
ታትሟል4 ሀምሌ 2026
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ
በሥርዓተ-ፆታ ፍትህ ላይ የሚሠራ ቼን (Chayn) የተባለ ድርጅት ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሠረት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች እና ባለሥልጣናት በምሥል ላይ ከተመሠረቱ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ከፈቃደኝነት ይልቅ ዕርቃንነት ላይ በማተኮር ሴቶች ላይ በደል እየፈጸሙ ነው።
ፓኪስታናዊቷ ተዋናይት አይሻ ዑመር በቼን የቀረበውን ትችት ትደግፋለች። የእርሷ እና የሌሎች ሴቶች ተሞክሮዎች በድርጅቱ የምርምር ሪፖርት ውስጥ ተካትተዋል።
የሪፖርቱ ዋነኛ ትኩረት ከሆኑት ሴቶች አንዷ የሆነችውና ማንነቷን ለመደበቅ ሲባል ስሟ ወደ ማህኑር የተቀየረ ሴት እንደምታብራራው፣ ሕይወቷን የቀየሩት ምሥሎች ዕርቃንነትን የሚያሳዩ አልነበሩም። ወሲባዊ ይዘትም አልነበራቸውም። ምሥሎቹ የሚያሳዩት ትከሻዋን የገለጠች እና የምዕራባውያንን አልባሳት የለበሰች ሴትን ነበር።
ይህች የ32 ዓመት ፓኪስታናዊት፣ ትዳሯ ከፈረሰ በኋላ ወደ ልጅነት ቤቷ ተመልሳ እንደነበር ለ’ቢቢሲ ግሎባል ዊሜን’ ተናግራለች። ከቤተሰቦቿ መጽናናትን እና ድጋፍን አገኛለሁ ብላ ተስፋ አድርጋ ብትሔድም፣ በተቃራኒው እሷና ታናሽ ልጇ የገጠማቸው ግን ቸልተኝነት የታከለበት ቀዝቃዛ አቀባበል ነበር።
ወደ ቤተሰቦቿ ከተመለሰች ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗታል። አባቷ እና ወንድሞቿ ግን አሁንም ድረስ አያናግሯትም። ለዓመታት የምታውቃቸው የሥራ ባልደረቦቿ እንኳን ዓይኗን ሊያዩ አይፈልጉም።
ማህኑር፣ አስቸጋሪ ፍቺ እንደሚጠብቃት ቀድሞውኑ አስባ ነበር። ትዳሯ ቀላል አልነበረም። በቤተሰብ ምርጫ ባገባችው ባሏ በትዳር ዘመናቸው ሁሉ የቃላትም ሆነ የአካል ጥቃት ይደርስባት እንደነበር ትናገራለች። ነገር ግን ከሁሉ በላይ ዋጋ ያስከፈላት የግል ሕይወቷ ለሕዝብ መጋለጡ ነበር።
እንደ ብዙዎቹ ወጣት ሴቶች፣ ማህኑር በስልኳ ላይ በርካታ ፎቶዎቿን አስቀምጣ ነበር። የዕለት ተዕለት ሕይወቷን የሚያሳዩ፡ በጥሩ የእራት ጊዜ፣ እንዲሁም ብርሃኑ ለፎቶ በሚያምርበት ጊዜ ራሷን በራሷ ያነሳቻቸው (ሰልፊ) ፎቶዎች ነበሩ።
አብዛኞቹ ለዓመታት የቆዩ ናቸው። ከእነዚህም አንዱ አዲስ የፀጉር ስታይል ከተሠራች በኋላ ፈገግ ብላ የሚያሳይ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር በውጭ አገር የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም ላይ እያለች የሚያሳይ ነው። ሌሎቹ ደግሞ ተራ ሰልፊዎች ነበሩ – አልጋ ላይ ተኝታ፣ ሰደርያ ለብሳ፣ እና የዐይን ኩሏን ለማሳየት ዐይኖቿን ጨፍና የተነሳቻቸው ናቸው።
ከእነዚህ ፎቶዎች ውስጥ አንዳቸውም ለሕዝብ ዕይታ አልተጋሩም ነበር። በፓኪስታን ያለውን የማኅበረሰቧን ወግ አጥባቂ ባህል ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ፎቶዎችን የምታጋራው በጣም አልፎ አልፎ ነበር።
የዩኒቨርሲቲ መምህርት የሆነችው ማህኑር እንደምትለው፣ የቀድሞ ባለቤቷ የዋትስአፕ አካውንቷን እና የግል ፎቶዎቿን ካገኘ በኋላ ለወንድ ዘመዶቿ፣ ለሥራ ባልደረቦቿ እና ለሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ አሠራጭቶባታል።
በተጨማሪም፣ ከጓደኞቿ ጋር የተነሳችውን ፎቶ ከአንድ ወንድ ጋር ብቻ የቆመች ለማስመስል ቆርጦ (ክሮፕ አድርጎ) በማዘጋጀት፣ በመካከላቸው የፍቅር ግንኙነት እንዳለ አድርጎ ማቅረቡንም ገልጻለች።
