July 22, 2026

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ውሳኔ ላይ የሚደረስባቸው፤ በየደረጃው ያሉ ተሳታፊዎች ከ70 እስከ 75 በመቶ ድጋፍ ሲያገኝ እንደሆነ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተዘጋጀ ሰነድ አመለከተ። ሁሉንም የውሳኔ ሂደቶች አልፈው ለጠቅላላ ጉባኤ ከቀረቡ በኋላ “ጠንካራ ተቃውሞ” የሚያጋጥማቸው አጀንዳዎች፤ ወደ ህዝበ ውሳኔ ”ሊመሩ” እንደሚችሉበሰነዱ ላይ ተጠቁሟል።
በ30 ገጾች የተዘጋጀው ይህ ሰነድ ባለፈው ሳምንት በይፋ የተከፈተውን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ “የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን” በዝርዝር የያዘ ነው። የምክክር ጉባኤው ዋና ዓላማ “ሀገራዊ መግባባት ማምጣት” መሆኑን በሰነዱ ላይ ያስታወሰው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ “ሁሉም ውሳኔዎች በመግባባት ላይ የተመሰረቱ መሆን አለባቸው” ሲል አቋሙን አስታውቋል።
በአጀንዳዎች ላይ የመጀመሪያዎቹ ውሳኔዎች የሚተላለፉት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ባሉት “ባለ ሁለት ደረጃ መዋቅር” እንደሆነ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል። የመጀመሪያው ደረጃ “የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ 211 አባል “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

“የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን” አንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተመካክሮ ምክረ ውሳኔ ወይም ምክረ ሃሳብ እንዲያመነጭ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሚያቋቁመው ቡድን ነው። በእንደዚህ አይነት ቡድን ውስጥ ላሉ ተመካካሪዎች “በቂ የምክክር ጊዜ” እና “ዕድል ለመስጠት” ሲባል አንድ የአጀንዳ ቡድን እንዳስፈላጊነቱ “በንዑስ ቡድኖች” እና “በጥቃቅን ቡድኖች” ሊዋቀር እንደሚችል ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ቡድን የታቀፉ አባላት በአንድ አጀንዳ ላይ ከተመካከሩ በኋላ “75 በመቶ ከመግባባት ላይ ለመድረስ እንደሚሞክሩ” የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ሰነዱ ያስረዳል። በተነሳው አጀንዳ ላይ መግባባት ላይ ካልተደረሰ ግን የምሁራን ፓነል እና ሽማግሌዎችን በውስጡ ያካተተ “የስምምነት ግብረ-ኃይል” “ጣልቃ እንደሚገባ” በኮሚሽኑ ሰነድ ላይ ተቀምጧል።
ይኸው ሰነድ የስምምነት ግብረ-ኃይሉ ጣልቃ ከገባም በኋላ መግባባት ላይ ካልተደረሰ፤ “ልዩ አብላጫ ድምጽ” የተሰኘው አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግም ጨምሮ ገልጿል። በዚህ አሰራር እንዲገኝ የሚጠበቀው ድምጽ 70 በመቶ ያህል ነው። ጉዳዩ ይህን ያህል የድጋፍ ድምጽ ማግኘት ካልተቻለ ግን “ቀሪ እንደሚሆን” በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ሁለተኛ ደረጃ መዋቅር የሆነው “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” ላይም፤ የመቶኛ ድጋፍ መጠኑ ዝቅ ቢልም ተመሳሳይ አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል። “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” ማለት ሁሉም ክልሎች፣ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል ተቋማት ተወካዮችን በውስጡ የሚያቅፍ ነው።
ጉዳዮችን “በልዩ ሁኔታ እንዲወስን ወይም እንዲያጸድቅ ታስቦ” መቋቋሙ የተገለጸው የእዚህ ጉባኤ አባላት ብዛት 211 ነው። በእዚህ ጉባኤ ውስጥ የፌዴራል መንግስት በ15 ግለሰቦች ሲወከል፤ ሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ደግሞ እያንዳንዳቸው 14 ተወካዮች አላቸው።
የክልሎቹ እና የከተማ አስተዳደሮቹ ተወካዮች፤ ከመንግስት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች፣ ከወጣቶች፣ ከሃይማኖታዊ ተቋማት ከሲቪል ማህበረሰብ ጥምረት የተውጣጡ ናቸው። የፌደራል መንግስትን በመወከል የእዚህ ጉባኤ አካል የሆኑት ደግሞ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ የሴቶች ፌዴሬሽን፣ የሴቶች ጥምረት፣ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን እና ወጣቶች ናቸው።

በእዚህ ጉባኤ ውሳኔ ለማሳለፍ 70 በመቶ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ሰነድ ላይ ሰፍሯል። “የክልል ተወካዮች ጉባኤ” ውሳኔ የሚሰጠው ከሁለት ሁኔታዎች አንዱን ሲያሟላ እንደሆነም በዚህ ሰነድ ላይ ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ካሉ ክልሎች ቢያንስ ሶስቱ አንድ ጉዳይ በጉባኤ እንዲታይ ጥያቄ ካቀረቡ ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚችል በኮሚሽኑ ሰነድ ላይ ተገልጿል። አንድ ጉዳይ በስራ ቡድኖች ውስጥ የሚፈለገውን 70 በመቶ ድጋፍ ማግኘት ሳይችል ሲቀር፤ ለጉባኤው ሊቀርብ ይችላል።
ጉዳዩ “ማንነት ወይም የህልውና አደጋን የሚመለከት ከሆነ” እና ጥያቄው “መሰረት እንዳለው” በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከተረጋገጠ ወደ ክልል ጉባኤ ሊመራ እንደሚችልም በሰነዱ ላይ ተብራርቷል። በክልል ጉባኤ ላይ የቀረበ አጀንዳ 70 በመቶ እና ከዚያ በላይ ካገኘ፤ “ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ያልፋል።”

