ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ
EPRP – Ethiopian People Revolutionary Party/ ኢሕአፓ- የኢትዮጵያ ህዝብ አቢዮታዊ ፓርቲ
Tatek Assefa ·t͏e͏o͏S͏p͏s͏n͏d͏o͏r͏8͏2͏a͏9͏a͏7͏c͏8͏7͏8͏m͏4͏m͏t͏g͏6͏3͏1͏9͏2͏7͏f͏7͏g͏5͏h͏8͏u͏a͏l͏c͏g͏6͏6͏8͏9͏0͏9͏2͏c͏8͏h͏4͏5͏h͏6͏4͏h͏1͏0͏ ·
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መ.ኢ.አ.ድ) All Ethiopian unity party ·
Tatek Assefa ·t͏e͏o͏S͏p͏s͏n͏d͏o͏r͏8͏2͏a͏9͏a͏7͏c͏8͏7͏8͏m͏4͏m͏t͏g͏6͏3͏1͏9͏2͏7͏f͏7͏g͏5͏h͏8͏u͏a͏l͏c͏g͏6͏6͏8͏9͏0͏9͏2͏c͏8͏h͏4͏5͏h͏6͏4͏h͏1͏0͏ ·
የሕዝብ ሕይወትና ክብር ይጠበቅ!
በማንነት ተኮር ጥቃቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የሕግ የበላይነት መጓደል ላይ
ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ በረጅሙ ታሪኳ በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁማ አሻራቸውን እያሳረፉ ያለፉ ታሪካዊ ወቅቶችን አሳልፋ የቆመች ጠንካራ ሀገር መሆኗን ወዳጅም ጠላትም የሚመሰክረው ቢሆንም፣
ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት ውስጥ በተፈጠሩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ምክንያት መተኪያ የሌላቸው ብዙ ልጆቿ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ ከሀገር ተሰደዋል፤ በሕግና በመብት ጥበቃ ላይም ከባድ ፈተናዎች ተፈጥረዋል። ዛሬ የምንገኝበት ጥልቅና ውስብስብ ችግር ካለፉት የተወረሰና በየጊዜው እየተባባሰ የመጣ እንጂ በአጋጣሚ የተፈጠረ አይደለም፤
የአንድነት ታሪኮቻችን፣ የጋራ ባህሎቻችን እና እምነቶቻችን የሀገሪቱ ቋሚ ሀብቶች ቢሆኑም፣ የፖለቲካ ልዩነቶች፣ የሥልጣን ውድድሮች እና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጽንፈኛ አመለካከቶች ሀገር ለምትገኝበት አጠቃላይ የመከራ ዶፍ ዋና ምክንያቶች ሆነዋል።
“የብሔሮችንና የክልሎችን መብት ለማስጠበቅ” በሚል ሽፋን የቋንቋና የዘር ሽንሸና እንደ ፖለቲካዊ ሥርዓት ተቆጥሮ ሕገ-መንግሥታዊ ሽፋን ተሰጥቶት የቆየው አካሄድ፣
በተጨባጭ ግን ሀገር ሀገር ሆና እንድትቀጥል መሠረት የሆኑትን ማኅበራዊ እሴቶች በማሳሳትና የሐሰት ትርክትን በመዝራት ሀገራዊ ህልውናችንን ለከፍተኛ አደጋ ዳርጎታል።
ወቅታዊው የሰብዓዊ መብትና የፀጥታ ሁኔታ፥ ባለፉት ዓመታት በተለይም በአንድ ብሔረሰብ ላይ ትኩረት ተደርጎ የቀጠለው ሀገራዊ ጭቆና፣ ግድያ፣ አፈና፣ ንብረት ነጠቃ፣ ጅምላ እስራት እና ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ክልከላ በፖለቲከኞች፣ በጋዜጠኞች፣ በአክቲቪስቶች፣ በነጋዴዎች፣ በሾፌሮች፣ በመንግሥት ሠራተኞች፣ በተማሪዎችና በሐኪሞች ጭምር ላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን እየተመለከትን ነው።
የአሁኑ ሥርዓት በመጀመሪያው ወቅት የቅርፅ ለውጥ በማሳየት የተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ይሰፍናል የሚል የሰላምና የፍትሕ ተስፋን ቀስቅሶ ነበር።
ይሁን እንጂ ወዲያውኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል በተፈጠሩ ጥቃቶች የአማራ ማኅበረሰብና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ግድያ፣ ከቦታ ማፈናቀል፣ ንብረት መዝረፍና ማውደም፣ የአምልኮ ቦታዎችን ማፍረስና በግድ እምነት ማስቀየር የመሳሰሉ ከባድ ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
በአማራ ክልል በሚካሄደው ግጭት ምክንያት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከሚደርሰው አሰቃቂ ግፍ በተጨማሪ፣ አብያተ ክርስቲያናትን በከባድ መሣሪያዎች ማውደም፣ ካህናትን፣ መነኮሳትንና ገዳማውያንን መግደል ተባብሷል።
ለአብነት ያህል፡-
* በጎጃም በደብረ ኤልያስ የተገደሉት ገዳማውያን፣
* በጎንደር ጠገዴ፣ በጨጨሆ መድኃኔዓለም የደረሰው ጥቃት፣
* በዝቋላ ገዳም በተደጋጋሚ የተፈጸመ የንጹሐን መነኮሳትና አገልጋዮች ሕይወት ያለፉበት አሰቃቂ ግድያ፣
* በምዕራብ ጎጃም በብራቃት ከተማ ዙሪያ በአብነት ተማሪዎች ላይ የደረሰው እልቂት፣
* በሸዋ ደራ አካባቢ በአንድ ትልቅ የእስልምና መምህር ላይ የደረሰው የግፍ ግድያ፣
