“ጽምዶ” እስከምን ድረስ?
ከሶስት ወር በላይ ለሆነ ጊዜ ከመገናኛ ብዙሃን እራቅ ያልኩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የ”ጽምዶ” ጉዳይ አወዛጋቢ
መሆኑን እያየሁ ነው። ሌላ ህዝብ ጨራሽ የሆነ ከፍተኛ ጦርነት ሊፈነዳ ከመቃረቡ ጋር በተያያዘ በስሜትም
በምክኒያትም “ጽምዶ” ሲደገፍም ሲነቀፍም ሰምቻለሁ። ከፊታችን እየመጣ ያለው ጦርነት ምን አልባትም
እስካሁን ካየናቸው ጦርነቶች ሁሉ የበለጠ ህዝብ ጨራሽ፣ የአገሪቱን ህልውናም የበለጠ አደጋ ላይ ሊጥል
የሚችል ቢሆንም ለብዙዎቻችን ብዙም ያሳሰበን አይመስልም። “ካልደፈረሰ አይጠራም” በሚል ስሜት
የጦርነቱን መባባስ በጉጉት ስንጠብቅ እንጂ ጦርነቱን ለማስቀረት ስንሞክር አንታይም።
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውንም ሆነ ከፊታችን እየመጣ ያለውን ጦርነት በሁለት መንገድ ማስቀረት
በተቻለ ነበር። በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ለህዝብና ለአገር ደህንነት ቅንጣቢ የተቆርቃሪነት ባህሪ ቢኖረው
ኖሮ እጁን ለሀቀኛ ድርድር በመዘርጋት ጦርነቱን ሊያስቀረው በቻለ ነበር። ተቃዋሚው ጐራም ከጦርነት
የተለዬ አዲስ የትግል አቅጣጫን ማዬት የተሳነው ደካማ ኃይል ባይሆን ኖሮ ጠንካራ ሰላማዊ ህዝባዊ
እምቢተኝነትን በአገሪቱ በማቀጣጠል ጦርነት የለውጥ አማራጭ መሆኑን ሊያስቀረው ይችል ነበር። ነገር ግን
በቀዳሚነት አገዛዙ፣ በመቀጠልም ተቃዋሚ ኃይሎች የህዝብና የአገር ደህንነትን ማስቀደም ባለመቻላችን
ሁላችንም ከጦርነት አዙሪት የመውጣት ፈተናን ወድቀናል። የግል ስሜታችንና እብሪታችን ከህዝብ ህልውናና
ደህንነት በመብለጡ የባሰ ትውልድ ጨራሽና አገር አፍራሽ ሊሆን የሚችል ጦርነት ውስጥ ልንዘፈቅ “አንድ
ሀሙስ” ቀርቶናል።
አገሪቱ በዚህ ዓይነት አስፈሪ ድባብ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች
የጐንዮሽ ግጭታቸውን አቁመው የብልጽግናን አገዛዝ ተባብረው ለመጣል ስምምነት ላይ የደረሱ መሆኑ
ከግምት ያለፈ ተጨባጭ እውነት እየሆነ የመጣ ይመስላል። “ይመስላል” ያልሁት ያለምክኒያት ሳይሆን
እስካሁን ተጽፎና ተፈርሞ ያዬነው ስምምነት ስለሌለ ነው። ቢያንስ ግን የፋኖና የትግራይ ኃይሎች ትብብር
ለመፍጠር ስለመስማማታቸው አመራሮቹ በድፍረት ሲናገሩ እየሰማን ነው። ይህ ከዓመት በፊት ፈጽሞ
ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ አዲስና አዎንታዊ ክስተት ነው።
እኔ የአገራችን የፖለቲካ ችግር በጦርነት ሊፈታ አይችልም ብዬ የማምን ነኝ። የእኔ ምርጫ ጦርነት
እንዲቀጥል ሳይሆን ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኛነት በአገራችን ተቀጣጥሎ በአንጻራዊነት በአጭር ጊዜ፣ በጣም
ባነሰ መስዋዕትነትና ለዘላቂ ለውጥ ዋስትና በሚሰጥ አግባብ ለውጥ እንዲመጣ ነው። መደማመጥና
መተማመን አቅቶን እንጂ በዚህ ስልት የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ጥርጥር የለኝም።
በዚህ አቋሜ ምክኒያት ይህንን መጣጥፌን በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች—፣ “ታዲያ አንተ ምን አገባህና ስለ
ተዋጊ ኃይሎች ትብብር አስተያዬት ትሰጣለህ?” የሚል ጥያቄ ሊያነሱ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ይሁንና ይህ
ዓይነቱ አስተያዬት ስህተት ነው። የሚካሄደውን የትጥቅ ትግል ብንዎደውም ባንዎደውም በሌሎች ቁጥጥር
