
ታትሟል4 ነሐሴ 2026, 09:39 EAT
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
በአሜሪካ ሚቺጋን ግዛት ‘ሳይክሎስፖራ’ ከተባለ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት ተናገሩ።
‘ሳይክሎስፖራ’ የተባለው ጥገኛ ተህዋስ በተበከለ ምግብ እና ውሃ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን አጣዳፊ ተቅማጥን ያስከትላል።
በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈው ሁለቱ ግለሰቦች በሳይክሎስፖሪያሰስ እና የሰውነት ፈሳሽ እጦት ምክንያት “እጅግ አሳሳቢ የጤና ሁኔታ ላይ እንደነበሩ” የግዛቷ የጤና ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
በተበከለ ምግብ የሚከሰተው ይህ ወረርሽኝ በ45 ግዛቶች እንደተዛመተ እና በአጠቃላይ በአገሪቱ ወደ ሰባት ሺህ የሚጠጉ የተረጋገጡ ኬዞች መመዝገባቸውን የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) መረጃ ያሳያል።
ወረርሽኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ቢያጠቃም ሲዲሲ “ብዙውን ጊዜ ለሕይወት አስጊ ባለመሆኑ” በበሽታው የሚከሰት ሞት የተለመደ አለመሆኑን ገልጿል።
የሚቺጋን የጤና መሥሪያ ቤት በወረርሽኙ ሕይወታቸው ስላለፈው ሰዎች የሰጠው ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ የለም።
የበሽታው ማዕከል እንደሆነች በተገለጸው ሚቺጋን ግዛት፣ ከ11 ሺህ በላይ ኬዞች የተመዘገቡ ሲሆን 193 ሰዎች ሆስፒታል ገብተዋል። ሆኖም አብዛኞቹ ኬዞች በላብራቶሪ የተረጋገጡ አይደሉም።
ሙቀት የሚወደው ጥገኛ ተህዋስ አንጀትን የሚያጠቃ ሲሆን በሰገራ በተበከለ ውሃ ወይም ምግብ አማካኝነት ይተላለፋል።
ከዚህ ቀደምም ወረርሽኙ ተከስቶ የነበረው ሰዎች በተበከለ የመስኖ ውሃ የተመረቱ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ከተመገቡ በኋላ ነበር።
በመሆኑም እንደታጠቡና ንጹህ እንደሆኑ የሚያሳይ መግለጫ ያላቸውን ጨምሮ በወንዝ ዳርቻ የበቀሉ ሁሉም ምርቶች ለምግብነት ከመዋላቸው በፊት በደንብ መታጠብ እንዳለባቸው ሲዲሲ መክሯል።
ሆኖም ጥገኛ ተህዋሱን ለመግደል ማጠብ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። 70 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በሆነ ሙቀት ማብሰል ጥገኛ ተህዋሱን መግደል እንደሚቻልም ተቋሙ ገልጿል።
በዚህ ዓመት የተከሰተው ወረርሽኝ፣ ሜክሲኮ ከሚገኘው እና የአሜሪካ ወሳኝ የምግብ ምርቶች አቅራቢ በሆነው ‘ታይለር ፋርም’ ከተመረተ ሰላጣ ጋር የተገናኘ መሆኑን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
የአሜሪካ ፈጣን ምግብ አቅራቢ ታኮ ቤልም ከምግብ ዝርዝሩ ውስጥ ሰላጣ ማውጣቱን አስታውቋል።
ታይለር ፋርም በበኩሉ በማዕከላዊ ሜክሲኮ የተመረቱ ሰላጣዎችን በፈቃደኝነት መልሶ መሰብሰብ መጀመሩን ገልጿል።
የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናትም ከአሜሪካ በሚመለሱ መንገደኞች ላይ የታዩትን ኬዞች ተከትሎ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
