር ነው” ይላል ግሬግ።

ከዚያም ቡድኑ ተጨማሪ ፍንጭ ፈለገ። ያኔ ነው በሉሲ መኝታ ቤት ውስጥ ተራ ነገር መስሎ በግልጽ የሚታየውን የግድግዳ ጡብ ያለችበተን ለማወቅ ፍንጭ አድርገው የተገነዘቡት።
ግሬግ “ስለዚህ ጉግል ላይ ጡብ መፈለግ ጀመርኩ። እናም ብዙም መፈለግ ሳይኖርብኝ የጡብ ኢንዱስትሪ ማኅበርን አገኘሁ” ይላል።
“እና በስልክ ያገኘኋት አንዲት ሴት ጥሩ ጥያቄ አቀረበችልኝ። ‘የጡብ ኢንዱስትሪው ምን ሊረዳህ ይችላል?’ ስትል።”
በመላው አገሪቱ ለሚገኙ የጡብ ባለሙያዎች ምሥሉን ለማጋራት እርዳታዋንም ለገሰችኝ። ምላሽ ወዲያው እንዳገኘም ይናገራል።
ካገኛቸው ሰዎች መካከል ጆን ሀርፕ የተባለ የጡብ ባለሙያ ከአውሮፓውያኑ 1981 ጀምሮ በጡብ ሽያጭ ላይ የተሰማራ ነው።
“ጡቡ ሮዝ የመሰለ ቀለም ያለው እንደሆነ እና ትንሽ የከሰል ድርብ እንዳለው አስተዋልኩ። ስምንት ኢንች ስፋት ያለው ጡብ እና አራት ማዕዘን ቅርፅ ያለው ነው” የሚለው ጆን፤ “ይህን ስመለከት ጡቡ ምን ዓይነት እንደሆነ በእርግጠኝነት አወቅኩ” በማለት ያክላል።
ለመርማሪው ግሬግ ጡቡ “ፍሌሚንግ አሊሞ” የተባለ እንደሆነ ተነገረው።
“ይህን ጡብ ኩባንያችን ከ60ዎቹ መጨረሻ እስከ 80ዎቹ አጋማሽ ድረስ ያመረተው ነው። እና እንዲህ ዓይነት ሚሊዮን ጡቦቹን ሸጫለሁ” ይላል።

በመጀመሪያ ግሬግ በዲጂታል የተመዘገበ የደንበኞች ዝርዝር አገኛለሁ ብሎ በመጠበቅ ደስተኛ ነበር። ይሁን እንጂ ጆን ሀርፕ የሽያጭ ማስረጃው ለአስርት ዓመታት በወረቀት የተፃፈ ክምር መሆኑን አረዳው።
ነገር ግን ስለ ጡቡ ቁልፍ ፍንጭ እንደገለጸለት ይናገራል።
“እንዲህ አለኝ ‘ጡቦቹ ከባድ ናቸው፤ ስለዚህም ረጅም ርቀት አይጓጓዙም።'”
ይህ ሁሉንም ነገር ቀየረው። ቡድኑ የደንበኞችን ዝርዝር በማገላበጥ ከጆን ሀርፕ የጡብ ፋብሪካ በ100 ማይል ዙሪያ የሚኖሩ ደንበኞች ላይ በማተኮር ቁጥሩን ቀነሱ።
ከ40 እና ከ50 ሰዎች ዝርዝር የማኅበራዊ የትስስር ገፃቸውን ማግኘት ቀላል ነበር። ያኔ ነው የሉሲን ፎቶ ዘመዷ ከምትመስል ሴት ጋር ፌስቡክ ላይ ያገኙት።
የሴቷን አድራሻ አገኙ። ከዚህ አድራሻ በመነሳት ከሴቷ ጋር አብረው የኖሩ እና የተገናኙ ሌሎች አድራሻዎችን ማግኘት ቻሉ።
ይህም ሉሲ ልትገኝበት የምትችለውን አድራሻ የበለጠ አጠበበው። ይሁን እንጂ መረጃ ለማግኘት በር ለበር መሄድ አልፈለጉም። አደራሻውን ከተሳሳቱ ተጠርጣሪው በሕግ አካላት ዐይን ውስጥ መግባቱን አውቆ እንዲሰወር ዕድል መስጠት ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ ግሬግ እና ባልደረቦቹ የእነዚህን ቤቶች ፎቶ ለጡብ ባለሙያው ጆን ሀርፕ መላክ ጀመሩ።
‘ፍሌሚንግ አሌሞስ’ የተባለው የጡብ ዓይነት በየትኞቹም ቤቶች አይታይም። ምክንያቱም ቤቶቹ በሌሎች ቁሶች ተሸፍነው ነበር።

