Share


በዶክተር ሶስና ታደሰ
ደራሲና ተመራማሪ ዶክተር ቹቹ አለባቸው ‹‹የተከዜ ፖለቲካ፤ ኃይል፣ ማንነት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነት›› የሚል ርዕስ የሰጡትን አዲስ መጽሐፋቸውን ለንባብ አውለዋል፡፡
መጽሐፉ በቀዳሚ ቃሉ ወልቃይት እንደ ሆርሙዝ ሲል፣ የአካባቢውን አስፈላጊነት በዓለም አቀፍ ንጽጽር ለማስቀመጥ ይሞክራል፡፡ ወልቃይት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኀልውና እና የስትራቴጂክ መተንፈሻ ቁልፍ ናት የሚል ሙግት ያለው ይህ መጽሐፍ፣ የተከዜ ተፋሰስን እና ወልቃይትን ዳግም እንድናጤናቸው ይወትውታል፡፡
በቅድሚያ ጥቂት ነጥቦች ስለ ሆርሙዝ ሰርጥ…
የሆርሙዝ ሰርጥ በፋርስ ባሕረ-ሰላጤ እና በኦማን ባሕር መካከል የሚገኝ፣ በዓለም ላይ እጅግ ስልታዊ እና ስሱ የተፈጥሮ የውኃ መተላለፊያ መስመር ነው። ይኽ ጠባብ መተላለፊያ የዓለምን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የያዘ ሲሆን፣ በየቀኑ ከዓለም ዓቀፉ የነዳጅ ንግድ ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የሚጓጓዝበት ዋነኛ ዋና የኢኮኖሚ የደም ስር ነው።
– Advertisement –

በጂኦ ፖለቲካ ሳይንስ አጠራር፣ ሆርሙዝ የ‘ሉላዊው ዓለም የመታነቂያ ነጥብ’ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህን ሀሳብ ዶክተር ቹቹ አለባቸው በመጽሐፋቸው ላይ በሚገባ አብራርተውታል፡፡ ይኽም ማለት ወታደራዊ ኃይሎች ወይም ተቀናቃኝ መንግሥታት ይኽንን ጠባብ መስመር በቁጥጥራቸው ሥር ካደረጉ ወይም ለመዝጋት ከሞከሩ፣ መላውን የዓለም ዓቀፍ ኃይል ሚዛን፣ የኢነርጂ ፍሰት እና የደኅንነት መዋቅር በአንድ ጊዜ የማናጋት እና ዓለምን ስትራቴጂካዊ እገታ ውስጥ የመክተት ግዙፍ መዋቅራዊ ኃይልን መዳፋቸው ላይ ያውላሉ እንደማለት ነው፡፡
ዶክተር ቹቹ በአዲሱ መጽሐፋቸው ይዘውት የመጡት ሙግት፣ ወልቃይት የኢትዮጵያ ሆርሙዝ ነች የሚል ነው፡፡
በዓለም ዓቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ጥናት ውስጥ፣ የተወሰኑ መልክዓ-ምድራዊ ይዞታዎች ከአካባቢያዊ ስፋታቸው በላይ የዓለምን የምጣኔ ሀብት እና የኃይል ሚዛን የመወሰን ብርቱ መዋቅራዊ አቅም አላቸው።
ለዚኽም ማሳያ የሚሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ ነው፤ ይኽ ጠባብ የባሕር መተላለፊያ ከተዘጋ የመላው ዓለም ንግድ እና ደኅንነት እንደሚናጋ ኹሉ፣ በዶክተር ቹቹ አዲሱ ሙግት ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ የወልቃይት-ጠገዴ የሁመራ ቀጠና ለኢትዮጵያ አገረ-መንግሥት ኀልውና የራሷ ‘የሆርሙዝ ሰርጥ’ ነው፡፡

