Getachew Shiferaw

አልተመካከሩም!

የምክክር ኮሚሽን ምክክር ጀምሬያለሁ ብሏል። ነገር ግን ተመካካሪ የተባሉት ራሳቸው የተመካከሩ አይመስሉም። እያንዳንዱ ተሳታፊ ትነስም ትብዛም ጥያቄዬ ያላት ትኖረዋለች። አስመዝግቤያለሁ የሚላት ጉዳይም አለችው። ይሁንና እያንዳንዱ ተሳታፊ ከሚመስለው ጋር እንኳን አልተመካከረም።

የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ሆነው የምክክር ኮሚሽኑ ስብሰባ ላይ በየአዳራሹ ይገኛሉ። ነገር ግን የፓርቲው ሊቀመንበር ከሆነ የሚገኘው ምክትሉ ተነጥሎ ሌላ ፓርቲ መስርቷል፣ ወይንም ፓርቲው ለእኔ ይገባል ብሎ የሚከራከረው ነው። የኦነግ፣ አብን፣ ኢዜማ፣ ኦፌኮ ወዘተ አመራሮችና አባላት ግማሹ ቢገኙ ግማሹ ትጥቅ ትግል ላይ ነው። ግማሹ ፓርቲው ለእኔ ነው የሚገባኝ ብሎ ምርጫ ቦርድ የሚመላለስ ነው! የራሳቸውን ችግር ሳይፈቱ አገራዊ ምክክር ኮምሽን ብለው የተቀመጡ ብዙ ናቸው።

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች ይገኛሉ። ጥያቄም አስመዝግበዋል። ነገር ግን በትግራይና ኦሮሚያ የራሳችንን ሲኖዶስ መስርተናል ከሚሉት ጋር መቀራረብም እነዚህን አካላት ማስቆም አልቻሉም። አልተመካከሩም!

ሙስሊሙን ወክለናል የሚሉት ጥያቄ አስመዝግበዋል። ነገር ግን መጅሊሱ አሁንም ጥያቄ አለበት። መስጊድ ከመቀማማት ጀምሮ ሌሎች የጠብ ምንጮች አሉ። አልተመካከሩም። የፕሮቴስንታንት ተወካይ ነኝ የሚሉት በርካታ ጠቦች አሉባቸው። አልተመካከሩም። አጠቃላይ የኃይማኖት ተቋማት የውስጥ ችግር አለባቸው። መለኮታዊ በሆነ ጉዳይ በፈጣሪ ስም ሳይግባቡ በፖለቲካ መሩ ምክክር ኮምሽን ውስጥ ተሳታፊዎች ናቸው!

በየክልሉ ያሉ ታጣቂዎች የምክክር መድረኩን አንቀበለውም ብለዋል። ከእነሱ አፈንግጠው የገቡት ግን በየመድረኮቹ ይገኛሉ። ታጣቂ የነበሩት አብረዋቸው ከነበሩት ጓዶቻቸው ተነጥለው ነው ከሌላ ጋር አዳራሽ ውስጥ የሚውሉት።

ክልሎችም ጥያቄዎች አሏቸው። ነገር ግን የብልፅግና መዋቅር መካከል ተመሳሳይ አቋም የለም። ኦህዴድ ሌሎችን አሰልፎ ሊያስመዘግበው የሚፈልገው ትርክት አለ። ሌሎቹ እንደየፊናቸው የሚያነሷቸው ቢኖራቸውም ተመሳሳይ አቋም የለም። የተወሰኑ ሰዎች እንዲህ እናደርጋለን ብለው የያዙትን ይዘው ነው።እንደ ብልፅግና የግል፣ የቡድን ወዘተ ጥቅም ልዩነት አለ። ብልፅግና ከምስረታው ጀምሮ በየቦታው ያንጠባጠባቸው አመራሮቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌላውም ጋር መግባባት የለውም። ራሱ ብልፅግና በዋነኛነት አሳካዋለሁ ብሎ የሚሄድበት ይህ መድረክ “ምክክር ወዘተ” ይባልና ብልፅግና ደግሞ በየቀኑ “አ*ጠ*ፋ*ችኋለሁ” ሲል ነው የሚውለው። በሕዝብ ላይ ጦርነት ሲያውጅ፣ አዲስ ጦርነት ሲነድፍ ነው የሚውለው። ጀኔራሎቹ ሲፎክሩ፣ ፖለቲከኞቹ ደግሞ የምክክር አዳራሹ ውስጥ ሞልተዋል። አልተመካከሩበትም። የምክክሩ ውጤት ነው የሚሉትን አያምኑበትምም። መጨረሻ ላይ ግን መጫናቸው አይቀርም!

