Yared Tibebu

ሃገረ ትግራይ?

ርዕሱ አስደንጋጭ ደራሲው ቆራጥ ሞጋች፣ የፍትህና መብት ተሟጋች ሲሆን ምን ታደርገዋለህ? በኢትዪጵያዬ ተስፋ እቆርጥና ድብርት ሊጨመድደኝ ሲል የሆነች ደፉር የማራቶን ጀግኒት፣ ወይም እንደ ታዬ ደንደአ ያለ የመንግስት ባለሥልጣን፣ ወይም እንደ ሙሉጌታ አረጋዊ ያለ የፍትህ ጠበቃ ብቅ ይልና “ይሄ ሁሉ ጀግና ያላት አገርማ ምንም አትሆንም ቀና በል” ብለው ያረጋጉኛል።

በመግቢያው ላይ እንደዘከረው ሙሉጌታ ያለውን ሁሉ አንጠፍጥፎ ነው የሰጠን።መሳሳት አላሳየንም። የሃገረ መንግሰ‍ት ደራሲያን አሉላዎች ካሉን ሙሉጌታ ፊታውራሪያቸው ነው። መንግስትን ብቻ ሳይሆን ጓደኞቹን ቤት አዝማዱን፣ የብሄረሰብ ልሂቃኑን፣ የጠረባ ቡድኖቹን አንዳቸውንም አልፈራም። ከፎቅ በዘለለው በተስፋዬ ደበሳይና እጁን ለደርግ ሲሰጥ ቢገደል እንኳ “ያለውን ሁሉ እንደሰጠ” ሳይግደረደር ወደ ደርግ የርሸና ሰልፍ እንደተቀላቀለው ብርሀነ መስቀል፣ ሙሉጌታም “እንካችሁ፣ ያማጥኩትን ጭንቀት ሁሉ ተቀበሉኝ” ብሎ ራሱን ለወዳጅ ዘመድ ሰይፍ አቅርቧል።

ይህን የመሰለ ልዕልና ለሁላችን የተሰጠ አይደለም። አሁንማ ለጥቂቶችም የተሰጠ አይደለም። እንደ ግሪኩ ፈላስፋ እንደ ሶቅራጥስ የመስዊያ ዋንጫውን ብድግ አድርጎ መጨለጥን ይጠይቃል። ለዚህ የታደሉ ደግሞ በታሪክ በጣም አልፈው አልፈው በየመቶ አመቱ አንዴ ብቅ የሚሉ ናቸው። በነርሱ ዘመን መወለድ ራሱም እድል ነው። ባንደርስባቸው እንኳ እንደነሱ ለመሆን እንድንቃትት ይጋብዙናልና።

በሃገረ ትግራይ ምርምሩ ሙሉጌታ ታሪክ ሠራ መባል አይደለም ያለበት፣ በማሰብ ሀይሉና ራሱን አሳልፎ በሰጠበት የትንተና አቅሙ የታሪክ ሰዎችን ተርታ ተቀላቀለ እንጂ። የአሉላን፣ የገብረህይወት ባይከዳኝን፣ የብርሀነ መስቀል ረዳን ወዘተ ሰልፍ ተቀላቀለ ነው መባል ያለበት። ትልቅ መታደል ነው።

ይህ ዛሬ መፅሀፉን ስጨርስ የተሰማኝ ጥልቅ ስሜት ነው፣ በቅርቡ በመፅሀፍ ዳሰሳ እመለስበታለሁ። እስከዚያው እያነበባችሁ ጠብቁኝ።

See less