ይህ የሚግት ሀሳብ ግነት ያለው መስሎ ቢታይም፣ ደራሲው መከራከሪያ ሀሳባቸውን አንድ በአንድ ያቀርባሉ፡፡
ወልቃይት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት የሚጠበቅበት ስትራቴጂካዊ በር፣ የቀጠናው የኃይል ሚዛን ማረጋገጫ እና የአገሪቱ የጂኦ ፖለቲካ ምጣኔ ሀብት መተንፈሻ ነው በሚለው ሀሳብ ብዙዎች ቢስማሙም፣ ወልቃይት እንደ ሆርሙዝ በሚለው የሙግት ሀሳብ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸው አይቀርም፡፡
ይኽንን ንጽጽር ከፖለቲካ ሳይንስ ንድፈ-ሐሳቦች አኳያ የመረመሩት፤ ደራሲው በኹለቱ ቀጠናዎች ማለትም በሆርሙዝ እና በወልቃይት መካከል ሦሥት መሠረታዊ ኃልዮታዊ መነሾ ያላቸውን ነባራዊ ትስስሮሾችን ያስቃኛሉ፡፡
አንደኛ፡- በጂኦ ፖለቲካ ፖለቲካ ሳይንስ፡-
በዚህ መመዘኛ፣ በተለይም በአልፍሬድ ታየር ማሃን የባሕር ኃይል የበላይነት መርኽ እና በኒኮላስ ስፓይክማን የባሕር ጠረፍ ንድፈ-ሐሳብ መሠረት፣ የአንድ አገር ወይም ቀጠና የዓለም ዓቀፍ የበላይነት የሚወሰነው እንደ ሆርሙዝ ሰርጥ ያሉ ቁልፍ የሆኑ የንግድ፣ የባሕር እና የሎጂስቲክስ መተላለፊያዎችን በመቆጣጠር ላይ ነው።
የሆርሙዝ ሰርጥ ለዓለም ዓቀፉ የነዳጅ ፍሰት ‘መታነቂያ ነጥብ’ እንደሆነው ኹሉ፣ የወልቃይት-ጠገዴ ሁመራ መተላለፊያ ለኢትዮጵያ ሰሜን-ምዕራብ የአገር ውስጥ ምርት መውጫ እና የረጅም ርቀት የምድር ላይ ስትራቴጂካዊ መተንፈሻ መስመር ነው የሚል ሀሳብ ያላቸው ዶክተር ቹቹ አለባቸ፣ ይኽንን መስመር የዘጋ ኃይል፣ የመላዋን ኢትዮጵያ ጂኦ ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ኀልውና የማነቅ መዋቅራዊ አቅም ያገኛል ይላሉ፡፡
ሁለተኛ፡- የሥጋት ሚዛን ንድፈ-ሐሳብ፦
በስቴፈን ዋልት መላምት መሠረት፣ የአገራት የደኅንነት ጥምረት እና ስልታዊ ውሳኔዎች የሚወሰኑት ከሌሎች አገራት የሚሰነዘርባቸውን የተቀናጀ የሥጋት ደረጃ (ቅርበትን፣ አቅምን እና የጠበኛነት ዓላማን) በመገምገም ነው።
በዚኽ መዋቅር ውስጥ፣ ታሪካዊ ተቀናቃኞች አንድን አገር ሥጋት አድርገው ካዩት የከበባ ስትራቴጂን በመጠቀም መዋቅራዊ ጫና ሊፈጥሩበት የሚችሉ ሲሆን፣ የተከበበው አገር ደግሞ ይህንን ሥጋት ለመመጣጠን አዲስ ጥምረቶችን ይፈጥራል።
ይህን መከራከሪያ ሀሳብ መነሻ ያደረጉት ደራሲው፣ የታችኛው የናይል ተፋሰስ አገራት በተለይም ግብፅ፣ ሱዳንን መሸሸጊያ በማድረግ ወልቃይትን ከኢትዮጵያ ለመቁረጥ የምትሸርበው ሴራ፣ ልክ ምዕራባውያኑ የሆርሙዝ ሰርጥን በመዝጋት ሌሎች ተገዳዳሪ ኃይላትን ስትራቴጂካዊ እገታ ውስጥ ለመክተት ከሚደረጉ ምዕራብ መር ስልቶች ጋር ተቀራራቢ መለዮ አለው የሚል መከራከሪያ ሀሳብ አላቸው።
