ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ጥቃት በተፈበት አካባቢ ጥቁር ጭስ እየተግተለተለ
የምስሉ መግለጫ,የዩክሬን ጦር የነዳጅ መስመሩን በሩሲያ “ከትላልቆቹ ውስጥ አንዱ” ነው ብሏል

ታትሟልከ 6 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩክሬን የሩሲያ ሁለተኛ ከተማ በሆነችው ሴንት ፒተርስበርግ የሚገኝ ትልቅ የነዳጅ መስመርን መደብደቧን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ አስታወቁ።

ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የነዳጅ መስመሩን “ለሩሲያ ጦርነት ገንዘብ የሚያመነጭ ቁልፍ መሠረተ ልማት” ሲሉ ገልፀውታል።

ዩክሬን ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው ትልቅ የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር መምታቷንም አስታውቃለች።

የሴንት ፒተርስበርግ ገዢ አሌክሳንደር ቤግሎቭ ከተማዋ “በከፍተኛ” የድሮን ጥቃት ስር እንደሆነች የተናገሩ ሲሆን፤ የነዳጅ መስመሩ መመታቱንም አምነዋል። ይሁን እንጂ በሰው ላይ የደረሰ አደጋ የለም ብለዋል።

ዩክሬን በሩሲያ የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈፅመው ረጅም ርቀት ተጓዥ የድሮን ጥቃቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተባባሱ ሲሆን፤ ኪዬቭ በጥቃቷ ሰፊ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰት አድርጋለች።

ኪዬቭ በጥቃቶቹ 43 በመቶ የሩሲያ የነዳጅ ማቀነባበሪያ አቅም “ተኮላሽቷል” ብላለች። ደርሷል የተባለው ይህ ውድመት በገለልተኛ አካል የተረጋገጠ አይደለም።

ዩክሬን የሩሲያ የነዳጅ እና ጋዝ ጣቢያዎች ሕጋዊ ዒላማዎች ናቸው ትላለች። ሞስኮ የጦርነት ዘመቻዋን ለመቀጠል በነዳጅ ሽያጭ ላይ ጥገኛ ናት።

በዩክሬን ጥቃቶች ምክንያት የነዳጅ እጥረት መከሰቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት ያመኑት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቅዳሜ ዕለት ለአገር ውስጥ ገበያ የነዳጅ አቅርቦትን የሚያሳድግ ሕግ ፈርመዋል።

ፑቲን በዩክሬን ላይ ሙሉ ለሙሉ ወረራ የከፈቱት እ.አ.አ የካቲት 2022 ነበር።

ዜለንስኪ ቅዳሜ ዕለት ጥቃት የተፈፀመበት ሴንት ፒተርስበርግ እና በዙሪያው ያለው አካባቢ ከዩክሬን ድንበር 850 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የጥቃቱ የውድመት መጠን ወዲያው ግልፅ ባይሆንም በዩክሬኑ ፕሬዝዳንት የተለጠፈ ተንቀሳቃሽ ምሥል በዒላማው አካባቢ ድሮን ሲበር እና ከጥቃቱ በኋላ ግዙፍ ጥቁር ጭስ ሲግተለተል ያሳያል።

ቢቢሲ የሴንት ፒተርስበርግ የነዳጅ መስመር መመታቱን አረጋግጧል።

የዩክሬን ጦር የነዳጅ መስመሩን በሩሲያ “ከትላልቆቹ አንዱ” ሲል የገለፀው ሲሆን፤ በዓመት 12.5 ሚሊዮን ቶን ፔትሮሊየም የማምረት አቅም ያለው ነው ብሏል።

ጦሩ በክሮነስዳት ቁልፍ የባሕር ኃይል ጣቢያ መምታቱንም አስታውቋል።

ሩሲያ እስካሁን ዩክሬን ፈፀምኩት ባለችው ጥቃት ዙሪያ በይፋ አስተያት አልሰጠችም።

የሴንት ፒተርስበርግ ገዢ ቤግሎቭ በከተማው እና በሌኒንግራድ ግዛት አካባቢ 72 የዩክሬን ድሮኖች ተመትተው መውደቃቸውን ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የድሮን ስጋቱ እስኪያበቃ ድረስ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ጠይቀዋል። ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በሴንት ፒተርስበርግ ይኖራሉ።

በሌላ ዜና የዩክሬን ጦር ቁልፍ የዩክሬን ምሥራቅ ከተማ የሆነችው ኮስትኣንቲኒቫ በሩሲያ ቁጥጥር ስር መውደቋን አስተባብሏል።

“ኮስትኣንቲኒቫ በዩክሬን መከላከያ ኃይል ቁጥጥር ስር እንደሆነች ነው” ብሏል።

ሰርጎ ለመግባት ሙከራዎች እንደነበሩ ያመኑት የጦሩ ቃል አቀባይ ሙከራው እንዳልተሳካ ተናግረዋል።

የጦሩ አስተያየት የተሰማው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከተማዋ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ገብታለች ባሉ በቀናት ውስጥ ነው። የሩሲያው መሪ ለዚህ ንግግራቸው ያቀረቡት ማስረጃ የለም።