July 10, 2026

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ፤ የሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሚሰጡት የመኝታ አገልግሎት ላይ አምስት በመቶ ታክስ እንዲሰበስቡ ግዴታ የሚጥል ደንብ ተግባራዊ አደረገ። ደንቡ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ሐምሌ 1፤ 2018 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር ቢሮው ቢገልጽም፤ የሆቴል ባለቤቶች ግን ለመዘጋጃ የተሰጠው ጊዜ አጭር መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን አስምተዋል።  

በሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ “የመኝታ አገልግሎት ማዘጋጃዊ ታክስ ለመጣል” የተዘጋጀው ይኸው ደንብ፤ የአዲስ አበባን የገቢ አሰባሰብ “ፍትሃዊነት ይበልጥ በማጎልበት” የከተማዋን ልማት “ቀጣይነት ለማረጋገጥ” የሚያስችል እንደሆነ ቢሮው አስታውቋል። ደንቡ የወጣው የአዲስ አበባ ከተማን “ለቱሪስቶች እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ” “ተጨማሪ የገቢ ምንጭ” በማስፈለጉ ምክንያት እንደሆነም በህግ ሰነዱ ላይ ተጠቅሷል።

በደንቡ ላይ “ሆቴል እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋም” ተብለው የሚጠሩት ሆቴሎች፣ ሞቴሎች፣ ፔንሲዮኖች፣ የእንግዳ ማረፊያዎችን እና ሎጆች ናቸው። በከተማ አስተዳደሩ የተመዘገቡት እነዚህ ተቋማት ወይም የመኝታ አገልግሎት ሰጪ ግለሰብ፤ የተገልጋዩቻቸውን መረጃ የሚያሰፍሩበት መዝገብ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው በደንቡ ላይ ሰፍሯል።

አገልግሎት ሰጪዎች የተገልጋዩቻቸውን “ሙሉ መረጃ” በተዘጋጀው መዝገብ ላይ “በተሟላ መልኩ” መመዝገብ እንደሚኖርባቸውም በደንቡ ላይ ተቀምጧል። የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለባቸው የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የመኝታ አገልግሎት ሲሰጡ በሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ወይም በማንዋል ደረሰኝ ላይ “የመኝታ አገልግሎት ክፍያ ታክስን” በማካተት ገቢ መሰብሰብ እንዳለባቸው ደንቡ ያዝዛል።

የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋይ የሆኑ ድርጅቶች የገቢ ማሳወቂያ ሪፖርታቸውን፤ በየወሩ ምዝገባ ላከናወኑበት የገቢ ሰብሳቢ ተቋም እንዲያሳውቁ በአዲሱ ደንቡ ይገደዳሉ። የደረጃ “ለ” ግብር ከፋይ የሆኑ የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪዎች ደግሞ በቁርጥ መክፈል የሚገባቸውን የማዘጋጃ ቤታዊ ታክስ ገቢ በየሩብ ዓመቱ ለተመደቡበት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ማሳወቅ እንዳለባቸው በደንቡ ተደንግጓል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው አዲሱ ደንብ፤ የመኝታ የአገልግሎት ክፍያ ስሌት ከተጨማሪ እሴት ታክስ በፊት ባለው ዋጋ ላይ የሚሰላ እንደሆነ ገልጿል። ደንቡ የመኝታ የአገልግሎት ክፍያ “የታክስ ምጣኔ” አምስት በመቶ እንደሚሆን አስታውቋል።

የሆቴል መኝታ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች እና ግለሰቦች፤ የተጣለባቸውን የታክስ ምጣኔ መሰረት አድርገው የሚጠበቅባቸውን ገቢ ካልሰበሰቡ እና ወቅቱን ጠብቀው ሪፖርት ካላደረጉ የሚከተላቸው ቅጣት ምን እንደሆነም በደንቡ ላይ ተዘርዝሯል። ድርጅቶቹ ለዘገዩባቸው ጊዜያት ከክፍያው 50 በመቶ ያልበለጠ፣ በየወሩ 5 በመቶ ቅጣት እንዲከፍሉ እንደሚደረግ በደንቡ ላይ ተደንግጓል። 

