ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የቀድሞው የዋይት ሀውስ የጤና አማካሪ አንቶኒ ፋውቺ
የምስሉ መግለጫ,የቀድሞው የዋይት ሀውስ የጤና አማካሪ አንቶኒ ፋውቺ

ታትሟል30 ሀምሌ 2026, 09:01 EAT

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የቀድሞው የዋይት ሀውስ የጤና አማካሪ አንቶኒ ፋውቺ ምክር ቤትን ተዳፍረዋል የሚለውን ለመወሰን ድምጽ ሊሰጥ እንደሆነ ተገለጸ።

የአሜሪካ ምክር ቤት ኮሚቴ ኃላፊ እንደገለጹት፤ ፋውቺ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ስለወሰዷቸው እርምጃዎች ተጠይቀው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክር ቤቱን ተዳፍረዋል ተብሎ ሊወሰን ይችላል።

የተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያው ፋውቺ ምክር ቤት ቀርበው የወረርሽኙን ወቅት በተመለከተ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ከ100 ጊዜ በላይ ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

ፋውቺ ለጥያቄዎቹ የሚሰጡት መልስ፤ በወንጀል ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ስለሚችል ከመናገር መቆጠብ የሚችሉበትን የሕገ መንግሥት አንቀጽ በመጥቀስ ምላሽ እንደማይሰጡ ደጋግመው ተናግረዋል።

ፋውቺ ምላሽ ለመስጠት አለመፍቀዳቸውን ተከትሎ የሕዝብ እንደራሴው ራንድ ፖል “ምክር ቤትን በመዳፈር ጥፋተኛ የሚባሉበት ዕድል ሰፊ ነው” ብለዋል።

የሕዝብ እንደራሴው ለረዥም ጊዜ ፋውቺን መረጃ በመደበቅ ሲከስሱ ቆይተዋል።

ፋውቺ ስለ ኮሮናቫይረስ መነሻ እንዲሁም ወረርሽኙ በተነሳበት ቻይና፣ ውሃን ለተደረገ ምርምር ስለተሰጠ የገንዘብ ድጋፍ መረጃ ለማፈን ሞክረዋል ተብለዋል።

ፋውቺ በበኩላቸው ምንም ጥፋት እንዳልፈጸሙ ገልጸዋል።

የቀድሞው የዋይት ሀውስ የጤና አማካሪ ክስ ይቀርብባቸው እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ረቡዕ ዕለት ምክር ቤት ቀርበው ከአገር ውስጥ ደኅንነት እና ሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ፋውቺ የብሔራዊ አለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ተቋም ኃላፊ ነበሩ።

ከጠበቃቸው በተሰጣቸውን ምክር መሠረት ጥያቄዎችን ላለመመስ የሚያስችላቸውን የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አንቀጽ አምስት ጠቅሰዋል።

አንቀጽ አምስትን ጠቅሶ ራስን በወንጀል ተጠያቂ ላለማድረግ መልስ አልሰጥም ማለት ጥፋት አይደለም።

በአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓት በመጀመሪያ ደረጃ የወንጀል ምርመራ ወቅት ይሄንን አንቀጽ መጥቀስም የተለመደ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2022 ስለ ‘ትራምፕ ኦርጋናይዜሽን’ በፍርድ ቤት ሲጠየቁ አንቀጽ አምስትን በተደጋጋሚ በመጥቀስ ምላሽ አልሰጡም ነበር።

የሕዝብ እንደራሴው ፖል እንዳሉት፤ ፋውቺ ምክር ቤትን ተዳፍረው ከሆነ ውሳኔ ለመስጠት በቀጣይ ሳምንት ድምጽ ይሰጣል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው፤ ምክር ቤትን ተዳፍረዋል ተብሎ የሚወሰነው 60 የድጋፍ ድምጽ ከተሰጠ ነው። ይሄን ያህል ድምጽ ለማግኘት ዲሞክራቶች ከሪፐብሊካኖች ጎን መቆም አለባቸው።

በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ከተገኘ ጉዳዩ ወደ ዲሲ ዋና ዐቃቤ ሕግ ይወሰድ እና የክስ ሒደት ይጀመራል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሥልጣን ሳይወርዱ በፊት ፋውቺ ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2025 በፈጸሟቸው ድርጊቶች ተጠያቂ እንዳይሆኑ ቅድመ ምሕረት (pre-emptive pardon) ሰጥተዋል።

ሆኖም ግን ፋውቺ ከዚህ ጊዜ በኋላ በተፈጸሙ ድርጊቶች ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም በምክር ቤት የነበራቸውን ቆይታ ያካትታል።

የምክር ቤቱ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት የሕዝብ እንደራሴ ፖል እንዳሉት ፋውቺ ምሕረት የተደረገላቸው ቢሆንም “ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ይሆናሉ” የሚለው የሚወሰነው በፍርድ ቤት ነው።

ፕሬዝዳንቶች የሚሰጡት ምሕረት የሚሸፍነው በፌደራል ደረጃ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ሲሆን ይህም በግዛቶች ደረጃ የሚተገበር አይደለም።

የፍሎሪዳ ዋና ዐቃቤ ሕግ ጄምስ ዩትሀመር፤ አንቶኒ ፋውቺ ላይ ምርመራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል። ምን ወንጀሎች ፈጽመዋል ተብሎ እንደሚታመን ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የሕዝብ እንደራሴ ፖል፤ ኮሮናቫይረስ በቻይና ውሃን ከሚገኝ የቫይረስ ምርምር ማዕከል ሾልኮ ወጥቶ ሊሆን እንደሚችል ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ሲአይኤ አምና ባወጣው መግለጫ ይሄንን ሐሳብ እንደሚደግፍ አስታውቋል።

ፋውቺ ኮሮናቫይረስ በተፈጥሯዊ መንገድ የተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል። የሕዝብ እንደራሴው እንደሚገልጹት ግን ፋውቺ በአደባባይ ይህንን ቢሉም በግላቸው “ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ሾልኮ የወጣ ነው” ብለው እንደሚያምኑ የውሎ መዝገባቸው ላይ የተጻፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ዲሞክራት የሕዝብ እንደራሴ ማጊ ሐሰን “የምክር ቤቱ ጥያቄ ፋውቺን ጠልፎ ለመጣል ያለመ ነው” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ፋውቺን “እብድ” ሲሉ አጣጥለዋል።

ትራምፕ “ከመጀመሪያውም እንዳልኩት ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ ሾልኮ ነው የወጣው። ፋውቺ ቻይናን ለመከላከል ሲል ሐሳቡን አጥብቆ ተቃውሟል” ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ዓመት ያወጣው መግለጫ የቫይረሱ መነሻ ተፈጥሯዊ እንደሆነ አስታውቋል።

ይህም ቫይረሱ ከእንሰሳት ወደ ሰዎች ተሻግሮ ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ነው።

ካለው ማስረጃ አንጻር ይህ መላ ምት “የተሻለ ድጋፍ” ያለው እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል። ሆኖም ግን መላ ምቱ የመጨረሻ ድምዳሜ አይደለም።

ፋውቺ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እና ከዚያ በኋላም የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል። አምና ትራምፕ ባስተላለፉት ውሳኔ የደኅንነት ጥበቃቸው ተነስቷል።

ከስድስት ዓመታት በፊት ስለ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፍጥነት መረጃ ለማግኘት ሳይንቲስቶች እየተጣጣሩ በነበረበት ወቅት፤ ፋውቺ በአሜሪካ ጤና ዘርፍ የታመኑ ከፍተኛ ባለሙያ ነበሩ።

ከትራምፕ ጋር ግን እምብዛም አይግባቡም።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2021 ፋውቺ ከኮሮናቫይረስ ክትባት ጋር ላከናወኗቸው ተግባሮች ከትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።