ከ40 በመቶ እስከ 69.9 በመቶ ድጋፍ ያገኘ አጀንዳ “ወዲያው ውድቅ እንደማይደረግ” የኮሚሽኑ ሰነድ ይገልጻል። ይህን ያህል የድጋፍ መጠን ያገኘ አጀንዳ ወደ “ስምምነት ግብረ-ኃይል ይመራል” ሲሉ ሰነዱ ያትታል። በሁለት ቀን ውስጥ “የተሻሻለ ሃሳብ” የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለበት የስምምነት ግብረ-ኃይሉ፤ ይህንኑ ለክልሉ ጉባኤ ማቅረብ ይጠበቅበታል።
ለክልሉ ጉባኤ የቀረበው “የተሻሻለው ሃሳብ” 70 በመቶ ድጋፍ ማግኘት እንዳለበት የሚያስረዳው ሰነዱ፤ ይህን ያህል መጠን ካልተገኘ ግን “ሙሉ ለሙሉ ውድቅ እንደሚደረግ” ያብራራል። በግብረ-ኃይሉ የሚደረገው ጥረት “በሂደቱ እውነተኛ መግባባት እንዲኖር ያበረታታል” ሲል ኮሚሽኑ በሰነዱ ላይ አቋሙን አስታውቋል።
ለክልል ጉባኤ የሚቀርብ አንድ አጀንዳ ከ40 በመቶ በታች ድጋፍ ካገኘ “ውድቅ እንደሚደረግ እና ጉዳዩን “እንደገና ማቅረብ እንደማይቻል” በዚሁ ሰነድ ላይ ሰፍሯል። ኮሚሽኑ ከተለያዩ የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች የሚመጡ ውሳኔዎችን፣ ምክረ ሃሳቦችን እና ረቂቆችን ለማጣጣም የሚያስችል “የጋራ ማረጋገጫ ስርዓትን” ተግባራዊ እንደሚያደርግ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

ይህ ስርዓት ተግባራዊ የሚደረገው በመጨረሻ የአጀንዳ ማጽደቅ ሂደት ውስጥ ነው። የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች “የጋራ ማረጋገጫ” ብቻ 8 ቀናትን እንደሚወስድ ሰነዱ ይገልጻል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል “የሰነድ ልውውጥ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የግምገማ እና የማጣጣም፣ የስራ ቡድን አስተያየት፣ የመጨረሻ ማጣጣም” የሚሉት ይገኙበታል።
እነዚህ ተግባራት ከተከናወኑ በኋላ አጀንዳው ለጠቅላላ ጉባኤው እንደሚቀርብ በሰነዱ ላይ ተጠቅሷል። የተጣጣመው አጀንዳ በክልል ተወካዮች ጉባኤ አማካኝነት ለጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርበው፤ 70 በመቶ ድጋፍ ሲያገኝ ብቻ ነው። አጀንዳው ከ70 በመቶ ያነሰ ድጋፍ ካገኘ፤ ጉዳዩ ወደ “ጋራ ማረጋገጫ ቡድን” ተመልሶ እንደሚመራ በሰነዱ ላይ ተገልጿል።
የጋራ ማረጋጋጫ ቡድኑ “የተሻሻለ ሃሳብ” አዘጋጅቶ ጉዳዩን ለሁለተኛ ጊዜ ለክልል ተወካዮች ጉባኤ እንደሚያቀርብም ሰነዱ ያስረዳል። የተሻሻለው ሃሳብ በክልል ተወካዮች ጉባኤው ውድቅ ከተደረገ ግን “ሃሳቡ ቀሪ ይሆናል”።

በዝርዝር ጉዳዮች ላይ “ድምጽ የማይሰጠው” አራት ሺህ ተሳታፊዎችን የሚይዘው ሀገራዊ ጠቅላላ ጉባኤ፤ አጀንዳዎች የሚያጸድቀው “በአጠቃላይ” ነው። ሆኖም ጠቅላላ ጉባኤው በአጀንዳዎች ላይ ማብራሪያ ሊጠይቅ ይችላል። በዚህ መልክ ለጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ወደ ህዝበ ውሳኔ ሊሄዱ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ኮሚሽኑ በሰነዱ ላይ አስታውቋል።
ተሳታፊዎች “ያልተፈቱ ጉዳዮች” በህዝበ ውሳኔ እንዲፈቱ ከጠየቁ ይህ አማራጭ ተግባራዊ እንደሚደረግ የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት ሰነዱ ያስረዳል። አንድ አጀንዳ ሁሉንም የውሳኔ ሂደቶች አልፎ ለጠቅላላ ጉባኤ ሲቀርብ እና “ጠንካራ ተቃውሞ ሲያጋጥመው” ወደ ህዝበ ውሳኔ ሊመራ እንደሚችልም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሰነድ ጨምሮ አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