የወልቃይት ቁጥጥርም፣ ይኽንን ታሪካዊ ከበባ የሚያከሽፍ፣ የተከዜ ተፋሰስን የውኃ ሉዓላዊነት የሚያስከብር እና ሌላ ግንባር እንዳይከፈት የሚከላከል የማይናጋ ግንብ ነው የሚል የጸና አቋም እንዳላቸው በመጽሐፋቸው ላይ በዝርዝር አስፍረዋል፡፡
ሦስተኛ፡- የግዛት ወጥመድ ስብራት እና የጁኦ ፖለቲካ ምጣኔ ሀብታዊ መተንፈሻ፦
በጆን አግኒው አመክንዮ መሠረት፣ ግዛት ዝም ብሎ በካርታ ላይ የሚሰመር ግዑዝ መስመር ሳይሆን፣ የአገረ-መንግሥት የኃይል መዋቅር እና የኀልውና ፍላጎት የሚገለጥበት ሕያው ምኅዳር ነው።
ይህን ሀሳብ በሚገባ የሚያፍታታው የተከዜ ፖለቲካ የተሰኘው መጽሐፍ፣ የሆርሙዝ ሰርጥ ለዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ መተንፈሻ እንደሆነው ሁሉ፣ የወልቃይት-ጠገዴ ሁመራ ቀጠናም ኢትዮጵያን ከተለመደው የግዛት ወጥመድ የሚያወጧት ብሔራዊ የስትራቴጂክ መተንፈሻዎቿ ናቸው የሚል ሙግት አለው፡፡
ይኽ ቀጠና በአስተማማኝ ኹኔታ በኢትዮጵያ እጅ መጽናቱ፣ አገሪቱ በጅቡቲ መስመር ላይ ያላትን ፍጹም የወደብ ጥገኝነት በመስበር፣ ከኤርትራ እና ሱዳን ወደቦች ጋር አዲስ የምጣኔ ሀብታዊ ትስስር እንድትፈጥር ያስችላታል የሚል ምልከታዎችን ያጋራል።
በመጽሐፉ መከራከሪያ ሀሳብ፣ ይኽም ልክ የሆርሙዝን ቁልፍ እንደመያዝ፣ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ፖለቲካ እና በሰሜን-ምዕራብ የንግድ መተላለፊያ ላይ ያላትን የኹለትዮሽ ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ በከፍተኛ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፣ በአማራ ማንነት እና በታሪካዊ ይዞታው ላይ የጸና ብቻም ሳይሆን ሊናጋ የማይችል ጠንካራ የሕዝብ ደኅንነት ጋሻ ይፈጥርላታል ሲል ለፖሊሲ አውጭዎች ምክረ -ሀሳቡን ይሰነዝራል፡፡
ይኽ መጽሐፍ የወልቃይትን ጉዳይ ከተራ የርስት እና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ በላይ አውጥቶ፣ ወልቃይት ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት እና ሉዓላዊነት ያለውን ፍጹም ምትክ የሌለው ስልታዊ ፋይዳ ‘ወልቃይት እንደ ሆርሙዝ’ በሚል ንድፈ-ሐሳባዊ መነጽር በጥልቀት ይተነትናል።
የጂኦ ፖለቲካ ልሂቃን እንደሚሉትም፣ የአገራት አንደኛው የጥንካሬ ምንጭ መልከዐ-ምድራዊ አቀማመጣቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንዱና ዋናው የጥንካሬ አቅሟ የዚኽ አካባቢ መልክዐ-ምድራዊ ይዞታ ሲሆን፤ በዚኽ ቀጠና የሚኖረው መዋቅራዊ መረጋጋትና የቁጥጥር አቅም ለሐገረ-መንግሥቱ የጥንካሬ መሠረት እንደኾነ ዶክተር ቹቹ አለባቸው በዚህ አነጋጋሪ መጽሐፋቸው በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡
የታሪክ ተቀናቃኞች ሲሉ የሚጠሯቸው እነ ግብጽ፣ በተለይም የዓባይን/የተከዜን የውኃ ፍሰት እንደ ብቸኛ የኀልውና መሠረት እንደሚመለከቱት ያብራራሉ፡፡ እነዚህ የውጭ ኃይሎች፣ ወልቃይትን ከኢትዮጵያ በመቁረጥ አገሪቱን ከሰሜን-ምዕራብ አቅጣጫ ለመክበብ የቆየ ሴራ ሲሸርቡ መኖራቸውንም ታሪካዊ ሁኔታዎችን ያነሳሉ፡፡
የዚኽ ቀጠና በጠላት እጅ መውደቅ ማለት፣ ኢትዮጵያን በገዛ የጀርባ አጥንቷ ላይ ስትራቴጂካዊ መታነቅ ውስጥ በመክተት ኹለተኛ ግንባር ለመክፈት የሚደረግ የጂኦ ፖለቲካዊ ወረራ አካል ነው የሚል ድምዳሜ አላቸው – ደራሲና ተመራማሪው ዶክተር ቹቹ አለባቸው።
እንደ ደራሲው መከራከሪያ፣ ወልቃይት-ጠገዴ በአስተማማኝ የታሪክ፣ የአሥተዳደር እና የማንነት መዋቅር በኢትዮጵያ እጅ መጽናቱ፣ አገሪቱን ከከበባ ከመከላከል ባለፈ አዲስ የምድረ-ፅፍ ምጣኔ ሀብታዊ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።
ቀጠናው ከኤርትራዋ ምጽዋ ወደብ ጋር ያለው የ400 ኪሎ ሜትር ቅርበት፣ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ላይ ያላትን ፍጹም የወደብ ጥገኝነት የምታቀልበት፣ የባሕር በር አማራጮቿን የምታሰፋበት እና በቀይ ባሕር ፖለቲካ ላይ የኹለትዮሽ ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ የምታሳድግበት የርሷ ብቻ የሆነ የሆርሙዝ ቁልፏ ነው የሚል አዲስ የሙግት ሀሳብ ወደኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ይዘው መጥተዋል፡፡
ይኹን እንጂ፣ ይኽ ስልታዊ ምሽግ ከመሬት መልክዓ-ምድር ጥንካሬ በላይ በሕዝብ የደኅንነት ጋሻ ላይ የቆመ ነው የሚሉት ደራሲው፤ ባለፉት ሦሥት ዐሥርታት በሕወሓት የተፈጸመው መዋቅራዊ የዘር ማጥፋት፣ የማንነት ነጠቃ እና የሥነ-ሕዝብ ምሕንድስና ዋና ዓላማ፣ ይኽንን ሀገር በቀል ጋሻ ሰብሮ ቀጠናውን ለውጭ ኃይሎች መተላለፊያ ቀዳዳ ማድረግ እንደነበር ይገልጻሉ።
በመሆኑም፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ አማራዊ ማንነቱን እና ታሪካዊ ይዞታውን ማስመለስ የወልቃይት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ የተሰበረውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ግንብ ዳግም የመገንባት አገራዊ አደራ ነው ሲሉ ደራሲው የሀሳብ ሙግታቸውን ያጠናክራሉ፡፡
ይኽ አካባቢ ከሆርሙዝ ጋር ካለው ተመሳስሎሽ ባለፈ ሕወሓት አካባቢው ላይ ያለውን ፖለቲካዊ ሕልም ማስታወስ ያሻል የሚሉት ዶክተር ቹቹ አለባቸው፣ ሌላ የስጋት ትንተናዎችን ያስከትላሉ፡፡
