June 24, 2026

ከመጪው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ለሶስት ሳምንት በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ ከሚቀርቡ አጀንዳዎች መካከል የህገ መንግስት ማሻሻያ እንዲሁም የመንግስት አደረጃጀት እና ቅርጽ እንደሚገኙበት ይፋ ተደረገ። የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ጉዳይ እንዲሁም የምርጫ ስርዓት በሀገር አቀፍ ጉባኤው ለምክክር ከሚቀርቡት አጀንዳዎች ውስጥ ተካትተዋል።

የምክክር አጀንዳዎቹን ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 17፤ 2018 ምሽት ይፋ ያደረገው፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አዳራሽ በተከናወነው በዚህ መርሃግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ “አጀንዳዎቹ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎችን አወያይተን ያሰባሰብናቸው ናቸው” ብለዋል።

አጀንዳዎቹ የህዝብን አካታችነት ባረጋገጠ መንገድ ከህዝቡ እና ተቋማት የተሰበሰቡ መሆናቸውን ዋና ኮሚሽነሩ በንግግራቸው አመልክተዋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ጥናት እና ምርምሮችንም በአጀንዳ ግብዓትነት መጠቀማቸውን ፕሮፌሰር መስፍን በተጨማሪነት ገልጸዋል።

https://youtube.com/watch?v=WJYR8agdwfQ%3Fstart%3D24%26feature%3Doembed

ሀገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽኑ ስምንት አጀንዳዎችን የመረጠው “እጅግ መሰረታዊ” መሆናቸውን እና “ሀገራዊ ፋይዳቸውን” ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። ከስምንቱ አጀንዳዎች ውስጥ ውስጥ ኮሚሽኑ በቀዳሚነት ያስቀመጠው “የሀገር ግንባታ” ጉዳይ ነው።

በዚህ አጀንዳ ስር የሀገር ግንባታ አቅጣጫ ማስቀመጥ፣ የማንነት እና የባለቤትነት እንዲሁም የታሪክ እና ማንነት ጉዳዮች መካተታቸውን ፕሮፌሰር መስፍን በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል። የብዝሃነት አስተዳደር ጉዳዮች፣ የቋንቋ ጉዳዮች፣ የባህል፣ ታሪክ እና ቅርስ ጥበቃ ጉዳዮችም በዚሁ አጀንዳ ስር ለምክክር እንደሚቀርቡም ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በሁለተኛ አጀንዳነት ያስቀመጠው “የመንግስት አደረጃጀት እና ስርዓት” ጉዳይን ነው። በዚህ አጀንዳ ውስጥ የፖለቲካ ስርዓት ግምገማ፣ የምርጫ ስርዓት፣ አማራጭ የፖለቲካ ስርዓቶች እንዲሁም የዴሞክራሲ ብሂል ማጎልበትን የሚመለከቱ ጉዳዮች በንኡስ አጃንዳነት ተዘርዝረዋል።

https://youtube.com/watch?v=uP-7tcpPwEY%3Ffeature%3Doembed%26enablejsapi%3D1

የመንግስት አደረጃጀት ስርዓት፣ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት አይነት፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት፣ የህገ መንግስት ማሻሻያ፣ የፌደራል ዋና ከተማ ጉዳይ እና የብሔር ብሔረሰቦች ትርጓሜ ጉዳዮችም በዚህ አጀንዳ ስር የተካተቱ ናቸው። በሁለተኛው አጀንዳ ስር ለምክክር ከሚቀርቡ ጉዳዮች ውስጥ የፌደራል መንግስት እና የክልል መንግስታት የስልጣን ዘመን እንዲሁም የፌደራል እና የክልል መንግስታት ግንኙነቶች ይገኙበታል።

ሶስተኛው የሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ አጀንዳ፤ የፌደራል ከተሞች በሆኑት የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች አደረጃጀት ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። የአዲስ አበባ ከተማ በጀት እና ከኦሮሚያ ክልል ጋር ያላት ግንኙነት፣ የከተማይቱ የስራ ቋንቋ ጉዳይ እንዲሁም የድሬደዋ ከተማ ውክልና ጉዳዮች በዚሁ አጀንዳ ስር ምክክር እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በአራተኛነት ያሳወቀው አጀንዳ የሃይማኖት ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። በአምስተኛ ደረጃ ላይ በተቀመጠው “የተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነት እና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች አጀንዳ” ስር ለምክክር ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል “የጸጥታ ተቋማት ገለልተኝነት” ጉዳይ ይገኝበታል።

https://youtube.com/watch?v=RAbseYF8ABc%3Ffeature%3Doembed%26enablejsapi%3D1

የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የአርብቶ እና አርሶ አደሮች ጉዳዮችን በሚመለከተው አጀንዳ ስድስት ስር የመሬት ባለቤትነት እና የህዝብ ቆጠራ በንዑስ የምክክር አጀንዳነት ተይዘዋል። በሰባተኛ አጀንዳነት በተያዘው “የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች” የተጠቃለሉት ደግሞ የተገለሉ ቡድኖች መብት ጥበቃ፣ የጣምራ ዜግነት ጉዳዮች፣ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እና ተጠያቂነትን የሚመለከቱ ንዑስ አጀንዳዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በስምንተኛነት የያዘው የመጨረሻ አጀንዳ የሰላም ግንባታ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። በዚህ አጀንዳ ስር የሽግግር ፍትህ፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ማጠናከር፣ የእርቅ ጉዳዮች እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ቀርበው ምክክር እንደሚደረግባቸው ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]