ማህኑር እንደምትለው፣ ፎቶግራፎቹ እርሷን “የተበላሸ ባህሪ ያላት ሴት” አድርጎ ለመሳል ጥቅም ላይ ውለዋል፤ ይህን ዓይነቱ ክስ ደግሞ በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሕይወትን ጉዞ የሚቀይር እና አንዳንድ ጊዜም ለሞት የሚዳርግ መዘዝ ሊኖረው ይችላል።
ጓደኞቿ፣ ቤተሰቦቿ እና የሥራ ባልደረቦቿ ከእሷ ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም በመቀነሱ፣ ማህኑር በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበራትን ማኅበራዊ ክብር እና በአንድ ወቅት የነበራትን ጠንካራ ስፍራ እንዳጣች ትናገራለች።
“ድምፄን አጣሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። “ከእንግዲህ በሰው ዘንድ እምታይ መስሎ አይሰማኝም፤ ቤተሰቦቼ በአንድ ወቅት ያከብሩኝ ነበር፣ ወንድሞቼም ያከብሩኝ ነበር። በወላጆችሽ ዘንድ ድምፅሽ መከበሩ በጣም ትልቅ ነገር ነው” ትላለች፣ ቀደም ሲል ምክሯን ይጠይቋት እንደነበር እና አሁን ግን ያ ነገር መቅረቱን በማስታወስ።
የማህኑር የቀድሞ ባል አሁን በድጋሚ ትዳር መሥርቷል።

በምሥል ላይ የተመሠረተ ጥቃት ምንድን ነው?
የማህኑርን ታሪክ የሚተርከው ሪፖርት የተዘጋጀው፣ ቼን በተባለ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን በሚያጠና ዓለም አቀፍ ለትርፍ ያልቆመ ድርጅት ነው። በምሥል ላይ የተመሠረተ ጥቃትን ባለሥልጣናትም ሆኑ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በተደጋጋሚ በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዱ ቼን ይከራከራል። ለዚህም ምክንያቱን ሲያስረዳ፣ እነርሱ ምሥል ተኮር ጥቃትን የሚተረጉሙት በዋናነት ከዕርቃነ (ራቁትነት) ጋር በማያያዝ ብቻ እንደሆነ ያነሳል።
“ግልጽ ያልሆኑ ምሥሎች የሚያስከትሏቸው ግልጽ ጉዳቶች” የተሰኘው ይህ የድርጅቱ ሪፖርት፣ ለብዙ ሴቶች ሙሉ ልብስ የለበሱበት ምሥል እንኳን፣ አብዛኛውን ጊዜ ወግ አጥባቂ በሆነው ማኅበረሰባቸው ውስጥ፣ ልክ እንደ ዕርቃን ፎቶግራፍ ሁሉ እኩል አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ይከራከራል።
የሪፖርቱ አዘጋጅ እና የቼን መሥራች የሆነችው ሄራ ሁሴን “አንድ ምሥል ጉዳት ለማድረስ የግድ ራቁት መሆን አይጠበቅበትም” ትላለች።
“አንዳንድ ጊዜ አንድም የሰውነት ክፍል ባይታይ እንኳን እኩል ጉዳት ሊያስከትል ይችላል” የምትለው ሄራ፣ “በምሥል ላይ ከተመሠረተ ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ርዕሰ ጉዳይ በዕርቃንነት ላይ ከማተኮር ይልቅ ወደ ፈቃደኝነት እንዲዞር ማድረግ እንፈልጋለን” በማለት ትገልጻለች።
ለዓመታት ምሥልን መሠረት ስላደረጉ ጥቃቶች የሚደረጉ ውይይቶች ትኩረታቸውን አድርገው የነበሩት “የበቀል ፖርኖግራፊ” (revenge pornography) በሚባለው ያለፈቃድ የግለሰብን አካላዊ ገፅታ የሚያሳዩ ምሥሎችን ለሌሎች ማጋራት፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተመሳስለው በተሠሩ የራቁት ምሥሎች እና ግልጽ የወሲብ ይዘት ባላቸው ምስሎች ላይ ነበር።
ነገር ግን፣ የቼን ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ይህ አመለካከት በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ውርደት፣ ዝና እና ማኅበራዊ ቁጥጥር እንዴት ተግባር ላይ እንደሚውሉ የሚዘነጋ ነው።