ማንኛውም የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋም የሰበሰበውን ክፍያ ገቢ ሳያደርግ ከዘገየ፤ መክፈል ከነበረበት ቀን ጀምሮ የሚታሰብ ወለድ እንደሚከፍልም በደንቡ ላይ ሰፍሯል። የቅጣት ክፍያው የንግድ ባንኮች የወቅቱ የማበደሪያ ወለድ ምጣኔ እና የወለዱ 15 በመቶን የሚጨምር ነው።   

አገልግሎት ሰጪ የሆነ የድርጅት ከመኝታ አገልግሎት የተገኘ ገቢ መረጃ መደበቅ እና የሀሰት የገቢ ማሳወቂያ ማቅረብ በሀገሪቱ የወንጀል ህግ መሰረት በወንጀል እንዲጠየቅ እንደሚደረግ ደንቡ ደንግጓል። ይህ ደንብ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ቢገልጽም፤ የሆቴል ባለቤቶች እና ሰራተኞች ግን የተሰጣቸው “አጭር ጊዜ” መሆኑን ይናገራሉ።

ፎቶ፦ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

ይህ ጉዳይ ደንቡን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት አርብ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተነስቶ እንደነበር፤ ውይይቱን የተካፈሉ በአንድ ሆቴል በኃላፊነት የሚሰሩ ግለሰብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ደንቡ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ቢታወቅም፤ አዲሱን ታክስ ያካተተ ክፍያ  ያካተተ ደረሰኝ በካሽ ሬጂስተር ለመቁረጥ እንዲቻል ይህንኑ ከሚያስተካክሉት ከሶፍትዌር ድርጅቶች ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ እኚሁ የሆቴል ባለሙያ ይስረዳሉ።      

የሶፍትዌር ድርጅቶቹ አዲሱን ታክስ በደረሰኝ ላይእንዲያካተት ለማድረግ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮው የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚፈልጉ የጠቆሙት የሆቴል ኃላፊው፤ ይህ ሂደት ጊዜ እንደሚጠይቅ እና የተሰጣቸው ጊዜ እንደማይበቃ ያብራራሉ። ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ከከተማይቱ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሰኞ ውይይት ማድረጉን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

እንደ ሆቴል ኃላፊው ሁሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንትም የአገልግሎት ክፍያን በሶፍትዌር ድርጅቶች አማካኝነት በሲስተም ላይ በመጫን በካሽ ሬጂስተር ማሽን ደረሰኝ ላይ ልክ እንደ ቫት (VAT) አካቶ ለማውጣት “በቂ ጊዜ ያስፈልጋል” ይላሉ። ይህ ጉዳይ በሰኞው ውይይት ላይ የተገለጻላቸው የከተማይቱ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊዎች፤ ሶፍትዌሮችን ከማሽኖቹ ጋር “የማስተሳሰር ስራ” ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲከናወን ደብዳቤ ለመጻፍ መስማማታቸውን ወ/ሮ አስቴር አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ ከ“መሪ ፖድካስት” የተወሰደ

የገቢዎች ቢሮ ኃላፊዎች የሶፍትዌር አቅራቢ ድርጅቶቹን ዝርዝር ሆቴሎቹ እንዲያቀርቡ ማዘዛቸውንም የማህበሩ ፕሬዝዳንት አክለዋል። በስሩ 188 ሆቴሎችን በአባልነት የያዘው የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር፤ የተጠየቀውን ዝርዝር ለቢሮው መላኩን ወ/ሮ አስቴር ገልጸዋል። በሶፍትዌር ድርጅቶቹ የሚከናወነው የቴክኒክ ትስስር (integration) ጥቂት ቀናት አሊያም ሳምንት ሊወስድ እንደሚችልም አክለዋል። 

“ማንኛውም ሆቴል ወይም ታክስ ከፋይ ይህንን እምቢ አላለም። ግን በእሱ እጅ ያለ ነገር አይደለም። የሚቻለውን ጥረት ማድረግ ብቻ ነው የሚችለው” የሚሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፤ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ሆቴሎቹ ደብዳቤውን የጻፉበትን ቀን አይተው የጊዜውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡላቸው መጠየቃቸውን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)