ትህነግ ጦርነት ሰበካ ላይ ነው። የትህነግ ፍንካች ደግሞ የምክክር ኮምሽኑ አዳራሽ ውስጥ የፊት ወንበር ተቀማጭ ናቸው። እነዚሁ ሰዎች አፋር ውስጥ ደግሞ ጦር አላቸው። አልተመካከሩም። አያምኑበትምም።

በርካታ ተገንጣይ ብሔርተኞች አሁን ቢያኮርፉ በአዳራሽ የሚገኙ ለጊዜው የተጣሏቸው ጓዶቻቸው የሆነ አካባቢ ለእኛ ይገባል፣ ቋንቋችን እንዲህ ይሆናል ሲሉ ቢሰሟቸው ተቃውሟቸውን አቁመው አብረዋቸው ይሆናል። በስልታዊ እየተቃወሙም ቢሆን የሚመዘገብ ጥያቄ፣ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ ይልካሉ።

የምክክር ኮምሽኑ በርካታ ፍንካቾች የሚሳተፉበት፣ በርካታ ፍንካቾች የሚቃወሙት መድረክ ነው። እያንዳንዱ ተሳታፊ የራሱ ጥያቄ ቢሰማለት ትርክት ቢቀመጥለት ይወዳል። ግን ከራሱ ወገን፣ ከጓዱ ተጣልቶ ከማይቀራረበው ኃይል ጋር ለመወያየት፣ ትርክት ቢያስመዘግብ አሸናፊ ነኝ ብሎ ለማወጅ ነው የሚቀርበው። በዚህ ሂደት ልክ እንደ ትህነግ መሩ ህገመንግስት አጀንዳዎቹ ከፀደቁ ያው ተወያየህም አልተወያየህም ትርክት ያስቀምጡብሃል። በምክክሩ አልቀመጥም እንዳትል በርካታ የራሳቸው ወገን ጋር የተኳረፉ አካላት አሉበት። ተሳትፌያለሁ እንዳትል በርካቶች አልተቀመጡም።

እጅግ አደገኛው ነገር ደግሞ!

1) እንደ ባለፈው ህገመንግስት ሳይሆን በደንብ አስልተውበት ብዙ አካል ተሳትፏል ለማስባል እየሄዱበት መሆኑ

2) ምዕራባዊያኑ በንቀትም ይሁን እኛም ካለብን ችግር አንፃር “ይሞክሩት” ብለው የተስማሙበት በመሆኑ ተመካከርክም አልተመካከርክም ትርክት ሊያስቀምጥብህ፣ ማህተም ሊያሳርፍብህ የተሰለፈው በርካታ ነው።

3) ብልፅግና ( በተለይም የኦህዴድ ብልፅግና) እንዲህ እንዲህ እንዲሆኑ ብሎ ቀድሞ የወሰነባቸው ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ያህል የአዲስ አበባ ጉዳይ። ምክክር ከሚባለው ቀድሞ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

4)በጣም አደገኛ ደግሞ እንደ አገር ችግር ባይፈታ እንኳን መርዘኛ ትርክቶችን ለማስቀመጥ ሲሰሩ የከረሙ፣ እስከመጨረሻው ግፊት ያደረጉ አካላት መኖራቸው ነው። እነዚህ አካላት እስካሁን በህገወጥ መንገድ ያደረጉትን ጭምር በዚህ መድረክ ማህተም ማስመታት ይፈልጋሉ።

በዝርዝር ሲታይ ግን ተወካዮች የተባሉትን ብዙ አካል ተወካዮቸ አይደሉም ይላቸዋል። ተወካይ የሚባሉት ወገናችን፣ ጓዳችን ከሚሉት ጋር ጭምር ያለባቸውን ችግር ያልፈቱ፣ ያልተመካከሩ ናቸው።

ብዙ ሰው እንደ ቀልድ ያየዋል። ባትመካከርም ተመካክረሃል ብለው ትርክት ሊያስቀሞጡ ነው። ተወካዬ አደለህም ብትለው በብሔርህ፣ በአካባቢህ፣ በሙያ ማህበርህ፣ በኃይማኖትህ ስም ሰው ተቀምጧል። ነገ ማስረጃ ሆኖ ይቀርብልሃል። ትርክቱ የአንተ ወገን የተመካከረበት፣ የተመካከርክበት ነው ልትባል ነው። አዳራሽ ውስጥ ያሉት ግን በርካታ ከራሳቸው ጓድና ወገን ጋር ተጣልተው ያልታረቁ ናቸው።

የምክክር ኮምሽኑ ራሱ ምክክር ያስፈልገዋል! ከራሳቸው ወገን ጋር ያልተመካከሩት አካላት ከምክክር ኮምሽኑ ስብሰባ በፊት ምክክር ያስፈልጋቸው ነበር። ግን አላደረጉትም። ይህም የሌላ አካራካሪ ዘመን መጀመሪያ እንዲሆን ያደርገዋል።

See less