ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ

ሰላም ማስከበር በሚል ሽፋን የትግራይን ሕዝብ እንደገና ወደ ጦርነት ለመግፋት የሚደረገው አደገኛ አካሄድ መቆም አለበት!

ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ

የፕሪቶሪያ ስምምነት በተለያዩ አካላት ከነሚጠቀሱት የአካታችነትና መሰል ጉድለቶቹ፤ የውሉ ዋና መንፈስ ጦርነትን በቋሚነት ማቆም፣ ፖለቲካዊ መፍትሔን ማስቀደም፣ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው መመለስ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን ማሰራጨት እና የተፈረሙትን ግዴታዎች መፈጸም ነበር። ዛሬ ግን መንግሥት በራሱ የገባውን ቃል በመጣስ ክልሉን እንደገና ወደ ዳግም ጦርነት ለመመለስ ተግቶ እየሰራ ነው።

ይሁን እንጂ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የመሳርያ ድምጾች ለጊዜው የቆሙ ቢመስልም ብልጽግና ግን የትግራይ ሕዝብ ላለፉት አመታት በድምጽ አልባ ከበባ (siege) ውስጥ እያኖረው እንዳለ ዓለም የሚያውቀው ሓቅ ነው። የመንግስት ሰራተኞችን ደመወዝ ከመከልከል ጀምሮ የነዳጅ ክልከላ፣ የሸቀጣሸቀጥ ዋጋ ንረት፣ የበጀት ክልከላ፣ የትራንስፖርት አማራጮች መዘጋት፣ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ማዕቀብ ፣ ለትግራይ ሕዝብ የተሰበሰበ የእርዳታ ገንዘብ ቅሚያ እና መሰል ቅጣቶች በሕዝብ ላይ ሲፈጸሙ ከርመዋል።

ይህ አልበቃ ብሎት አሁን ደግሞ ሕግ ማስከበር እና ተመሳሳይ መፈክሮች ሽፋን በመጠቀም ትግራይን እንደገና ወደ አውዳሚ ጦርነት ለመክተት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በከፍተኛ ስጋት እየተከታተልን ያለነው ጉዳይ ነው።

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ እንዳይታይ፣ እንዳይሰማ፣ እንዳይታሰብ ያደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ‘በትግራይ ልከፍት ያሰብኩትን ጦርነት ኑ እና ‘ከሕዝብ’ የመጣ ጥያቄ አስመስሉልኝ ‘ ብሎ በራሱ ያደራጃቸውን ጥቂት ግለሰቦች ማሰለፍ ጀምሯል። ይህንን የመቀጠል እቅድ እንዳለውም በየመግለጫው በመለፈፍ ላይ ነው።

በተለይ ከትግራይ የመጡ አንዳንድ ግለሰቦች በሚያሳዝን ሁኔታ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር በመተባበር ለዚህ አደገኛ አካሄድ ፖለቲካዊ ሽፋን ሲሰጡ መታየታቸው እጅግ የሚያስተዛዝብ ነው።

በተጨማሪም አንዳንድ በተቃዋሚ ስም የሚንቀሳቀሱ የስርኣቱ ተላላኪ ፓርቲዎችም ህግ ከመጣስ አልፎ ለኢትዮጵያ የታሪክ ጠባሳ የሆነውን ብልጽግናን ‘ሕግ አስከብርልን፤ ለዚህም ሙሉ በሙሉ ከጎንህ ነን’ በማለት የስልጣንና የወንበር ዳረጎት በተቀበሉ ማግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም ለስርኣቱ ያላቸውን ታማኝነት ለማሳየት ሰማይ ሲቧጥጡ ታዝበናል።

በስርኣቱ ሚዲያዎች የሚካሄደው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እና የሕዝብ ስነ-ልቦና ለጦርነት የማዘጋጀት ሙከራ፣ እ.ኤ.አ ከ2020 በፊት በትግራይ ጦርነት ዋዜማ ከታየው ሂደት ጋር በአስደንጋጭ ሁኔታ አንድና አንድ አይነት ነው።