* በወልዲያ በቤተ ክርስቲያን መርጌታና ተማሪዎች ላይ የደረሰው ፍጅት፣
* እንዲሁም በደቡብ ወሎ በገዳም ላይ በተተኮሰ የድሮን ጥቃት የተገደሉ መነኮሳት፣
በመላ አገሪቱ የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ ሃይማኖትና ዘር ተኮር ጥቃቶች አሳሳቢ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን ያሳያሉ።
ከዚህም በላይ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል አዲስ አውዳሚ ጦርነት ሊከሰት የሚችልበት የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ አገሪቱን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስድና ቋፍ ላይ ያለውን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነው።
በዚህም ምክንያት ባሳለምነው ጦርነት የወደመው ቅርስና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የአማኙ ህዝብና የአገልጋዮች ፍጅት ዳግም እንዲቀጥል የታቀደ ከመምሰሉም ባሻገር።
እነዚህ አሰቃቂ ሁኔታዎች የአገር አንድነትን፣ የሕዝብ መተማመንን እና የናኘውን ሰላም አጥፍተው የቀጣይነታችን ሂደትን የሚያዳክሙ ናቸው። በመሆኑም የፖለቲካ ልዩነቶችና አለመግባባቶች በእውነተኛ ውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፈታት ግድ ይላቸዋል።
መኢአድ በፀና መሠረቱና በማይናወጠው አቋሙ ሁለገብ የሰብዓዊ መብት ከለላ እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንዳለበት ያምናል።
ማንኛውም የሕግ ጥሰት በገለልተኛ አካል መመረመሩ የማይቀር በመሆኑ፣ ከወዲሁ ተጠያቂነት ማስፈንና ተጎጂዎች ፍትሕን እንዲቋደሱ መደረግ አለበት።
ሕግ ለሁሉም ዜጎችና ተቋማት በእኩልነት መሥራት አለበት፤ የመንግሥት አካላትም ሆኑ ዜጎች ከሕግ በላይ ሊሆኑ አይችሉም።
የሀገራችን ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙት በእውነተኛና በአካታች ብሔራዊ ምክክር፣ በነፃና ገለልተኛ ፍትሕ ሥርዓት፣ በተጎጂዎች ላይ ፍትሕና እርቅን በማረጋገጥ፣ እንዲሁም የሁሉንም ዜጎች እኩል ክብር በማስጠበቅ ብቻ ነው።
ፓርቲያችን መኢአድም የሚከተሉትን ሀገራዊ የመፍትሔ ሐሳቦችና ጥሪዎች በአጽንኦት ያስተላልፋል፦
1. ሰላምንና አንድነትን ማስቀደም: ሁሉም ወገኖች ለሰላም፣ ለፍትሕና ለሀገራዊ አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ እናቀርባለን።
2. ሕግ ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዲሠራ እና የፍትሕ ተቋማት የደረሱ ሁለገብ በደሎችን ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲያዩ እንጠይቃለን።
3. የተፈፀሙና እየተፈፀሙ ያሉ ዘርና ማንነትን መሠረት ያደረጉ የመብት ጥሰቶች ሁሉ በእውነትና በሕግ መሠረት እንዲመረመሩ፤ ተጎጂዎችም ፍትሕን በአደባባይ እንዲያገኙ እናሳስባለን።
4. ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቀደም ሲል በነበረውና አሁን ተጠናክሮ በቀጠለው የዘርና ሃይማኖታዊ ጥቃት ላይ እያየ እንዳለየና እየሰማ እንዳልሰማ ከመሆን ወጥቶ፣ ጥፋት ያደረሱ አካላት ላይ ያለ ወገንተኝነት ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት እንጠይቃለን።
5. የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ህልውና የሚረጋገጠው የበቀልን፣ የጥላቻን ዘር በመዝራትና የሐሰት ትርክትን በመከተል ሳይሆን፤ በእውነት፣ በፍትሕ፣ በዘመናዊ የፖለቲካ ውይይትና በሕግ የበላይነት መረጋገጥ መሆኑን እንገነዘባለን።
6. ሀገር ለምትገኝበት አጠቃላይ ቀውስ መነሻና ማጉኛ! ከሆኑትና በተለያየ ጊዜና መድረክ የጥላቻ ቅስቀሳ ከሚያደርጉ ባለሥልጣናት፣ ጋዜጠኞች፣ ነብያት፣ አክቲቪስቶችና አርቲስት ነን ባዮች ከዚህ አጥፊ ድርጊታቸው በጥብቅ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።
7. በማንኛውም ወገን በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ኃይሎች የሰላምና የመቻቻል ባህልን እንዲያጠናክሩ እንጠይቃለን።
Ø የሕዝብ ትግል ያሸንፋል ሁሉም አካላት የታሪክ ተጠያቂ ከመሆን ጭላንጭል እድል አለችና ዛሬ እንጠቀምባት!!?
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!”
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
See less