አካባቢው የቀጣናው ፖለቲካዊ መስፈንጠሪያ ማዕከል እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኀንነት አስኳል መሆኑን ደጋግመው የሚያነሱት ደራሲው፤ የወልቃይት ጉዳይ፣ ተለዋዋጭ የሆነውን የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካን የመወሰን አቅም አለው ይላሉ፡፡
ትልቁ ጉልበቱ ለቀጠናው ጂኦ-ፖለቲካ ያለው ጠቀሜታ ነው፡፡ የተከዜ-አጥባራ ንዑስ ተፋሰስ ድንበሮች ይኽን አካባቢ በሰፊው ያካልላሉ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱዳን በዚህ ተፋሰስ በርካታ ከተሞቻቸውን ያዳርሳሉ፡፡
በሰብል ምርት አቅሙ የአፍሪካን የግብርና ታሪክ የቀየረ አካባቢ ስለመሆኑ በመጽሐፉ ላይ የምሁራን ጥናቶች በማጣቃሻነት ቀርበዋል፡፡ ከምንም በላይ የሚሉት ደራሲው፣ ወልቃይት የኢትዮጵያ የምድር በር ብሔራዊ ደኀንነት መጠበቂያ ምሽግ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
ሕወሓት ዕድል ቀንቶት ይኽን አካባቢ ዳግም በጉልበት ቢቆጣጠር የዓባይና ተከዜ ተፋስስ መነሻዎችን የመቆጣጠር የዘመናት ሕልም ያላትን ግብፅ፣ ኢትዮጵያን የመክበብ ስትራቴጂ የበለጠ እንድታሳካ በሩን ይከፍትላታል ሲሉም ከባድ የስጋት ትንተናቸውን ያቀርባሉ፡፡
ምናልባትም የሚሉት ደራሲው፣ ሕወሓት ወልቃይትን በጉልበት ቢወር ለግብፅና ሱዳን ወታደራዊ የጦር ሰፈር በመስጠት በቀጥታ ራሱን ወደነጻ አገርነት ለማወጅ የሚያበቃ መዋቅራዊ አቅም በእጁ ሊያስገባ ይችላል ይላሉ፡፡
ሕወሓት ወልቃይትን በመቆጣጠር ከሱዳን ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፤ ያልተገደበና በራሱ የሚመራ የውጭ ግንኙነት በመፍጠር፤ አገር የመሆን ሕልሙን እውን ለማድረግ ከመጠቀም አልፎ፣ በአካባቢያችን እንደሚስተዋለው የራስ ገዞች ልምምድ፣ ለማዕከላዊ መንግሥቱ ስጋት ሊኾኑ የሚችሉ ተጻራሪ ኃይሎችን የጦር ሰፈር ግንባታ መፍቀድ የደረሰ የተለጠጠ ብሔራዊና ቀጠናዊ የደኀንነት አደጋ ሊፈጥር ይችላል የሚሉት ዶክተር ቹቹ አለባቸው፣ ሕወሓት ትግራይን በሶማሌላንድ ሞዴል፣ ከማዕከላዊ መንግሥቱ በመነጠል በቅርብ ጊዜ ዕቅድ ራስ ገዝ ፤ በረዥም ጊዜ ግቡ ደግሞ ነጻ የትግራይ ሪፐብሊክ ሊያዋልድ ይችላል የሚል ጠንካራ የስጋት ትንተና አቅርበዋል፡፡
በዚህ ሂደት ሕወሓት ቢሳካለት እስከ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ያለውንና በምናብ ካርታው ላይ ያሳየንን መሬት አካትቶ የ “ታላቋ ትራግይ” ን ምስረታ እውን ሲያደርግ፤ የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ደግሞ ባልተጨበጠ የታሪክ ዳራ እና የሕግ ማዕቀፍ ከኢትዮጵያ “አለን” የሚለውን መሬት እስከ መሀል አርማጭኾ በመዝለቅ ይነጥቃል የሚል አስፈሪ የስጋት ትንተና ይዘው የቀረቡት ደራሲው፤ ግብፅ የዓባይና ተከዜ ተፋሰሶችን ከመነሻ መሰረታቸው ጀምሮ ለመቆጣጠር ከፖለቲካና ዲፕሎማሲ ወደወታደራዊ የበላይነትና የቁጥጥር አቅም በማደግ አካባቢያዊ ዕድል በእጇ ታስገባለች ሲሉ ስጋታቸውን አመላክተዋል፡፡
በዚህ የተቀናጀና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ባሳተፈ የወረራ ተግባር የተዳከመች ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የተበታተነች ኢትዮጵያን ልንመለከት እንችላለን የሚሉት ደራሲና ተመራማሪው፣ በጠቅላላ ሂደቱና ውጤቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከመኖር ወደአለመኖር፤ የዓባይና የተከዜ ተፋሰስ ደግሞ ከመነሻቸው በባዕዳን እጅ የመውደቅ ዕጣ ያጋጥማቸዋል ሲሉ ምሁራዊ ሙግታቸውን በስጋት ትንተና መልኩ አቅርበዋል፡፡
እንደአገርም ሆነ እንደሕዝብ ከተጋረጠብን አደጋ አኳያ በዚህ ጉዳይ ላይ የጠራ ግንዛቤ ለመፍጠር ወሳኙን አጀንዳ ደግሞ ደጋግሞ ማጤንና ማስታወስ አስፈላጊ ነው የሚለው የተከዜ ፖለቲካ የተሰኘው መጽሐፍ፤ የሚሞግተው የሐሳብ ጭብጥ ጂኦ-ፖለቲካ፣ ኃይል፣ ማንነት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኀንነት ጉዳይ ላይ ነው፡፡
በአጠቃላይ፣ ደራሲው እንደ ሆርሙዝ ኹሉ የወልቃይት ጉዳይ ለአንባቢዎች ሲቀርቡ፣ ወልቃይት ዝም ብሎ የአንድ አካባቢ ወሰን ወይም የይገባኛል ሽኩቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚከበርበት፣ ታሪካዊ ፍትሕ የሚነግሥበት እና የአገራችን ‘የሆርሙዝ ቁልፍ’ በአስተማማኝ መሠረት ላይ የሚቆምበት ብሔራዊ ምሰሶ መሆኑን በአዲስ የሙግት ሀሳብ በመታጀብ ነው፡፡
ይህ መጽሐፍ በይዘቱ ደረጃ በርካታ የሙግት ሀሳቦች የተነሱበት ነው፡፡ በተለይም ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለታሪክ ተመራማሪዎች፣ ለደኅንነት ባለሙያዎች፣ ለዲፕሎማቶች እና ለከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ጠቃሚ የማጣቀሻ ግብዓት ይሆናል የሚል ግምገማ አለኝ፡፡
በከፍተኛ የቋንቋ ደረጃ እና በምሁራዊ ጥልቀት የተጻፈው ይህ መጽሐፍ፣ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ትንተናዎች ከታሪካዊ እውነታዎች ጋር ይበልጥ የተሰናሰሉ፣ መሆኑ ሥራው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ብየ አስባለሁ፡፡
ውድ የቦርከና ድረ-ገጽ አንባቢ ቤተሰቦች እናንተስ ወልቃይት እንደ ሆርሙዝ በሚለው የሙግት ሀሰብ ትስማማላችሁ…. ሐሳባችሁን በአስተያየት መስጫ ሳጥኑ ላይ አስቀምጡ፤ በግላችሁም ተወያዩበት፡፡
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