የገዢው ፓርቲ ዋና ዓላማ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንደገና ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድና ጦርነት መክፈት እንጂ ሰላምን ማስፈን አይደለም። ለዚህም ያለፈውን ጦርነት መመልከት እና ከአሁናዊ ሁነቶች ጋር ማዛመድ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ከሕወሓት ማዳን በሚል ሽፋን በትግራይ ሕዝብ ላይ የታወጀው እልቂት ቁስል ሳይደርቅ ዛሬ ደግሞ የትግራይ ሕዝብን ከህወሓት ማዳን የሚለው መፈክር ለሌላ ዙር ጦርነት የፖለቲካ ሽፋን እየሆነ ነው።

ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ቃላት የተጀመረው ጦርነት ለመቶ ሺዎች ሕይወት መጥፋት፣ ለሚሊዮኖች መፈናቀል፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሴቶች መደፈር፣ ለጦር ወንጀሎች መፈጸም እና በትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ አደጋ መፈጠር ምክንያት ሆኗል። በዚያ ጦርነት ወቅት በተፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እና ተጠያቂነት እንዲኖር የተነሱ ጥሪዎች እስካሁን አንዳችም አልተፈጸሙም።

ያለፉት ስምንት አመታት ያሳዩን እውነታ ከብልጽግና ጋር ተሆኖ፤ እንኳን በተጠቀሰው አካል ያንን ሁሉ መከራ ያየውን የትግራይ ሕዝብ ይቅርና በየተራ የጦርነት ወላፈን እየፈጀው ያለውን የትኛውንም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማዳን የሚቻል እንዳይደለ ነው። የችግሩ ጠማቂ እንዴት የመፍትሄ አምጪ ሊሆን ይችላል?!

ለትግራይ ሕዝብ የምናስተላልፈው መልእክት ግልጽ ነው!

ያንን የማይቻል የሚመስል ጊዜ ያሳለፋችሁን አንድነታችሁን እና ጽናታችሁን ጠብቁ! ትናንት የደረሰባችሁን በቃላት የማይገለጽ መራር ዋጋ ከፍላችሁም ቢሆን ራሳችሁን የተከላከላችሁት በአንድነታችሁ እና በመተጋገዛችሁ ነው።

አሁንም ቢሆን እያንዣበበ ያለው የጦርነት ጥቁር ደመና እና የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ የምትከላከሉት የጦርነት ሰባቂ ጌቶች ወደ አዘጋጁት የፓለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር መበታተንና የእርስ በእርስ መናቆር ወጥመድ ሰተት ብላችሁ በመግባት ሳይሆን አንድነታችሁን ጠብቃችሁ በመናበብ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብም በመላው ማህበረሰብ መካከልና በተለይም በትግራይ እና በአማራ ሕዝብ መካከል በተደጋጋሚ ጥላቻን ለመዝራት ታሪክን ሲያዛባ እና ሲፈበርክ የሚውለውን ስርኣት እኩይ ሴራ በመረዳት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲደግፍ እና እንዲያጠናክር አደራ እንላለን።

ኢሕአፓ ለአለም ሕዝብ እና በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ የዲፕሎማቲክ ማሕበረሰብ ከገዥው ስርኣት እና ዳረጎት ፈላጊዎቹ የፖለቲካ ትወና እና ፕሮፖጋንዳ በዘለለ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ እንዲመለከቱ ጥሪውን ያቀርባል። በትግራይ እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ በዜጎች እያደረሰው ያለው የዜጎች ሰቆቃና እልቂት እኩል እንዲያወገዙና ከስርኣቱ ይልቅ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለማስቀጠል እንዲተባበሩና የችግሩ ሳይሆን የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ይጠይቃል።

በጥላቻ፣ በጦርነት እና በክፍፍል ፖለቲካ ላይ በጋራ ድምፃችንን እናሰማ፤ ኢትዮጵያ ተጨማሪ የደም መፋሰስን መሸከም አትችልም።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ

ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