በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ

አገዛዙ ስልጣን ከያዘበት ዕለት አንስቶ ለዘመናት በወንድማማችነት መከባበር አብሮ በኖረ ሕዝብ መካከል ግጭትና እልቂት እንዲፈጠር ሆን ብሎ አጀንዳዎችን በመምዘዝ አያሌ ጥፋቶችን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም መቆየቱን በተደጋጋሚ ያየንና የሰማነው ሓቅ ነው። ይህ አልበቃ ብሎት—ባቀደው ልክ ሕዝቡ እርስ በእርሱ ባለመተላለቁ የተቆጨ ይመስል የመጨረሻውን የሃይማኖት ካርድ ስቧል። ይህንን እኩይ እቅዱንም ከላይ እስከ ታች ባለው መዋቅሩ በሚገኙት ‘አመራሮች’ በተደጋጋሚ በአደባባይ ገልጧል።

ከዚህ ቀደም በወለጋ እና በአርሲ በሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና አገልጋዮች ላይ የተፈጸመው ግድያ እና ማሳደድ፣ በጦርነት ስም በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ በአብያተ-ክርስቲያናት እና መስጅዶች ላይ የተቃጣው ውድመት እና የምዕመናን ዕልቂት፤ በዚህም ፍትሕ በጠየቁና በተለይም በሁለቱ ሀይማኖቶች ላይ በአገዛዙ ሴራ እየደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ለዓለም ባጋለጡ ንጹሀን ላይ የደረሰው እስራት አገዛዙ የመጨረሻዋን ካርድ ስለመምዘዙ በቂ ማሳያዎች ናቸው።

አሁን ደግሞ በዳንግላ ከተማ በሚገኘው የኹጥባ መስጂድ ኢማም ሸይኽ ሱፍያን ሙሀመድ ትናንት ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ሳሉ በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።

በተመሳሳይ ሰኔ 17 ቀን 2018 ዓ.ም በከሚሴ ሀገረ ስብከት የባቲ ጓሀ ጽባህ አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ፍሬው ሀብታሙ በባቲ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተከፈተባቸው ተኩስ ሕይወታቸው አልፏል።

በእምነት አባቶች እና ምዕመናን ላይ የሚደርሰውን ተደጋጋሚ ጥቃትን ለማስቆምና ፍትሕ ለማስፈን የሚሻ መዋቅር አለመኖሩን አውቆ ምዕመኑ ተደራጅቶ ራሱን እና ሀይማኖቱን ከጥቃት እንዲጠብቅ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም ካለፉት አመታት ወዲህ የተደራጀ መዋቅራዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታዮች በአገዛዙ ከተደገሰላቸው የፖለቲካ የጥፋት ሴራ እርስ በእርስ እንዲጠባበቁና በዘመናቸው ሁሉ ያሳዩትን የወንድማማችነት እና የመከባበር ዕሴት አሁንም አስጠብቀው እንዲኖሩ አደራ እንላለን።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ ለሸይኽ ሱፍያን ሙሀመድ እንዲሁም ለቀሲስ ፍሬው ሀብታሙ ቤተሰቦች እና ወዳጆች መፅናናትን ይመኛል።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ

ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