ለአንድ ሰው ፍጹም ተራ የሚመስል ፎቶግራፍ ለሌላው ሰው ከባድ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። በአንድ ሰርግ ላይ አንዲት ሴት ስትጨፍር የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ፣ አንዲት ሴት ባሕር ዳርቻ ላይ የተነሳችው ፎቶግራፍ፣ ወይም ደግሞ ያለፈቃዷ የተጋራ ሰልፊ ፎቶ ለዚህ በማሳያነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ባህላዊ ስሱነት
የቼን ሪፖርት እንደሚለው፣ ምሥል ተኮር ጥቃት ብዙውን ጊዜ የሚወሰነው ምሥሉ በያዘው ነገር ሳይሆን፣ ምሥሉ ለምን ተጋራ፣ ለማን ተላከ እና ምን ዓይነት መዘዝ ያስከትላል በሚለው ነው።
ድርጅቱ ከሐምሌ 2025 እስከ የካቲት 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ 64 ቃለ-መጠይቆችን ያደረገ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹም ዋና ዋና የፓኪስታን አካባቢዎችን እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም፣ በካናዳ፣ በጀርመን፣ በማሌዥያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በኩዌት የሚገኙ የዳያስፖራ ማኅበረሰቦችን ያካተቱ ናቸው።
ጥናቱ ሴቶች ሊጋሩብኝ ይችላሉ ብለው የሚፈሯቸውን የምሥል ዓይነቶች የሚዘረዝር ሲሆን፣ ያለ ሂጃብ (ያለ ራስ መሸፈኛ) የተነሷቸው ፀጉርን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች፣ ምዕራባዊ ወይም የሰውነት ቅርጽን የሚያሳዩ ልብሶችን ለብሰው የተነሱት፣ ዘመድ ካልሆነ ወንድ አጠገብ የተነሱት፣ በሐሰት የተፈበረኩ፣ ወይም የአንድን ሰው የፊት ፎቶ ብቻ በመጠቀም በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የተሠሩ ምሥሎች ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳቸውም ዕርቃንን አያሳዩም። ሆኖም ሁሉም ምሥሎች ስም አጥፊ ታሪክ እንዲተርኩ ተደርገው ሊዘጋጁ ይችላሉ።
ለአይሻ ኦማር ይህ ክርክር ንድፈ-ሳሃባዊ ብቻ አይደለም። በፓኪስታን የፊልም እና የቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ የሠራችው ይህች ተዋናይት፣ ማኅበራዊ ሚዲያ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የተለመደ ከማድረጉ ከብዙ ጊዜ በፊት የእርሷ ምሥሎች ተሰርቀው እንደተሠራጩባት ትናገራለች።
ከአሥር ዓመት በፊት ከሴት ጓደኛዋ ጋር በታይላንድ በነበራቸው የእረፍት ጊዜ፣ ባሕር ዳርቻ ላይ የመዋኛ ልብስ እና ቁምጣ ለብሳ የተነሳቻቸው ፎቶግራፎች፣ እሷ ሳታውቅ ከላፕቶፕ ላይ ተወስደው ኢንተርኔት ላይ ተለጥፈውባታል።
ድርጊቱ “ለሥራዬ በጣም ጎጂ ነበር” ትላለች አይሻ። “የማስታወቂያ ሥራዎችን አጣሁ። አንዳንድ የሥራ ዕድሎችንም አጣሁ” ካለች በኋላ ለአፍታ ቆም ብላ በመቀጠል እንዲህ ስትል ታክላለች፦ “ምክንያቱም በእኔ ባህል፣ አንድን የንግድ ምልክት የምትወክዪ ወይም በቴሌቪዥን ላይ አንድን ገጸ-ባህሪ የምትጫወቺ ብትሆኚ እንኳን፣ ከሆነ ምሥል (ባህል) ጋር መጣጣም አለብሽ። ስለዚህ በሥነ-ልቦናም በስሜት ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብኛል።”
ይህ ተሞክሮ “ከፍተኛ ጥንቃቄ” እንድታደርግ እና በዙሪያዋ ሆነው ቪዲዮ የሚቀርጿት ሰዎች እንዳሉ ለማረጋገጥ ሁልጊዜ አካባቢዋን በንቃት እንድትከታተል እንዳደረጋት ትናገራለች።
ሄራ ሁሴን እንደምትለው፣ ማኅበረሰቡ በምሥል ላይ ከተመሠረተ ጥቃት ጋር በተያያዘ እየጠየቀ ያለው የተሳሳቱ ጥያቄዎችን ነው። የቼን መዋቅር በሦስት መመዘኛዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ እነርሱም በግለሰቡ ላይ የደረሰው ጉዳት፣ ምሥሉን ከማጋራት በስተጀርባ ያለው ዓላማ፣ እና የፈቃደኝነት አለመኖር ናቸው።