ስር ያለ በመሆኑ እኔና እኔን መሰል ሰዎች ስለተቃዎምን ብቻ ልናስቆመው አንችልም። የጦርነቱ መቀጠል
ደግሞ በእያንዳንዳችን የዛሬም ሆነ የወደፊት ህይዎት ላይ የሚያስከትለው አንደምታ ከፍተኛ ስለሆነ
በርዕሰ-ጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት የሁላችንም መብት መሆኑ መታዎቅ አለበት። እኔም በጉዳዩ ላይ
የምሰጠው ይህ አስተያዬት ከዚህ መብቴና ጥቅሜ ጋር የተያያዘ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
የአገዛዙ ተቃዋሚ የሆኑ ታጣቂ ኃይሎች የጋራ ጥቅምን ማስቀደም ተስኗቸው እንደዚህ ዓይነቱን ትብብር
ለመፍጠር ዓመታትን ማባከናቸው የሚያጸጽት ነው። ዘግይተውም ቢሆን ዛሬ ላይ ወደዚህ ዓይነቱ ትብብር መምጣታቸው ከአሁን በፊት ከሚታዎቁበት የተካረረ አቋም አኳያ የማይጠበቅ ክስተት ነው ሊባል ቢችልም
ከገጠማቸው የህልውና ፈተና አኳያ ግን መተባበራቸው የሚጠበቅ ነው።
አንደኛ፦ የሚፋለሙት የብልጽግና አገዛዝ ሁሉንም ቅራኔ በጦርነት መንገድ ብቻ ለመፍታት በማሰብ
ለውይይትና ለድርድር በሩን የዘጋ በመሆኑ፤ ሁለተኛ፦ አገዛዙ በታጣቂ ኃይሎችና በሚታገሉለት ህዝብ ላይ
የጋረጠው አደጋ ከማንም ጋር ለመተባበር የሚያስገድድ የህልውና አደጋ በመሆኑ ምክኒያት እንዲህ ዓይነቱን
አገዛዝ ለማስዎገድ መተባባራቸው እንዴት ዘገዬ? ሊባል የሚችል እንጂ፣ ለምን ሆነ? የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ
የሚገባው አይደለም። የአገዛዙ የጦረኝነትና የጭካኔ አካሄድ እንኳንስ በአገር ውስጥ ካሉ ኃይሎች ጋር
በኢትዮዽያ “ታሪካዊ ጠላትነት” ከሚታዎቁ የውጭ መንግስታትም ጋር ጭምር ለመተባበር የሚያስገድድ
ሲሆን እያዬን ነው። ለዚህ ዓይነቱ ታሪካችንን የሚያጐድፍ ክስተት ለመዳረጋችን ዋናውና ቀዳሚው ተጠያቂ
በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ነው።
ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ችግራችን በዘላቂነት በጦርነት መፍትሄ አያገኝም የሚል የጠነከረ አቋም ያለኝ
ቢሆንም፣ ታጣቂ ኃይሎች የጐንዮሽ የእርስ-በርስ ትግልን አቁመው ከአገዛዙ በተጻራሪ ተባብረው መቆማቸው
በህዝባችን ላይ ወደፊት ሊደርስ የሚችለውን እልቂት ከመቀነስና አገሪቱን ከመፍረስ አደጋ ከማዳን አኳያ
አንጻራዊ የሆነ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
አገራችን ከህልውና ጥፋት እንድትድን ከተፈለገ ሁለት መሰረተዊ ለውጦች መምጣት አለባቸው።
የመጀመሪያው፣ የሁላችንም የህልውና አደጋ የሆነው የብልጽግና አገዛዝ ከስልጣን መወገድ አለበት።
ሁለተኛው፦ ከአገዛዙ ውድቀት ማግስት ሁሉን-አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግስት መቋቋም ይኖርበታል።
የታጣቂ ኃይሎቹ ትብብር ቢያንስ የመጀመሪያውን አጀንዳ ማሳካት ያስችላል። ታጣቂዎቹ ግልጽ የጋራ
አጀንዳ ይዘው ከተባበሩ አገዛዙን በአጭር ጊዜ ከስልጣን እንደሚያስዎግዱት በእኔ በኩል ጥርጥር የለኝም።
አገዛዙ የ“ጽምዶ”ን ወይንም የተቃዋሚ ኃይሎችን ትብብር አብዝቶ ሲፈራው የምናየውም የሚያስከትለውን
ውጤት ስለሚረዳው ነው። ታጣቂ ኃይሎቹ ከተበታተነና ከጐንዮሽ ትግል ወጥተው የብሄርና የፖለቲካ አጀንዳ
ልዩነትን የተሻጋረ፣ ለጋራ የህልውና አጀንዳ ቅድሚያ የሰጠ ትብብር መፍጠራቸውም ሁለተኛውን አጀንዳ
ለማሳካት የራሱ አወንታዊ ድርሻ ሊኖረው ይችላል። በእነዚህ ምክኒያቶች ጦርነቱ መቀጠሉ እስካልቀረ ድረስ
ታጣቂ ኃይሎቹ መተባበር መቻላቸው ቢያንስ በህዝብና በአገር ላይ ሊከሰት የሚችልን አደጋ ከመቀነስ አኳያ
