
ታትሟል30 ሀምሌ 2026, 08:51 EAT
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በቅርቡ አንድ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ሞዴል በራሱ ሌላ ኩባንያን ‘ሃክ’ ማድረጉን ተከትሎ፣ አስተዳደራቸው የኤአይ መገልገያዎች ላይ ያለውን የቁጥጥር ኃይል ለመጨመር ማሰቡን አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ፣ የቻትጂፒቲ ባለቤት የሆነው የ ‘ኦፕንኤአይ’ ኩባንያ የኤአይ መገልያዎች ወደሌሎች ኩባንያዎችን የግል ቴክኖሎጂ ሰርገው ስለመግባታቸው ተጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱም፣ “ኤአይን እየተመለከትነው ነው። የቁጥጥር መንገዶችንም እያየን ነው፤ [በቴክኖሎጂው] እየመራን መሆኑንም እያረጋገጥን ነው” ብለዋል።
ይህ የትራምፕ ንግግር ከዚህ ቀደም ኤአይን በተመለከተ ጣልቃ አለመግባትን ሲመርጥ የነበረው አስተዳደራቸው በጉዳዩ ላይ ድምጸቱን እየለወጠ መሆኑን የሚጠቁም ሆኗል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን አስተያየት የሰጡት ታዋቂ የኤአይ መገልገያዎች አላቸው የሚባለው የሳይበር ጥቃት የማድረስ አቅም አከራካሪ እየሆነ በመጣበት ወቅት ነው። በተመሳሳይም ዋይት ሀውስ በተፎካካሪው የቻይና ቴክኖሎጂ ላይ ዛቻ የሰነዘረበት ጊዜ ነው።
የኤአይ መገልገያዎች ላይ ቁጥጥር ሊደረግ የሚችልባቸው የተወሰኑ አማራጮች ጠረጴዛው ላይ መሆናቸውን የገለጹት ትራምፕ፤ ይህ አይነቱ እርምጃ ግን በጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት አክለዋል።
“በድንገት ከቻይና ሁለተኛ የምንሆንበት ደረጃ ላይ በሚያስቀምጠን መልኩ [የኤአይ ኩባንያዎቹን] ልንገድባቸው አንፈልግም” ሲሉም ሀሳባቸውን አብራርተዋል።
“ቻይና በተጨባጭ [ኤአይ ላይ] ምንም ቁጥጥር የላትም። በትንሹ ያለገደብ እየሰራች ነው” ብለዋል።
ቢቢሲ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለዋይት ሀውስ ጥያቄ አቅርቧል። በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲም አስተያየቱን እንዲሰጥ ተጠይቋል።
የኦፕንኤአይ የኤአይ መገልገያዎች ከተሰሩበት ዓላማ እና ከተሰጣቸው ትዕዛዝ ውጪ ላደረሷቸው ቢያንስ ሁለት የሳይበር ጥቃቶች ኩባንያው ባለፈው ሳምንት ላይ ኃላፊነቱን ወስዷል።
ረቡዕ ዕለት ወደ ዋሽንግተን የተጓዙት የኦፕንኤአይ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳም አልትማን በኩባንያው የኤአይ መገልገያዎች ‘ሀክ’ የተደረጉ ተጨማሪ የቴክኖሎጂ ስርዓቶች ይኖሩ እንደሆነ በጋዜጠኞች ተጠይቀው ነበር።
ዋና ሥራ አስፈፃሚውም “ማለት፤ አዎ ሊኖር ይችላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ቀደም፤ የኦፕንኤአይ ዋነኛ ተፎካካሪ ኩባንያ በሆነው ‘አንትሮፒክ’ የተሰራ የኤአይ ሞዴል እንዳይለቀቅ አድርጎ ነበር። መንግሥት ጣልቃ የገባው የኤአይ ሞዴሉን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አደጋ ያመጣል በሚል ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ የትራምፕ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አማካሪ ማይክራቲሲኦስ የቻይና የኤአይ ኩባንያዎችን በአሜሪካን የኤአይ ቴክኖሎጂ ላይ “በኢንዱስትሪ ደረጃ” ስርቆት ፈጽመዋል የሚል ክስ ማቅረባቸውን ሚያዝያ ላይ የወጣ አንድ የዋይት ሀውስ የውስጥ ማስታወሻ አሳይቷል።
ባለፈው ሳምንት ላይም የቴክኖሎጂ አማካሪው፤ ‘ሙንሻት ኤአይ’ በተባለው የቻይና ኩባንያ የተለቀቀው ‘ኪሚ 3’ የኤአይ ሞዴል የበለጸገው ከአንትሮፒክ በተሰረቀ መረጃ ነው ሲሉ በድጋሚ ከስሰዋል።
የቻይና መንግሥት ይህ አይነት ክሶችን በተደጋጋሚ ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሰንትም በዚህ አይነቱ እንቅስቃሴ ምክንያት የቻይና ኤአይ ኩባንያዎች ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
