ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ስደተኞች

ታትሟል4 ነሐሴ 2026, 08:09 EAT

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ቮን ዲር ሊይን የድንበሮች ደኅንነት ለማስከበር የትብብር እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቡ።

ፕሬዚደንቷ ይህን ያሉት ባለፈው ሳምንት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከሞሮኮ ወደ ስፔን መሻገራቸውን ተከትሎ ነው።

አሁን ላይ ከተሻግረው የነበሩት 69 ሺህ 500 ገደማ ስደተኞች ወደ ሞሮኮ መመለሳቸው ተገልጿል።

ስደተኞቹ በዋና እና በእግር የስፔን ግዛት ወደሆነችው ሲዩታ ለመግባት በሚሞክሩበት ጊዜ በስፔን በኩል 72 ሰዎች ሲሞቱ በሞሮኮ በኩል ደግሞ 11 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

የአውሮፓ ኅብረት የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ዛሬ ማክሰኞ በቪዲዮ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሂዳሉ።

አስቸኳይ ስብሰባው የተጠራው በሲዮታ የታየው ክስተት በተወሰኑ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ከከተተው በኋላ ነው።

በሲዩታ ያጋጠመውን የስደተኞች ጎርፍ ተከትሎ ጣልያን ከስፔን ጋር ያላትን እና ያለቪዛ በአገራቱ መካከል መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ሸንገን ቪዛ በጊዜያዊነት አግዳለች።

የሸንገን ስምምነት ከ450 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ 29 የአውሮፓ አገራት ያለድንበር ፍተሻ ወይም ያለቪዛ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ይፈቅዳል።

ፊንላንድ እና ዴንማርክ የጣልያንን እርምጃ የደገፉ ሲሆን የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድርጅ ባቢስ የስፔን የሸንገን አባልነት በጊዜያዊነት እንዲታገድ አሳስበዋል።

ሳንቼዝ ለዚህ በሰጡት ምላሽ የሲዩታ ክስተት የሸንገን አካባቢ አካል እንዳልሆነ ጠቅሰው ” የተወሰኑ የአውሮፓ መንግሥታት እየወሰዱት ባለው እርምጃ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው” ገልጸዋል።

“አብዛኞቹ አገራት ድጋፍ እና ትብብር አሳይተዋል።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሌሎች የአውሮፓ መንግሥታት ግን ” “በጭፍን ጥላቻ፣ በሐሰተኛ ዜና፣ በግድ የለሽነት ወይም በፖለቲካዊ ፍላጎት” ስፔንን ለማጥቃት ወስነዋል ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ለስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር በፃፉት ደብዳቤ ያጋጠመውን ቀውስ “በፍጥነት ለመቆጣጠር” ቃል ገብተዋል።

ሆኖም “ከዚህ ክስተት እንዳየነው ድንበሮቻችንን ለማጠናከር ብዙ መሥራት እንደሚኖርብን ግልጽ ነው” ብለዋል።

” የውጭ ድንበሮቻችንን መጠበቅ የአውሮፓውያን የጋራ ኃላፊነት ነው” ሲሉ ጥብቅ ቁጥጥር እና በሚያስፈልግበት ቦታ የድንበር ኬላዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ” አሳስበዋል።

ዛሬ የሚካሄደው ስብሰባ ከክስተቱ ለመማር ዕድል ይሰጣል ያሉት ፕሬዚደንቷ፣ የሕገ ወጥ ስደት ተግዳሮት ” ወጥ የሆነ ምላሽ፣ የአንድነት እርምጃ እና ትብብር” እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

ሳንቼዝ በሲዩታ ለታየው ክስተት የአገሪቷ ፍርድ ቤት በቅርቡ በባሕር አቋርጠው የገቡ ስደተኞችን ወዲያውኑ መመለስ እንደማይቻል ያሳለፈውን ውሳኔ በተሳሳተ መልኩ ተርጉመዋል ያሏቸውን ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ወቅሰዋል።

የአገሪቷ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፌርናንዶ ግራንዴ ማርላስካ ቅዳሜ ዕለት ሁኔታው ወደ መደበኛነት መመለሱን እና በውሃ አካሉ በኩል የሚደረገውን ሕገ ወጥ ስደት ለመከላከል ተንሳፋፊ ኬላዎች ለመዘርጋት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።