ጠቃሚ ይሆናል።
ይሁንና እነዚህ ዓላማዎችም ሊሳኩ የሚችሉት እንዲሁ ትብብር ስለተፈጠረ ብቻ ሊሆን አይችልም።
ትብብር የዓላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያ እንጂ በራሱ ግብ አይደለም። ስለሆነም ትብብሩን መፍጠር ያስፈለገው
ለምንድን ነው? ትብብሩ ዘላቂ ውጤት እንዲያስገኝስ በመካከላችሁ ያሉ መሰረታዊ
ቅራኔዎችስ በምን አግባብ /Mechanism/ እንዲፈቱ ተስማማችሁ? የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች
አስቀድመው መልስ ማግኘት አለባቸው።
በሰነድ የተደገፈ ስምምነት እስካሁን ባናይም የሰሞኑን የወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄርን አስተያየት
ጨምሮ የታጣቂ ኃይሎቹ አመራሮች ከሚሰጧቸው የተለያዩ ቃለ-መጠይቆች ለመረዳት እንደሚቻለው
የሁሉም ህልውና አደጋ የሆነውን የብልጽግናን አገዛዝ በጋራ ታግሎ ለመጣል ስምምነት ላይ የተደረሰ
ይመስላል። ይህ ስምምነት “ትብብሩን መፍጠር ያስፈለገው ለምንድን ነው?” የሚለውን የመጀመሪያውን
ጥያቄ በግልጽ ይመልሳል። ይህ በራሱ የፖለቲካ ብስለት የተያበት በጐ ለውጥ ቢሆንም በአገሪቱ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዘው ሁለተኛው ጥያቄ ግን ገና መልስ አላገኘም። ጥያቄውም እንደ ጥያቄ ትኩረት
ተሰጥቶት ሲነሳ እየታዬ አይደለም።
ታጣቂ ኃይሎቹ በመካከላቸው ላሉ መሰረታዊ ቅራኔዎች ምን ዓይነት የተጨበጠ መፍትሄ /Solution/
እንዳላቸው መጠየቅም ሆነ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በአሁኑ ወቅት መጠበቅ ተገቢ አይደለም ብዬ
አምናለሁ። ነገር ግን ቅራኔዎቹ በምን አግባብ /Mechanism/ መፈታት እንዳለባቸው አስቀድሞ
መስማማትና ውጤቱን ለህዝብ ማሳዎቅ ይገባል።
ጉዳዩን በአንድ ተጨባጭና ብዙዎች ሊያነሱት በሚፈሩት ምሳሌ የበለጠ ግልጽ ላድርገው። ለምሳሌ—፣ ፉኖ
እና የትግራይ ኃይሎች ወልቃይትን በተመለከተ “የአማራ ክልል አካል ይሁን ወይንስ የትግራይ?” በሚለው
ቅራኔ ዙሪያ አሁንም ሆነ ወደፊት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ መጠበቅ የለብንም። በእንዲህ ዓይነቱ ዝርዝር
ጉዳይ መፍትሄ ላይ እንዲደረስ መጠየቅም ጊዜውን ያልዋጀና ትብብርን ሳይሆን ቅራኔን የማስቀጠል ውጤት
የሚያስከትል ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ጊዜውን ያልጠበቀና ተገቢ ያልሆነ ጥያቄና ግፊትም ከአገሩና ከህዝቡ
ይልቅ አገዛዙን የበለጠ የሚጠቅም ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በሱ የቁማር ካርታ መጫዎት ነውና።
በነገራችን ላይ መፍትሄውን የመወሰኑ መብትም የፖለቲካ ኃይሎች ሳይሆን የህዝብ መሆኑ መታዎቅ አለበት።
የፖለቲካ ኃይሎቹ በአንዳንዶቹ አጀንዳዎች ዙሪያ እንኳንስ የህልውና አደጋ ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት
ለዘለዓለምም ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ። አንዳንዶቹ የልዩነት አጀንዳዎች ሁልጊዜም የምርጫ
መፎካከሪያ አጀንዳ ሆነው የሚቀጥሉ ናቸው። ስለዚህ ከፖለቲካ ኃይሎች የሚጠበቀው በመፍትሄው ላይ
መስማማት ሳይሆን በቅራኔ አፈታት ስልቱ /Mechanism/ ላይ መስማማት ነው። ብዙውን ጊዜ በዚህ መርህ
ላይ የተንሻፈፈ አረዳድ ስላለ ነው አንዳንድ እራሳቸውን እንደ መፍትሄ ሰጭ የሚቆጥሩ የፖለቲካ ኃይሎች