ነገር ግን የምርመራ ቡድኑ የቤቶቹን የአሠራር ዘይቤ እና ውጫዊ ሁኔታ በመመልከት ጡቦቹ ለሽያጭ በቀረቡበት ጊዜ ተሠርተው ሊሆን ከቻለ በሚል ጆር ሀርፕ እንዲያጤን ጠየቀው።
ቤቱን ፎቶ አንስተን ለጆን ‘ይህ ቤት ውስጡ ጡብ ሊኖረው ይችላል?’ እያልን እየላክን ነበር ይላል ግሬግ።
በመጨረሻም አንድ ነገር አገኙ። ጆን ሀርፕ ግድግዳው ላይ ‘ፍሌሚንግ አሌሞ’ የተባለው ጡብ ያለው ቤት ብሎ ያመነው አድራሻ በሶፋ የደንበኞች ዝርዝር ውስጥ ተገኘ።
“ስለዚህ እዚህ አድራሻ ላይ አተኮርን። . . . እና በግዛቲቱ መዝገቦች፣ በመንጃ ፈቃድ፣ በትምህርት ቤት መረጃ መሠረት በዚህ አድራሻ ማን እንደሚኖር የማረጋገጥ ሂደቱን ጀመርን” ሲል ግሬግ ያብራራል።
የምርመራ ቡድኑ ሉሲ የምትኖርበት ቤት የእናቷ ፍቅረኛ የሆነው የወሲብ ወንጀለኛ መሆኑን ተገነዘበ።
በሰዓታት ውስጥ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መኮንኖች ሉሲን ለስድስት ዓመታት ሲደፍር የነበረውን ወንጀለኛ በቁጥጥር ስር አዋሉ። በኋላም ከ70 ዓመት በላይ እስር ተፈረደበት።
የጡብ ባለሙያው ጆን ሀርፕ ለረጁም ዓመታት የማደጎ ልጆችን ሲንከባከብ የነበረ በመሆኑ ሉሲ በመገኘቷ ደስታው ወደር አልነበረውም።
“ቤታችን ውስጥ ከ150 በላይ የተለያዩ ልጆች ነበሩ። ሦስት ልጆችን በጉዲቻ ወስደናል። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት ይህን በማድረጋችን ጥቃት የደረሰባቸው በርካታ ልጆች ቤታችን ነበሩ” ይላል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የሥራው ጫና በግሬግ የአእምሮ ጤና ላይ ጠባሳ ማሳረፍ ጀመረ። ሥራ ላይ ካልሆነ አልኮልን ወዳጁ ማድረጉን ያምናል።

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት
ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ
End of podcast promotion
ይህ በእንዲህ እንዳለ ራሱን ማጣቱን የሚናገረው ግሬግ “ምን እንደሚወድ እንኳ ማወቅ አልቻልኩም። ቀን ቀን ሁሉም ጓደኞቼ ወንጀሎኞች ናቸው። . . .ሁሌም ቀኑን ሙሉ የሚያወሩት ስለፈጽሙት ዘግናኝ ነገር ነው” ይላል።
ከዚያም ብዙ ሳይቆይ ትዳሩ ፈረሰ፤ እና ራሱን ስለማጥፋት ማሰብ እንደጀመረ ይናገራል።
ባልደረባው ፒት ማኒንግ የጓደኞውን ስቃይ አስተውሎ እርዳታ እንዲያገኝ አበረታታው።
“በጣም ኃይል እና ብርታት የሚሰጥህ ነገር ቀስ እያለ ሲሰብርህ ማየት በጣይ ከባድ ነው” ይላል ፒት ማኒንግ።
ግሬግ ስሜትን ሳይደብቁ ማውጣት ለመዳን የመጀሪያው እርምጃ እንደሆነ እና የሚኮራበትን ሥራ ለመቀጠል እንዳስቻለው ይገልጻል።
“በቴሌቪዥን ከመመልከት ወይም ከመስማት ይልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችል ቡድን አባል በመሆኑ ክብር ይሰማኛል። ለማስቆም በሚደረገው ፍልሚያ ግንባር ላይ መገኘትን እመርጣለሁ።”
ባለፈው የበጋ ወቅት ግሬግ አሁን 20 ዓመት የሆናትን ሉሲን ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝቷታል።
አሁን ስለደረሰባት በደል ማውራት መቻሏ በዙሪያዋ ባላት ድጋፍ ምክንያት መሆኑን ለግሬግ ነግራዋለች።
“የበለጠ ተረጋግቻለሁ። ስለ ጥቃቱ ከሰዎች ጋር ለመዋውራት ብርታቱ አለኝ። ከዚህ ቀደም አድርጌው የማውቀው ነገር አይደለም።”
ጥቃቱ እንዲቆም እየጸለየች በነበረችበት ወቅት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ጣልቃ ገብቶ ሆምላንድ ሴኩሪቱ ጥቃቷን መቋጨቱን ትናገራለች።
“የሰለቸ ንግግር ቢመስልም ፀሎቴ ተመልሷል።”
ቢቢሲ ፌስቡክ ሊሱን ለማግኘት ፊት የሚለየውን ቴክኖሎጂውን ለምን ለመጠቀም እንዳልቻለ ጠይቋል።
“የተጠቃሚዎችን ግለኝነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን የሕግ ሂደት መከተል አስፈላጊ ነው። ነገር ግን የሕግ አስከባሪዎችን በቻልነው ልክ እንደግፋለን” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