አንዳንድ አጀንዳዎችን “የማንደራደርባቸው ቀይ መስመሮቻችን ናቸው
” በማለት ሲመጻደቁ የምንሰማው።
ነገር ግን ቅራኔውን በምን አግባብ ወይም ስልት /Mechanism/ እንዲፈታ ተስማምታችኋል? በውይይትና
በድርድር? በህዝበ-ውሳኔ? በህገ-መንግስት ማሻሻያ? በሌላ ዙር ጦርነት? ወይስ በምን? የሚለው ጥያቄ
አስቀድሞ ስምምነት ላይ ሊደረስበት የሚገባና ባልተድበሰበሰ ሁኔታም የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮዽያ
ህዝብ መገለጽ ያለበት ነው። በዚህ እረገድ የሚደርሱበት ስምምነትም ምንጊዜም የህዝቡን የመወሰን
መብትና ስልጣን የማይሸራርፍ ሊሆን ይገባዋል።
ሌሎቹና አብዛኛዎቹ በአገራችን ታጣቂ ኃይሎች መካከል ያሉ ቅራኔዎችም በዋናነት ከሕገ-መንግስት ጋር
የተያያዙ ናቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ ከሕገ-መንግስቱ ውስጥ የትኛው ድንጋጌ በምን ዓይነት ሌላ ድንጋጌ
ይቀየር? ብሎ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ለመስማማት መሞከር በአሁኑ ወቅት የሚጠቅምና የሚገባ አይደለም።
ነገር ግን ሕገ-መንግስታዊ የሆኑ ቅራኔዎችን ወደፊት በምን አግባብ /Mechanism/ እንዲፈቱ እንደሚፈለግ
አስቀድሞ መስማማት የግድ ያስፈልጋል። በዚህ እረገድ እስካሁን የተደረገ ስምምነት የለም፤ ወይም
ስለተደረሰው ስምምነት ለህዝቡ በግልጽ አልተነገረም።
ታጣቂ ኃይሎች የሚፈጥሩት ትብብር ቢያንስ የቅራኔ አፈታት ስልቶች ላይ ግልጽ የሆነ ስምምነት ላይ
የተደረሰበት ሊሆን ይገባዋል። የቅራኔ አፈታት ስልቱ ላይ መስማማት እስከተቻለ ድረስም “አይነኬ”
ወይም
“ቀይ መስመር” የሚባልና ለትብብር እንቅፋት የሚሆን ከባድ አጀንዳ አይኖርም። በችግር አፈታት ስልቱ ላይ
የሚደረሰው ስምምነትም እንደ የጦርነት የአፈጻጸም ስምምነት በሚስጥር መያዝ ያለበት ሳይሆን የጉዳዩ ዋና
ባለቤት ለሆነው ህዝብ በግልጽ ሊነገር የሚገባው ነው። ይህንን ማድረግም የሚፈጠረው ትብብር በህዝብና በዓለም-አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ የተሻለ ድጋፍ እንዲያገኝ፣ ትብብሩም የተሻለ አቅም እንዲኖረውና
ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ እረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ይሆናል።
ስለሆነም ታጣቂ ኃይሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥታችሁ በአስቸኳይ ልትነጋገሩና ውጤቱንም ለህዝብ
ልታሳውቁ ይገባል እላለሁ። የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ህዝብም ካለፈ ታሪኩ በመማር ትውልዱ ሌላ ዙር የባሰ
መስዋዕትነት ከመክፈሉ በፊት ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ግልጽ መልስ እንዲያገኝ አስፈላጊውን ግፊት ማድረግ
አለበት። ለህዝቡ ትግል ውጤታማነት ተቆርቋሪ የሆናችሁ መገናኛ ብዙሃንም ይህንን ርዕሰ-ጉዳይ ወቅታዊ
የመዎያያ አጀንዳ ልታደርጉት ይገባል። የህዝብ የለውጥ ፍላጐት ዳግም እንዳይከሽፍ ከተፈለገ ይህንን ጥያቄ
ሳያሳድሩ መመለስ እጅግ አስፈላጊ ነው። የጋራ የህልውና ጥያቄን ላስቀደመ ማንኛውም የፖለቲካ ኃይልም
በዚህ አጀንዳ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ ሊሆን አይችልም።
ልደቱ አያሌው ልደቱ አያሌው-3ኛ መንገድ
ሀምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም





